የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 8/1 ገጽ 14-19
  • እስከ ዘመናችን ድረስ ከይሖዋ መማር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እስከ ዘመናችን ድረስ ከይሖዋ መማር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በጣም ጥሩ የሆነ የአስተማሪና የተማሪ ግንኙነት
  • ሰፊ የማስተማር መርሐ ግብር
  • በጉባኤ ስብሰባዎች ውስጥ መማር
  • በትልልቅ ስብሰባዎች መማር
  • ለማስተማር ከአምላክ መማር
  • የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን መማር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • አስተማሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • መለኮታዊ ትምህርት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ቅመሱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • “ምሳሌ ትቼላችኋለሁ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 8/1 ገጽ 14-19

እስከ ዘመናችን ድረስ ከይሖዋ መማር

“እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል።”—ኢሳይያስ 50:4

1, 2. (ሀ) ይሖዋ በጣም የሚወደውን ተማሪውን ያዘጋጀው ለምን ነገር ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ? (ለ) ኢየሱስ ትምህርቱን ከማን እንዳገኘው የገለጸው እንዴት ነው?

ይሖዋ አምላክ አባት ከሆነበት ጊዜ አንሥቶ ሲያስተምር ቆይቷል። አንዳንድ ልጆቹ ካመፁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የበኩር ልጁ የሆነውን በጣም የሚወደውን ተማሪውን በምድር ላይ ለሚያከናውነው አገልግሎት አዘጋጀው። (ምሳሌ 8:30) የኢሳይያስ ምዕራፍ 50 ትንቢት “የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል” በማለት ይህን ተማሪ ያስተዋውቀዋል። (ኢሳይያስ 50:4) ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት የአባቱን ትምህርት በሥራ ላይ ስላዋለ ‘ለደከሙትና ሸክማቸው ለከበዳቸው’ ሁሉ የእረፍት ምንጭ ነበር።—ማቴዎስ 11:28–30

2 ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙ ተአምራትን ፈጽሟል። የዕውራን ዓይን እንዲገለጥ አድርጓል፣ ሌላው ቀርቶ ሙታንን አስነሥቷል፤ ነገር ግን በዘመኑ በነበሩት ሰዎች ዘንድ በተለይ የሚታወቀው በአስተማሪነቱ ነበር። ተከታዮቹም ሆኑ ተቃዋሚዎቹ የሚጠሩት መምህር ብለው ነበር። (ማቴዎስ 8:19፤ 9:11፤ 12:38፤ 19:16፤ ዮሐንስ 3:2) ኢየሱስ ባስተማረው ትምህርት ራሱ እንዲከበር አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ በትሕትና እንደሚከተለው ብሏል፦ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም።” ‘አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን ነገሮች እናገራለሁ።’—ዮሐንስ 7:16፤ 8:28፤ 12:49

በጣም ጥሩ የሆነ የአስተማሪና የተማሪ ግንኙነት

3. ይሖዋ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ያለውን አሳቢነት የኢሳይያስ ትንቢት የሚጠቁመው እንዴት ነው?

3 አንድ ጥሩ አስተማሪ ለእያንዳንዱ ተማሪ በግል ፍቅራዊና ጥንቃቄ የተሞላበት አሳቢነት ያሳያል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 50 ይሖዋ አምላክ ለሚያስተምራቸው ሰዎች እንዲህ ዓይነት አሳቢነት እንደሚያሳይ ይገልጻል። ትንቢቱ “ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፣ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል” በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 50:4) እዚህ ላይ የገባው ቃል ተማሪዎቹን ለማስተማር በማለዳ የሚቀሰቅሳቸውን አስተማሪ ያመለክታል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር በትንቢቱ ትርጉም ላይ አስተያየት ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ሐሳብ በምሳሌያዊ አባባል መድኃኒታችን . . . በአምላክ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደሚገባ ያመለክታል፤ በዚህ አማካኝነት ሌሎችን ለማስተማር ብቁ ይሆናል። . . . መሲሑ በመለኮታዊ ትምህርት አማካኝነት የሰው ልጆች አስተማሪ ለመሆን ብቁ ይሆናል።”

4. ኢየሱስ ለአባቱ ትምህርት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

4 ተማሪዎች ለአስተማሪያቸው ትምህርት አዎንታዊ ምላሽ ቢሰጡ ጥሩ ነው። ኢየሱስ ለአባቱ ትምህርት ምን ምላሽ ሰጠ? እሱ የሰጠው ምላሽ ኢሳይያስ 50:5 ላይ “ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፣ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም” ከሚለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነበር። አዎን፣ ኢየሱስ ለመማር ይጓጓ ነበር። በጥሞና ያዳምጥ ነበር። ከዚህም በላይ አባቱ የጠየቀውን በሙሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። ዓመፀኛ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ “የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ” በማለት ጸልዮአል።—ሉቃስ 22:42

5. (ሀ) ኢየሱስ በምድር ላይ የሚደርስበትን መከራ አስቀድሞ እንደሚያውቅ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በኢሳይያስ 60:6 ላይ ያለው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው?

5 ልጁ የአምላክን ፈቃድ ማድረጉ ምን ነገሮች እንደሚያስከትልበት በቅድሚያ እንደተነገረው ትንቢቱ ይጠቁማል። ይህም ተማሪው “ጀርባዬን ለገራፊዎች ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ፣ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም” ሲል በተናገረው ቃል ታይቷል። (ኢሳይያስ 50:6) ትንቢቱ እንደሚጠቁመው ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ከፍተኛ መንገላታት ደርሶበታል። ሐዋርያው ማቴዎስ ‘በፊቱ ተፉበት፤ ሌሎች ደግሞ በጥፊ መቱት’ ሲል ጽፏል። (ማቴዎስ 26:67) ይህ የሆነው በ33 እዘአ በማለፍ በዓል ምሽት በሃይማኖታዊ መሪዎች እጅ አልፎ በተሰጠበት ወቅት ነበር። በሚቀጥለው ቀን የሮም ወታደሮች በእንጨት ላይ ሰቅለው ከመግደላቸው በፊት ያለ ርኅራኄ ሲገርፉት ኢየሱስ ዝም ብሎ ተገርፏል።—ዮሐንስ 19:1–3, 16–23

6. ኢየሱስ በአስተማሪው ላይ የነበረውን ትምክህት በጭራሽ እንዳላጣ የሚያሳየው ምንድን ነው? በአስተማሪው ላይ ያለው ትምክህት የተካሰው እንዴት ነው?

6 ልጁ ቀደም ሲል በሚገባ የተማረ ስለነበር በአስተማሪው ላይ የነበረውን ትምክህት አላጣም። ይህም በትንቢቱ መሠረት ቀጥሎ በሚናገረው “ልዑል እግዚአብሔር ስለሚረዳኝ የእነርሱ ስድብ ሊጎዳኝ አይችልም” በሚለው ቃል ታይቷል። (ኢሳይያስ 50:7 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ አስተማሪው በሚሰጠው እርዳታ ላይ መተማመኑ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶለታል። አባቱ ከሌሎች የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አድርጎታል። (ፊልጵስዩስ 2:5–11) ከይሖዋ ትምህርት ጋር በታዛዥነት ከተጣበቅንና ‘ወደ ኋላ ካልተመለስን’ ከፍተኛ በረከቶች ይጠብቁናል። ይህ ትምህርት እስከ ዘመናችን ድረስ እንዴት እንደተዳረሰ እንመልከት።

ሰፊ የማስተማር መርሐ ግብር

7. ይሖዋ በምድር ላይ የማስተማር ሥራውን ሲያካሄድ የቆየው እንዴት ነው?

7 ከዚህ በፊት እንደተመለከትነው ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መለኮታዊ ትምህርት ለመስጠት ምድራዊ ወኪሉ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ተጠቅሞበታል። (ዮሐንስ 16:27, 28) ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጊዜያት የአምላክ ቃል የትምህርቱ ምንጭ እንደሆነ የጠቆመ ሲሆን ይህን በማድረጉም ላስተማራቸው ሰዎች ምሳሌ ሆኗል። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10፤ 21:13፤ 26:24, 31) ከዚያ በኋላ ይሖዋ ያወጣው የማስተማር መርሐ ግብር እነዚህ የተማሩ ሰዎች ባከናወኑት አገልግሎት አማካኝነት በምድር ላይ ሲካሄድ ቆይቷል። ኢየሱስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ እንዳዘዛቸው አስታውስ። (ማቴዎስ 28:19, 20፣ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) እነዚህ ደቀ መዛሙርት ‘የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው . . . የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን’ አባላት ሆኑ። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) በተጨማሪም ከይሖዋ የሚማሩባቸው ራሳቸውን የቻሉ ጉባኤዎች ተቋቋሙ። (ሥራ 14:23፤ 15:41፤ 16:5፤ 1 ቆሮንቶስ 11:16) በዚህ መንገድ መለኮታዊ ትምህርት እስከ ዘመናችን ድረስ መሰጠቱን ቀጥሏልን?

8. ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ የሚያካሄደውን የስብከት ሥራ የሚመራበትን መንገድ የጠቆመው እንዴት ነው?

