በመላው ዓለም ጥላቻ የሚያከትምበት ጊዜ
ሁለት ሺህ ከሚያህሉ ዓመታት በፊት አንድ አናሳ ቡድን የጥላቻ ዒላማ ሆኖ ነበር። “ሰማያት ዝናብ ካልሰጡ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ረሐብ ወይም ቸነፈር ከተከሰተ ወዲያውኑ የሚሰማው ጩኸት ‘ክርስቲያኖችን ለአንበሳ ስጧቸው!’ የሚል ነው” በማለት ሮማውያን ለመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የነበራቸውን አመለካከት ተርቱሊያን ገልጿል።
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የጥላቻ ዒላማ ቢሆኑም እንኳ የተፈጸመባቸውን ግፍ ለመበቀል የሚገፋፋቸውን ፈተና ተቋቁመዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ . . . ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:43, 44
‘ጠላትን መጥላት’ ትክክል ነው የሚለው እምነት በቃል የተላለፈው የአይሁዳውያን ወግ ነበር። ኢየሱስ ግን ባልንጀራችንን ብቻ ሳይሆን ጠላታችንንም መውደድ እንዳለብን ተናግሯል። እንዲህ ማድረጉ አስቸጋሪ ቢሆንም የማይቻል ግን አይደለም። ጠላትን መውደድ ማለት ጠቅላላ የአኗኗር መንገዱን ወይም ተግባሩን መውደድ ማለት አይደለም። በማቴዎስ ዘገባ ውስጥ የሚገኘው የግሪክ ቃል ከመሠረታዊ ሥርዓት ጋር ተስማምቶ የሚሠራ ፍቅርን ከሚገልጸው አጋፔ ከሚለው ቃል የመነጨ ነው። አጋፔ የተባለውን በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅር የሚያንጸባርቅ ሰው ለሚጠላውና ለሚበድለው ጠላቱ እንኳ ጥሩ ነገር ያደርጋል። ይህንን የሚያደርገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጉ ክርስቶስን የሚመስልበትና ጥላቻን ድል የሚያደርግበት መንገድ ስለሆነ ነው። አንድ የግሪክ ምሁር “[አጋፔ] ለንዴትና ለምሬት ያለንን የተፈጥሮ ዝንባሌ እንድናሸንፍ ያስችለናል” በማለት ገልጸዋል። ነገር ግን ባለንበት በጥላቻ የተሞላ ዓለም ውስጥ ይህ ተግባራዊ ይሆናልን?
ክርስቲያን ነን የሚሉት ሁሉ የክርስቶስን ምሳሌ ይከተላሉ ለማለት እንደማይቻል የታወቀ ነው። ሩዋንዳ ውስጥ በቅርቡ ተከስቶ የነበረው ግፍ የተፈጸመው አብዛኞቹ አባሎቻቸው ክርስቲያኖች ነን እያሉ በሚናገሩ ጎሳዎች ነው። በሩዋንዳ ለ20 ዓመታት የሠሩ ፒላር ዲዪስ ኤስፔሎሲን የተባሉ አንዲት የሮማ ካቶሊክ መነኩሲት ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ድርጊት በዝርዝር ተናግረዋል። አንድ ሰውዬ ከዚህ በፊት ሰው እንደገደለበት በግልጽ የሚያስታውቅ ጦር ይዞ ወደ መነኩሲቷ ቤተ ክርስቲያን መጣ። “እየዞርክ ሰዎችን የምትገድለው ለምንድን ነው? ክርስቶስን አትፈራም?” በማለት መነኩሲቷ ጠየቁት። ክርስቶስን እንደሚፈራ ተናገረና ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ገብቶ ተንበረክኮ መቁጠሪያውን ይዞ ጸለየ። ሲጨርስ ግን ጭፍጨፋውን ለመቀጠል ወጣ። “ይህ ሁኔታ ወንጌልን በተገቢው መንገድ እያስተማርን አለመሆናችንን ያሳያል” በማለት መነኩሲቷ ስህተታቸውን አምነዋል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቶቹ የተሳሳቱ ድርጊቶች የኢየሱስ አባባል ጉድለት እንዳለበት አያሳዩም። ጥላቻ እውነተኛውን ክርስትና በሚከተሉ ሰዎች ሊሸነፍ ይችላል።
በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ጥላቻን ማሸነፍ
ማክስ ሊብስተር በጀርመኑ ታላቅ እልቂት ውስጥ ያለፈ አይሁዳዊ ዝርያ ያለው ሰው ነው። ምንም እንኳ ቅጽል ስሙ “የተወደደ” የሚል ትርጉም ያለው ቢሆንም ከአቅሙ በላይ የሆነ ጥላቻ አይቷል። በናዚ ጀርመን ውስጥ ስለ ፍቅርና ጥላቻ የተማረውን ቀጥሎ ባለው ሁኔታ ገልጿል።
“በ1930ዎቹ ዓመታት ጀርመን ውስጥ በምትገኘው ማንሄዪም ከተማ አቅራቢያ አደግሁ። ሂትለር አይሁዶች በጠቅላላ የጀርመንን ሕዝብ በመበዝበዝ ራሳቸውን ያለ አግባብ እንዳበለጸጉ ተናግሮ ነበር። ነገር ግን አባቴ ተራ ጫማ ሰፊ ነበር። ያም ሆነ ይህ የናዚ ቅስቀሳ ባሳደረው ተጽዕኖ ጎረቤቶቻችን በእኛ ላይ ጥላቻ ማሳደር ጀመሩ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለሁ አንድ መንደርተኛችን በጉልበት ተጠቅሞ ግንባሬ ላይ የአሳማ ደም ቀባኝ። ይህ ከባድ የሆነ ማዋረድ ወደፊት ለሚመጣው ነገር ቅምሻ ብቻ ነበር። በ1939 የምሥጢር ፖሊሶች ያዙኝና ያለኝን ንብረት በጠቅላላ ወረሱት።
“ከጥር 1940 እስከ ግንቦት 1945 ድረስ ዛክሰንሃውዘን፣ ኔየንጋሜ፣ ኦሽቪትዝ፣ ቡና እና ቡከንቫልድ በተባሉ አምስት የተለያዩ የእስረኛ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ሕይወቴን ለማትረፍ ታገልኩ። ወደ ዛክሰንሃውዘን ተልኮ የነበረው አባቴም በጣም አስቸጋሪ በነበረው በ1940 ክረምት ሞተ። የአባቴን አስከሬን በእሳት የሚቃጠሉ አስከሬኖች ወደተቆለሉበት ሥፍራ የወሰድኩት እኔው ራሴ ነበርኩ። በካምፖቹ ውስጥ በአጠቃላይ ስምንት ቤተሰቦቼ ሞተዋል።
“ካፖስ የሚባሉት እስረኞች ከሂትለር ኤስ ኤስ ወታደሮች ይበልጥ የተጠሉ ነበሩ። ካፖስ የሚባሉት ከሂትለር ኤስ ኤስ ወታደሮች ጋር የተባበሩና በዚህም የተነሳ አንዳንድ መብቶችን ያገኙ እስረኞች ናቸው። የምግብ እደላውን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ ከመሾማቸውም በተጨማሪ ሌሎች እስረኞችን እንዲገርፉ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። ብዙውን ጊዜ ግፈኞችና ፍርደ ገምድል ነበሩ። የናዚ ኤስ ኤስ ወታደሮችንና ካፖስ እስረኞችን የምጠላበት ብዙ ምክንያት እንዳለኝ ቢሰማኝም እስረኛ በነበርኩበት ወቅት ፍቅር ከጥላቻ ይበልጥ ኃይል እንዳለው ተምሬአለሁ።
“የይሖዋ ምሥክር የሆኑ እስረኞች ያላቸው ጥንካሬ እምነታቸው በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ስላሳመነኝ እኔም ራሴ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። በኔየንጋሜ የእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ያገኘሁት ኧርነስት ቫኡር የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንድኮተኩት ያበረታታኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ ‘ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ’ ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:23) በቀልን የሁሉም ነገር ፈራጅ በሆነው አምላክ ላይ በመተው ልክ እንደ ኢየሱስ ለማድረግ ጥረት አደረኩ።
