ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እድገት ያስገኛል
ዡዜ ማግሎቭስኪ እንደተናገረው
ፖሊሱ ክንዴን ሲይዘኝ አባቴን በዓይኔ ፈለግሁት። እኔ አላወቅሁም እንጂ ቀድሞውኑ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ተወስዶ ነበር። እዚያም ስደርስ ፖሊሱ መጽሐፍ ቅዱሶቻችንን ጨምሮ ሁሉንም ጽሑፎቻችንን ቀማንና ወለሉ ላይ ከመራቸው። አባቴ ይህንን በመመልከት “መጽሐፍ ቅዱሶቹንም መሬት ላይ ጣልካቸው?” በማለት ጠየቀው። የፖሊስ አዛዡ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሶቹን አንስቶ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጣቸው።
ወደ ፖሊስ ጣቢያው የተወሰድነው ለምንድን ነው? ያደረግነው ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ሳይቀር የተወሰደብን የሕዝቦቹን ነፃነት በደህንነት ፖሊስ በሚቆጣጠር አምላክ የለሽ አገር ውስጥ ስለነበርን ነውን? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ወደ 1925 ማለትም ገና ከመወለዴ በፊት ወደነበረው ዓመት መመለስ ያስፈልገናል።
በዚህ ዓመት አባቴ ኤስቴፋኖ ማግሎቭስኪ እና እናቴ ዡሊያና በጊዜው ዩጎዝላቪያ ትባል የነበረውን አገር ለቀቁና ወደ ብራዚል ተዛውረው በሳኦ ፖሎ መኖር ጀመሩ። ምንም እንኳ አባቴ ፕሮቴስታንት እናቴ ደግሞ ካቶሊክ ብትሆንም ሃይማኖት በመካከላቸው መለያየትን የሚፈጥር ነገር አልነበረም። እንዲያውም ከአሥር ዓመታት በኋላ ሃይማኖታዊ ትስስር ያስገኘላቸው አንድ ነገር ተከስቷል። የአባቴ አማች ስለ ሙታን ሁኔታ የሚናገር በሀንጋሪ ቋንቋ የተዘጋጀ ባለ ሙሉ ቀለም ቡክሌት ለአባቴ አመጣለት። ቡክሌቱን የተቀበለው በስጦታ መልክ ሲሆን እንዲያነበውና በይዘቱ ላይ በተለይም ስለ “ሲኦል” በሚናገረው ክፍል ላይ ያለውን አስተያየት እንዲያካፍለው አባቴን ጠየቀው። አባባ ሌሊቱን ሙሉ ቡክሌቱን ደጋግሞ በማንበብ አሳለፈ፤ በማግስቱ አማቹ ምን ሐሳብ እንዳለው ለማወቅ ወደ እርሱ ሲመጣ አባቴ ቁርጥ ባለ ሁኔታ “እውነቱ ይህ ነው!” በማለት ገለጸለት።
አነስተኛ ጅምሮች
ጽሑፉ የተገኘው ከይሖዋ ምሥክሮች ስለነበር ስለ እምነቶቻቸውና ትምህርቶቻቸው ይበልጥ ለማወቅ ሁለቱም የይሖዋ ምሥክሮችን ይፈልጉ ጀመር። በመጨረሻም ከምሥክሮቹ ጋር ተገናኙና አብዛኞቹ የቤተሰባችን አባላት የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ጀመሩ። በዚያው ዓመት ማለትም በ1935 በአማካይ ስምንት ሰዎች የሚገኙበት መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሀንጋሪ ቋንቋ የተጀመረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እቤታችን ውስጥ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይካሄዱ ነበር።
አባቴ ከሁለት ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በኋላ በ1937 ተጠመቀና ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የስብከት ሥራ በመካፈል እንዲሁም የተሾመ አገልጋይና የጥናት መሪ ሆኖ በማገልገል ግለት ያለው የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በቪላ ማሪያና ሰፈር ለተቋቋመው ለመጀመሪያው የሳኦ ፖሎ ጉባኤ ምሥረታ የግሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በኋላም ጉባኤው ወደ ከተማዋ እምብርት ተዛወረና ሴንትራል ጉባኤ ተብሎ ተሰየመ። ከአሥር ዓመት በኋላ ሁለተኛው ጉባኤ ይፒራንጋ በተባለ ሰፈር ተቋቋመና አባቴ እዚያ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ተሾመ። በ1954 ሞኢንዮ ቬልዮ በሚባል ሰፈር ሦስተኛ ጉባኤ ተቋቋመ፤ እዚያም የጉባኤ አገልጋይ በመሆን አገልግሏል።
