በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ አምላካዊ ታዛዥነት ማሳየት
“ከማንኛውም አካላዊ ድብደባ በከፋ ሁኔታ ጉዳት ያስከትላል። . . . መላው አካላቴ ሰንበር እንዳወጣ ሆኖ ይሰማኛል፤ ቢሆንም ማንም ሰው ሊያየው አይችልም።” “አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እንደቆረጥኩ ይሰማኛል . . . ወይም ጭራሹኑ ቤቱን ትቼ ለመሄድ እፈልጋለሁ።” “አንዳንዴ በትክክል ማሰብ ያስቸግራል።”
እነዚህ ብሶትን የሚያንፀባርቁ ቃላት የተስፋ ማጣትንና የብቸኝነትን ስሜት ይገልጻሉ። ሐሳቦቹ የተሰነዘሩት ከትዳር ጓደኛቸውና ከቤተሰብ አባሎቻቸው ውንጀላዎች፣ የሚያንቋሽሹ አነጋገሮች፣ ኩርፊያና እነዚህን የመሳሰሉ ስሜትን የሚጎዱ ነገሮችና አልፎ ተርፎም አካላዊ ድብደባ ከደረሰባቸው ሰዎች ነው። እነዚህ ሰዎች በጣም የተጎሳቆሉት ለምንድን ነው? የተለየ ሃይማኖታዊ እምነቶች ስላሏቸው ብቻ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ባሉበት በሃይማኖት የተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ እየኖሩ ይሖዋን ማምለክ ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅ ነው። ቢሆንም የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች አምላካዊ ታዛዥነትን በተሳካ ሁኔታ አሳይተዋል።
የሚያስደስተው ግን እንዲህ ያለው ሥቃይና ውጥረት የሚገኘው በሁሉም በሃይማኖት የተከፋፈሉ ቤተሰቦች ውስጥ አይደለም። ሆኖም በአንዳንዶቹ ቤተሰቦች ውስጥ ይህ ሁኔታ ይታያል። ቤተሰባችሁ ይህ ችግር አለበትን? እንዲህ ከሆነ ለትዳር ጓደኛችሁ ወይም ለወላጆቻችሁ ያላችሁን አክብሮት ይዞ መቀጠል አስቸጋሪ ሆኖ አግኝታችሁት ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለሽ ሚስት ከሆንሽ ወይም እንዲህ ዓይነት ችግር እየደረሰባችሁ ያላችሁ ልጆች ከሆናችሁ በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ አምላካዊ ተገዥነት ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው? ሌሎች ምን እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ? አምላክ ነገሩን እንዴት ይመለከተዋል?
ታዛዥ መሆን በጣም አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
የዚህ ዓለም የራስ ወዳድነትና የውለታ ቢስነት ተግባር ከራስህ የአለፍጽምና ዝንባሌ ጋር ተዳምሮ አምላካዊ ታዛዥነት የማያቋርጥ ትግል የሚጠይቅ ነገር እንዲሆን ያደርገዋል። ሰይጣን ይህንን ስለሚያውቅ ቅስምህን ለመስበር ይፈልጋል። ብዙውን ጊዜ ለአምላካዊ የአቋም ደረጃዎች አነስተኛ ወይም ምንም አድናቆትና አክብሮት በሌላቸው የቤተሰብ አባላት ይጠቀማል። ለመንፈሳዊ ነገሮችና ለሥነ ምግባር የምትሰጠው ከፍ ያለ ዋጋ አብዛኛውን ጊዜ አማኝ ያልሆኑት ቤተሰቦችህ ለእነዚህ ነገሮች ከሚሰጡት ዋጋ ፈጽሞ የተለየ ነው። ይህም በጠባይና በምታከናውኗቸው ነገሮች ረገድ የአመለካከት ልዩነት ይኖራል ማለት ነው። (1 ጴጥሮስ 4:4) “ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ” የሚለውን ትእዛዝ ስለምትከተል ክርስቲያናዊ የአቋም ደረጃዎችን እንዳትጠብቅ ለማድረግ የሚደርስብህ ተጽዕኖ በጣም ይጨምርብህ ይሆናል። (ኤፌሶን 5:11) በእነርሱ አመለካከት የምታደርገው ነገር ሁሉ ትክክል አይደለም። አለመግባባቱም የሚመጣው በአንተ ሃይማኖት ምክንያት ነው። አንዲት እናት በልጆቿ መታመም የተነሳ በተቸገረች ጊዜ ባሏን እርዳታ ስትጠይቀው “ለሃይማኖትሽ በቂ ጊዜ ካለሽ ለዚህም ይኖርሻል፤ የኔ እርዳታ አያስፈልግሽም” በማለት በአሽሙር መለሰላት። እንዲህ ዓይነት አነጋገሮች ታዛዥ መሆንን ይበልጥ ተፈታታኝ ያደርጉታል።
በቀጥታ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የማይጋጩ አንተ ግን የማትስማማባቸው ነገሮች የሚያጋጥሙህ ጊዜያት ይኖሩ ይሆናል። ቢሆንም የቤተሰቡ አባል እንደሆንክና በዛው መጠን አንዳንድ ግዴታዎች እንዳሉብህ ታውቃለህ። “አባቴ እንዴት እንደሚይዘን ሳስብ በጣም እናደዳለሁ ምክንያቱም ብቸኝነት እንደሚሰማው አውቃለሁ። ብዙውን ጊዜ በአባቴ ተቃውሞ መከፋት እንደሌለብኝ ራሴን ማሳሰብ አስፈልጎኝ ነበር። የያዝነውን አቋም የሚቃወምበትና የማይደግፍበት ጠንካራ ምክንያት እንዳለው መረዳት ያስፈልገኛል። ሰይጣን የዚህ የነገሮች ሥርዓት ገዢ ነው” በማለት ኮኒ ተናግራለች። አማኝ ያልሆነ ባል ያላት ሱዛን እንዲህ በማለት ሐሳቧን አካፍላለች፦ “መጀመሪያ ላይ መለያየት እንዳለብን ይሰማኝ ነበር፤ አሁን ግን እንደዚያ አይሰማኝም። ሰይጣን እኔን ለመፈተን እየተጠቀመበት እንዳለ አውቄአለሁ።”
ሰይጣን ዋጋ እንደሌለህ ሆኖ እንዲሰማህ የሚያደርገው ጥረት ምንም የማያቋርጥ ሊመስል ይችላል። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ምንም ሳትነጋገሩ ቀናት ያልፉ ይሆናል። ሕይወትህ በብቸኝነት ስሜት ሊዋጥ ይችላል። ይህም በራስ የመተማመን መንፈስህን እንዲሁም ለራስህ ያለህን አክብሮት ሊያጠፋውና አምላካዊ ታዛዥነትህን ሊፈታተነው ይችላል። ልጆችም ስሜታዊና አካላዊ ድካም ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል ምንም እንኳ ወላጆቻቸው ቢቃወሟቸውም ሦስት ወጣት የአምላክ አገልጋዮች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ ነበር። ከእነዚህም ወጣቶች አንዷ (አሁን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነችው) እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “በድንነት እንዲሁም የስሜት ድካም ይሰማን ነበር፤ መተኛት አልቻልንም፤ ሁኔታው በጣም ያሳዝነን ነበር።”
አምላክ ምን ይጠብቅብሃል?
ምንጊዜም ቢሆን አምላክን መታዘዝ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፤ ለባል የራስነት ሥልጣን የሚሰጠው ገደብ ያለው ታዛዥነት ደግሞ ይሖዋ እንዳዘዘው መሆን አለበት። (ሥራ 5:29) ይህ ምናልባት አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም የማይቻል አይደለም። አምላክ እንዲረዳሽ መለመንሽን አታቋርጪ። እርሱ ‘በመንፈስና በእውነት እንድታመልኪው’ እንዲሁም የሚለውን እንድትሰሚና ለመመሪያዎቹ እንድትገዢ ይፈልግብሻል። (ዮሐንስ 4:24) ከአምላክ ቃል የሚገኘው እውቀት ትክክለኛ ዝንባሌ ባለው ልብ ውስጥ ሲሞላ በፈቃደኝነት ለመታዘዝ ያነሳሳናል። የግል ሁኔታዎችሽ ይለወጡ ይሆናል እንጂ ይሖዋም ሆነ ቃሉ አይለወጡም። (ሚልክያስ 3:6፤ ያዕቆብ 1:17) ይሖዋ የራስነትን ሥልጣን ለባል ሰጥቷል። ባል የክርስቶስን የራስነት ሥልጣን ተቀበለም አልተቀበለ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት አይለወጥም። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ያለማቋረጥ የሚያጎሳቁልና የሚያዋርድ ድርጊት በጸጋ ተቀብሎ ተቋቁሞ መኖር አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ላይኛይቱ ጥበብ . . . ለመታዘዝ ዝግጁ ናት” ይላል። (ያዕቆብ 3:17 አዓት) ለዚህ የራስነት ሥልጣን ሙሉ እውቅና ለመስጠትና ለመቀበል የአምላክ መንፈስ በተለይም የዚህ መንፈስ ፍሬ የሆነው ፍቅር ያስፈልጋል።—ገላትያ 5:22, 23
ለአንድ ሰው ፍቅር ካለሽ ለመለኮታዊ ሥልጣኑ አምላካዊ ታዛዥነት ማሳየት ቀላል ይሆናል። ኤፌሶን 5:33 እንዲህ በማለት ይመክረናል፦ “ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፣ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ። [“ለባልዋ የጠለቀ አክብሮት ሊኖራት ይገባል።” አዓት]”
የኢየሱስን ሁኔታ አስታውሱ። በቃልም ሆነ በአካል ቢደበደብም ማንንም ሰው ክፉ ቃል አልተናገረም። ጥቁር ነጥብ የሌለበት ታሪክ አስመዝግቧል። (1 ጴጥሮስ 2:22, 23) ኢየሱስ እንዲህ ያለ ታላቅ ውርደት ሲደርስበት ከፍተኛ የሆነ ድፍረትና ለአባቱ ለይሖዋ የጠለቀ ፍቅር ማሳየት አስፈልጎት ነበር። ፍቅር ደግሞ “በሁሉ ይጸናል።”—1 ቆሮንቶስ 13:4–8
ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው ለሆነው ጢሞቴዎስና ዛሬ ለምንኖረው ለእኛ “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና” በማለት አሳስቧል። (2 ጢሞቴዎስ 1:7) ለይሖዋና ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለህ የጠለቀ ፍቅር ያለህበት ሁኔታ ለመጽናት የማያስችል በሚመስልበት ጊዜ ለአምላካዊ ታዛዥነት ሊያነሳሳህ ይችላል። ጤናማ አስተሳሰብ ሚዛናዊ አመለካከትህን ይዘህ እንድትቀጥል እንዲሁም ከይሖዋና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ በማተኮርህ እንድትገፋበት ይረዳሃል።—ከፊልጵስዩስ 3:8–11 ጋር አወዳድር።
አምላካዊ ታዛዥነት በማሳየት በኩል የተሳካላቸው የትዳር ጓደኞች
አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ያሉብሽን ችግሮች እንዴት እንደሚያቃልልሽ ለማየት የግድ ረዘም ያለ ጊዜ መቆየት ያስፈልግሻል። ቢሆንም የይሖዋ እጅ አጭር አይደለም። “ምንጊዜም ይሖዋ የሰጣችሁን መብት ማለትም በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ እርሱን የማምለክ፣ የማጥናት፣ የማገልገልና የመጸለይ ልዩ መብት ተጠቀሙበት” በማለት አምላካዊ ታዛዥነት በማሳየት በኩል የተዋጣላት አንዲት ሴት መክራለች። ይሖዋ የሚባርከው የምታከናውኛቸውን ነገሮች ብቻ ሳይሆን የምታደርጊያቸውን ጥረቶች ጭምር ነው። በ2 ቆሮንቶስ 4:17 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘መከራችን ጊዜያዊ ነው፤ ቢሆንም ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል’ ብሏል። በዚህ ላይ አሰላስዪ። እንዲህ ማድረግሽ ሚዛንሽን ጠብቀሽ እንድትመላለሺ ያስችልሻል። አንዲት ሚስት እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “የቤተሰቤ ሕይወት እየተሻሻለ ባለመሄዱ አንዳንድ ጊዜ ምናልባት ይሖዋ አይደሰትብኝም ይሆን እንዴ? ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ከባለቤቴ የተሻለ የአእምሮ ሰላም አግኝቼ እነዚህን ችግሮች መቋቋም መቻሌ ራሱ አንዱ እንደ ይሖዋ በረከት አድርጌ የምቆጥረው ነገር ነው። የምንሠራቸው ነገሮች ይሖዋን እንደሚያስደስቱ ማወቃችን የምናደርገው ትግል ዋጋ ያለው መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል።”
ይሖዋ ልትቋቋሚው ከምትችዪው በላይ የሆነ ሁኔታ እንዲደርስብሽ እንደማይፈቅድ ቃል ገብቷል። በእርሱ ታመኚ። አንቺ ከምታውቂው የተሻለ ያውቃል፤ እንዲሁም አንቺ ራስሽን ከምታውቂው የተሻለ እርሱ ያውቅሻል። (ሮሜ 8:35–39፤ 11:33፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ወደ ይሖዋ መጸለይ ጠቃሚ ነው። በተለይ ምን ማድረግ እንዳለብሽ ወይም ያጋጠመሽን ችግር እንዴት መወጣት እንደምትችዪ ሳታውቂ ስትቀሪ መንፈሱ እንዲመራሽ ጸልዪ። (ምሳሌ 3:5፤ 1 ጴጥሮስ 3:12) ለራስነት ሥልጣን ለመታዘዝ የሚያስችሉሽን ትዕግሥትን፣ ራስን መግዛትንና ትሕትናን እንዲሰጥሽ ያለማቋረጥ ጠይቂው። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር መጠጊያዬና ጠንካራ ምሽጌ ነው” ብሏል። (መዝሙር 18:2 የ1980 ትርጉም) በእምነት በተከፋፈሉ ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ይህን ማስታወሳቸው ብርታት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
በተለይም ትዳርሽን ደስታ የሰፈነበት ለማድረግ ማንኛውንም ጥረት አድርጊ። አዎን፣ ምሥራቹ መከፋፈልን እንደሚያመጣ ኢየሱስ አስቀድሞ አውቆ ነበር። ቢሆንም በአንቺ ዝንባሌ ወይም ጠባይ ሳቢያ አንዳችም ዓይነት መከፋፈል እንዳይፈጠር ጸልዪ። (ማቴዎስ 10:35, 36) ይህንን በአእምሮ ይዞ እርስ በርስ መተባበር የጋብቻ ችግሮችን ይቀንሳል። ይህንን ተገቢ ጠባይ የምታሳዪው አንቺ ብቻ በምትሆኚበት ጊዜም እንኳ ከፍተኛ ግጭት ወይም አለመግባባት የሚያስከትሉ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ እጅግ ሊረዳ ይችላል። ትዕግሥትና ፍቅር በጣም አስፈላጊ ናቸው። “ገር” እና ‘ትዕግሥተኛ’ ሁኚ።—2 ጢሞቴዎስ 2:24
ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ” ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 9:22) ልክ እንደዚሁ ክርስቲያናዊ ግዴታዎችሽን ወደ ጎን ገሸሽ ሳታደርጊ ከትዳር ጓደኛሽና ከቤተሰብሽ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ አንዳንድ ጊዜ ፕሮግራምሽን ማስተካከል ያስፈልግሽ ይሆናል። ከመረጥሽው የትዳር ጓደኛ ጋር የቻልሽውን ያህል አብረሽ ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ሞክሪ። ክርስቲያናዊ አሳቢነት አሳዪ። ይህንን ማድረጉ የአምላካዊ ታዛዥነት መግለጫ ነው።
የሌላውን ሰው ስሜት የምትረዳ ፈሪሃ አምላክ ያላትና ለሥልጣን የምትገዛ ሚስት አምላካዊ ታዛዥነት ማሳየትን ቀላል ሆኖ ታገኘዋለች። (ኤፌሶን 5:22, 23) ጸጋ የተሞሉ ‘በጨው የተቀመሙ’ ቃላት አለመግባባቶች እንዳይነሱ ለማድረግ ይረዳሉ።—ቆላስይስ 4:6፤ ምሳሌ 15:1
አምላካዊ ጥበብ ‘ተቆጥተሽ’ ወደ መኝታሽ ከመሄድ ይልቅ ልዩነቶችን በፍጥነት እንድትፈቺና በሚገነቡ መልካም ቃላት የጠፋውን ሰላም እንድትመልሺ ምክር ይሰጥሻል። (ኤፌሶን 4:26, 29, 31) ይህ ትሕትናን ይጠይቃል። ጥንካሬ ለማግኘት በይሖዋ ላይ ከፍተኛ ትምክህት ሊኖርሽ ይገባል። አንዲት ክርስቲያን ሚስት “ልባዊ ጸሎት ካቀረብኩ በኋላ የይሖዋ መንፈስ የትዳር ጓደኛዬን ይበልጥ እንድወደው ያበረታኛል” በማለት ይህንን በትሕትና አምና ተቀብላለች። የአምላክ ቃል “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ . . . ክፉውን በመልካም አሸንፍ” በማለት ምክር ይሰጣል። (ሮሜ 12:17–21) ይህ ጥበባዊ ምክርና የአምላካዊ ታዛዥነት አካሄድ ነው።
አምላካዊ ታዛዥነት የሚያሳዩ ልጆች
በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ለምትኖሩ ልጆች ይሖዋ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።” (ቆላስይስ 3:20) እዚህ ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተጠቀሰ ልብ በሉ። ለወላጆቻችሁ መታዘዝ ያለባችሁ ያለምንም ገደብ አይደለም። “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል” የሚለው የሥራ 5:29 ምክር ባንድ በኩል ወጣት ክርስቲያኖችንም ይመለከታል። በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ትክክል እንደሆነ በምታውቀው ነገር ላይ በመመርኮዝ ምን እንደምታደርግ መወሰን የሚኖርብህ አጋጣሚ ይፈጠራል። ምናልባትም በሐሰት አምልኮ ተግባራት አልካፈልም ማለትህ ቅጣት ያስከትልብህ ይሆናል። ምንም እንኳ ይህ መጥፎ አጋጣሚ ቢሆንም መከራ የሚደርስብህ በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን በማድረግህ ምክንያት ስለሆነ መጽናናትን እንዲያውም ደስታን ማግኘት ትችላለህ።—1 ጴጥሮስ 2:19, 20
አስተሳሰብህ የሚመራው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለሆነ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከወላጆችህ ትለይ ይሆናል። ይህ እነርሱን እንደ ጠላት እንድታያቸው አያደርግህም። ምንም እንኳ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ባይሆኑም ተገቢ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል። (ኤፌሶን 6:2) ሰሎሞን ‘የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህንም አትናቃት’ በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 23:22) ለእነርሱ መጤ የሚመስላቸውን ሃይማኖት በመከተልህ ምክንያት የሚሰማቸውን ብስጭት ለመረዳት ሞክር። ከእነርሱ ጋር የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ‘ምክንያታዊነትህ ይታወቅ።’ (ፊልጵስዩስ 4:5) ስሜቶችህንና የሚያሳስቡህን ጉዳዮች አካፍላቸው። ለአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥብቅ ብትሆኑም “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።” (ሮሜ 12:18) አሁን ወላጆችህ ለሚያወጡት መመሪያዎች መታዘዝህ የአምላክ መንግሥት ዜጋ ሆነህ ታዛዥ በመሆን መቀጠል እንደምትፈልግ ይሖዋ እንዲመለከት ያስችለዋል።
ሌሎች ሊያደርጓቸው የሚችሏቸው ነገሮች
በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን የአምልኮ መሰሎቻቸው ሊደግፏቸውና ችግሮቻቸውን ሊረዱላቸው ይገባል። ይህንንም አንዲት ሴት ከተናገረችው ከሚከተለው ቃል መረዳት ይቻላል፦ “ማንኛውም ሰው ሊያደርግልኝ የሚችለው ምንም ነገር ስለሌለና ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ በበኩሌ ማድረግ የምችለው ነገር ስለሌለ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ቢስነትና የከንቱነት ስሜት ይሰማኛል። የፈለገው ነገር ቢሆን በቤተሰባችን ውስጥ ፍቃዱን እንደሚፈጽም በይሖዋ እታመናለሁ።”
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ጋር አዘውትሮ መገናኘት ከለላ ይሆናል። ይህችው ሴት የራሷን ሕይወት እንዴት እንደምትመለከተው ስትገልጽ ሕይወቴ “ሁለት ዓይነት ዓለም ነው። አንዱ የምኖርበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ልኖርበት የምፈልገው ነው” ብላለች። የወንድማማችነት ፍቅር የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች በሁሉም ሁኔታዎች ሥር እንዲጸኑና እንዲያገለግሉ ያስችላቸዋል። እነዚህን ሰዎች በጸሎትህ አስባቸው። (ኤፌሶን 1:16) ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ሳታሰልስ በሚያበረታቱ፣ ገንቢ በሆኑና በሚያጽናኑ ቃላት አናግራቸው። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ጥሩና ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜ በቲኦክራሲያዊና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችህ አብረውህ እንዲሠሩ አድርግ።
አምላካዊ ታዛዥነት የሚያስገኛቸው በረከቶችና ጥቅሞች
በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ አምላካዊ ታዛዥነት ማሳየት የሚያስገኛቸውን በረከቶችና ጥቅሞች በየቀኑ አሰላስሉ። ታዛዥ ለመሆን ትጉ። ‘አትታክቱ።’ (ገላትያ 6:9) ‘በእግዚአብሔር ፊት የሚኖረንን ሕሊና በማሰብ’ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙንና ግፍ ሲፈጸምብን መጽናታችን ከአምላክ ‘ምስጋና ያስገኝልናል።’ (1 ጴጥሮስ 2:19, 20) የይሖዋን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሕግጋት እንድታፈርስ የሚያደርግህ ነገር እስካልሆነ ድረስ ታዛዥ መሆን ይኖርብሃል። ይህ ለይሖዋ ዝግጅት ያለንን ታማኝነት ያሳያል። አምላካዊ ጠባይህ ምናልባት የትዳር ጓደኛህን፣ የልጆችህን ወይም የወላጆችህን ሕይወት ያድን ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 7:16፤ 1 ጴጥሮስ 3:1
በሃይማኖት የተከፋፈለ ቤተሰብ የሚጠይቅብህንና የሚጠብቅብህን ለማሟላት ስትጥር ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለህን ንጹሕ አቋም የመጠበቅን አስፈላጊነት አስታውስ። በብዙ ጉዳዮች የእሺ ባይነት ባሕርይ ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ንጹሕ አቋምህ እንዲጎድፍ ማድረግ ማለት ሕይወትን ራሱ ጨምሮ ሁሉንም ነገር ማጣት ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር . . . ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን።” “እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን” ማወቅህ ታዛዥ እንድትሆን ያበረታሃል።—ዕብራውያን 1:1, 2፤ 2:3
ከታዛዥነት አቋማችሁ ውልፍት አለማለታችሁና ለትክክለኛ ሥነ ምግባር ያላችሁ የጸና አቋም ለእናንተም ሆነ ለማያምን የትዳር ጓደኛችሁ ጥሩ ጥበቃ ነው። ታማኝ መሆን ጠንካራ የሆነ የቤተሰብ ትስስር ይገነባል። ምሳሌ 31:11 ባለሙያና ታማኝ የሆነች ሚስት “የባልዋ ልብ ይታመንባታል” ይላል። ንጹሕ ሥነ ምግባርሽና ያለሽ ጥልቅ አክብሮት የማያምን ባልሽ ዓይን እንዲከፈት ያደርግ ይሆናል። ይህም የአምላክን እውነት ወደ መቀበል ይመራዋል።
በእርግጥም አምላካዊ ታዛዥነት ውድና ሕይወት አዳኝ ነው። በቤተሰባችሁ ውስጥ አምላካዊ ታዛዥነት እንዲኖር ጸልዩ። የአእምሮ ሰላም ያስገኛል፤ ለይሖዋም ውዳሴ ያመጣል።