የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 9/15 ገጽ 26-29
  • ማሶሬቶች እነማን ናቸው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ማሶሬቶች እነማን ናቸው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የቤን አሽር ቤተሰብ
  • ለየት ያለ የቃል ጥናት ያስፈልግ ነበር
  • ምን ብለው ያምኑ ነበር?
  • ከሥራቸው መጠቀም
  • የማሶሬቲክ ጽሑፍ ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ለዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ናሙና የሚሆን በብራና የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች ከሽፈዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016
  • ከእነዚህ ወንድሞች ምን ትምህርት ታገኛለህ?
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2019
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 9/15 ገጽ 26-29

ማሶሬቶች እነማን ናቸው?

“የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ጠብቆ አቆይቶልናል። (መዝሙር 31:5) ይሁን እንጂ የእውነት ጠላት የሆነው ሰይጣን መጽሐፍ ቅዱስን ለመበከልና ለማጥፋት ጥረት እያደረገ ሳለ መሠረተ ሐሳቡን ሳይለቅ ለእኛ ሊደርሰን የቻለው እንዴት ነው?—ማቴዎስ 13:39ን ተመልከት።

ፕሮፌሰር ሮበርት ጆርዲስ በሰጡት አንድ አስተያየት ላይ ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ከፊል መልስ ልናገኝ እንችላለን፦ “ማሶሬቶች ወይም ‘ወግ ጠባቂዎች’ ተብለው የሚጠሩት ዕብራውያን ጸሐፊዎች ያከናወኑት ተግባር የሚገባውን ያህል አልተደነቀም። እነዚህ ስማቸው ያልተጠቀሱ ጸሐፊዎች ቅዱስ ጽሑፉን ተጨንቀው ተጠበው በከፍተኛ ጥንቃቄ ገልብጠውታል።” በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ ገልባጮች መካከል የአብዛኞቹን ስም ባናውቅም ከማሶሬቶች ወገን የሆኑት የቤን አሽር ቤተሰብ ስም በግልጽ ተመዝግቦ እናገኘዋለን። የቤን አሽር ቤተሰብንና የሥራ ባልደረቦቻቸው የሆኑትን ሌሎች ማሶሬቶች በተመለከተ የምናውቀው ምን ነገር አለ?

የቤን አሽር ቤተሰብ

አይሁዳውያን ጸሐፊዎች ብዙውን ጊዜ ብሉይ ኪዳን ተብሎ የሚጠራውን በመጀመሪያ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በታማኝነት ገልብጠውት ነበር። ከስድስተኛው እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖሩ የነበሩት እነዚህ ጸሐፊዎች ማሶሬቶች ተብለው ይጠሩ ነበር። ሥራቸው ምን ነገሮችን የሚያካትት ነበር?

ለብዙ መቶ ዘመናት የዕብራይስጥ ቋንቋ በተነባቢ ፊደላት ብቻ ይጻፍ ነበር፤ አንባቢው አናባቢ ፊደላትን ጨምሮ ያነብ ነበር። ሆኖም በማሶሬቶች ዘመን ብዙ አይሁዳውያን ቋንቋውን አቀላጥፈው መናገር ስላልቻሉ ትክክለኛው የዕብራይስጥ አነባበብ ጠፍቶ ነበር። በባቢሎንና በእስራኤል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የማሶሬቶች ቡድን በተነባቢ ፊደላት መካከል የሚገቡ የአናባቢ ፊደላትን አነጋገርና ትክክለኛ አነባበብ የሚያመለክቱ የተጻፉ ምልክቶችን ፈለሰፉ። ቢያንስ ሦስት ዘዴዎችን የፈጠሩ ቢሆንም ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ሆኖ የተገኘው በገሊላ ባሕር አቅራቢያ በምትገኘው በጥብርያዶስ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት የቤን አሽር ቤተሰብ የሆኑት ማሶሬቶች ያቀረቡት ነበር።