8 በእርግጥም ቀጥሏል! ኢየሱስ ከመሞቱ ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ ይህ የነገሮች ሥርዓት ከማክተሙ በፊት ከፍተኛ የስብከት ሥራ እንደሚካሄድ ተንብዮአል። “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። ኢየሱስ ከዚህ በመቀጠል ይህን ዓለም አቀፍ የስብከትና የማስተማር መርሐ ግብር ለመምራት በምን እንደሚጠቀም ገለጸ። ለአገልጋዮቹ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ እንደ መገናኛ መስመር ወይም መሣሪያ ሆኖ ስለሚያገለግለው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14, 45–47) ይሖዋ አምላክ በመላው ምድር ላይ ያሉትን የመንግሥቱን ጥቅሞች በበላይነት ለመቆጣጠር በዚህ “ባሪያ” እየተጠቀመ ነው።

9. ታማኝና ልባም ባሪያ እነማንን ያቀፈ ነው?

9 በአሁኑ ወቅት ታማኝና ልባም ባሪያ የመንግሥቱ ወራሾች የሆኑትን ቀሪዎች ያቀፈ ነው። እነዚህ “የአብርሃም ዘር” ክፍል እና “የክርስቶስ የሆኑት” ከ144,000ዎቹ መካከል በምድር ላይ የቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። (ገላትያ 3:16, 29፤ ራእይ 14:1–3) ታማኝና ልባም ባሪያን ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ታማኝና ልባም ባሪያን ለይቶ ማወቅ የሚቻለው በተለይ በሚሠሩት ሥራና የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ባላቸው የጠበቀ ቁርኝት ነው።

10. ባሪያው የይሖዋን ትምህርቶች ለማሰራጨት የተጠቀመባቸው ጽሑፎች የትኞቹ ናቸው?

10 በአሁኑ ወቅት ይሖዋ ይህን “ባሪያ” ሰዎችን ለማስተማር እንደ መሣሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። እነዚህ የባሪያው ክፍል የሆኑ ሰዎች በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን ስም ተቀብለዋል። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከእነሱ ጋር መሰብሰብ ከመጀመራቸውም በላይ ይህን ስም በመቀበል የአምላክን መንግሥት በማወጁ ተግባር ተባባሪ ሆነዋል። የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት ‘የባሪያው’ ክፍል ለማስተማር የሚጠቀምበት ዋነኛው መሣሪያ ነው። ሆኖም ባሪያው መጻሕፍትን፣ ብሮሹሮችን፣ ትራክቶችንና ንቁ! መጽሔትን ጨምሮ በሌሎች ጽሑፎችም ይጠ ቀማል።

11. ይህ “ባሪያ” የሚያካሄዳቸው ትምህርት ቤቶች የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙባቸው ዓላማዎች ምንድን ናቸው?

11 ከዚህም በላይ ይህ “ባሪያ” የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን ያካሄዳል። ከእነዚህም መካከል ወጣት አገልጋዮችን ለውጭ አገር የሚስዮናዊነት አገልግሎት የሚያዘጋጃቸው የአምስት ወራት ኮርስ የሚሰጥበት የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤትና ያላገቡ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ለልዩ ቲኦክራሲያዊ ምድቦች የሚሠለጥኑበት ሁለት ወራት የሚፈጀው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ኮርስ ይገኙበታል። በተጨማሪም ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ጉባኤ ኃላፊነቶቻቸውን በተመለከተ በየጊዜው ትምህርት የሚያገኙበት የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤትና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራቸው ይበልጥ የተዋጣላቸው እንዲሆኑ የሚያስታጥቃቸው የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት አለ።

12. በማስተማሩ መርሐ ግብር ውስጥ የሚካተተውና በየሳምንቱ የሚከናወነው ነገር ምንድን ነው?

12 በማስተማሩ መርሐ ግብር ውስጥ የሚካተተው ሌላው ነገር በመላው ዓለም ባሉ ከ75,500 በሚልቁ ጉባኤዎች ውስጥ የሚካሄዱት አምስት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ናቸው። ከእነዚህ ስብሰባዎች በተቻለ መጠን ሙሉ በሙሉ ትጠቀማለህን? ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት በትኩረት በመከታተል በምሳሌያዊ አባባል በአምላክ ትምህርት ቤት ውስጥ እንዳለህ እንደምታምን ታሳያለህን? የምታሳየው መንፈሳዊ እድገት ‘የተማሩት ምላስ’ እንዳለህ ለሌሎች ሰዎች ግልጽ ያደርጋልን?—ኢሳይያስ 50:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16

በጉባኤ ስብሰባዎች ውስጥ መማር

13. (ሀ) በአሁኑ ወቅት ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚያስተምርበት አንዱ ዐቢይ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ለመጠበቂያ ግንብ አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