“በካምፖቹ ውስጥ ያሳለፍኳቸው ዓመታት ሰዎች ብዙውን ጊዜ መጥፎ ነገር የሚያደርጉት ካለማወቅ የተነሳ እንደሆነ አስተምረውኛል። ሌላው ቀርቶ ከሂትለር ኤስ ኤስ ወታደሮች መካከል እንኳ አንዳንዶቹ ጥሩዎች ናቸው። ሕይወቴን ያተረፈልኝ አንድ የሂትለር ወታደር ነበር። አንድ ጊዜ ኃይለኛ የተቅማጥ በሽታ ስለተነሳብኝ ከሥራ ወደ ካምፑ ለመሄድ ምንም ጉልበት አልነበረኝም ነበር። በማግሥቱ ጠዋት ወደ ኦሽቪትዝ የጋዝ ምድጃ መላክ ነበረብኝ፤ ነገር ግን እኖርበት ከነበረው የጀርመን ክልል የመጣ አንድ የሂትለር ኤስ ኤስ ወታደር ረዳኝ። እስካገግም ድረስ ጥቂት እረፍት ማግኘት በምችልበት የሂትለር ኤስ ኤስ ወታደሮች ካፍቴሪያ ውስጥ እንድሠራ አመቻቸልኝ። አንድ ቀን እንዲህ በማለት የልቡን አጫወተኝ፦ ‘ማክስ፤ ፍሬኑ ተበጥሶ በከፍተኛ ፍጥነት በሚጓዝ ባቡር ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ ይሰማኛል። ከዘለልኩ እሞታለሁ። እንደተሳፈርኩ ከቀጠልኩ ከባቡሩ ጋር አብሬ እከሰከሳለሁ!’
“እኔ ፍቅር ያስፈልገኝ እንደነበረ ሁሉ እነዚህ ሰዎችም ፍቅር ያስፈልጋቸው ነበር። እንዲያውም አስከፊ ሁኔታዎችንና በየዕለቱ የሚደርሱብኝን የግድያ ዛቻዎች እንድቋቋም ያስቻለኝ ፍቅርና ርኅራኄ በአምላክ ላይ ካለኝ እምነት ጋር ተዳምረው ነው። ምንም ጉዳት ሳይደርስብኝ በሕይወት ተርፌአለሁ ማለት ባልችልም የደረሰብኝ የስሜት ጠባሳ ግን አነስተኛ ነው።”
ማክስ ከ50 ዓመት በኋላ አሁንም የሚያንጸባርቀው ሞቅ ያለ ስሜትና ደግነት የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን በግልጽ የሚመሠክሩ ናቸው። የማክስ ሁኔታ ከሌሎች የተለየ አይደለም። ማክስ በጥላቻ ላይ ድል ለመቀዳጀት ያስቻለው ጠንካራ ምክንያት ነበረው፤ ይኸውም ክርስቶስን ለመምሰል መፈለጉ ነው። ሕይወታቸው በቅዱሳን ጽሑፎች የሚመራ ሌሎች ሰዎችም ልክ እንዲሁ አድርገዋል። ፈረንሳይ ውስጥ የምትኖር ሲሞን የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ራስ ወዳድ ያልሆነ ፍቅር ምን ማለት መሆኑን እንዴት እንዳወቀች ቀጥሎ በሰፈረው ሁኔታ ገልጻለች።
“ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ ጥቂት ቀደም ብላ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ኤማ የተባለችው እናቴ ሰዎች ብዙውን ጊዜ መጥፎ የሚያደርጉት ሌላ ጥሩ ነገር ስለማያውቁ ነው በማለት ታስተምረኝ ነበር። ኢየሱስ ጠላቶቻችንን እንድንወድና ለሚያሳድዱን ሰዎች እንድንጸልይ ስለተናገረ እነርሱ ሲጠሉን መልሰን የምንጠላቸው ከሆነ እውነተኛ ክርስቲያኖች አይደለንም ማለት ነው ትለኛለች።—ማቴዎስ 5:44
