የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 4/15 ገጽ 10-14
  • ታላቅ ሥራ አከናውኖ ያለፈ መጽሐፍ አታሚ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታላቅ ሥራ አከናውኖ ያለፈ መጽሐፍ አታሚ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተሻሻለ ቨልጌት
  • የንጉሡ መጽሐፍ አታሚ
  • ሰርቦኒ ተሐድሶውን ተቃወመ
  • የሰርቦኒ ጥቃቶች
  • ሃይማኖታዊ ምሁራን በመጽሐፍ ቅዱሶቹ ላይ እገዳ ጣሉበት
  • በመናፍቅነት ተከሰሰ
  • የውጪ አገር ተወላጁ መጽሐፍ አታሚ
  • ታስታውሳለህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • በምዕራፍና በቁጥር መጽሐፍ ቅዱስን የከፋፈለው ማን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • በርካታ ቋንቋዎችን የያዘው የኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ የትርጉም መሣሪያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 4/15 ገጽ 10-14

ታላቅ ሥራ አከናውኖ ያለፈ መጽሐፍ አታሚ

አንድ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማውጣት ፈልገህ ቦታው ጠፍቶብህ ያውቃልን? ሆኖም አንድ ቃል ብቻ በማስታወስ በመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንስ ተጠቅመህ ጥቅሱን አግኝተኸው ይሆናል። ወይም ደግሞ የተጠቀሰውን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው በጥቂት ሰኮንዶች ውስጥ ገልጠው ማንበብ የሚችሉ በመቶዎች እንዲያውም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያሉበት አንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ ይሆናል።

በሁለቱም ሁኔታዎች ቢሆን ምናልባት አንተ የማታውቀው የአንድ ሰው ውለታ አለብህ። ሰውዬው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ቀላል እንዲሆን ከማድረጉም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱሶች እንዲኖረን በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል። በብዙ መጽሐፍ ቅዱሶች ቅንብር ላይም ለውጥ አምጥቷል።

ይህ ሰው ሮበርት ኤቲን ነው።a በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ገደማ በፈረንሳይ አገር በፓሪስ ውስጥ ይኖር የነበረ ከአንድ መጽሐፍ አታሚ የተወለደ መጽሐፍ አታሚ ነበር። ጊዜው ሥነ ጽሑፍ የተስፋፋበትና የተሐድሶ ዘመን ነበር። የጽሑፍ ማተሚያ ሥነ ጽሑፍን ለማስፋፋትና ተሐድሶን ለማራመድ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። የሮበርት አባት ኤንሪ ኤቲን በዚህ ሥነ ጽሑፍ በተስፋፋበት ዘመን የወጡትን አንዳንድ ምርጥ መጻሕፍት በማተም በጣም የታወቀ መጽሐፍ አታሚ ነበር። ሥራው በፓሪስ ዩኒቨርሲቲና በመንፈሳዊ ትምህርት ቤቱ ማለትም ሰርቦኒ ያሉትን የቀለም ትምህርትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥራዎች የሚጨምር ነበር።

ይሁን እንጂ በልጁ በሮበርት ኤቲን ላይ እናተኩር። ስለ መደበኛ ትምህርቱ ብዙም የሚታውቅ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ከልጅነቱ አንስቶ ላቲን አቀላጥፎ ይናገር ነበር፤ ከዚህ ብዙም ሳይቆይ የግሪክና ዕብራይስጥ ቋንቋዎችን ጭምር ተማረ። ሮበርት ከአባቱ የኅትመት ሥራ ተማረ። ሮበርት ኤቲን በ1526 የአባቱን የኤንሪን ማተሚያ ሲረከብ በከፍተኛ የቋንቋ ምሁርነት ይታወቅ ነበር። ምንም እንኳ በላቲን ሥነ ጽሑፎች ላይ የተደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎችንና ሌሎች ምሁራዊ ሥራዎችን ቢያትምም ቅድሚያ የሚሰጠውና ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ለመጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ኤቲን በጥንታዊ የላቲን ቋንቋ ተዘጋጅቶ የነበረውን የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ የተሟላ ለማድረግ ጉጉት ስለነበረው በአምስተኛው መቶ ዘመን ከነበረው ከመጀመሪያው የጀሮም የላቲን ቨልጌት መጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተቻለ መጠን እንዲቀራረብ ለማድረግ የላቲን መጽሐፍ ቅዱስን እንደገና ማስተካከል ጀመረ።

