ቀረዓታውያንና እውነትን ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ
በእኔ ሐሳብ ሳትመሩ “[በቅዱሳን ጽሑፎች] ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር አድርጉ።” እነዚህን ቃላት የተናገረው በስምንተኛው መቶ ዘመን የነበረ የቀረዓታውያን መሪ ነው። ቀረዓታውያን እነማን ነበሩ? ከእነሱ ምሳሌ ልንማረው የምንችለው ጠቃሚ ነገር አለን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ወደ ቀረዓታውያን ንቅናቄ የመራውን ለረጅም ጊዜ የቆየ ውዝግብ ያለውን ታሪክ መለስ ብለን መመልከት ያስፈልገናል።
ውዝግቡ እንዴት ጀመረ?
ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበሩት የመጨረሻዎቹ መቶ ዓመታት በአይሁድ እምነት ውስጥ አዲስ ፍልስፍና ተስፋፋ። ይህ ፍልስፍና አምላክ በሲና ተራራ ላይ ሁለት ሕጎችን ማለትም የተጻፉና የቃል ሕጎችን ሰጥቷል የሚል ነበር።a በመጀመሪያ መቶ ዘመን እዘአ ይህን ትምህርት በሚደግፉና በማይደግፉ ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ውዝግቦች ተፈጥረው ነበር። ፈሪሳውያን የዚህ ፍልስፍና አራማጆች ሲሆኑ ሰዱቃውያንና ኤሴናውያን ደግሞ ከተቃዋሚዎች መካከል ነበሩ።
በዚህ ውዝግብ መሃል የናዝሬቱ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ሆኖ ብቅ አለ። (ዳንኤል 9:24, 25፤ ማቴዎስ 2:1–6, 22, 23) ኢየሱስ እነዚህ ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚወዛገቡ የአይሁዳውያን ቡድኖች አጋጥመውታል። ኢየሱስ ከእነሱ ጋር ምክንያቱን እያቀረበ በተወያየበት ወቅት ለወጋቸው ሲሉ የአምላክን ቃል በመሻራቸው አውግዟቸዋል። (ማቴዎስ 15:3–9) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ መሲሑ ብቻ ሊያስተምር በሚችልበት መንገድ መንፈሳዊ እውነቶችን አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 7:45, 46) ከዚህም በላይ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳላቸው ያስመሰከሩት የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ብቻ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ።—ሥራ 11:26
የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በ70 እዘአ በጠፋበት ወቅት የተረፈው የሃይማኖት ቡድን የፈሪሳውያን የሃይማኖት ቡድን ብቻ ነበር። በወቅቱ ክህነት፣ መሥዋዕትና ቤተ መቅደስ ስላልነበረ ፈሪሳውያን አይሁዶች እነዚህን ሁሉ የሚተኩ ነገሮች ሊፈጥሩ ችለው ነበር፤ የተጻፈውን ሕግ ወደ ጎን በመተው ወጎችንና የራሳቸውን ትርጉም ማስፋፋት ጀመሩ። ይህም አዳዲስ “ቅዱሳን መጻሕፍት” እንዲጻፉ መንገድ ከፈተ። በመጀመሪያ በቃል ሕጋቸው ላይ የሚጨመሩ ሐሳቦችንንና የቃል ሕጉን ትርጓሜዎች ያካተተው ሚሽና ተጻፈ። ከዚያ በኋላ ሌሎች መጻሕፍት ታከሉበትና እነዚህ መጻሕፍት ታልሙድ ተብለው ተጠሩ። በዚሁ ጊዜ ከሃዲ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ትምህርቶችን መሠረታዊ ሥርዓቶች መጣስ ጀመሩ። በአንድ ወገን የረቢዎችን ሥልጣን በሌላ ወገን ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን በማስፋፋት ሁለቱም ቡድኖች ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ፈጠሩ።