የተለያዩ የመረጃ ምንጮች በስምንተኛው መቶ ዘመን እዘአ ከነበረው ከአንጋፋው ከአሽር ጀምረው የዚህን ልዩ ቤተሰብ አምስት ትውልዶች ይጠቅሳሉ። ሌሎቹም ነህምያ ቤን አሽር፣ አሽር ቤን ነህምያ፣ ሞሰስ ቤን አሽር እና በመጨረሻም በአሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ የነበረው አሮን ቤን ሞሰስ ቤን አሽር ነበሩ።a እነዚህ ሰዎች የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ አነባበብ በተሻለ መንገድ ይገልጻሉ ብለው የተስማሙባቸውን የተጻፉ ምልክቶች እንደገና በማዘጋጀት ረገድ ግምባር ቀደም ሆነዋል። እነዚህን ምልክቶች ለመፍጠር ለዕብራይስጥ የሰዋስው ሥርዓት መሠረት የሆኑትን ነገሮች ለይተው ማወቅ ነበረባቸው። ከዚያ በፊት የዕብራይስጥን የሰዋስው ሕግጋት የሚገልጽ ተመዝግቦ የሚገኝ የተወሰነ ሥርዓት አልነበረም። ስለዚህ እነዚህ ማሶሬቶች የመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥ ሰዋስው ምሁራን ነበሩ ማለት ይቻላል።

የቤን አሽር ወግ ጠባቂ ቤተሰብ የመጨረሻው ማሶሬት የሆነው አሮን ይህን መግለጫ ለመመዝገብና ለመጻፍ የመጀመሪያው ሰው ነበር። ይህን ያደረገውም “ሴፈር ዲክደኪ ሃቴአሚም” በተሰኘው የዕብራይስጥ የሰዋስው ሕግጋት የመጀመሪያ መጽሐፍ በሆነው ሥራው ላይ ነበር። ይህ መጽሐፍ ለቀጣዮቹ መቶ ዘመናት ለሌሎች የዕብራይስጥ የሰዋስው ምሁራን ሥራዎች መሠረት ሆኗል። ይሁን እንጂ ይህ በጣም ጠቃሚ የሆነው የማሶሬቶች አንድ የሥራ ውጤት ብቻ ነበር። ይህ ሥራ ምን ነበር?

ለየት ያለ የቃል ጥናት ያስፈልግ ነበር

ማሶሬቶች በጣም ያሳስባቸው የነበረው ነገር እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል፣ ፊደሉ እንኳ ሳይቀር የያዘው መልእክት በትክክል መተላለፉ ነበር። ማሶሬቶች መልእክቱን በትክክል ለማስተላለፍ ሲሉ የቀድሞዎቹ ገልባጮች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በጽሑፉ ላይ ያስገቧቸውን ለውጦች የሚጠቁም ማብራሪያ በየገጹ ኅዳጎች ላይ ያሰፍሩ ነበር። በተጨማሪም ማሶሬቶች በእነዚህ የኅዳግ ማስታወሻዎች ላይ በእያንዳንዱ መጽሐፍ ወይም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንደሚገኙ በማመልከት ያልተለመዱ የቃላት ዓይነቶችንና ኅብረ ቃላትን በግልጽ አብራርተዋል። ቦታ ስለማይበቃቸው እነዚህን አስተያየቶች በምሕጻረ ቃላት አስፍረዋቸው ነበር። የጽሑፉን ትክክለኛነት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማረጋገጥ እንደ ተጨማሪ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በማለት የአንዳንድ መጻሕፍትን መሐል ላይ የሚገኝ ቃልና ፊደል ምልክት ያደርጉበታል። በትክክል መገልበጡን ለማረጋገጥ ሲሉ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ፊደል ቆጥረዋል።

