ሚሽና እና ለሙሴ የተሰጠው የአምላክ ሕግ
“ርዕሱ ምን እንደሆነ ለመረዳት አዳጋች በሆነብንና ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ በነበረ አንድ ውይይት ውስጥ የገባን በሚመስል ስሜት እንጀምራለን . . .። በርቀት በሚገኝ አንድ የአውሮፕላን ማረፊያ የተሳፋሪዎች መቆያ ክፍል ውስጥ እንዳለን ሆኖ . . . ይሰማናል። ሰዎቹ የሚናገሯቸውን ቃላት እናውቃቸዋለን፤ ነገር ግን ቃላቱ ያዘሉት ትርጉም ወይም ሰዎቹ የሚያሳስባቸው ነገርና ከሁሉም በላይ ደግሞ በድምፃቸው ውስጥ የሚንጸባረቀው የጥድፊያ ስሜት ያደነጋግረናል።” አይሁዳዊው ምሁር ጄኮብ ኖይስነር አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሚሽናን ሲያነብ ሊሰማው የሚችለውን ስሜት የገለጹት ከላይ ያለውን በማለት ነበር። ኖይስነር አክለው ሲናገሩ “ሚሽና ይህ ነው የሚባል መግቢያም ሆነ መደምደሚያ የለውም” ብለዋል።
ዳንየል ጄረሚ ሲልቨር ኤ ሂስትሪ ኦቭ ጁዳይዝም (የአይሁድ እምነት ታሪክ) በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ሚሽናን “የረቢዎች የአይሁድ እምነት መሠረታዊ ጽሑፍ” ብለው ጠርተውታል። እንዲያውም “ሚሽና መጽሐፍ ቅዱስን በመተካት ቀጣይ ለሆነው [የአይሁዶች] ትምህርት ዋነኛ ሥርዓተ ትምህርት ሆኗል” ብለዋል። እንደዚህ ያለው ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ መጽሐፍ ይህን ያህል ተፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አንዱ ምክንያት በሚሽና ውስጥ በሚገኘው በሚከተለው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል:- “ሙሴ በሲና ተራራ ቶራህን ተቀብሎ ለኢያሱ ሰጠው፣ ኢያሱ ለሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ሽማግሌዎች ለነቢያት ሰጡት። ነቢያት ደግሞ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች አስረከቡት።” (አቮት 1:1) ሚሽና፣ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ከተቀበለውና አምላክ ለእስራኤላውያን ከሰጣቸው ሕግ ውስጥ በጽሑፍ ያልሰፈረውን መረጃ እንደያዘ ይገልጻል። በታላቁ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች (በኋላ ላይ ሳንሄድሪን የተባሉት) የተወሰኑ ትምህርቶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል የሚያስተላልፉ ጥበበኛ የሆኑ ሃይማኖታዊ ምሁራን ወይም አዋቂዎች ተደርገው ይታዩ ነበር። በመጨረሻ እነዚህ ትምህርቶች በሚሽና ላይ ተመዝግበዋል። ይሁን እንጂ ይህ ተአማኒነት ያለው ነው? ሚሽናን የጻፈው ማን ነው? ለምንስ? በውስጡ የሰፈረው ነገር ሙሴ በሲና ተራራ የተቀበለው ቃል ነውን? በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛስ ትርጉም ያለው ነገር ነውን?