አይሁዳውያን ቀደም ሲል ከአረማዊው የሮም መንግሥት በኋላ ደግሞ “ክርስቲያን” ከተባለው የሮም መንግሥት ጋር በነበራቸው ግጭቶች የተነሣ ባቢሎን የአይሁድ እምነት ማዕከል ሆነች። የታልሙድ መጻሕፍት በተሟላ መልኩ የተጻፉት እዚያ ነበር። ረቢዎች ታልሙድ የአምላክን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት እንደሚያስችል ቢናገሩም ብዙ አይሁዳውያን እየጨመረ የሚሄደው የረቢዎች ተጽዕኖ ተሰምቷቸው በሙሴና በነቢያት አማካኝነት የተሰጣቸውን የአምላክ ቃል ይፈልጉ ነበር።
በስምንተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ መገባደጃ ላይ የረቢዎችን ሥልጣንና በቃል ሕጋቸው ላይ የነበራቸውን እምነት የሚቃወሙ በባቢሎን የነበሩ አይሁዳውያን ዓናን ቤን ዴቪድ ለተባለ አንድ ምሁር መሪ አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ። ዓናን እያንዳንዱ አይሁዳዊ የረቢዎችን አተረጓጎም ወይም ታልሙድን ሳይቀበል የእውነተኛ ሃይማኖት ብቸኛ ምንጭ አድርጎ በመመልከት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን የማጥናት መብት እንዳለው አስታውቋል። ዓናን “በቶራህ [በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክ ሕግ] ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር አድርጉ፤ በእኔ ሐሳብ አትመሩ” በማለት አስተምሯል። የዓናን ተከታዮች ለቅዱስ ጽሑፉ ከፍተኛ ትኩረት ስለሚሰጡ ቋራይም በመባል ታወቁ፤ ይህም “አንባብያን” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ስም ነው።
የቀረዓታውያንና የረቢዎች ውዝግብ
የረቢዎች ቡድኖችን ግራ ያጋቧቸው አንዳንድ የቀረዓታውያን ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? ረቢዎች ሥጋንና ወተትን በአንድ ላይ መብላትን ይከለክሉ ነበር። ይህንንም በዘጸአት 23:19 ላይ ለሚገኘው “ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል” ለሚለው ጥቅስ የቃል ሕግ ማብራሪያ አድርገው ያቀርቡ ነበር። በሌላ በኩል ግን ቀረዓታውያን ይህ ጥቅስ በጥቅሱ ላይ ከተገለጸው በቀር ሌላ ትርጉም እንደሌለው ያስተምሩ ነበር። ረቢዎች የከለከሏቸው ነገሮች የሰው ፈጠራ ናቸው ብለው ይከራከሩ ነበር።
ረቢዎች ለዘዳግም 6:8, 9 በሚሰጡት ትርጉም መሠረት አይሁዳውያን ወንዶች ክታቦች አድርገው እንዲጸልዩና በእያንዳንዳቸው ቤት መቃን ላይ ሜዙዛ እንዲያደርጉ አዘው ነበር።b ቀረዓታውያን እነዚህን ጥቅሶች ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳላቸው ያምኑ ስለነበር እንዲህ ዓይነቶቹን ረቢዎች ያወጧቸውን ደንቦች አይቀበሏቸውም ነበር።
በሌሎች ጉዳዮች ደግሞ ቀረዓታውያን ከረቢዎች የባሰ በጣም ጥብቅ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ “በማደሪያዎቻችሁ ውስጥ በሰንበት ቀን እሳትን አታንድዱ” ለሚለው ለዘጸአት 35:3 የነበራቸውን አመለካከት ተመልከት። ቀረዓታውያን ከሰንበት በፊት የበራ መብራት እንኳ መጥፋት አለበት ብለው ያምኑ ነበር።