ይህ ቡድን በጥሩ ሁኔታ እንደተጠናከረ ሳኦ በርናርዶ ዶ ካምፖ ከተማ ውስጥ አንድ በአቅራቢያችን የሚገኝን ቡድን መርዳት ጀመረ። እነዚህ አነስተኛ የምሥክሮች ቡድኖች ለዓመታት ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ በመባረኩ በጣም አስደናቂ እድገት ሊታይ ችሏል። በ1994 በሳኦ ፖሎና በአካባቢዋ በሚገኙ 760 ጉባኤዎች ውስጥ ከ70,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ነበሩ። የሚያሳዝነው ግን አባቴ በሕይወት ቆይቶ ይህንን እድገት አላየም። በ57 ዓመቱ በ1958 ሞተ።
የአባቴን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረግ
እንደ ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሁሉ እንግዳ ተቀባይነት የአባቴ ጉልህ ባሕርይ ነበር። (3 ዮሐንስ 1, 5–8ን ተመልከት።) በዚህም ምክንያት ከወንድም ዩል እና ባለቤቱ ጋር በ1936 ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ብራዚል የመጡትን አንቶኒዮ አንድራድንና ባለቤቱን እንዲሁም ወንድ ልጃቸውን በእንግድነት የመቀበል መብት አግኝተናል። በተጨማሪም ሁለቱን የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ምሩቆች ማለትም ሃሪ ብላክንና ዲላረድ ሌትኮንንም በእንግድነት የተቀበልን ሲሆን እነዚህ ወንድሞች በ1945 ብራዚል የተመደቡ የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን ነበሩ። ሌሎችም ብዙዎች ከእነርሱ በኋላ መጥተዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በቤተሰባችን ውስጥ ለሚገኝ ለእያንዳንዱ ሰው ቋሚ የመበረታቻ ምንጭ ነበሩ። ይህንን በመገንዘብ እንዲሁም ለቤተሰቤ ጥቅም ስል ክርስቲያናዊ ጠባይ የሆነውን እንግዳ ተቀባይነትን በተመለከተ የአባቴን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርጌአለሁ።
አባቴ በ1935 እውነትን ሲማር ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ የነበርኩ ቢሆንም ታላቅ ልጅ እንደመሆኔ መጠን በሚያደርጋቸው ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ከእርሱ ጋር መሥራት ጀመርኩ። በሳኦ ፖሎ ከተማ ኤሳ ደ ካሮዝ ቁጥር 141 ጎዳና በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጽሕፈት ቤት ውስጥ ባለው የመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ሁላችንም ከእርሱ ጋር እንገኝ ነበር። አባቴ በሰጠኝ ትምህርትና ማሠልጠኛ የተነሳ ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት በውስጤ ስለተቀጣጠለ በ1940 ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩ፤ ይህንንም ሳኦ ፖሎን መሐል ለመሐል አቋርጦ በሚያልፈው በአሁኑ ጊዜ በተበከለው ታይታ በተባለው ወንዝ ውስጥ በመጠመቅ አሳየሁ።
ብዙም ሳልቆይ መደበኛ የመንግሥቱ አስፋፊ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይኸውም በሌሎች ውስጥ የእውነትን መልእክት መትከልና ማጠጣት እንዲሁም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ማለት እንደሆነ ተማርኩ። አሁን ብራዚል ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ስመለከት ከእነዚህ ብዙዎቹ እውነትን እንዲያውቁ አለዚያም ለእውነት ያላቸውን አድናቆት እንዲያሰፉ ለመርዳት ይሖዋ እንደተጠቀመብኝ ስለማውቅ ጥልቅ ደስታ ይሰማኛል።