ማሶሬቶች በኅዳጉ ላይ በምሕጻረ ቃላት የጻፏቸውን ማስታወሻዎች በተመለከተ በገጹ አናትና ግርጌ በሚገኙት ኅዳጎች ላይ ሰፋ ያሉ አስተያየቶችን አስፍረዋል።b እነዚህ ኅዳጎች የሥራቸውን ትክክለኛነት በተለያዩ ዘዴዎች እንዲያረጋግጡ ረድተዋቸዋል። በዚያ ወቅት ጥቅሶቹ በቁጥር ስላልሰፈሩና የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንሶች ስላልነበሩ ማሶሬቶች እነዚህን የማረጋገጫ ዘዴዎች ለመጠቀም ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ማመሳከር የሚችሉት እንዴት ነበር? በገጹ አናትና ግርጌ በሚገኙት ኅዳጎች ላይ ቃሉ ወይም ቃሎቹ በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የት ቦታ እንደሚገኝ የሚያስታውሳቸውን የአንድ ተመሳሳይ ጥቅስ ክፍል ይጽፋሉ። ብዙውን ጊዜ ቦታ ስለማይበቃቸው እያንዳንዱን ተመሳሳይ ጥቅስ የሚያስታውሳቸውን አንድ ቁልፍ ቃል ብቻ ይጽፉ ነበር። እነዚህ ጽሑፍ ገልባጮች የኅዳግ ማስታወሻዎቹ እንዲጠቅሟቸው ጠቅላላውን የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በቃላቸው ማጥናት የነበረባቸው ይመስላል።

በኅዳጉ ላይ ለመጻፍ የሚያስቸግሩ ረጅም የሆኑ ዝርዝር ሐሳቦች በእጅ ወደ ተገለበጠው ጽሑፍ ሌላ ክፍል ይዛወራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዘፍጥረት 18:3 ዳር በኩል ባለው ኅዳግ ላይ የሰፈረው የማሶሬቲክ ማስታወሻ קלד የሚሉ ሦስት የዕብራይስጥ ፊደላትን ይጠቁማል። ይህ በዕብራይስጥ 134 ቁጥር ማለት ነው። ከማሶሬቶች በፊት የነበሩ ገልባጮች ሆነ ብለው ይሖዋ የተባለውን ስም “ጌታ” በሚለው ቃል በመተካት ከዕብራይስጡ ጽሑፍ ያስወጡባቸውን 134 ቦታዎች የሚጠቁም ዝርዝር ሐሳብ በእጅ ጽሑፉ ግልባጭ መጨረሻ ላይ ይገኛል።c ማሶሬቶች እነዚህን ስሕተቶች ቢያውቁም ለእነሱ የተላለፈላቸውን ጽሑፍ ለመለወጥ አልመረጡም። ከዚህ ይልቅ እነዚህን ለውጦች በኅዳግ ማስታወሻዎቻቸው ላይ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ገልባጮች ጽሑፉን ሲለውጡት ማሶሬቶች ላለመለወጥ በጣም የተጠነቀቁት ለምንድን ነው? እነሱ ይከተሉት ከነበረው የአይሁድ ሃይማኖት የቀድሞዎቹ ገልባጮች ይከተሉት ከነበረው የተለየ ነበርን?

ምን ብለው ያምኑ ነበር?

ማሶሬቶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሱበት በዚህ ዘመን የአይሁድ እምነት ሥር በሰደደ የሥነ ልቦና ጦርነት ውስጥ ነበር። ከመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ጀምሮ ረቢዎች የሚያራምዱት የአይሁድ እምነት ተጽዕኖ እየጨመረ ሄዶ ነበር። ታልሙድና የረቢዎች ትርጓሜዎች በጽሑፍ ሲሰፍሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ከረቢዎች የቃል ሕግ ትርጓሜ ይልቅ አነስተኛ ቦታ የሚሰጠው ሆነ።d ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን ጽሑፍ በጥንቃቄ ጠብቆ ማቆየት ያለው ጠቀሜታ ሊያጣ ይችል ነበር።

በስምንተኛው መቶ ዘመን እዘአ ቀረዓታውያን በመባል የሚታወቅ አንድ ቡድን እንደዚህ ዓይነቱን ሁኔታ ተቃወመ። መጽሐፍ ቅዱስን በግል የማንበብን ጠቀሜታ በማጉላት ሪቢዎች ያላቸውን ሥልጣን፣ ትርጓሜያቸውንም ሆነ ታልሙድን ገሸሽ አደረጉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ጽሑፍ ብቻ እንደ መጨረሻ ባለ ሥልጣናቸው አድርገው ተቀበሉት። ይህ እምነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ይዘቱን ሳይለቅ በትክክል የመተላለፉን አስፈላጊነት እንዲጨምር አድርጓል፤ ይህም ለማሶሬቲክ ጥናቶች በር ከፈተ።

የረቢዎችና የቀረዓታውያን እምነት በማሶሬቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው ምን ያህል ነው? በብራና የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ኤክስፐርት የሆኑት ኤም ኤች ጎሸን ጎትስቲን “ማሶሬቶች የጥንቱን ወግ እንደሚጠብቁና ሆነ ብለው እሱን መለወጣቸው ሊፈጽሙት ከሚችሉት ወንጀል ሁሉ የከፋው ወንጀል እንደሆነ ያምኑ ነበር” በማለት ገልጸዋል።

ማሶሬቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ጽሑፍ በትክክል መገልበጥን እንደ ቅዱስ ተግባር አድርገው ይመለከቱት ነበር። በግላቸው ሌሎች ሃይማኖታዊ ምክንያቶች ሊኖሯቸው ቢችልም የማሶሬቲክ ሥራ በእነዚህ ጉዳዮች የተነካ አይመስልም። እጥር ምጥን ያሉት የኅዳግ ማስታወሻዎች ለሃይማኖታዊ ክርክር አንዳች ቦታ የሚሰጡ አልነበሩም። በሕይወታቸው ውስጥ በጣም የሚያሳስባቸው ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ነበር፤ ሊለውጡት አልፈለጉም።

ከሥራቸው መጠቀም

ሥጋዊ እስራኤላውያን የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች መሆናቸው ቢያከትምም እንኳ እነዚህ አይሁዳውያን ጽሑፍ ገልባጮች የአምላክን ቃል በትክክል ጠብቀው ለማቆየት ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ያዋሉ ነበሩ። (ማቴዎስ 21:42–44፤ 23:37, 38) የቤን አሽር ቤተሰብና ሌሎች ማሶሬቶች ያከናወኗቸው ተግባራት እንዲህ በማለት በጻፉት በሮበርት ጆርዲስ በሚገባ ተገልጿል፦ “እነዚያ ትሑት የሆኑና የማይበገሩ ሠራተኞች . . . ዝናቸው ሳይነዛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ እንዳይጠፋ ወይም እንዳይለወጥ በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ተግባር አከናውነዋል።” (ዘ ቢብሊካል ቴክስት ኢን ዘ ሜኪንግ) በውጤቱም የ16ኛው መቶ ዘመን የተሃድሶ አራማጆች እንደ ነበሩት እንደ ሉተርና ቲንደል ያሉት ሰዎች የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን በተቃወሙበትና መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም ሰው በሚያነባቸው የተለመዱ ቋንቋዎች መተርጎም በጀመሩበት ወቅት ለሥራቸው መሠረት የሚሆን በሚገባ ተጠብቆ የቆየ የዕብራይስጥ ጽሑፍ አግኝተው ነበር።

በዛሬው ጊዜ የማሶሬቶች የሥራ ውጤት እኛንም እየጠቀመን ነው። የዕብራይስጥ ጽሑፋቸው ለአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ሆኗል። ይህ ትርጉም የጥንት ማሶሬቶች ባሳዩት ዓይነት ራስን የመወሰንና መልእክቱን በትክክል ለማስተላለፍ የመጣር መንፈስ ወደ ብዙ ቋንቋዎች መተርጎሙን ቀጥሏል። እኛም ለይሖዋ አምላክ ቃል ትኩረት በመስጠት ተመሳሳይ ዝንባሌ ማሳየት ይኖርብናል።—2 ጴጥሮስ 1:19

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዕብራይስጥኛ “ቤን” ማለት “ልጅ” ማለት ነው። ስለዚህም ቤን አሽር ማለት “የአሽር ልጅ” ማለት ነው።

b በገጹ ዳር በኩል በሚገኙት ኅዳጎች ላይ የሰፈሩት የማሶሬቲክ ማስታወሻዎች ትንሿ ማሶራ ተብለው ይጠራሉ። በገጹ አናትና ግርጌ በሚገኙት ኅዳጎች ላይ የሰፈሩት ማስታወሻዎች ትልቁ ማሶራ ይባላሉ። በእጅ ጽሑፍ ግልባጮች በሌላ ቦታ ላይ የሰፈሩት ዝርዝር ሐሳቦች ደግሞ የመጨረሻው ማሶራ ይባላሉ።

c የባለ ማጣቀሻውን አዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ተጨማሪ መግለጫ (Appendix) 1B ተመልከት።

d የቃል ሕግንና ረቢዎች የሚያራምዱትን የአይሁድ እምነት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣ ይሆን? የተባለውን የእንግሊዝኛ ብሮሹር ከገጽ 8–11 ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለዕብራይስጥ የሚሆን የአነባበብ ሥርዓት