ቤተ መቅደስ አልባ የሆነ የአይሁድ እምነት
ቅዱሳን ጽሑፎች በመንፈስ አነሳሽነት እየተጻፉ በነበረበት ጊዜ በጽሑፍ ከሰፈረው የሙሴ ሕግ በተጨማሪ መለኮታዊ የቃል ሕግ የሚባል ነገር አልነበረም።a (ዘጸአት 34:27) ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ይህን ፅንሰ ሐሳብ ያዳበረውና ያስፋፋው በአይሁዳውያን እምነት ውስጥ የሚገኘው የፈሪሳውያን ቡድን ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ሰዱቃውያንና ሌሎች አይሁዳውያን ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ትምህርት ተቃውመው ነበር። ይሁን እንጂ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ የአይሁድ አምልኮ ማዕከል ሆኖ እስከ ቀጠለ ድረስ ስለ ቃል ሕግ የሚነሳው ጥያቄ ያን ያህል አወዛጋቢ አልነበረም። በቤተ መቅደሱ ይከናወን የነበረው አምልኮ ለእያንዳንዱ አይሁዳዊ ሕይወት ቋሚ ሥርዓትንና የተወሰነ መረጋጋትን የሚሰጥ ነበር።
ይሁን እንጂ የአይሁድ ብሔር በ70 እዘአ ይህ ነው ተብሎ የማይገመት ሃይማኖታዊ ቀውስ ውስጥ ገባ። የሮማውያን ጦር ሠራዊት ኢየሩሳሌምን በማውደም ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ አይሁዳውያንን ገደለ። የመንፈሳዊ ሕይወታቸው ማዕከል የነበረው ቤተ መቅደስ ጠፋ። በቤተ መቅደሱ ውስጥ መሥዋዕት እንዲቀርብና ክህነታዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚጠይቀውን የሙሴን ሕግ ጠብቆ መኖር የማይቻል ነገር ሆነ። የአይሁድ እምነት የመሠረት ድንጋይ ፈራረሰ። የታልሙድ ምሁር የሆኑት ኤዲን ስታይንሳልትስ “በ70 እዘአ በደረሰው . . . ጥፋት ሳቢያ የሃይማኖታዊውን ሕይወት አጠቃላይ ሥረ መሠረት እንደገና መገንባቱ አጣዳፊ ጉዳይ ሆኖ ነበር” በማለት ጽፈዋል። ስለዚህም እንደገና እንዲገነባ ተደርጓል።
የፈሪሳውያን መሪ የነበሩት የሂለል የተከበሩ ደቀ መዝሙር የሆኑት ዮሃናን ቤን ዛካይ ገና ቤተ መቅደሱ ከመጥፋቱ በፊት የአይሁድ እምነት መንፈሳዊ ማዕከልንና ሳንሄድሪንን ከኢየሩሳሌም ወደ ያቭኔህ ለማዛወር ከቬስፓሲያን (ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ሊሆን ከነበረው) ፈቃድ አግኝተው ነበር። ዮሃናን ቤን ዛካይ ከኢየሩሳሌም ውድመት በኋላ “ቤተ መቅደሱ በመጥፋቱ ምክንያት ለሕዝቡ አዲስ ማዕከል የማቋቋምና ሕዝቡ ከተፈጠሩት አዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ራሱን አስማምቶ ሃይማኖታዊ ቅናቱን ወደ ሌላ የትኩረት አቅጣጫ እንዲያዞር የመርዳት ተፈታታኝ ሁኔታን መጋፈጥ ነበረባቸው” በማለት ስታይንሳልትስ ገልጸዋል። ይህ አዲስ የትኩረት አቅጣጫ የቃሉ ሕግ ነበር።
ቤተ መቅደሱ ከወደመ በኋላ ሰዱቃውያንና ሌሎች የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች አሳማኝ የሆነ አማራጭ አላቀረቡም። ፈሪሳውያን፣ ተቃዋሚዎችን በማቀፍ የአይሁድ ዋና ግንባር ሆኑ። ግንባር ቀደም የነበሩት ረቢዎች ለአንድነት ትልቅ ትኩረት በመስጠት ወገናዊነትን በሚያንጸባርቀውና ከፋፋይ የሆነ አንድምታ ባለው ፈሪሳዊ በሚለው ቃል ራሳቸውን መጥራት አቆሙ። ረቢዎች ማለትም “የእስራኤል አዋቂዎች” ተብለው መጠራት ጀመሩ። እነዚህ አዋቂዎች የቃሉን ሕግ ለማጠናቀር የሚያስችላቸውን አንድ የሃይማኖት ሥርዓት አቋቋሙ። ይህ የሃይማኖት ሥርዓት ሰዎች በሚፈጽሙት ጥቃት እንደ ቤተ መቅደሱ በቀላሉ ሊጎዳ የማይችል መንፈሳዊ መዋቅር ይሆናል።
የቃል ሕጉን ማጠናቀር
በወቅቱ ዋነኛ ማዕከል የነበረው በያቭኔህ (ከኢየሩሳሌም በስተ ምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር) የሚገኘው የረቢዎች አካዳሚ ቢሆንም የቃሉን ሕግ የሚያስተምሩ ሌሎች አካዳሚዎች በመላው እስራኤልና እንዲያውም እስከ ባቢሎንና ሮም ድረስ ማቆጥቆጥ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ይህ አንድ ችግር ፈጠረ። ስታይንሳልትስ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሁሉም አዋቂዎች አንድ ላይ እስከተሰባሰቡና ዋነኛው የማስተማር ሥራ [በኢየሩሳሌም በሚገኝ] በአንድ የሰዎች ቡድን መከናወኑን እስከ ቀጠለ ድረስ የባህል አንድነት ተጠብቆ ሊቆይ ይችል ነበር። ነገር ግን የአስተማሪዎች መብዛትና የተለያዩ ትምህርት ቤቶች መቋቋም . . . ከመጠን ያለፈ ብዛት ያላቸው ፎርሙላዎችና የአገላለጽ ዘዴዎች እንዲኖሩ አድርጓል።”
የቃሉ ሕግ መምህራን ታናይም ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ቃሉ ከአረማይክ የተገኘና “ማጥናት፣” “መድገም” ወይም “ማስተማር” የሚል ትርጉም ያለው ነው። ይህ ብዙ ጊዜ በመደጋገምና በመሸምደድ የቃልን ሕግ የመማርና የማስተማር ዘዴያቸውን የሚያጎላ ነው። የቃል ወጎችን በአእምሯቸው ሸምድደው ለመያዝ እንዲችሉ እያንዳንዱ ድንጋጌ ወይም ወግ አጭርና ግልጽ ሐረግ እንዲሆን ይደረግ ነበር። በጣም ጥቂት ቃላት ያሉት ከሆነ ለመሸምደድ ይቀላል። አንድ ዓይነት ቅላጼ ያላቸው ግጥሞች እንዲሆኑ በማድረግ ሐረጎቹን ያነበንቧቸዋል ወይም ያዜሟቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ድንጋጌዎች በሥርዓት ያልተቀመጡ ከመሆናቸውም በላይ እንደየአስተማሪው የተለያዩ ነበሩ።
ለእነዚህ የተለያዩ በርካታ የቃል ወጎች ወጥ የሆነ ቋሚ ቅርጽ የሰጡት የመጀመሪያው ረቢ አኪቫ ቤን ጆሴፍ (50–135 እዘአ ገደማ) ናቸው። ስታይንሳልትስ እኚህን ሰው አስመልክተው ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል:- “በጊዜያቸው የነበሩ ሰዎች የእኚህን ሰው ሥራ ቅርጫቱን ይዞ ወደ እርሻ ቦታ በመሄድ አልፎ አልፎ የሚያገኘውን ማንኛውንም ነገር ሰብስቦ ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ የሰበሰበውን ነገር በዓይነት በዓይነቱ ከሚያስቀምጥ ከአንድ ሞያተኛ ተግባር ጋር አመሳስለውታል። አኪቫ ብዛት ያላቸውን በሥርዓትና በቅደም ተከተል ያልተቀመጡ ርዕሰ ጉዳዮችን በማጥናት በተለያዩ ክፍሎች ከፋፍለው አስቀምጠዋቸዋል።”
ኢየሩሳሌም ከወደመች ከ60 ዓመታት በኋላ በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ አይሁዳውያን ለሁለተኛ ጊዜ የሮም መንግሥትን በመቃወም በባር ኮክባ የተመራ ከፍተኛ ዓመፅ አካሄዱ። ዓመፃቸው እንደገና ጥፋት አስከተለባቸው። አኪቫንና የእርሳቸው ደቀ መዛሙርት የነበሩትን አብዛኞቹን ሰዎች ጨምሮ አንድ ሚልዮን የሚሆኑ አይሁዳውያን የጥፋቱ ሰለባ ሆኑ። ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ሃድሪያን ቤተ መቅደሱ የጠፋበትን ቀን ለማክበር ካልሆነ በስተቀር አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይገቡ በመከልከሉ ምክንያት ቤተ መቅደሱን እንደገና ለመገንባት የነበረው ተስፋ ጨለመ።