በተለይ ዓናን ከሞተ በኋላ የቀረዓታውያን መሪዎች አንዳንድ እገዳዎች ምን ያህል እንደሚሠሩና ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳላቸው ብዙውን ጊዜ አይስማሙም ነበር፤ መልእክታቸውም አብዛኛውን ጊዜ ግልጽ አልነበረም። ቀረዓታውያን አንድነት ያጡት በማንም ከመመራት ይልቅ ረቢዎች ካላቸው ሥልጣን በሚጻረር መንገድ ቅዱሳን ጽሑፎችን በግል በማንበብና በመተርጎም ላይ ያተኩሩ ስለነበር ነው። ሆኖም ይህ የቀረዓታውያን ንቅናቄ በባቢሎን ውስጥ ከነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ አልፎ በጠቅላላው መካከለኛው ምሥራቅ ተስፋፍቶ ስለነበር ከፍተኛ ተቀባይነትና ተጽዕኖ ነበረው። ሌላው ቀርቶ አንድ ዋነኛ የቀረዓታውያን የአምልኮ ማዕከል በኢየሩሳሌም ተቋቁሞ ነበር።
በዘጠነኛውና በአሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ የቀረዓታውያን ምሁራን የዕብራይስጥን ቋንቋ እንደገና በማጥናትና ከፍተኛ ተግባር በማከናወን ረገድ የላቀ ሥፍራ ይዘው ነበር። እንደ ቅዱስ አድርገው ይመለከቷቸው የነበረው የቃል ወጎችን ሳይሆን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ነበር። አንዳንድ ቀረዓታውያን ጠንቃቃ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ገልባጮች ሆነው ነበር። እንዲያውም በአይሁዳውያን መካከል የማሶሬቲክ ቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት እንዲስፋፋ ያደረገው የቀረዓታውያን ፈታኝ ሁኔታ ነበር፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ ድረስ በትክክል ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል።
በዚህ ፈጣን እድገት በተካሄደበት ዘመን ቀረዓታውያን አይሁዳውያን በሌሎች አይሁዳውያን መካከል የሚስዮናዊነት ሥራ በግልጽ ሲያካሂዱ ነበር። ይህም በአይሁዳውያን ረቢዎች ላይ ስጋት ፈጠረ።
ረቢዎች ምን ምላሽ ሰጡ?
ረቢዎች አጸፋውን የመለሱት በብልሃት ራሳቸውን ከሁኔታው ጋር በማስማማትና ዓላማቸው ግቡን እንዲመታ ትምህርታቸውን በመለዋወጥ ኃይለኛ የቃላት ጦርነት በመግጠም ነበር። ከዓናን ጥቃት በኋላ በነበረው መቶ ዘመን አይሁዳውያን ረቢዎች ቀረዓታውያን የሚጠቀሙባቸውን በርካታ ዘዴዎች ቀዱ። ረቢዎች የቀረዓታውያንን ዘዴ ከራሳቸው ዘዴ ጋር በማቀናጀት ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጥቀስ ረገድ ይበልጥ የተካኑ ሆኑ።
ከቀረዓታውያን ጋር በተደረገው በዚህ የቃላት ሽኩቻ በመሪነቱ የሚታወቀው በአሥረኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በባቢሎን ይኖር የነበረው የአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ራስ የነበረው ሳዲያ ቤን ጆዜፍ ነበር። የሳዲያ የሥራ ውጤት የሆነው ዘ ቡክ ኦቭ ቢሊፍስ ኤንድ ኦፕንየንስ የተባለው መጽሐፍ በሳሙየል ሮዘንብላት ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሟል፤ ሳሙየል ሮዘንብላት በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “. . . [ሳዲያ] በዘመኑ ታልሙድን ጠንቅቆ የተማረ ቢሆንም ይህን የአይሁዶች ወግ እምብዛም ያልተጠቀመበት የተጻፈው ሕግ ብቻ እንደሚሠራ አድርገው የሚመለከቱትን ቀረዓታውያን በራሳቸው መሣሪያ ለማጥቃት ብሎ ሳይሆን አይቀርም።”