የተሻሻለ ቨልጌት

ጀሮም የተተረጎመው ከመጀመሪያው የዕብራይስጥና የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር፤ ይሁን እንጂ በኤቲን ዘመን ቨልጌት ለአንድ ሺህ ዓመት ቆይቶ ነበር። ቨልጌት ለብዙ ትውልዶች በእጅ ሲገለበጥ ቀስ በቀስ ብዙ ስሕተቶችና የተዛቡ ሐሳቦች ገብተውበት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት በመካከለኛው ዘመን ወቅት በገቡባቸው የመካከለኛው ዘመን አፈ ታሪኮች፣ በራስ አገላለጽ በተተረጎሙ ሐሳቦችና በተጨመሩባቸው የሐሰት ጥቅሶች ተበርዘው ነበር። እነዚህ ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር በጣም ከመደባለቃቸው የተነሣ በመንፈስ አነሣሽነት እንደተጻፉት ጽሑፎች ተደርገው ተቀባይነት ማግኘት ጀምረው ነበር።

ኤቲን የመጀመሪያ ያልሆኑትን በሙሉ ለማጥራት ሲል ጥንታዊ ሥነ ጽሑፎችን ለማጥናት ያገለግል የነበረውን ዘዴ ይጠቀም ነበር። ያሉትን ይበልጥ የቆዩና የተሻሉ በእጅ የተጻፉ ጽሑፎች ፈልጎ አገኘ። በፓሪስ ውስጥና በአካባቢዋ ባሉ ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም እንደ ኤቭረና ሷሶ ባሉ ቦታዎች ብዙ በእጅ የተጻፉ የጥንት ጽሑፎችን አገኘ፤ ካገኛቸው ጽሑፎቹ ውስጥ አንዱ በስድስተኛው መቶ ዘመን እንደተጻፈ ይገመታል። ኤቲን የተለያዩ የላቲን ጽሑፎችን አንድ ባንድ በጥንቃቄ አወዳደረና ይበልጥ አሳማኝ የሆኑትን ብቻ መረጠ። የኤቲን መጽሐፍ ቅዱስን ያስገኘ ሥራው ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1528 ነበር፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ እመርታ ነበር። ኤቲን ሌሎች የተሻሻሉ እትሞችን ማውጣቱን ቀጠለ። ከእሱ በፊት የነበሩ ሌሎች ሰዎች ቨልጌትን ለማረም ቢጥሩም ለጥናት የሚረዱ ውጤታማ የሆኑ የግርጌ ማስታወሻዎችን በማቅረብ ረገድ የእሱ የመጀመሪያ እትም ነበር። ኤቲን አንዳንድ አጠራጣሪ ክፍሎችን የተወባቸውን ወይም ከአንድ በላይ አነባበብ ያለባቸውን ቦታዎች በሕዳጉ ላይ ጠቁሟል። በተጨማሪም እነዚህን እርማቶች ለማድረግ ያስቻሉትን በእጅ የተጻፉ ጽሑፎች ጠቅሷል።

ኤቲን ለ16ኛው መቶ ዘመን በጣም አዲስ የሆኑ ብዙ ሌሎች ገጽታዎችን አስተዋውቋል። በአዋልድ መጻሕፍትና በአምላክ ቃል መካከል ያለው ልዩነት እንዲታወቅ አድርጓል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ከወንጌሎች በኋላና ከጳውሎስ ደብዳቤዎች በፊት አስቀምጦታል። አንባብያን የተወሰኑ ክፍሎችን ለይተው ለማውጣት እንዲችሉ ለመርዳት በገጹ አናት ላይ ጥቂት ቁልፍ ቃላትን አቅርቧል። ይህ ሥራው በአሁኑ ወቅት በየገጹ አናት የሚጻፍ ርዕስ እንደምንለው ዓይነት ከሆኑት በጣም ጥንታዊ ምሳሌ ነው። ከጀርመን የመጣውን እጅግ የተራቀቀ ወይም ጋደል ያለ ደማቅ ፊደል ከመጠቀም ይልቅ በጣም ደማቅ ባልሆኑና ለንባብ በሚቀሉ የላቲን ፊደሎች ተጠቅሞ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በማተም ረገድ ኤቲን የመጀመሪያ ሰው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ክፍሎችን ለማብራራት ብዙ የሕዳግ ማጣቀሻዎችንና የቋንቋ መግለጫዎችን አቅርቧል።

የኤቲን መጽሐፍ ቅዱስ ከየትኛውም የቨልጌት እትም የተሻለ በመሆኑ ምክንያት የብዙ እውቅ ሰዎችንና የሃይማኖት ሊቃውንትን አድናቆት አትርፎለት ነበር። እትሙ በውበት፣ በአሠራርና በአጠቃቀም ረገድ ሞዴል ሆነና ብዙም ሳይቆይ መላው አውሮፓ ተከተለው።

የንጉሡ መጽሐፍ አታሚ

ምሳሌ 22:29 “በሥራው የቀ[ለ]ጠፈ ሰውን አይተሃልን? በነገሥታት ፊት ይቆማል” ይላል። የኤቲን የፈጠራ ሥራና የቋንቋ ችሎታ በፈረንሳዩ ንጉሥ ፍራንሲስ አንደኛ ሳይስተዋል አልቀረም። ኤቲን በላቲን፣ በዕብራይስጥና በግሪክኛ የንጉሡ መጽሐፍ አታሚ ለመሆን በቃ። የኤቲን የሥራ ውጤቶች እስካሁንም ድረስ ከአንዳንዶቹ ምርጥ የፈረንሳይ የኅትመት ሥራዎች መካካል እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። በፈረንሳይ ውስጥ ለመታተም የመጀመሪያ የሆነውንና ከሁሉ የተሻለውን የተሟላ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ በ1539 ማተም ጀመረ። በ1540 በላቲን መጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ ሥዕላዊ መግለጫዎችን አስተዋወቀ። ይሁን እንጂ ኤቲን በመካከለኛው ዘመን የተለመዱትን ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ድርጊቶች የሚሰጡትን በግምት ላይ የተመሠረቱ ሥዕላዊ መግለጫዎች ከመጠቀም ይልቅ በከርሰ ምድር ጥናት በተገኙ መረጃዎች ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ መለኪያዎችና መግለጫዎች ላይ የተመሠረቱ ትምህርት ሰጪ ሥዕሎችን አቀረበ። እነዚህ ሥዕሎች የቃል ኪዳኑን ታቦት፣ የሊቀ ካህኑን ልብሶች፣ የሰሎሞንን ቤተ መቅደስና የመሳሰሉትን የሚያሳዩ ነበሩ።

ኤቲን የንጉሡን በእጅ የተጻፉ መጻሕፍት ስብስብ ለማተም ባዘዘው ልዩ የግሪክኛ የተቀረጹ ፊደላት ተጠቅሞ የመጀመሪያውን ግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች እትም ማውጣቱን ቀጠለ። ምንም እንኳ የመጀመሪያዎቹ ሁለት የኤቲን እትሞች ከዴስዴሪየስ ኢራስመስ ሥራዎች ብዙም የተሻሉ ባይሆኑም ኤቲን በ1550 ባተመው ሦስተኛ እትሙ ኮዴክስ ቤዛዬና የሴፕቱጀንትን መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ 15 የሚያህሉ በእጅ የተጻፉ ጽሑፎችን አወዳድሮ ያሰባሰባቸውን ልዩነቶችና ማመሳከሪያዎች አከለ። ይህ የኤቲን እትም ከፍተኛ ተቀባይነት ስላገኘ ቆየት ብሎ ቴክስተስ ሬሰፕተስ ወይም ተቀባይነት ያገኘ ጽሑፍ ለመሆን ችሏል፤ በ1611 የተተረጎመውን ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ጨምሮ ለሌሎች ብዙ ትርጉሞች መሠረት የሆነላቸው ይኸው ጽሑፍ ነው።

ሰርቦኒ ተሐድሶውን ተቃወመ

የሉተርና የሌሎች ተሐድሶ አራማጆች ሐሳብ በመላው አውሮፓ ሲሰራጭ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚነበቡ ጽሑፎችን በመግታት የሰዎችን ሐሳብ ለመቆጣጠር ፈለገች። ሰኔ 15, 1520 ጳጳስ ሊዮ አሥረኛ በማንኛውም ካቶሊካዊ አገር “ኑፋቄዎችን” የያዘ ማንኛውም መጽሐፍ እንዳይታተም፣ እንዳይሸጥና እንዳይነበብ የሚያዝ ኤክሱርጅ ዶሚኔ (ጌታ አስወግዳቸው) የተባለ ድንጋጌ አወጡና ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች ድንጋጌውን በግዛቶቻቸው ውስጥ እንዲያስፈጽሙ ጠየቁ። በኢንግላንድ ውስጥ ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ ሳንሱር የማድረጉን ሥልጣን ካትበርት ታንስተል ለተባሉት የካቶሊክ ጳጳስ ተዉላቸው። ሆኖም በመላው አውሮፓ ውስጥ ከጳጳሱ ቀጥሎ በመሠረተ ትምህርት ነክ ጉዳይ የማያጠያይቅ ሥልጣን ያለው በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለው የመንፈሳዊ ትምህርት ተቋም ማለትም ሰርቦኒ ነበር።

ሰርቦኒ ለካቶሊክ ልማዳዊ እምነቶች የሚሟገት ቡድን ነበር። ሰርቦኒ የካቶሊክ እምነትን ለብዙ መቶ ዘመናት እንደጠበቀ ይታመን ነበር። የሰርቦኒ ሳንሱር አድራጊዎች “ለቤተ ክርትስቲያኒቱ የማይጠቅም ብቻ ሳይሆን የሚጎዳም ጭምር ነው” ብለው ስለሚያስቡ በቨልጌት ላይ የሚቀርቡ ማናቸውንም የጥናት ጽሑፎችና ቨልጌት ብዙ ሰው በሚናገረው ቋንቋ መተርጎሙን ይቃወሙ ነበር። ተሐድሶ አራማጆች በቅዱስ ጽሑፉ ላይ ባልተመሠረቱ ማናቸውም የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶች፣ ሥርዓቶችና ልማዶች ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ በገለጹበት ወቅት ይህ መባሉ አያስደንቅም። ሆኖም በሰርቦኒ ውስጥ ያሉት ብዙ የሃይማኖት ምሁራን ቤተ ክርስቲያኒቱ ያቀፈቻቸውን መሠረተ ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ከመተርጎም ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቱ ነበር። አንድ የሃይማኖት ምሁር “መሠረተ ትምህርቶችን አንዴ ከተቀበልናቸው በኋላ ቅዱሳን ጽሑፎች አንድ ግንብ ከተገነባ በኋላ እንደ ተነሣ መወጣጫ ናቸው” ብለው ነበር። ብዙዎቹ የተቋሙ አባላት ዕብራይስጥና ግሪክኛ ባያውቁም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ቃላት ትክክለኛ ትርጉም ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ የነበሩትን የኤቲንና የሌሎች የሥነ ጽሑፍ ምሁራንን ጥናቶች ይንቁ ነበር። እንዲያውም ከሰርቦኒ ፕሮፌሰሮች አንዱ “የግሪክና የዕብራይስጥ ቋንቋዎች እውቀት መስፋፋት ሁሉም ሃይማኖቶች እንዲጠፉ ያደርጋል” ሲሉ ተናግረዋል።

የሰርቦኒ ጥቃቶች

ምንም እንኳ የመጀመሪያዎቹ የኤቲን ቨልጌት እትሞች የተቋሙን ሳንሱር ቢያልፉም ውዝግብ ሳያስከትሉ አልቀሩም። ከ13ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ቨልጌት የዩኒቨርሲቲው መጽሐፍ ቅዱስ ሆኖ ነበር፤ እንዲሁም ጽሑፉ በብዙ አንባቢዎች ረገድ እንከን የማይወጣለት ነበር። ሌላው ቀርቶ ተቋሙ ቨልጌትን ለማሻሻል በመጣሩ የተከበረ ምሁር የነበረውን ኢራስመስን አውግዞታል። አንድ ተራ መጽሐፍ አታሚ በይፋ የታወቀውን ጽሑፍ ለማረም መዳፈሩ ለአንዳንዶች አስደንጋጭ ሆኖባቸው ነበር።

ምናልባት ከሁሉም በላይ የሃይማኖት ምሁራኑን ያስጨነቃቸው የኤቲን የኅዳግ ማስታወሻዎች ነበሩ። ማስታወሻዎቹ በቨልጌት ጽሑፍ ላይ ጥርጣሬ ያሳድራሉ። ኤቲን አንዳንድ ክፍሎችን ለማብራራት መጣሩ በሃይማኖት ምሁራን ሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብተሃል ተብሎ እንዲከሰስ አደረገው። ማስታወሻዎቹ አጭር ገለጻዎች ወይም የቋንቋ መግለጫዎች እንደሆኑ በመግለጽ ክሱን አስተባበለ። ለምሳሌ ያህል በዘፍጥረት 37:35 ላይ “ሲኦል” [በላቲን ኢንፌርነም] ብሎ ያሰፈረውን ማስታወሻ አንባብያን ክፉዎች የሚቀጡበት ቦታ እንደሆነ አድርገው ላይረዱት ይችሉ ነበር። ተቋሙ የነፍስን አለመሞትና ‘የቅዱሳንን’ አማላጅነት ክደሃል ብሎ ከሰሰው።

ሆኖም ኤቲን በንጉሡ ዘንድ ተወዳጅ ስለ ነበር ጥበቃ አግኝቷል። ፍራንሲስ አንደኛ በሥነ ጽሑፍ ጥናቶች በተለይም ደግሞ በኤቲን ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ነበር። እንዲያውም ፍራንሲስ አንደኛ ኤቲንን ሊያነጋግረው ሄዶ ኤቲን በአንድ ጽሑፍ ላይ የመጨረሻ እርማቶችን እስኪያደርግ ድረስ በትዕግሥት እንደተጠባበቀው ተገልጿል። ኤቲን የንጉሡን ድጋፍ ስላገኘ ሰርቦኒን ለመቋቋም ቻለ።

ሃይማኖታዊ ምሁራን በመጽሐፍ ቅዱሶቹ ላይ እገዳ ጣሉበት

ሆኖም በ1545 ሁኔታዎቹ የሰርቦኒን ቷቋም በሙሉ ኃይሉ በኤቲን ላይ እንዲያተኩር አደረጉት። የኮሎኝ (ጀርመን)፣ የሉቨ (ቤልጅየም) እና የፓሪስ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች የተሐድሶ አራማጆችን ለመቋቋም የተባበረ ግንባር የመፍጠርን ጥቅም ተገንዝበው ትክክለኛ ያልሆኑ ትምህርቶችን በሕብረት ሳንሱር ለማድረግ ቀደም ሲል ተስማምተው ነበር። የሉቨ ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ምሁራን የኤቲን መጽሐፍ ቅዱሶች በፓሪስ የተወገዙ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ አለመግባታቸው እንዳስገረማቸው በመግለጽ ለሰርቦኒ ጻፉ፤ የሰርቦኒ አባላት ደግሞ ቢያዩአቸው ኖሮ እንደሚያወግዟቸው በመግለጽ የሐሰት መልስ ሰጡ። በዚህ ወቅት በተቋሙ ውስጥ ያሉት የኤቲን ጠላቶች የሉቨ እና የፓሪስ ተቋማት የንጉሡን መጽሐፍ አታሚ ስሕተት ለፍራንሲስ አንደኛ ለማሳመን እንደሚበቁ ተሰማቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤቲን የጠላቶቹን ሐሳብ ስለተረዳ ከሃይማኖት ምሁራኑ ቀድሞ ንጉሡን አነጋገረው። ኤቲን የሃይማኖት ምሁራኑ ያገኟቸውን ስሕተቶች ዝርዝር በሙሉ ካቀረቡ እነዚህን እርማቶች በሚሸጠው በእያንዳንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማስገባት ፈቃደኛ እንደሆነ ገለጸ። ይህን መፍትሔ ንጉሡ ደገፈው። ፒዬር ደ ሻስቴል የተባለውን ባለሟሉ ጉዳዩን እንዲከታተል አዘዘው። በጥቅምት 1546 ተቋሙ የኤቲን መጽሐፍ ቅዱሶችን “እምነታችንን ለሚክዱ ምግብ የሆኑ፣ የወቅቱን . . . ኑፋቄዎች የሚደግፉ” እንዲሁም ስሕተት የሞላባቸው “ጨርሶ ሊወገዱና ሊጠፉ የሚገባቸው ናቸው” ሲል በመቃወም ለፒዬር ደ ሻስቴል ጻፈ። ንጉሡ ሐሳባቸውን ባለማመን ከኤቲን መጽሐፍ ቅዱሶች ጋር እንዲታተሙ ሳንሱራቸውን እንዲያቀርቡ ንጉሡ ራሱ ተቋሙን አዘዘ። ይህን እንደሚያደርጉ ቃል ቢገቡም ስሕተት የሚሏቸውን ሐሳቦች በዝርዝር በጽሑፍ ለማቅረብ ሰበብ አስባብ ይፈልጉ ነበር።

ፍራንሲስ አንደኛ በመጋቢት 1547 ሲሞት ኤቲን ሰርቦኒን እንዲቋቋም ያስቻለውን ኃያል አጋሩን አጣ። ሄንሪ ሁለተኛ ሥልጣኑን ሲረከብ ተቋሙ ሳንሱሩን በጽሑፍ እንዲያቀርብ አባቱ የሰጠውን ትእዛዝ በድጋሜ አቀረበ። ሆኖም ሄንሪ ሁለተኛ የጀርመን መሳፍንት ተሐድሶን የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው እንደሚጠቀሙበት ሲገነዘብ የንጉሡ መጽሐፍ አታሚ ያሳተማቸው መጽሐፍ ቅዱሶች ያስገኛሉ የሚባሉት ጥቅሞች ወይም የሚያስከትሉት ጉዳቶች የፈረንሳይን ካቶሊክ ከመጠበቅና በአዲስ ንጉሥዋ ሥር አንድ ከማድረግ የበለጠ ብዙም አላስጨነቀውም። ታኅሣሥ 10, 1547 ንጉሡ የጠራው ምክር ቤት የሃይማኖት ምሁራኑ ሳንሱሩን በዝርዝር እስኪያቀርቡ ድረስ የኤቲን መጽሐፍ ቅዱሶች ከመሸጥ መታገድ እንዳለባቸው ወሰነ።

በመናፍቅነት ተከሰሰ

ተቋሙ በዚህ ወቅት የኤቲንን ክስ የኑፋቄዎችን ጉዳይ ለማየት ወደ ተሰየመው ልዩ ፍርድ ቤት እንዲዛወር ለማድረግ ዘዴ ይፈልግ ነበር። ኤቲን የተደቀነበትን አደጋ በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። ፍርድ ቤቱ በተሰየመ በሁለት ዓመታት ውስጥ ሻምብር አርዶንት ወይም “የሚነድ ክፍል” በመባል ታወቀ። በኤቲን ደጃፍ አቅራቢያ በፕላስ ሞቤር ከነሕይወታቸው በእንጨት ላይ ተሰቅለው በእሳት የተቃጠሉትን አንዳንድ መጽሐፍ አታሚዎችና ሻጮች ጨምሮ 60 የሚያህሉ ሰዎች በእንጨት ላይ ተሰቀሉ። እሱን ለመክሰስ የሚያስችል አነስተኛ መረጃ እንኳን ቢገኝ ተብሎ የኤቲን ቤት በተደጋጋሚ ተፈተሸ። ከ80 በላይ ምሥክሮች ተጠየቁ። መናፍቅነቱን ማረጋገጥ ከተቻለ አንድ አራተኛ ንብረቱ እንደሚሰጣቸው መረጃ ለሚሰጡ ሰዎች ቃል ተገባላቸው። ሆኖም ያገኟቸው መረጃዎች ኤቲን በግልጽ ባሳተማቸው መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች ብቻ ነበሩ።

ንጉሡ ተቋሙ ሳንሱሩን ጉዳዩን ለማጣራት ላቋቋመው ምክር ቤት በጽሑፍ እንዲያቀርቡ በድጋሜ አዘዘ። ‘የሃይማኖት ምሁራን ኑፋቄ ነው ብለው ያወገዙትን ነገር በቃል ብቻ የመመለስ እንጂ በጽሑፍ የመግለጽ ልማድ የላቸውም፤ የሚናገሩትን ቃል ማመን አለብህ። ይጻፍ ከተባለ የሚጻፈው ነገር ማለቂያ አይኖረውም’ በማለት ተቋሙ ተቃውሞውን አቀረበ። ሄንሪ ተስማማ። የመጨረሻው እገዳ ተጣለ። የኤቲን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥራ በሙሉ ተወገዘ ማለት ይቻላል። ምንም እንኳ ከፕላስ ሞቤር እሳት ቢተርፍም በመጽሐፍ ቅዱሶቹ ላይ ጠቅላላ እገዳ ስለ ተጣለባቸውና ሌላ ጥቃት ሊደርስበት እንደሚችል በማሰብ ፈረንሳይን ለቆ ወጣ።

የውጪ አገር ተወላጁ መጽሐፍ አታሚ

በኀዳር 1550 ኤቲን ወደ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተዛወረ። ተቋሙ በፈረንሳይ ውስጥ ከቨልጌት በስተቀር ማንኛውንም መጽሐፍ ቅዱስ ማተምን አግዶ ነበር። አሁን ኤቲን የፈለገውን መጽሐፍ ለማተም ነፃነት ስላገኘ ጎን ለጎን ባሉ አምዶች ካሰፈራቸው ከሁለት የላቲን ትርጉሞች (ቨልጌት እና ኢራስመስ) ጋር አድርጎ በ1551 “አዲስ ኪዳን”ን በግሪክኛ እንደገና አተመ። ከዚህ ቀጥሎ በ1552 ከኢራስመስ የላቲን ጽሑፍ ጋር በማድረግ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የፈረንሳይኛ ትርጉም አቀረበ። በእነዚህ ሁለት ትርጉሞች ኤቲን መጽሐፍ ቅዱስን በጥቅሶች የመከፋፈል ዘዴውን አስተዋወቀ፤ ይህ ዘዴ አሁንም በስፋት እየተሠራበት ካለው ዘዴ ጋር ይመሳሰላል። ከእሱ ቀደም ብለው ሌሎች ጥቅስ የሚከፋፈልባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች የሞከሩ ቢሆንም የኤቲን ዘዴ ተቀባይነት አግኝቷል። በ1553 ያተመው የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱሱ የጥቅስ ክፍፍሎችን በማቅረብ ረገድ የመጀመሪያው የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር።

በተጨማሪም በ1557 የታተመው ሁለት ትርጉሞችን የያዘው የኤቲን የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ በጠቅላላው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጅሆቫ የተባለውን የአምላክ የግል ስም የሚጠቀም መሆኑ ሊስተዋል ይገባል። በሁለተኛው መዝሙር ኅዳግ ላይ የአምላክን ስም የሚወክሉትን አራቱን የዕብራይስጥ ፊደላት (יהוה) አዶናይ በሚለው ቃል መተካት በአይሁዶች አጉል ልማድ ላይ የተመሠረተ እንደሆነና ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ገልጿል። ኤቲን በዚህ እትም ላይ የዕብራይስጡን ሐሳብ ሙሉ በመሉ ለማስተላለፍ ሲባል የታከሉትን የላቲን ቃላት ለመጠቆም ጋደል ባሉ የላቲን ፊደላት ተጠቅሟል። የኋላ ኋላ በሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች በሥራ ላይ የዋለው ይህ ዘዴ ብዙውን ጊዜ ነጥቡን ለማጉላት ተብሎ ፊደላትን ጋደል አድርጎ የመጻፍ ዘዴ ዘመናዊ አጠቃቀም የሚያውቁትን የዛሬዎቹን አንባብያን የሚያስገርማቸው ቅርስ ነው።

ኤቲን ያገኘውን እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ቆርጦ በመነሳት ሕይወቱን ቅዱሳን ጽሑፎችን በማተሙ ሥራ ላይ አውሎታል። በአሁኑ ወቅት ለአምላክ ቃል ከፍተኛ ግምት የሚሰጡ ሰዎች የኤቲንና የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት መጀመሪያ እንደተጻፈ ለማስተላለፍ ያልተቆጠበ ጥረት ያደረጉ የሌሎች ሰዎች ውለታ አለባቸው። እነሱ የጀመሩት ሂደት በጥንት ቋንቋዎች ላይ ተጨማሪ እውቀት ባገኘንና ይበልጥ ትክክለኛ የሆኑ የአምላክን ቃል የያዙ የብራና ጽሑፎችን ባገኘን መጠን ይቀጥላል። ኤቲን ከመሞቱ (1559) ጥቂት ቀደም ብሎ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን አዲስ ትርጉም እየተረጎመ ነበር። “ማን ይገዛዋል? ማንስ ያነበዋል?” ተብሎ ተጠይቆ ነበር። ‘ለአምላክ ማደርን የተማሩ ሰዎች በሙሉ’ ሲል በትምክህት መልሷል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በተጨማሪም በላቲን ስቲፋነስ እንዲሁም በእንግሊዝኛ ስቲቨንስ ተብሎ ይጠራ ነበር።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮበርት ኤቲን ያደረገው ተጋድሎ ለብዙ ትውልዶች የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ጠቅሟል

[ምንጭ]

Bibliothèque Nationale, Paris

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኤቲንን ትምህርት አዘል ሥዕላዊ መግለጫዎች ብዙ ትውልዶች ኮርጀዋቸዋል

[ምንጭ]

Bibliothèque Nationale, Paris

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