የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 5/15 ገጽ 26-28
  • የማሶሬቲክ ጽሑፍ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የማሶሬቲክ ጽሑፍ ምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የይሖዋ ቃል
  • ቀስ በቀስ ስህተት የሚያስገባ በር ተከፈተ
  • በሩን ለመዝጋት የተደረጉ ሙከራዎች
  • “የጠራ” የማሶሬቲክ ጽሑፍ ልናገኝ እንችላለንን?
  • ማሶሬቶች እነማን ናቸው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ለዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ናሙና የሚሆን በብራና የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ዕድሜ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?
    ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ህልውናውን ለማስጠበቅ ያደረገው ትግል
    መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 5/15 ገጽ 26-28

የማሶሬቲክ ጽሑፍ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን የምታነበው በየትኛውም ቋንቋ ቢሆን የመጽሐፉ የተወሰኑ ክፍሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሙሉው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም “ብሉይ ኪዳን” ከሚገኝበት ከማሶሬቲክ ጽሑፍ የተተረጎመ መሆኑ የማይቀር ነው። እርግጥ ነው፣ ከአንድ በላይ የማሶሬቲክ ጽሑፎች አሉ። ታዲያ የትኛው ተመረጠ? ለምንስ? እንዲያውም የማሶሬቲክ ጽሑፍ ምንድን ነው? አስተማማኝ መሆኑንስ እንዴት እናውቃለን?

የይሖዋ ቃል

መጽሐፍ ቅዱስ በ1513 ከዘአበ በሲና ተራራ ላይ መጻፍ ጀመረ። ዘጸአት 24:3, 4 እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። ሙሴም የእግዚአብሐርን ቃሎች ጻፈ።”

የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዓመታት ይኸውም ከ1513 ከዘአበ ጀምሮ እስከ 443 ከዘአበ ገደማ ሲጻፉ ቆይተዋል። ጸሐፊዎቹ የጻፉት በአምላክ መንፈስ ተነድተው በመሆኑ ይኸው ያስጻፋቸው አምላክ መልእክቱ ሳይለወጥ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረጉ አይቀርም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። (2 ሳሙኤል 23:2፤ ኢሳይያስ 40:8) ነገር ግን ይህ ማለት ቅጂዎች በሚዘጋጁበት ጊዜ የአንድ ፊደል ለውጥ እንኳ እስከማይኖር ድረስ የሰዎችን ስህተት አስወግዷል ማለት ነውን?

ቀስ በቀስ ስህተት የሚያስገባ በር ተከፈተ

የቅዱሳን ጽሑፎች የእጅ ጽሑፍ ግልባጮች ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተገለበጡ የተላለፉት ለአምላክ ቃል አክብሮት በነበራቸው ሰዎች ቢሆንም አንዳንድ ስህተቶች ሠርገው መግባታቸው አልቀረም፤ ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት ጸሐፊዎቹ ነበሩ እንጂ ገልባጮቹ ሥራቸውን በመለኮታዊ ገፋፊነት አልፈጸሙም።

አይሁዶች በ537 ከዘአበ ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ ባቢሎን ሳሉ የተማሩትን የአራት ማዕዘን ፊደላት የአጻጻፍ ስልት መጠቀም ጀመሩ። ይህ መሠረታዊ ለውጥ ችግር አስከትሏል፤ ይኸውም ተመሳሳይ መልክ ያላቸውን አንዳንድ ፊደላት መለየት አስቸጋሪ ሆነ። ዕብራይስጥ በተነባቢ ፊደላት ላይ የተመሠረተ ቋንቋ ስለሆነ አናባቢ ፊደላት የሚጨመሩት የሚያነበው ሰው የምንባቡን አገባብ በተረዳበት መንገድ ነው፤ በዚህም የተነሳ የአንድ ተነባቢ ፊደል መለወጥ በቀላሉ የቃሉን ትርጉም ሊለውጠው ይችላል። ነገር ግን እንዲህ ያለ ነገር በሚያጋጥምበት አብዛኛውን ጊዜ ስህተቶቹን ለማግኘትና ለማረም ይቻል ነበር።

ከባቢሎን ውድቀት በኋላ አብዛኞቹ አይሁዳውያን ወደ እስራኤል አልተመለሱም። ስለዚህ ምኩራቦች በመላው መካከለኛ ምሥራቅና አውሮፓ ለሚገኙ የአይሁድ ማኅበረሰቦች መንፈሳዊ ማዕከል ሆኑ።a እያንዳንዱ ምኩራብ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥቅሎች ቅጂ ያስፈልገው ነበር። ቅጂዎች እየበዙ ሲሄዱ የገልባጮች ስህተትም እየተበራከተ መጣ።

በሩን ለመዝጋት የተደረጉ ሙከራዎች

በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መባቻ ላይ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ጻፎች ሌሎቹን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጥቅሎች ለማረም የሚያስችል አንድ ዋና ጽሑፍ ለማዘጋጀት ሞክረው ነበር። ሆኖም በኩረ ጽሑፎችን የገልባጮች ስህተቶች ካሉባቸው የእጅ ጽሑፎቹ ለመለየት የሚያስችል ወጥ የሆነ የአሠራር ስልት አልነበረም። ከሁለተኛው መቶ ዘመን ወዲህ በተነባቢ ፊደላት ብቻ የተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች የተወሰነ ደረጃ እንዲጠብቁ የተደረገ ቢሆንም አንድ ዓይነት እንዲሆኑ ለማድረግ አልተቻለም። በታልሙድ (በሁለተኛውና በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መካከል ተጠናቅሮ የተዘጋጀ) ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የተጠቀሱ ክፍሎች ከጊዜ በኋላ ማሶሬቲክ ጽሑፍ ተብለው ከታወቁት ቅጂዎች ከተለየ ምንጭ የተጠቀሱ እንደሆኑ ተመልክቷል።

“ወግ” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቋንቋ ማሶራህ ወይም ማሶሬት ነው። በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በትክክል የመገልበጥን ወግ ይጠብቁ የነበሩ ሰዎች ማሶሬትስ በመባል ይታወቁ ጀመር። የገለበጧቸው ቅጂዎች ማሶሬቲክ ጽሑፎች በመባል ተሰየሙ። ሥራቸውንና ያዘጋጁአቸውን ጽሑፎች ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

ዕብራይስጥ ሕያው ብሔራዊ ቋንቋ መሆኑ እየተዳከመ በመሄዱ አያሌ አይሁዳውያን ከቋንቋው ጋር ያላቸው ትውውቅ እየከሰመ ሄደ። በዚህም የተነሳ በተነባቢ ፊደላት ብቻ የተጻፉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የመረዳት ችሎታ አደጋ ላይ ወደቀ። ማሶሬቶች እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጠብቆ ለማቆየት በማሰብ በነጠብጣቦችና በሰረዞች የሚወከሉ አናባቢዎችን ጨምሮ የመጻፍን ስልት አዳበሩ። እነዚህ አናባቢዎች ከተነባቢው አናት ላይ ወይም ከታች ይቀመጡ ነበር። በተጨማሪም ማሶሬቶች በሥርዓተ ነጥብነትና ይበልጥ ትክክለኛ ለሆነ አነባበብ አመልካች በመሆን የሚያገለግሉ ውስብስብ የምልክት ዘዴዎች አዳብረው ነበር።

ማሶሬቶች ጽሑፉ እንደተለወጠ ወይም ባለፉት ትውልዶች በነበሩ ጻፎች በትክክል እንዳልተገለበጠ ከተሰማቸው ጽሑፉን ከመለወጥ ይልቅ በሕዳጉ ላይ ማስታወሻዎችን ይጽፉ ነበር። ያልተለመዱ የቃላት ዓይነቶችንና ኅብረ ቃላትን ይጠቁማሉ እንዲሁም በእያንዳንዱ መጽሐፍ ወይም በመላው ዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንደሚገኙ ይገልጻሉ። ገልባጮች ከተለያየ አቅጣጫ ትክክለኛነቱን ሲያረጋግጡ እንዲረዳቸው ተጨማሪ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ይህንን መረጃ እጅግ በጣም አጭር አድርጎ ለመመዝገብ እንዲቻል በምሕጻረ ቃል በተጻፉ “የምሥጢር ጽሑፎች” የመጠቀም ዘዴ ዳብሮ ነበር። በላይና በግርጌ ማስታወሻዎቹ ላይ አንድ አነስተኛ ማጣቀሻ በኅዳግ ማስታወሻዎቹ ውስጥ ሐሳብ ከተሰጠባቸው ቃላት ጋር የሚዛመዱ ጥቅሶችን የተወሰኑ ክፍሎች ዘርዝሯል።

ከሁሉ ይበልጥ ታዋቂ ዘዴ የሆነው ተሻሽሎ የቀረበው በገሊላ ባሕር አካባቢ በምትገኘው ጥብርያዶስ በሚኖሩ ማሶሬቶች ነው። በተለይ ደግሞ በዘጠነኛውና በአሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ የኖሩት የቤን አሽር እና የቤን ናፍታላይ ቤተሰቦች (ካራይታውያን ሳይሆኑ አይቀርም) ስመ ጥር ሆነው ነበር።b ምንም እንኳ በእነዚህ የየራሳቸው መሠረተ ትምህርት ባላቸው ሁለት ቡድኖች መካከል የአነባበብ መንገድና የግርጌ ማስታወሻዎችን በተመለከተ ልዩነቶች ቢኖሩም በጽሑፎቻቸው ውስጥ የሰፈሩት ተነባቢ ፊደላት ያላቸው ልዩነት በመላው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከአሥር አይበልጥም።

የየራሳቸው መሠረተ ትምህርት ያላቸው ሁለቱም ማሶሬቶች ማለትም ቤን አሽር እና ቤን ናፍታላይ በጊዜያቸው ለነበረው የሥነ ጽሑፍ እውቀት ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ማይሞኒደስ (ተደማጭነት ያለው የ12ኛው መቶ ዘመን የታልሙድ ምሁር) የቤን አሽር ጽሑፎችን ካደነቃቸው በኋላ የሌሎችም ምርጫ እርሱ ብቻ ሆነ። በዚህም የተነሳ በጊዜው የቤን ናፍታላይን የብራና መጽሐፍ ጠፍቶ ነበር። ከዚህ ጽሑፍ የቀረ ቢኖር የየራሳቸውን መሠረተ ትምህርት በሚከተሉት ሁለቱ ቡድኖች መካከል ያሉት ልዩነቶች ዝርዝር ብቻ ነው። የሚያስገርመው ግን ማይሞኒደስ የሰጠው አስተያየት በአንቀጾች መካከል ክፍተት ማድረግን በመሳሰሉ ከሥነ ጽሑፍ ጋር በተያያዙ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው እንጂ መልእክቱ በትክክል ለመተላለፉ ከፍ ያለ ትኩረት አልሰጠውም።

“የጠራ” የማሶሬቲክ ጽሑፍ ልናገኝ እንችላለንን?

“ትክክለኛውን” የማሶሬቲክ ጽሑፍ ለማግኘት ይረዳ ይመስል በአሁኑ ጊዜ ከሚገኙት ኮዴክሶች መካከል “የጠራ” የቤን አሽር ጽሑፍ የትኛው ነው የሚለው ጉዳይ በምሁራን መካከል ከፍተኛ ጭቅጭቅ ፈጥሯል። በእርግጥም አንድ ልዩ፣ “የጠራ” እና ተቀባይነት ያገኘ ማሶሬቲክ ጽሑፍ የለም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዳቸው ከሌሎቹ በትንሹ የሚለያዩ ብዙ ማሶሬቲክ ጽሑፎች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ያሉ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ኮዴክሶች ሁሉ የቤን አሽርንና የቤን ናፍታላይንን አነባበቦች የያዙ ቅልቅል ጽሑፎች ናቸው።

ዛሬ ያለ ማንኛውም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተርጓሚ የተደቀነበት ሥራ አዳጋች ነው። ራሱን በጥሩ ሁኔታ ማስተዋወቅ ያለበት ከዕብራይስጡ ጽሑፍ ጋር ብቻ ሳይሆን ጽሑፉ በገልባጮች ስህተት ወይም በማወቅ ተለውጦ ይሆናል ብሎ እንዲያስብ ከሚያደርጉት ምክንያታዊ አማራጮች ጋር ጭምር ነው። የተለያዩ ማሶሬቲክ ጽሑፎች እንደ መሠረት ሆነው ቢያገለግሉም ተርጓሚው በተነባቢ ፊደላት ብቻ የተጻፈው ጽሑፍ የተተረጎመባቸውን ምናልባትም ይበልጥ ትክክለኛ የሆኑ ትርጉሞችን የያዙ አስተማማኝ ምንጮችን መመልከት ያስፈልገዋል።

ኧርነስት ቩርትቪን ዘ ቴክስት ኦቭ ዘ ኦልድ ቴስታመንት በተባለው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ አሉ፦ “አስቸጋሪ ምንባብ ሲያጋጥመን አንድ ጊዜ የዕብራይስጡን ጽሑፍ ሌላ ጊዜ ሴፕቱጀንትን እንዲሁም ሌላ ጊዜ ደግሞ የአረማይኩን ታርገም በመምረጥ እንዲሁ የተለያዩ ዓይነት አነባበቦችን አሰባስበን ቀላል መፍትሔ የሚሰጥ የሚመስለውን መምረጥ አንችልም። የጽሑፍ ማስረጃዎች ሁሉም በእኩል ደረጃ እምነት የሚጣልባቸው አይደሉም። እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የሆነ ባሕርይ እንዲሁም የየራሳቸው የሆነ ልዩ ታሪክ አላቸው። አጥጋቢ ያልሆኑ ወይም ሐሰተኛ መደምደሚያዎችን ለማስወገድ ከፈለግን ከእነርሱ ጋር በደንብ መተዋወቅ አለብን።”

ይሖዋ ቃሉን ጠብቆ እንዳቆየ ሙሉ በሙሉ ለመተማመን የሚያስችል ጽኑ መሠረት አለን። ባለፉት መቶ ዘመናት በኖሩ አያሌ ቅን ሰዎች የተቀናጀ ጥረት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት መሠረተ ሐሳብ፣ ይዘቱና አልፎ ተርፎ ዝርዝሩ በእጃችን ይገኛል። የትኛውም አነስተኛ የፊደል ወይም የቃል ለውጥ ያለንን ቅዱሳን ጽሑፎችን የመረዳት ችሎታ አያቃውሰውም። በጣም አስፈላጊው ጥያቄ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ተከትለን እንኖር ይሆን? የሚለው ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከእስራኤል ውጪ ይኖሩ የነበሩት ብዙ አይሁዳውያን የዕብራይስጥ ቋንቋን አቀላጥፎ የማንበብ ችሎታቸው እየተዳከመ በመሄዱ በግብጽ በአሌክሳንድሪያ ከተማ እንዳሉት የመሳሰሉ የአይሁዳውያን ማኅበረሰቦች ዕለታዊ መነጋገሪያቸው ወደ ሆነው ቋንቋ የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ። ይህንን ፍላጎት ለማሟላት የግሪኩ ሴፕቱጀንት ትርጉም በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ተዘጋጀ። ይህ ትርጉም ከጊዜ በኋላ ጽሑፎችን ለማወዳደር የሚረዳ ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ ሊሆን ችሏል።

b በ760 እዘአ ገደማ ካራይታውያን በመባል የሚታወቅ አንድ የአይሁድ ቡድን ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥብቅ እንከተል የሚል ጥያቄ አቀረበ። የረቢዎችን ሥልጣን፣ ‘በቃል የሚተላለፈውን ሕግና’ ታልሙድን ገሸሽ በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስን ጽሑፎች ሥርዓት ባለው ሁኔታ የሚጠብቁበት ትልቅ ምክንያት ነበራቸው። ከዚህ ቡድን መካከል የሆኑ አንዳንድ ቤተሰቦች የተካኑ የማሶሬቲክ ገልባጮች ሆነዋል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአሌፖው ኮዴክስ የማሶሬቲኩን ጽሑፍ ይዟል

[ምንጭ]

Bibelmuseum, Münster

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