“ይህንን ጠንካራ እምነቷን የፈተነ አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ አስታውሳለሁ። ናዚ ፈረንሳይን ተቆጣጥሮ በነበረበት ጊዜ እኛ ባለንበት ሕንፃ ውስጥ በምትኖር ጎረቤታችን የተነሳ እናቴ ብዙ መከራ ደረሰባት። ይህች ሴት እናቴን ለናዚ የምሥጢር ፖሊሶች ጠቆመቻት፤ በዚህም የተነሳ ለሞት እስክትቃረብ ድረስ በተሠቃየችበት በጀርመን የእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ሁለት ዓመታት አሳለፈች። ከጦርነቱ በኋላ ይህች ሴት የጀርመኖች ተባባሪ እንደነበረች በሚገልጽ ወረቀት ላይ እናቴ እንድትፈርም የፈረንሳይ ፖሊሶች ፈልገው ነበር። ነገር ግን እናቴ ‘አምላክ ለጥሩውና ለመጥፎው እንደ ሥራው የሚሰጥ ፈራጅ ነው’ በማለት አልፈርምም አለች። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይህችው ጎረቤታችን ሞት በሚያስከትል ካንሰር ታመመች። እናቴ ይህች ሴት በደረሰባት መጥፎ አጋጣሚ ከመደሰት ይልቅ ልትሞት በተቃረበችበት በዚህ ወቅት የተቻላትን ያህል ረዳቻት። ፍቅር በጥላቻ ላይ የተቀዳጀውን ይህንን ድል መቼም ቢሆን አልረሳውም።”
እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅር የፍትሕ መጓደል በሚፈጸምበት ጊዜ ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያሳያሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ለመውደድ ጊዜ አለው፣ ለመጥላትም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 8) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
ለመጥላት ጊዜ አለው
አምላክ ሁሉንም ዓይነት ጥላቻ አላወገዘም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ” በማለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይናገራል። (ዕብራውያን 1:9) ቢሆንም መጥፎውን በመጥላትና መጥፎ ነገር የፈጸመውን ሰው በመጥላት መካከል ልዩነት አለ።
ኢየሱስ በፍቅርና በጥላቻ መካከል ያለውን ተገቢ የሆነ ሚዛናዊ አመለካከት አሳይቷል። ግብዝነትን ይጠላ ነበር፤ ነገር ግን ግብዞች አመለካከታቸውን እንዲለውጡ ለመርዳት ጥሯል። (ማቴዎስ 23:27, 28፤ ሉቃስ 7:36–50) ዓመፅን አውግዟል፤ እርሱን ለገደሉት ሰዎች ግን ጸልዮአል። (ማቴዎስ 26:52፤ ሉቃስ 23:34) ምንም እንኳ ዓለም ከመሬት ተነስቶ ቢጠላውም ዓለም ሕይወት እንዲያገኝ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 6:33, 51፤ 15:18, 25) በመሠረታዊ ሥርዓት ስለሚመራው ፍቅርና ስለ አምላካዊ ጥላቻ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል።
የፍትሕ መጓደል ልክ እንደ ኢየሱስ ተገቢ የሆነ ቁጣ ያስቆጣን ይሆናል። (ሉቃስ 19:45, 46) ነገር ግን ክርስቲያኖች ራሳቸው እንዲበቀሉ አልተፈቀደላቸውም። ጳውሎስ “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ” በማለት ሮም የሚኖሩትን ክርስቲያኖች መክሯል። በመቀጠልም “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ” አላቸው። (ሮሜ 12:17–21) የጥላቻ ቂም መያዝን ወይም በቀልን ወደ ጎን ካደረግን ፍቅር ድል ይቀዳጃል።
