ታስታውሳለህን?
በቅርብ ጊዜ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተደስተሃልን? እንግዲያው የሚከተሉትን ማስታወሱ አስደሳች ሆኖ ታገኘዋለህ፦
▫ ሃይማኖታዊ እውነት ሊደረስበት ይቻላልን?
ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:32) ኢየሱስ እውነት ሊደረስበት እንደሚቻል ከመጠቆሙም በላይ አምልኮታችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከተፈለገ እውነትን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አሳይቷል። ለሳምራዊቷ ሴት “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” በማለት ነግሯታል። (ዮሐንስ 4:23)—4/15፣ ገጽ 5
▫ ሮበርት ኤቲን ማን ነው? ታላቅ ሥራ አከናውኖ ያለፈውስ እንዴት ነው?
ሮበርት ኤቲን በ16ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ መጽሐፍ አታሚ ነው። ሕይወቱን ቅዱሳን ጽሑፎችን በማተሙ ሥራ ላይ አውሎታል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መጀመሪያ እንደተጻፉ ለማስተላለፍ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስን በጥቅሶች የመከፋፈል ዘዴው በአሁኑ ጊዜ በስፋት ይሠራበታል።—4/15፣ ገጽ 10, 14
▫ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ በማንበባችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?
ቅዱሳን ጽሑፎች ሁልጊዜ አዲስ ትርጉም ያዘሉ ይሆኑልናል። እንዲሁም ስለመጨረሻዎቹ ቀናት የሚናገሩትን ትንቢቶች በቅርብ ወራት ካየናቸው፣ ከሰማናቸውና በግል ካጋጠሙን ነገሮች አንፃር ስለምንመለከታቸው ይበልጥ እምነት ይጨምሩልናል። የሕይወት ተሞክሮአችን በካበተና ችግሮችን እየተቋቋምን በሄድን መጠን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ይበልጥ በተሟላ መንገድ ልንገነዘብ እንችላለን። (ምሳሌ 4:18)—5/1፣ ገጽ 15
▫ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማስታወስ የሚቻለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ልታስታውሳቸው የምትፈልጋቸውን ጥቅሶች ምልክት አድርግባቸው ወይም በካርዶች ላይ ገልብጣቸውና እነዚህን ካርዶች በየቀኑ ልታያቸው በምትችላቸው ቦታዎች ላይ አስቀምጣቸው። በቃልህ አጥናቸው፣ አሰላስልባቸው፣ በሥራ ላይ አውላቸው። በአንዴ ብዙ ጥቅሶችን ለማጥናት አትሞክር፤ ምናልባት በየሳምንቱ አንድ ወይም ሁለቱን በቃል ለማጥናት ሞክር።—5/1፣ ገጽ 16, 17
▫ የሉቃስ ወንጌል ሌሎቹ የወንጌል ጸሐፊዎች ከሰጡት በተጨማሪ የያዘው መረጃ ምንድን ነው?
አብዛኛው የሉቃስ ወንጌል ክፍል ከማቴዎስ ዘገባ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም 59 በመቶ የሚሆነው ተጨማሪ ነገሮችን ያካተተ ነው። ሉቃስ እርሱ በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ስድስት የኢየሱስ ተአምራትን የመዘገበ ሲሆን ሌሎች የወንጌል ጸሐፊዎች ከጠቀሷቸው የኢየሱስ ምሳሌዎች በእጥፍ ያህል የሚበልጡ ምሳሌዎቸን ዘግቧል።—5/15፣ ገጽ 12
▫ በ1935 የፈነጠቀው ደማቅ የብርሃን ብልጭታ ምንድን ነው?
በዚህ ዓመት የይሖዋ ሕዝቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ መልእክት ቤዛው ሳይሆን መንግሥቱ እንደሆነ አስተዋሉ። በተጨማሪም በራእይ 7:9, 14 ላይ የተጠቀሱት እጅግ ብዙ ሰዎች ሁለተኛ ደረጃ ያላቸው ሰማያዊ ክፍል ሳይሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እንደሆኑ ተገልጦ ነበር። (ዮሐንስ 10:16)—5/15፣ ገጽ 20
▫ ሐዘንተኞችን በየትኞቹ ተግባራዊ መንገዶች ማጽናናት እንችላለን?
አዳምጥ። አጽናናቸው። አትለያቸው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በራስህ ተነሳስተህ እርዳቸው። ደብዳቤ ጻፍ ወይም የሚያጽናና መልእክት የሰፈረበት ፖስት ካርድ ላክ። አብረሃቸው ጸልይ። (ያዕቆብ 5:16)—6/1፣ ገጽ 13, 14
▫ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦች ጸንተው እንዲቆሙ ለመርዳት መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
ሳታሰልስ በሚያበረታቱ፣ ገንቢ በሆኑና በሚያጽናኑ ቃላት አነጋግራቸው። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ይህም አእምሯቸውንና አካላቸውን ያድስላቸዋል። ጥሩና ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜ በቲኦክራሲያዊና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችህ አብረውህ እንዲሠሩ አድርግ። በጸሎትህ አስባቸው። (ሮሜ 1:9፤ ኤፌሶን 1:16)—6/1፣ ገጽ 29
▫ በመስክ አገልግሎት ላይ ትዕግሥት ማሳየት ምን ምን ወሮታዎች ያስገኛል?
ትዕግሥት የመንግሥቱ አስፋፊ የሚያጋጥመውን የግዴለሽነት ስሜት ወይም ተቃውሞ ጸንቶ እንዲቋቋም ይረዳዋል። ታጋሽ አገልጋዮች የሚያነጋግሯቸው ሰዎች ሲቆጡ ከእነሱ ጋር ከመከራከር ይልቅ ሰላማቸውንና ደስታቸውን ሳያጠፉ በለዘበ ምላስ መልስ ለመስጠት ወይም ዝም ብለው ለመሄድ ይችላሉ። (ማቴዎስ 10:12, 13) በዚህ ሳቢያም በግ መሰል የሆኑ ሰዎች የመንግሥቱ መልእክት ይማርካቸው ይሆናል።—6/15፣ ገጽ 9
▫ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ በጣም ውድ ዋጋ የሚገባው የሆነው ለምንድን ነው?
እውነትን ማወቃችን ከውሸት፣ ግራ ከመጋባትና ከአጉል እምነት ነፃ አውጥቶናል። ይህንን እውነት በተግባር ስናውለው መከራዎችን ተቋቁመን እንድናልፍ ብርታት ይሰጠናል፤ እንዲሁም ፈተና ቢደርስብን ጸንተን እንድንቆም በሚያስችለን ተስፋ አማካኝነት ያበረታታናል።—7/1፣ ገጽ 8
▫ የቅቡዓን ክርስቲያን ጉባኤ ከሥጋዊ እስራኤል የተረከበው ተቀዳሚ ኃላፊነት ምንድን ነው?
በአሕዛብ መካከል ስለ ይሖዋ ታላቅነት የመመሥከር መብት ነው። (ኢሳይያስ 43:21፤ 1 ጴጥሮስ 2:9)—7/1፣ ገጽ 19
▫ ባል ሚስቱን ‘በክብር መያዝ’ አለበት በማለት ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት ምን ያመለክታሉ? (1 ጴጥሮስ 3:7 አዓት)
ሚስቱን የሚያከብር ባል ሚስቱን በሌሎች ፊት አያዋርዳትም ወይም ደግሞ አያቃልላትም። ከዚህ ይልቅ በቃሉና በድርጊቱ ብቻቸውን ሲሆኑም ሆነ በሰዎች ፊት እንደሚያከብራት ያሳያል። (ምሳሌ 31:10–31)—7/15፣ ገጽ 19
▫ አንድን ንስሐ የማይገባ መጥፎ አድራጊ ከጉባኤ ማስወገድ የፍቅር መግለጫ ነው ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
ማስወገድ ለይሖዋና ለመንገዶቹ የፍቅር መግለጫ ነው። (መዝሙር 97:10) በሌሎች ላይ መጥፎ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችለውን ግለሰብ ከመካከላቸው ስለሚያርቅላቸው ይህ ድርጊት በጽድቅ መንገድ እየተጓዙ ላሉት ሰዎች ፍቅር መግለጫ ነው። በተጨማሪም የጉባኤውን ንጽሕና ይጠብቃል። (1 ቆሮንቶስ 5:1–13)—7/15፣ ገጽ 25
▫ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:45–47 ላይ የተናገረለት “ታማኝና ልባም ባሪያ” በዛሬው ጊዜ ተለይቶ ሊታወቅ የሚችለው እንዴት ነው?
ይበልጥ ተለይተው የሚታወቁት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማዘጋጀትና ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ለመስበክ በሚሠሩት ሥራና የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ባላቸው የጠበቀ ቁርኝት ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20)—8/1፣ ገጽ 16