ከረዳኋቸው መካከል ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ያገኘሁት ዦአኪም ሜሎ ይገኝበታል። ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር እነጋገር ነበር፤ እነዚህ ሰዎች እያዳመጡኝ የነበረ ቢሆንም እጅግም ፍላጎት አልነበራቸውም። ከዚያም አብሮን የነበረ አንድ ወጣት በተመስጦ እንደሚያዳምጥ አስተዋልኩ። ፍላጎቱን በመመልከት ትኩረቴን በእርሱ ላይ አነጣጠርኩና ጥሩ ምሥክርነት ከሰጠሁት በኋላ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ እንዲገኝ ጋበዝኩት። በጥናቱ ላይ ባይገኝም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ ከመገኘቱም በላይ ከዚያ በኋላ በስብሰባዎች ላይ በቋሚነት ይገኝ ነበር። ጥሩ እድገት አድርጎ ተጠመቀ፤ እንዲሁም ከሚስቱ ጋር በመሆን ለብዙ ዓመታት ተጓዥ አገልጋይ ሆኖ አገልግሏል።
ሌላው ደግሞ በምሠራበት ቦታ ያገኘሁት አርናልዶ ኦርሲ ነበር። ለሥራ ባልደረቦቼ ዘወትር እመሠክርላቸው ነበር፤ ነገር ግን አንድ ጢሙን ያሳደገ ወጣት ሁልጊዜ ዝም ብሎ ያዳምጥ እንደነበረ ልብ ስላልኩ እርሱን በቀጥታ ማነጋገር ጀመርኩ። ቤተሰቦቹ አጥባቂ ካቶሊኮች የነበሩ ቢሆንም እንደ ማጨስ፣ የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ፊልሞችን መመልከት እንዲሁም ራስን የመከላከል ስልት የሆነውን ጁዶን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች ብዙ ጥያቄዎች ጠየቀ። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል አሳየሁት፤ በማግሥቱ ኢየሱስ ተሰቅሎ የሚታይበትን መስቀሉን ጨምሮ ፒፓውንና ላይተሩን አብሮ እንደሰባበራቸው፣ የጾታ ስሜት የሚያነሳሱ ፊልሞቹን እንዳስወገደና ጢሙን እንደተላጨ ሊያሳየኝ ሲጠራኝ ያልጠበቅሁት ነገር ስለነበር በጣም ተደሰትኩ። በጥቂት ጊዜ ውስጥ ተለወጠ! በተጨማሪም ጁዶ መለማመዱን አቆመና መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ እንዳስጠናው ጠየቀኝ። ምንም እንኳ ከሚስቱና ከአባቱ ተቃውሞ ቢደርስበትም በአቅራቢያው በሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አደረገ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመጠመቁም በተጨማሪ ዛሬ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። በተጨማሪም ሚስቱና ልጆቹ እውነትን ተቀብለዋል።
በመንግሥቱ አገልግሎት መካፈል
የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ በአንድ የማስታወቂያ ኩባንያ ውስጥ መሥራት ጀመርኩ፤ እዚያም የንግድ ቦታ መጠቆሚያ ማስታወቂያዎችን እንዴት መጻፍ እንደሚቻል ተማርኩ። ይህም በጣም ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል፤ ሳኦ ፖሎ ውስጥ ለአያሌ ዓመታት ንግግሮችንና የይሖዋ ምሥክሮችን ትልልቅ ስብሰባዎች ለማስተዋወቅ የሚያገለግሉ ፊት ለፊትና ጀርባ ላይ የሚነገቱ እንዲሁም በጨርቅ ላይ ተጽፈው መንገድ ላይ የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎችን የምጽፈው እኔ ብቻ ነበርኩ። ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት በአውራጃ ስብሰባ ላይ የማስታወቂያ ምልክቶች በሚዘጋጅበት ዲፓርትመንት ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ መሥራት እንድችል ከመሥሪያ ቤት የማገኘውን የዕረፍት ቀኖች ለዚህ ወቅት አቆያቸው ነበር፤ እንዲያውም የማስታወቂያ ምልክቶቹን በጊዜው ማጠናቀቅ እንድችል በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ አድር ነበር።
