የአንባብያን ጥያቄዎች
የኢየሱስ እናት የሆነችው ማርያም ዘመዷን ኤልሳቤጥን ልትጠይቅ ስትሄድ እርጉዝ ነበረችን?
አዎን፣ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው አርግዛ ነበር።
በሉቃስ ምዕራፍ 1 ላይ በመጀመሪያ የምናነበው ዮሐንስን (አጥማቂውን) ስለ ወለደቸው ስለ ካህኑ ዘካርያስ ሚስት ስለ ኤልሳቤጥ እርግዝና ነው። ኤልሳቤጥ ባረገዘች “በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል” እንደምትፀንስና “የልዑል ልጅም” እንደምትወልድ ለመንገር ወደ ማርያም ዘንድ መጣ። (ሉቃስ 1:26፣ 30–33) ታዲያ ማርያም የፀነሰችው መቼ ነው?
ማርያም ከዚህ በኋላ ብዙም ሳትቆይ ነፍሰ ጡር የነበረችውን ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ እንደሄደች በመግለጽ ሉቃስ የጻፈው ታሪክ ሐሳቡን ይቀጥላል። ሁለቱ ሴቶች በተገናኙ ጊዜ በኤልሳቤጥ ማኅፀን ውስጥ ያለው ፅንስ (ዮሐንስ) ዘለለ። ኤልሳቤጥ ‘በማርያም ማኅፀን ያለውን ፍሬ’ በማመልከት ማርያምን “የጌታዬ እናት” በማለት ጠራቻት። (ሉቃስ 1:39–44) ስለዚህ ትክክለኛ የሆነው መደምደሚያ ማርያም ኤልሳቤጥን ለማየት በሄደችበት ጊዜ እርጉዝ ነበረች ማለት ነው።
ሉቃስ 1:56 እንዲህ ይነበባል፦ “ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርሷ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤቷም ተመለሰች።” ይህ ጥቅስ ትክክለኛውን ቀን ለማወቅ የሚያስችል ሐሳብ አልሰጠም። “ሦስት ወር የሚያህል” ጊዜ ይላል፤ ይህ ደግሞ ኤልሳቤጥን ወደ ዘጠነኛው የእርግዝና ወሯ ያስገባታል።
ማርያም ኤልሳቤጥን በመጨረሻዎቹ የእርግዝናዋ ወራት ስትረዳት ከቆየች በኋላ ማርያም ወደ ቤቷ ወደ ናዝሬት ተመለሰች። ምናልባት ኤልሳቤጥ (ዮሐንስን) ከወለደች በኋላ ብዙ ጠያቂዎች እንደሚመጡ፣ ከእነዚህም ውስጥ ዘመዶቿ ሊኖሩ እንደሚችሉ ማርያም አስባ ሊሆን ይችላል። ያ ደግሞ ሳታገባ ላረገዘች አንዲት ወጣት ሴት የሚያሳፍርና የሚያስጨንቅ ነው። ማርያም ወደ ናዝሬት ስትመለስ ከፀነሰች ምን ያህል ጊዜ ሆኗት ነበር? ከኤልሳቤጥ ጋር “ሦስት ወር የሚያህል” ጊዜ አብራ ስለነበረች ማርያም ወደ ናዝሬት ስትመለስ ምናልባት ሦስተኛ ወሯን ጨርሳ አሊያም አራተኛ ወሯን ጀምራ ሊሆን ይችላል።