ከአኪቫ በኋላ የነበሩት ታናይሞች በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ ፈጽሞ አይተውት አያውቁም። ይሁን እንጂ የቃል ሕጉን ወጎች የሚያጠኑበት አንድ ወጥ ሥርዓት ለእነሱ “ቤተ መቅደስ” ወይም የአምልኮ ማዕከል ሆኖላቸው ነበር። በአኪቫና በደቀ መዛሙርቱ የተጀመረውን የቃል ሕጉን የማደራጀት ሥራ የመጨረሻው ታናይም የሆኑት ጁዳ ሃ-ናሲ ተረከቡት።
ሚሽና የተጠናቀረባቸው ነገሮች
ጁዳ ሃ-ናሲ የሂለልና የገማልያል ዝርያ ናቸው።b ሰውየው የተወለዱት ባር ኮክባ ባስነሳው ዓመፅ ወቅት ሲሆን በሁለተኛው መቶ ዘመን ማብቂያና በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ላይ በእስራኤል የአይሁድ ማኅበረሰብ መሪ ሆነዋል። “ልዑል” የሚል ትርጉም ያለው ሃ-ናሲ የሚለው ማዕረግ ጁዳ በአይሁዳውያን ወገኖቻቸው ዘንድ የነበራቸውን ክብር የሚያመለክት ነው። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ ረቢ ብቻ ተብለው ይጠራሉ። ጁዳ ሃ-ናሲ በመጀመሪያ በቤት ሺአሪምና በኋላ ደግሞ በገሊላ ከተማ በምትገኘው በሰፎሪስ መንደር በመሆን የራሳቸው ትምህርት ቤት እና የሳንሄድሪን መሪ ሆነው ሠርተዋል።
ጁዳ ሃ-ናሲ ወደፊት ከሮም ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶች የቃሉ ሕግ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተተላለፈ እንዳይሄድ እንቅፋት ሊሆኑበት ይችላሉ ብለው በማሰብ ሕጉ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያስችለውን አንድ ወጥ የሆነ ቅርጽ ለመስጠት ቆርጠው ተነሱ። በእሳቸው ዘመን ታዋቂ የነበሩ ምሁራንን በአካዳሚያቸው ሰበሰቡ። በቃል ሕጉ ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ነጥብና ወግ ክርክር ተካሄደበት። የእነዚህ ውይይቶች ማጠቃለያ ሐሳቦች በሚያስደንቅ ሁኔታ አጫጭር በሆኑ ሐረጎች ውስጥ ተካተው የዕብራይስጥን ቅኔያዊ ስልት በጥብቅ የተከተለ ድርሰት ሆኑ።
እነዚህ የማጠቃለያ ሐሳቦች እንደየአርዕስታቸው በስድስት ዋና ዋና ክፍሎች ወይም መደቦች የተደራጁ ናቸው። ጁዳ እነዚህን በስድስት ክፍሎች የተደራጁ የማጠቃለያ ሐሳቦች 63 ትንንሽ መጻሕፍት አድርገው ከፋፈሏቸው። መንፈሳዊው ሕንፃ አሁን ተጠናቀቀ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ እነዚህን የመሳሰሉ ወጎች የሚተላለፉት በቃል ነበር። ነገር ግን ለቃሉ ሕግ ተጨማሪ ጥበቃ ለማድረግ ሲባል የመጨረሻውን የለውጥ እርምጃ በመውሰድ ሁሉም ነገር በጽሑፍ እንዲሰፍር ተደረገ። ይህ የቃሉን ሕግ አካቶ የያዘው አስደናቂ አዲስ ወጥ ጽሑፍ ሚሽና ተብሎ ተጠራ። ሚሽና የሚለው ስም የመጣው “መድገም፣” “ማጥናት” ወይም “ማስተማር” የሚል ትርጉም ካለው ሻና ከተባለው መሠረታዊ የዕብራይስጥ ቃል ነው። የሚሽና መምህራን ይጠሩበት የነበረው ታናይም የሚለው ቃል ከተገኘበት ቲና ከሚለው የአረማይክ ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሚሽና የተዘጋጀው አንድ ቋሚ የሆነ ደንብ ለማቋቋም ተብሎ አይደለም። ሚሽናን የሚያነብ ሰው መሠረታዊ የሆኑ ሥርዓቶችን ያውቃል ተብሎ ስለሚገመት ሚሽና ይበልጥ የሚያወሳው ከመሠረታዊ ሥርዓቶች ውጭ ስለሆኑ ነገሮች ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሚሽና በጁዳ ሃ-ናሲ ዘመን በረቢዎች አካዳሚዎች ውስጥ ይወያዩባቸውና ያስተምሯቸው የነበሩትን ትምህርቶች ጠቅለል ባለ መልኩ የያዘ ነው። ሚሽና የተዘጋጀው ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል የቃሉ ሕግ ንድፍ እንዲሁም ወደፊት ተጨማሪ ሐሳቦች ለማዳበር የሚያስችል መነሻ ወይም የመሠረት ድንጋይ እንዲሆን ታስቦ ነው።
ሚሽና ሙሴ በሲና ተራራ የተቀበለውን ነገር ከመግለጽ ይልቅ የፈሪሳውያን ፅንሰ ሐሳብ ስለሆነው ስለ ቃሉ ሕግ እድገት ጥልቀት ያለው ማብራሪያ ይሰጣል። በሚሽና የተመዘገበው መረጃ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገኙ መግለጫዎችና በኢየሱስ ክርስቶስና በፈሪሳውያን መካከል በተደረጉ አንዳንድ ውይይቶች ላይ አነስተኛ ብርሃን ይፈነጥቃል። ይሁን እንጂ በሚሽና ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች የሚያንጸባርቁት ከሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ወዲህ ያለውን የአይሁዳውያንን አመለካከት ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሚሽና በሁለተኛው የቤተ መቅደስ ዘመንና በታልሙድ መካከል የሚገኝ ድልድይ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣ ይሆን? የተባለውን የእንግሊዝኛ ብሮሹር ከገጽ 8-11 ተመልከት።
b በሐምሌ 15, 1996 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የሚገኘውን “ገማልያል የጠርሴሱን ሳውል አስተምሮታል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሚሽና ክፍሎች
ሚሽና በስድስት ክፍሎች የተከፋፈለ ነው። እነዚህ ክፍሎች በምዕራፎችና በሚሽናዮት ወይም በአንቀጾች (በቁጥሮች ሳይሆን) የተከፋፈሉ 63 ትናንሽ መጻሕፍት የያዙ ናቸው።
1. ዜራይም (ግብርና ነክ ሕጎች)
እነዚህ ትናንሽ መጻሕፍት ምግብንና እርሻን አስመልክቶ ስለሚቀርቡ ጸሎቶች ይገልጻሉ። በተጨማሪም ስለ አሥራት፣ ስለ ካህናት ድርሻ፣ ስለ ቃርሚያ እና ስለ ሰንበት ዓመታት የሚገልጹ መመሪያዎችን ይዘዋል።
2. ሞኤድ (የተቀደሱ ወቅቶች፣ በዓላት)
በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ መጻሕፍት ከሰንበት፣ ከሥርየት ቀንና ከሌሎች በዓላት ጋር የሚዛመዱ ሕጎችን ይዘረዝራሉ።
3. ናሺም (ሴቶች፣ የጋብቻ ሕግ)
እነዚህ ትናንሽ መጻሕፍት ስለ ጋብቻና ፍቺ፣ ስለ ስለት፣ ስለ ናዝራውያን እና ምንዝር እንደፈጸመ ስለ ተጠረጠረ ሰው የሚገልጹ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዘዋል።
4. ነዚኪን (ካሳዎችና የፍትሐ ብሔር ሕግ)