በተጨማሪም በጊዜው ብርቅ በሆነው የድምፅ ማጉያ መሣሪያ በተገጠመበት የማኅበሩ መኪና ላይ የመሥራት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከፍ ያለ ቦታ ላይ እናስቀምጥና የድምፅ ማጉያ መሣሪያ የተገጠመበት መኪና የተቀረጸውን መልእክት ሲያሰማ እኛ ደግሞ ምን እንደተፈጠረ ለማየት ከቤታቸው ከወጡት ሰዎች ጋር እንነጋገር ነበር። የመንግሥቱ ምሥራች እንዲታወቅ የተጠቀምንበት ሌላኛው ዘዴ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀስ ሸክላ ማጫወቻ ሲሆን የማኅበሩን ጽሑፎች ለማስተዋወቅ የሚጠቅሙ እነዚህ ቅጂዎች እስከአሁን ድረስ አሉኝ። በዚህ መሣሪያ በመጠቀማችን ምክንያት ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ተበርክቷል።
በእነዚያ ጊዜያት በሳኦ ፖሎ ጎዳናዎች ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባላት ረዣዥም ሰልፎችን በማድረግ ያከብሯቸው የነበሩ በዓላት የነበሯቸው ሲሆን ብዙውን ጊዜ ሰዎችን ከመንገዱ ላይ ገለል የሚያደርጉ ወንዶች ከሰልፉ ፊት ፊት ይሄዱ ነበር። አንድ እሁድ ቀን ረዥሙ ሰልፍ ሲመጣ እኔና አባቴ በመንገዱ ላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! እያበረከትን ነበር። አባቴ እንደወትሮው ኮፍያውን አድርጓል። ከሰልፉ ፊት ፊት ከሚሄዱት ሰዎች መካከል አንዱ “ኮፍያህን አውልቅ! ሰልፈኛው እየመጣ እንደሆነ አታይም?” በማለት ጮኸ። አባቴ ኮፍያውን ሳያወልቅ ሲቀር ብዙ ሰዎች ወደ እኛ መጡና ወደ አንድ ሱቅ መስኮት እየገፈተሩን ሁከት ይፈጥሩ ጀመር። ሁኔታው የአንዱን ፖሊስ ትኩረት ሳበው፤ ፖሊሱ ምን እንደተፈጠረ ሊጠይቀን መጣ። ከሰዎቹ መካከል አንዱ ከእርሱ ጋር ለመነጋገር በመፈለግ ክንዱን እየጎተተ ወሰደው። ፖሊሱ የሰውዬውን እጅ ከላዩ እየወረወረ “እጅህን ከደንብ ልብሴ ላይ አንሳ!” በማለት አዘዘው። ከዚያም ምን እንደተፈጠረ ጠየቀ። አባቴ ለሰልፉ ኮፍያውን እንዳላወለቀ ሰውዬው ከተናገረ በኋላ “እኔ ሐዋርያዊ የሆነችው የሮማ ካቶሊክ አባል ነኝ” በማለት ተናገረ። “ሮማዊ ነኝ ማለትህ ነው? እንግዲያው ወደ ሮም ተመለስ! ይህ ብራዚል ነው” የሚለው የፖሊሱ መልስ ያልተጠበቀ ነበር። ከዚያም ወደ እኛ ዞረና “መጀመሪያ እዚህ የነበረው ማን ነው?” በማለት ጠየቀ። አባቴ መጀመሪያ እኛ እንደነበርን ሲመልስለት ፖሊሱ ሰዎቹን ከአካባቢው አባረረና እኛ ሥራችንን እንድንቀጥል ነገረን። ፖሊሱ መላው ሰልፈኛ እስኪያልፍ ድረስ ከጎናችን ቆመ፤ የአባቴም ኮፍያ ሳትወልቅ ቀረች!
እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች እምብዛም አይከሰቱም። በሚከሰቱበት ጊዜ ግን ለአናሳው ሕዝብ ፍትሕ መስፈን እንዳለበት የሚያምኑና ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማያጎበድዱ ሰዎች እንዳሉ ማወቁ ያበረታታል።
በሌላ ጊዜ ከአንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኝ ወጣት ጋር ተገናኘሁ፤ ይህ ወጣት ፍላጎት ከማሳየቱም በተጨማሪ በሚቀጥለው ሳምንት እንድመለስ ጠየቀኝ። ተመልሼ ስሄድ በጥሩ ሁኔታ ተቀበለኝና ወደ ውስጥ እንድገባ ጠየቀኝ። በሚያላግጡብኝና ሊያበሽቁኝ በሚሞክሩ ዱርዬ ወጣቶች መከበቤን ሳውቅ በጣም ደነገጥኩ! ሁኔታው እየከፋ ከመሄዱም በላይ ብዙም ሳይቆዩ ጉዳት እንደሚያስከትሉብኝ ተሰማኝ። ማናቸውም ነገር ቢደርስብኝ ተጠያቂ እንደሚሆንና ወላጆቼ የት እንዳለሁ እንደሚያውቁ ወደዚያ እንድመጣ ጋብዞኝ ለነበረው ወጣት ነገርኩት። መሄድ እንደምፈልግ ነገርኳቸው፤ እነርሱም ተስማሙ። ነገር ግን ትቻቸው ከመሄዴ በፊት ከመካከላቸው ከእኔ ጋር ብቻውን ለመነጋገር የሚፈልግ ካለ ሊያነጋግረኝ እንደሚችል ነገርኳቸው። የአካባቢው ቄስ ጓደኞች የሆኑ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች እንደሆኑ ከጊዜ በኋላ አወቅሁ፤ ይህንንም ስብሰባ እንዲያቀነባብሩ ያበረታታቸው ይኸው ቄስ ነበር። ከእነርሱ እጅ ለማምለጥ በመቻሌ ተደሰትኩ።