የሳዲያን ፈለግ በመከተል አይሁዳውያን ረቢዎች ከፍተኛ የበላይነት ማሳየት ጀመሩ። የተጻፈውን ሕግ ጠንቅቀው ከማወቃቸው የተነሣ ቀረዓታውያን የሚያቀርቧቸውን ሐሳቦች የሚያፈርሱ ኃይለኛ ማስረጃዎች ለማቅረብ ቻሉ። የ12ኛው መቶ ዘመን ዝነኛ የታልሙድ ምሁር የነበረው ሙሴ ማይሞኒደስ የመጨረሻውንና የማያዳግመውን ጥቃት ሰነዘረባቸው። በግብጽ አብሯቸው ይኖር ለነበሩት ቀረዓታውያን በነበረው ለዘብ ያለ አቋምም ሆነ የማሳመን ችሎታ በሞላበት ምሁራዊ ችሎታው አድናቆታቸውን ከማትረፉም በላይ ይዘውት የነበረውን የመሪነት ቦታ አዳከመ።
የቀረዓታውያን ንቅናቄ ድጋፍ አጣ
በወቅቱ የነበረው የቀረዓታውያን እንቅስቃሴ ይህን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል አንድነትና በሚገባ የተቀናጀ ድርጅት ስላልነበረው ድጋፍና ብዙ ተከታዮችን አጣ። ከጊዜ በኋላ ቀረዓታውያን በአመለካከታቸውና በመሠረታዊ ሥርዓቶቻቸው ላይ አንዳንድ ለውጦችን አደረጉ። ደራሲው ሊያን ነሞይ ስለ ቀረዓታውያን ንቅናቄ ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፦ “ታልሙድ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የተከለከለ ቢሆንም አብዛኛው የታልሙድ ሐሳብ ሳይታወቅ ከቀረዓታውያን ሕግና ልማድ ጋር ተቀላቅሏል።” በመሠረቱ ቀረዓታውያን መጀመሪያ የነበራቸውን ዓላማ ትተው አብዛኛውን የአይሁዳውያንን ረቢዎችን እምነት ተቀብለዋል።
አሁንም ቢሆን በእስራኤል ውስጥ 25,000 የሚያህሉ ቀረዓታውያን ይገኛሉ። ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ቀረዓታውያን በሌሎች ማኅበረሰቦች ውስጥ ይገኛሉ፤ አብዛኞቹ የሚገኙት በሩሲያና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነው። ሆኖም የራሳቸው የቃል ሕጎች ስላላቸው ከመጀመሪያዎቹ ቀረዓታውያን ይለያሉ።
ከቀረዓታውያን ታሪክ ምን ልንማር እንችላለን? ‘ለወግ ሲባል የእግዚአብሔርን ቃል መሻር’ ከባድ ስህተት መሆኑን ልንማር እንችላለን። (ማቴዎስ 15:6) ሸክም ከሆኑት የሰው ወጎች ነፃ መሆን የቅዱሳን ጽሑፎችን ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ይጠይቃል። (ዮሐንስ 8:31, 32፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) አዎን፣ የአምላክን ፈቃድ ለማወቅና ለማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ በሰው ወግ አይመሩም። ከዚህ ይልቅ በትጋት መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናታቸውም በላይ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል የሚሰጣቸውን ጠቃሚ መመሪያ በሥራ ላይ ያውላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የቃል ሕግ የሚባለውን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣ ይሆን? የተባለውን የእንግሊዝኛ ብሮሹር ከገጽ 8–11 ተመልከት።
b ክታቦች ጥቅሶች የተጻፉባቸው ትናንሽ የብራና ቁራጮችን የያዙ ሁለት አነስተኛ ከቆዳ የተሠሩ መያዣዎች ናቸው። እነዚህ አነስተኛ መያዣዎች በሥራ ቀናት በሚደረጉ የጠዋት ጸሎቶች ወቅት በዘልማድ በራስና በግራ ክንድ ላይ ይደረጋሉ። ሜዙዛ ዘዳግም 6:4–9 እና 11:13–21 የተጻፉበት አነስተኛ ብራና ሲሆን በመያዣ ተደርጎ በመቃን ላይ ይታሰራል።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ የቀረዓታውያን ቡድን]
[ምንጭ]
በ1910 ከታተመው ዘ ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔድያ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