ጥላቻ የማይኖርበት ዓለም
ጥላቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲወገድ ከተፈለገ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያላቸው ሥር የሰደደ ጠባይ መለወጥ አለበት። ይህ እንዴት ሊሰምር ይችላል? ፕሮፌሰር ኧርቨን ሰታኡብ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፦ “ዝቅ አድርገን የምንመለከታቸውን ሰዎች እንጎዳቸዋለን እንዲሁም ከፍ አድርገን የምንመለከታቸውን ሰዎች እንረዳቸዋለን። ሰዎችን ከፍ አድርገን በተመለከትናቸው መጠን እንረዳቸዋለን፤ በዚህም ከመርዳት የሚገኘውን እርካታ ከማግኘታችንም በተጨማሪም ሌሎችን የምንረዳና ለሌሎች አሳቢ እንሆናለን። ካሉን ግቦች አንዱ ለሌሎች መልካም የማድረግ ሰፊ ተሳትፎ ያለበት ኅብረተሰብ መፍጠር መሆን አለበት።”—ዘ ሩትስ ኦቭ ኢቭል
በሌላ አባባል ጥላቻን ማስወገድ ሰዎች እርስ በርስ በመረዳዳት መፈቃቀርን የሚማሩበት ኅብረተሰብ መፍጠርን፤ በዘር ልዩነት፣ በብሔራዊ ስሜት፣ በዘረኝነትና በጎሰኝነት ምክንያት የተከሰቱትን ጥላቻዎች በሙሉ ወደኋላ በመተው እርስ በርስ ተስማምተው የሚኖሩ ሰዎች ያሉበት ኅብረተሰብ መፍጠርን ይጠይቃል። እንዲህ ያለ ኅብረተሰብ ይገኛልን? ቻይና ውስጥ የባሕል አብዮት በተካሄደበት ወቅት ጥላቻን የተመለከተ የአንድ ሰው ተሞክሮ ተመልከት።
“የባሕል አብዮቱ ሲጀምር ‘ከመደብ ትግሉ’ ማፈግፈግ እንደማይቻል ተምረን ነበር። የሬድ ጋርድ አባል ከሆንኩ በኋላ ሌላው ቀርቶ ከራሴ ቤተሰቦች መካከል እንኳን ሳይቀር ‘የመደብ ጠላቶች’ የሆኑትን ሁሉ ከያሉበት እያደንኩ መያዝ ጀመርኩ። ምንም እንኳ ያን ጊዜ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ብገኝም ‘የተቃውሞ ዝንባሌ’ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት በሚደረገው አሰሳ ተካፍያለሁ። ‘ፀረ አብዮተኞችን’ የሚያወግዙ ሕዝባዊ ስብሰባዎቸንም መርቼአለሁ። እርግጥ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ክሶች ከፖለቲካዊ አመለካከቶች ይልቅ በግል ጥላቻ ላይ የተመሠረቱ ነበሩ።
“ወጣትና ሽማግሌ፣ ወንድና ሴት ሳይባሉ ብዙ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አሠቃቂ እየሆነ የመጣ ግርፋት ሲደርስባቸው ተመልክቻለሁ። በጣም ጥሩ ሰው የነበረ አንድ የትምህርት ቤት አስተማሪዬ ወንጀለኛ እንደሆነ ተደርጎ ለመቀጣጫ በየጎዳናው እንዲዞር ተደርጓል። ከሁለት ወራት በኋላ በምማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምር አንድ ሌላ ጎበዝ አስተማሪ ሱጆ ወንዝ ውስጥ ሞቶ ተገኘ፤ እንዲሁም የእንግሊዝኛ አስተማሪዬ ራሱን እንዲሰቅል ተገደደ። ደነገጥኩ እንዲሁም ግራ ተጋባሁ። እነዚህ ደግ ሰዎች ነበሩ። በእነዚህ ሰዎች ላይ ይህንን መፈጸሙ ስህተት ነበር! ስለዚህ ከሬድ ጋርዶች ጋር የነበረኝን ማንኛውንም ግንኙነት አቆምኩ።
“ቻይናን ለአጭር ጊዜ የዋጣት ይህ የጥላቻ ወቅት በዓይነቱ ብቸኛ አይመስለኝም። ባለንበት መቶ ዘመን በጣም ብዙ የሆኑ ጥላቻዎቸ ሲፈነዱ ታይተዋል። ቢሆንም ፍቅር ጥላቻን ማሸነፍ እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ። ይህም በራሴ ላይ የደረሰ ነው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ስጀምር ከተለያየ ዘርና የኑሮ ደረጃ ለመጡ ሰዎች በሚያሳዩት ልባዊ ፍቅር ተመሰጥኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንደሚሰጠው ሁሉም ሰዎች እርስ በርስ መፈቃቀር የሚማሩበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።”
አዎን፣ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ማኅበር ጥላቻ ከነአካቴው ሊወገድ እንደሚችል የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። ምሥክሮቹ የትኛውም ዓይነት አስተዳደግ ቢኖራቸው የዘር ልዩነትን እርስ በርስ በመከባበር ለመተካትና ማንኛውንም የጎሰኝነት፣ የዘረኝነት ወይም የብሔራዊ ስሜት ምልክት ለማስወገድ ይጥራሉ። ይህ እንዲሳካላቸው ያስቻለው አንዱ ምክንያት በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራውን ፍቅር በማሳየት ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል ያደረጉት ቁርጥ ውሳኔ ነው። ሌላኛው ምክንያት ደግሞ የአምላክ መንግሥት የሚደርስባቸውን ማንኛውንም የፍትሕ መጓደል ወደ ፍጻሜ እንደሚያመጣላቸው መጠባበቃቸው ነው።
ጥላቻ የሌለበት ማለትም የምንጠላው ክፉ ነገር እንኳ የማይኖርበትን ዓለም የሚያስገኘው አስተማማኝ መፍትሄ የአምላክ መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘አዲስ ሰማይ’ ተብሎ ተገልጿል፤ ይህ ሰማያዊ መንግሥት የፍትሕ መጓደል ለሌለበት ዓለም ዋስትና ይሆናል። ይህ መንግሥት ‘በአዲስ ምድር’ ወይም እርስ በርስ መዋደድን በሚማር አዲስ የሰዎች ኅብረተሰብ ላይ ይገዛል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 54:13) የማክስ፣ የሲሞንና የሌሎች ብዙ ሰዎች ተሞክሮ እንደሚያረጋግጠው ይህ ትምህርት አሁንም በመሰጠት ላይ ነው። አሁን ያለው መለኮታዊ ትምህርት ጥላቻንና መንስዔዎቹን ለማስወገድ ወደፊት በዓለም ዙሪያ ለሚሰጠው የትምህርት መርሐ ግብር ቅምሻ ብቻ ነው።
ይሖዋ በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል የትምህርት መርሐ ግብሩ የሚያስከትለውን ውጤት ሲገልጽ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 11:9) አምላክ ራሱ ጥላቻ ይበቃል የሚልበት ጊዜ ይመጣል። በእርግጥም ያ ጊዜ የእርስ በርስ ፍቅር የሰፈነበት ይሆናል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ናዚዎች በማክስ ሊብስተር ግራ እጅ ላይ የእስር ቤት ቁጥር ነቅሰውበት ነበር
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥላቻ በቅርቡ ጊዜ ያለፈበት ነገር ይሆናል