እርግጥ ነው መጀመሪያ ላይ በብራዚል የነበረው እድገት በጣም አዝጋሚ ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ በሆነው ‘የመትከሉ’ ሥራ ላይ ነበርን፤ ‘ለመኮትኮት’ እና የጉልበታችንን ፍሬ ‘ለመሰብሰብ’ ጊዜ አልነበረንም። ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም” ብሎ የጻፈውን ሁልጊዜ እናስታውስ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 3:6, 7) የመጀመሪያዎቹ ሁለት የጊልያድ ምሩቃን በ1945 ሲመጡ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው እድገት ጊዜው እንደደረሰ ተሰማን።
ተቃውሞ ሲያጋጥም ደፋር መሆን
እድገት ቢኖርም የተገኘው ያለምንም ተቃውሞ አልነበረም፤ በተለይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ከተጀመረ በኋላ ይህ በግልጽ ታይቷል። ሕዝቡ በአጠቃላይ እንዲሁም ጥቂት ባለሥልጣኖች ገለልተኛ አቋማችንን ስላልተረዱት ቀጥተኛ ተቃውሞ ነበረ። በ1940 አንድ ወቅት ላይ በሳኦ ፖሎ ከተማ እምብርት ላይ ፊት ለፊትና ጀርባ ላይ በሚነገቱ ማስታወቂያዎች የመንገድ ላይ ምሥክርነት እያከናወንን ሳለ አንድ ፖሊስ ከጀርባዬ መጥቶ ያነገትኳቸውን ማስታወቂያዎች ከላዬ መንጭቆ አነሳና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሊወስደኝ ክንዴን ያዘኝ። አባቴን ለማግኘት ዙሪያ ገባውን በዓይኔ ፈለግሁ፤ ነገር ግን በአካባቢው አልነበረም። እርሱና በብራዚል ያለውን ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠረውን ወንድም ዩልን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ወንድሞችና እህቶች ቀድሞውኑ ወደ ፖሊስ ጣቢያው መወሰዳቸውን አላወቅሁም ነበር። በመክፈቻው አንቀጽ ላይ እንደተገለጸው አባቴን እዚያ አገኘሁት።
ለአካለ መጠን ያልደረስኩ ስለሆንኩ ይዘው ሊያቆዩኝ አልቻሉም፤ ወዲያውኑ አንድ ፖሊስ ወደ ቤት ወሰደኝና ለእናቴ አስረከበኝ። በዚያው ምሽት እህቶችም ተለቀቁ። ከጊዜ በኋላ ፖሊሱ ከወንድም ዩል በስተቀር በቁጥር አሥር የሚያክሉትን ሁሉንም ወንድሞች ለመልቀቅ ወሰነ። ነገር ግን ወንድሞች “ሁላችንንም ልቀቁን አለዚያ አንሄድም” አሉ። ፖሊሱ ግትር ስለነበር ሁሉም አንድ ላይ ሆነው በአንድ ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ በሲሚንቶ ወለል ላይ ሌሊቱን አሳለፉ። በሚቀጥለው ቀን ሁሉም በነፃ ተለቀቁ። ወንድሞች ከፊትና ከጀርባ በሚነገቱ ማስታወቂያዎች በመመሥከራቸው ምክንያት ብዙ ጊዜ ተይዘዋል። ማስታወቂያዎቹ የሕዝብ ንግግርና ፋሺዝም ወይም ነፃነት የተባለውን ቡክሌት (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) ያስተዋውቁ ነበር፤ አባባሉ ራሱ የተሳሳተ ግንዛቤ ስለሚፈጥር አንዳንድ ባለሥልጣኖች የፋሺዝም ደጋፊዎች እንደሆንን አድርገው ተረድተው ነበር።