በዚህ ክፍል ሥር የሚገኙት ትናንሽ መጻሕፍት ስለ ፍትሐ ብሔርና ስለ ንብረት ሕግ፣ ስለ ፍርድ ቤቶችና መቀጮዎች፣ ስለ ሳንሄድሪን አሠራር፣ ስለ ጣዖት አምልኮ፣ ስለ መሐላ እና ስለ አባቶች (አቮት) የሥነ ምግባር ደንብ የሚገልጹ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚሸፍኑ ናቸው።
5. ኮዳሺም (መሥዋዕቶች)
እነዚህ ትናንሽ መጻሕፍት ከእንስሳና ከእህል መሥዋዕቶች ጋር የተዛመዱ ሥርዓቶችንና ስለ ቤተ መቅደሱ ወርድና ስፋት የሚገልጹ ሐሳቦችን የያዙ ናቸው።
6. ቶሃሮት (የመንጻት ሥነ ሥርዓቶች)
ይህ ክፍል ስለ ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥነ ሥርዓት፣ ሰውነትን ስለ መታጠብ፣ እጆችን ስለ መታጠብ፣ ስለ ቆዳ በሽታዎች እና ስለ ተለያዩ የረከሱ እቃዎች የሚናገሩ ትናንሽ መጻሕፍትን ያካተተ ነው።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሚሽና እና የክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች
ማቴዎስ 12:1, 2:- “በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። ፈሪሳውያንም አይተው:- እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት።” የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያደረጉትን ነገር አይከለክሉም። ይሁን እንጂ ረቢዎች በሰንበት ቀን እንዳይደረጉ የከለከሏቸው 39 ተግባራት በሚሽና ውስጥ ተዘርዝረው እናገኛለን።—ሻባት 7:2
ማቴዎስ 15:3:- “እርሱም [ኢየሱስም] መልሶ እንዲህ አላቸው:- እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?” ሚሽና እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንደነበራቸው ያረጋግጥልናል። (ሳንሄድሪን 11:3) እንዲህ እናነባለን:- “ይበልጥ [ሊከበር] የሚገባው [በጽሑፍ የሰፈረው] የሕግ ቃል ሳይሆን የጻፎች ቃል ነው። አንድ ሰው ‘ክታቦችን የማሰር ግዴታ የለም’ ብሎ በመናገር የሕጉን ቃል ቢጥስ ጥፋተኛ አይሆንም፤ [ነገር ግን] ‘እነዚህ ክታቦች ለአምስት መከፋፈል አለባቸው’ በማለት በጻፎች ቃል ላይ ጨምሮ ቢናገር ጥፋተኛ ይሆናል።”—ዘ ሚሽና በኸርበርት ዳንቢ፣ ገጽ 400
ኤፌሶን 2:14:- “እርሱ [ኢየሱስ] ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን ያፈረሰ።” ሚሽና “በቤተ መቅደሱ ጉብታ ላይ አሥር ጋት ከፍታ ያለው አንድ አጥር (ሶሬግ) ነበረ” ይላል። (ሚዶት 2:3) አሕዛብ ይህን ቦታ በማለፍ ወደ ውስጠኛው አደባባይ እንዳይገቡ ተከልክለው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ግድግዳው ከመፍረሱ በፊት በ60 ወይም በ61 እዘአ ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍ ይህን ግድግዳ በምሳሌያዊ መንገድ መጥቀሱ ይሆናል። ምሳሌያዊው ግድግዳ አይሁዶችንና አሕዛብን ለረዥም ጊዜ ለያይቶ የነበረው የሕጉ ቃል ኪዳን ነበር። ይሁን እንጂ በ33 እዘአ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ይህ ግድግዳ ተወግዷል።