ማሶሬቶች ለአናባቢ ፊደላት የሚሆኑ ምልክቶችንና የድምፅ አወጣጥን የሚጠቁሙ ጭረቶችን ለማስፈር የሚያስችል የተሻለ ዘዴ ለማግኘት ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲመረምሩ ቆይተዋል። ስለዚህ እያንዳንዱ የቤን አሽር ቤተሰብ ትውልድ እድገት ማድረጉን መቀጠሉን መረዳት አያስደንቅም። በአሁኑ ወቅት የሚገኙት የእጅ ጽሑፍ ግልባጮች የመጨረሻዎቹ ማሶሬቶች የሆኑትን የቤን አሽር ቤተሰብ አባላት የሞሰስና የአሮንን የአጻጻፍ ስልቶችና ዘዴዎች ብቻ የሚወክሉ ናቸው።e እነዚህን የእጅ ጽሑፍ ግልባጮች በማነጻጸር የተካሄደው ጥናት አሮን ከአባቱ ከሙሴ ጋር አንዳንድ ጥቃቅን ልዩነቶች ያሏቸውን የቃላት አነባበቦችና ምልክቶች የሚወስኑ ሕግጋትን እንደፈጠረ ያሳያል።

ቤን ናፍታላይ በአሮን ቤን አሽር ዘመን የነበረ ሰው ነው። የካይሮው የሞሰስ ቤን አሽር ኮዴክስ ቤን ናፍታላይ የሠራቸው ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ብዙ አነባበቦችን የያዘ ነው። ስለዚህ ወይ ቤን ናፍታላይ ከሞሰስ ቤን አሽር ጋር አጥንቷል አሊያም ሁለቱም አንድ በጣም ጥንታዊ የሆነ ወግ ጠብቀው አቆይተዋል። ብዙ ምሁራን በቤን አሽርና በቤን ናፍታላይ የአጻጻፍ ስልቶች መካከል ያለውን ልዩነት ቢናገሩም ጎሸን ጎትሲን እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በቤን አሽር ቤተሰብ ውስጥ ያሉትን ሁለት ክፍሎች ጠቅሶ የአነባበቦችን ልዩነት ማነጻጸር ቤን አሽርን ከቤን አሽር ጋር ከማወዳደር ብዙም አይለይም።” ስለዚህ የቤን አሽርን የአጻጻፍ ስልቶች ብቻ ጠቅሶ መናገር ትክክል አይሆንም። የአሮን ቤን አሽር የአጻጻፍ ስልቶች ተቀባይነት ያገኙት ከሌሎች ስልቶች ብልጫ ስለነበራቸው አይደለም። የአሮን ቤን አሽር ጽሑፍ የተመረጠው የ12ኛው መቶ ዘመን የታልሙድ ምሁር የነበረው ሞሰስ ማይሞኒደስ ስላደነቀለት ብቻ ነበር።

[ሰንጠረዥ]

አናባቢ ነጥቦችና የድምፅ አወጣጥን የሚያመለክቱ ጭረቶች የተደረጉበትና ያልተደረጉበት ዘጸአት 6:2 በከፊል

[የግርጌ ማስታወሻ]

e የመጀመሪያዎቹንና የኋለኞቹን የነቢያት መጻሕፍት የያዘው የካይሮው ኮዴክስ (895 እዘአ) ለሞሰስ የአጻጻፍ ስልቶች ምሳሌ ይሆናል። የአሌፖ (930 እዘአ ገደማ) እና የሌኒንግራድ (1008 እዘአ) ኮዴክሶች ለአሮን ቤን አሽር የአጻጻፍ ስልቶች ምሳሌዎች እንደሚሆኑ ይገመታል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥብርያዶስ ከስምንተኛው እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን ድረስ የማሶሬቶች እንቅስቃሴ ማዕከል ነበረች

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