ግዴታ የሆነው ወታደራዊ አገልግሎትም በወጣት ወንድሞች ላይ ችግሮች አስከትሎባቸዋል። በ1948 በብራዚል ውስጥ በዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ ምክንያት በመጀመሪያ የታሰርኩት እኔ ነበርኩ። ባለሥልጣኖቹ በእኔ ላይ ምን እርምጃ እንደሚወስዱ አያውቁም ነበር። ካሳፓቫ ወደሚገኘው የጦር ሰፈር ተዛወርኩና በአትክልት ቦታው ተክሎችን እንድተክልና እንድንከባከብ እንዲሁም ባለሥልጣኖች ለሻቦላ ጨዋታ የሚጠቀሙበትን ክፍል እንዳጸዳ ተመደብኩ። ለሰዎቹ ለመመሥከርና ጽሑፎችን ለማበርከት ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩኝ። ልጆች (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የተባለውን የማኅበሩን መጽሐፍ አንድ ቅጂ መጀመሪያ የወሰዱት ኃላፊው ነበሩ። እንዲያውም የሰውነት እንቅስቃሴ መሥራት አቅቷቸው ከአንድ ክፍል እንዳይወጡ ለተደረጉ 30 ወይም 40 ለሚያክሉ ወታደሮች ስለ ሃይማኖት እንዳስተምር ተመድቤ ነበር። በእስር ቤት አሥር ወራት ካሳለፍኩ በኋላ በመጨረሻ ፍርድ ቤት ቀረብኩና ተለቀቅሁ። አንዳንዶቹ ሲዝቱብኝ፣ ሲያዋርዱኝና ሲያሾፉብኝ ብርታት በመስጠት እነዚህን ነገሮች እንድቋቋም ያደረገኝን ይሖዋን አመስግነዋለሁ።
ታማኝና ከጎን የምትቆም ረዳት
ሰኔ 2, 1951 ባርብራን አገባሁ፤ ከዚያ ወዲህ ልጆቻችንን በማስተማርና “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” በማሳደግ ከጎኔ የምትቆም ታማኝ ጓደኛ ሆናልኛለች። (ኤፌሶን 6:4) ከአምስቱ ልጆቻችን መካከል አራቱ በተለያዩ የአገልግሎት ምድቦች ይሖዋን በደስታ ያገለግላሉ። እነርሱም አብረውን በእውነት ውስጥ በመጽናት ይቀጥላሉ እንዲሁም ለድርጅቱ እድገትና እየተሠራ ላለው ሥራ የድርሻቸውን ያበረክታሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ በወጣው ፎቶግራፍ ላይ ያሉት የቤተሰቡ አባላት በእቅፍ ካለችው ከትንሿ ሕፃን በስተቀር ሁሉም ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው። አራቱ ሽማግሌዎች ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል ሁለቱ የዘወትር አቅኚዎች ናቸው፤ ይህም “የሽማግሌዎች አክሊል የልጅ ልጆች ናቸው፤ የልጆችም ክብር አባቶቻቸው ናቸው” የሚለውን የምሳሌ 17:6 እውነተኝነት ያሳያል።
አሁን ዕድሜዬ 68 ዓመት ሲሆን ጤንነቴ የተሟላ አይደለም። የደም ስሬን የዘጋውን ነገር ለማስወገድ በ1991 በሦስት የደም ስሮቼ ላይ ቀዶ ጥገና ተደረገልኝ፤ እንዲሁም ከጊዜ በኋላ ካቴተር በተባለ የሕክምና መሣሪያ አማካኝነት የደም ስር ቀዶ ጥገና ተደረገልኝ። የሆነ ሆኖ እዚህ የሚሠራውን ሥራ ለማስጀመር ቀዳሚ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የአባቴን ፈለግ በመከተል በሳኦ በርናርዶ ዶ ካምፖ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ መሪ የበላይ ተመልካች ሆኜ እያገለገልኩ ለመቀጠል በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። ያለንበት ትውልድ የይሖዋ መሲሐዊት መንግሥት መቋቋሟን በማሳወቁ ዳግመኛ የማይገኝ መብት የመካፈል አጋጣሚ ስላለው በእርግጥም ልዩ ትውልድ ነው። ስለዚህ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “አንተ ግን . . . የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፣ አገልግሎትህን ሙሉ በሙሉ ፈጽም” ብሎ የተናገራቸውን ቃላት መቼም ቢሆን መርሳት የለብንም።—2 ጢሞቴዎስ 4:5 አዓት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆቼ፤ ኤስቴፋኖ እና ዡሊያና ማግሎቭስኪ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዡዜ እና ባርብራ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ከሆኑት የቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር