ለዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ናሙና የሚሆን በብራና የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ
በ1947 የሙት ባሕር ጥቅሎች ከመገኘታቸው በፊት ከጥቂት ቁርጥራጮች በስተቀር የጥንታዊ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የብራና ጽሑፍ እንደሆነ የሚታወቀው ከ9ኛው መቶ ዘመን ማለቂያ እስከ 11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተጻፈው ነበር። ይህም አንድ ሺህ ዓመት ያህል ነው። ታዲያ ይህ ማለት ከ1947 በፊት ዕብራይስጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የማያስተማምን ነበር ማለት ነው? ጥንታዊ የዕብራይስጥ ጽሑፎች በጣም ጥቂት የነበሩትስ ለምንድን ነው?
የመጨረሻውን ጥያቄ መጀመሪያ ብንመለከተው በጥንታዊው የይሁዲነት ሥርዓት መሠረት በጣም ከማርጀቱ የተነሳ ወደፊት ሊሠራበት እንደማይገባ የተገመተ ማንኛውም የዕብራይስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ የብራና ጽሑፍ በምኩራብ ውስጥ ባለ ገኒዛ በሚባል መጋዘን ውስጥ ይቆለፍበት ነበር። በኋላም የተጠራቀሙት ያረጁ ጽሑፎች ወደ ውጭ ይወሰዱና ይቀበራሉ። አይሁዶች እንዲህ የሚያደርጉት ቅዱሳን ጽሑፎቻቸው እንዳይረክሱ ወይም አላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለመከላከል ነበር። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ጽሑፎች በአብዛኛው በእንግሊዝኛ “ጂሆቫ” ወይም በአማርኛው “ይሖዋ” ተብሎ የሚጠራውን ቴትራግራማቶን (አራት ፊደላት ያሉት) ማለትም ቅዱስ የሆነውን የአምላክን ስም የሚወክሉትን የዕብራይስጥ ፊደላት ስለያዙ ነው።
“ዘውዱ”
የጥንቱ የዕብራይስጥ የብራና ጽሑፍ ብዙው ክፍል ከጥንት ዘመን ጀምሮ ምንም ያህል ሳይለወጥ ተላልፏል። ለምሳሌ ኬተር ማለትም “ዘውድ” የተባለ ሁሉንም የመጀመሪያዎቹን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም “ብሉይ ኪዳንን” የያዘ ጠቃሚ የዕብራይስጥ የብራና ጽሑፍ ነበር። እሱም በአብዛኛው የእስላሞች ከተማ በሆነችው በሶሪያ የምትገኝ አሌፖ በተባለች ከተማ አይሁዶች በሚኖሩባት አነስተኛ መንደር ውስጥ በሚገኝ የጥንት ምኩራብ ተጠብቆ ቆይቷል። ጽሑፉ በፊት ኢየሩሳሌም ለሚኖሩ የካራይት አይሁዶች የተተወ ሲሆን በ1099 በመስቀል ጦረኞች ተያዘ። ቆይቶም ጽሑፉ ተመለሰና ወደ ግብጽ ወደ ድሮዋ ካይሮ ተወሰደ። አሌፖ የደረሰው ቢያንስ ቢያንስ በ15ኛው መቶ ዘመን ነበር። የኋላ ኋላም የአሌፖ ኮዴክስ በመባል ይታወቅ ጀመር። ቢያንስ በ930 ከዘአበ የተጻፈው ይህ የብራና ጽሑፍ ስሙ እንደሚያመለክተው የማሶሬቲክ ምሁርነት ቁንጮ ወይም ዘውድ ተደርጎ ይቆጠር ጀመር። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን ጽሑፎች ለማስተላለፍ የተደረገውን ጥንቃቄ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው። በእርግጥም ለዕብራይስጥ ጽሑፍ እንደ ምሳሌ የሚሆን በብራና ላይ የተጻፈ ነው።
በቅርብ ጊዜያት የዚህ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የብራና ጽሑፍ ጠባቂዎች ቅዱሱ ዕቃችን ይረክስብናል በሚል አጉል እምነት የተነሳ ምሑራን እንዲያዩት አይፈቅዱም። ከዚህም በላይ ፎቶግራፍ የተነሳው አንዱ ቅጠል ብቻ እንደመሆኑ መጠን ለጥናት የሚሆን ትክክለኛ ቅጂ ለማተም አልተቻለም።
በ1948 ብሪታንያ ፍልስጥኤምን ለቅቃ ስትወጣ በአሌፖ ውስጥ በአይሁዶች ላይ ረብሻ ተነሳባቸው። ምኩራባቸው ተቃጠለ። ውድ የሆነው ኮዴክስም ጠፋና ተቃጥሏል ተብሎ ተገመተ። ከአሥር ዓመታት በኋላ የጽሑፉ አንድ ሦስተኛ ተርፎ ከሶሪያ ወደ ኢየሩሳሌም በድብቅ እንደተወሰደ ማወቁ ምንኛ አስደናቂ ነው! በመጨረሻም በ1976 ጥሩ የሆኑ 500 ትክክለኛ ቅጂዎች በሙሉ ቀለም ለማተም ተቻለ።
የከፍተኛ ጥንቃቄ የሥራ ውጤት
ይህ የብራና ጽሑፍ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ በመገልበጥና በማስተላለፍ የታወቁ ምሑር በሆኑት በአሮን ቤን አሽር አማካኝነት ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ የሆነው የመጀመሪያው ጽሑፍ ታርሞና ሥርዓተ ነጥቡ ተስተካክሎ የነበረው ወደ 930 ከዘአበ ገደማ ስለነበር ነው። ስለዚህ ወደፊት አነስተኛ ችሎታ ባላቸው ጸሐፊዎች ለሚገለበጡት ቅጂዎች መመሪያ የሚሆናቸው ናሙና የሚሆን ኮዴክስ ነበር።
በመሠረቱ በትልቅ ወረቀት ላይ ያሉ 380 ወረቀቶች (760 ገጾች) የነበሩት ሲሆን በብራናው ገጽ ላይ የተጻፈው በሦስት ዓምዶች ነው። አሁን 294 ወረቀቶች ሲኖሩት የኦሪቶች አብዛኛው ክፍልና የመጨረሻው ክፍል ይጎድሉታል። ይሁን እንጂ ሰቆቃወ ኤርምያስ፣ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን፣ ዳንኤል፣ አስቴር፣ ዕዝራ እና ነህምያ አሉት። ማጣቀሻ ባለው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ላይ “አል” ተብሎ ተጠቅሷል። (ኢያሱ 21:37 የግርጌ ማስታወሻ) በ12ኛው መቶ ዘመን የነበሩ የታወቁ የመካከለኛው ዘመን አይሁዳዊ ምሑር የሆኑት ሙሴ ማይሞኒድስ (እዚህ ስዕሉ ላይ የታዩት) የአሌፖ ኮዴክስ ካዩአቸው ጽሑፎች ሁሉ የላቀው እንደሆነ ተናግረዋል።a
ከ13ኛው እስከ 15ኛው መቶ ዘመን በእጅ የተገለበጡት የዕብራይስጥ ጽሑፎች ከሁለቱ ዋና ዋና ማሶሬቲክ የጽሑፍ ምንጮች ማለትም ከቤን አሽርና ከቤን ናፍታሊ ተደባልቀው የተወሰዱ ነበሩ። በ16ኛው መቶ ዘመን ጃኮብ ቤን ሃዪም ከዚህ የተደባለቀ ምንጭ የተወሰደውን የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ አትመው አወጡት። ይህም ለሚቀጥሉት 400 ዓመታት ለታተሙት የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱሶች መሠረት ሆኖ ቆይቷል።
በ1937 ቢቢሊያ ሂብራይካ (የታተመው የዕብራይስጥ ጽሑፍ) የተባለ ሦስተኛ እትም ከወጣ በኋላ የቤን አሽር የአጻጻፍ ልምድ እንደ ማመሳከሪያ ሆኖ አገልግሏል። ምክንያቱም በሩሲያ ሌኒንግራድ ቢ 19ኤ (B 19A) ተብሎ በሚጠራ ጽሑፍ አማካኝነት ተጠብቆ ቆይቷል። የሌኒንግራዱ ቢ 19ኤ በ1008 ከዘአበ እንደተጻፈ ይገመታል። በኢየሩሳሌም ያለው የዕብራውያን ዩኒቨርሲቲ ከጊዜ በኋላ ሙሉውን የአሌፖ ዕብራይስጥ ጽሑፍ የሙት ባሕር ጥቅሎችን ጨምሮ ከሌሎችም አስፈላጊ የብራና ጽሑፎችና እትሞች ማናበቢያ ጋር ሊያወጣው አቅዷል።
ዛሬ የምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ጥራቱ እምነት የሚጣልበት ነው። በመለኮታዊ አነሳሽነት የተጻፈና አስደናቂ ችሎታ በነበራቸው ጻፎች ገልባጭነት በመቶ ለሚቆጠሩ ዘመናት ሲተላለፍ የቆየ ነው። የእነዚህን ገልባጮች ከፍተኛ ጥንቃቄ በ1947 በሙት ባሕር አጠገብ የተገኘውን የኢሳይያስ ጥቅልና የማሶሬቲክ ጽሑፍን በማወዳደር ለማየት ይቻላል። ምንም እንኳን ይህ የሙት ባሕር ጥቅል በፊት ከነበረው የቆየ ከተባለው የማሶሬቲክ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ሺህ ዓመት የሚበልጥ ቢሆንም እምብዛም ልዩነት አለመገኘቱ የሚያስደንቅ ነው። ከዚህም በላይ አሁን የአሌፖ ኮዴክስን ምሑራን በቀላሉ ሊያገኙት ስለቻሉ ለዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እውነተኛነት እርግጠኛ ለመሆን የበለጡ ተጨማሪ ምክንያቶችን ይሰጣል። በእውነትም “የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—ኢሳይያስ 40:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለጥቂት ዓመታት ያህል አንዳንድ ምሑራን የአሌፖ ኮዴክስ ሥርዓተ ነጥብ በቤን አሽር የተስተካከለ ለመሆኑ ይጠራጠሩ ነበር። ይሁን እንጂ ኮዴክሱ ለጥናት ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ የተገኙት ማስረጃዎች በማይሞኒድስ የተጠቀሰው ጽሑፍ እውነተኛው የቤን አሽር የብራና ጽሑፍ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]
Bibelmuseum, Münster
[በገጽ 29 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]
Jewish Division / The New York Public Library / Astor, Lenox, and Tilden Foundations