13 ይሖዋ በተለይ ሕዝቦቹን የሚያስተምረው መጠበቂያ ግንብ ን እንደ ማስተማሪያ መሣሪያ በመጠቀም በሚደረገው ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ነው። ይህን ስብሰባ ከይሖዋ ልትማር እንደምትችልበት ቦታ አድርገህ ትመለከተዋለህን? ኢሳይያስ 50:4 በመጀመሪያ ደረጃ የሚሠራው ለኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም “የተማሩትን ምላስ” ለማግኘት በአምላክ ዝግጅቶች ለሚጠቀሙ ሁሉ ሊሠራ ይችላል። መጠበቂያ ግንብ ን እንደ ውድ ሀብት እንደምትመለከተው የምታሳይበት አንዱ መንገድ በተቻለ መጠን እያንዳንዱ እትም እንደ ደረሰህ በማንበብ ነው። ከዚያም መጠበቂያ ግንብ በጉባኤ ሲጠና በስብሰባው ላይ በመገኘትና ተስፋህን በሕዝብ ፊት ለመግለጽ ተዘጋጅተህ በመሄድ ለይሖዋ አድናቆት ማሳየት ትችላለህ።—ዕብራውያን 10:23

14. (ሀ) በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ትልቅ መብት የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ይበልጥ የሚያበረታታው ልጆች ምን ዓይነት ሐሳቦችን ሲሰጡ ነው?

14 በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት በይሖዋ ታላቅ የማስተማር መርሐ ግብር ላይ ተሳትፎ ልታደርግ መቻልህን ታደንቃለህን? እንደምታደንቅ አያጠራጥርም፣ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት በጣም አስፈላጊ የሆነ እርስ በርስ “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ” የምንነቃቃበት አንዱ መንገድ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) ልጆችም ጭምር በዚህ የማስተማር መርሐ ግብር ሊሳተፉ ይችላሉን? አዎን፣ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ልጆች የሚሰጧቸው ከልብ የመነጩ ሐሳቦች አዋቂዎችን ያበረታቷቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ወደ ስብሰባዎቻችን የመጡ አዳዲስ ሰዎች ልጆች በሰጧቸው ሐሳቦች ተገፋፍተው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ይበልጥ በቁም ነገር ተመልክተዋል። አንዳንድ ልጆች ከአንቀጹ እያነበቡ ወይም አዋቂዎች በጆሮአቸው ከነገሯቸው በኋላ በመድገም ሐሳብ መስጠት ለምደዋል። ሆኖም የሚሰጡት ሐሳብ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ሲሆን ይበልጥ ያበረታታል። እንደዚህ ዓይነቱ ሐሳብ ለታላቁ አስተማሪያችንና ከፍ ላለው የማስተማር መርሐ ግብሩ ክብር እንደሚያመጣ የተረጋገጠ ነው።—ኢሳይያስ 30:20, 21

15. ልጆቻቸው ይበልጥ የተሻለ ሐሳብ እንዲሰጡ ለመርዳት ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?

15 ልጆች ይሖዋን በማወደሱ ተግባር ለመሳትፍ ሲፈልጉ ማየት በጣም ያስደስታል። ኢየሱስ ልጆች ላቀረቧቸው የውዳሴ መግለጫዎች ከፍተኛ ግምት ሰጥቷል። (ማቴዎስ 21:15, 16) አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦ “በልጅነቴ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ሐሳብ መስጠት እፈልግ ነበር። አባቴ አንድ ሐሳብ እንድዘጋጅ ከረዳኝ በኋላ ሐሳቡን ቢያንስ ሰባት ጊዜ እንድለማመድ ይፈልግብኝ ነበር።” እናንት ወላጆች በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ ወቅት ልጆቻችሁ መጠበቂያ ግንብ ውስጥ ካሉ አንቀጾች የሚሰጧቸውን ሐሳቦች መርጣችሁ በራሳቸው ቃላት እንዲዘጋጁ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። ልጆቻችሁ በይሖዋ የማስተማር መርሐ ግብር ለመሳተፍ ያላቸውን ታላቅ መብት እንዲያደንቁ እርዷቸው።

16. ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ምን ጥቅም ሲያስገኝ ቆይቷል? በዚህ ትምህርት ቤት መሳተፍ የሚችሉት እነማን ናቸው?

16 በሌሎች ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጡ ትምህርቶችም ጭምር ትምህርቶቹን ለማቅረብ መብት ባገኙትም ሆነ ትምህርቱ ሲቀርብ በሚያዳምጡት ዘንድ በቁም ነገር ሊታሰብባቸው ይገባል። ይሖዋ ሳምንታዊውን ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተጠቅሞ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶችን የመንግሥቱን መልእክት እንዲያቀርቡ ሲያሠለጥን ከ50 በላይ ዓመታት ሆኖታል። ከክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው እስከ ኖሩ ድረስ ዘወትር ከጉባኤው ጋር የሚሰበሰቡ ሰዎች በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሊሳተፉ ይችላሉ፤ ይህም በቅርቡ በስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመሩ ሰዎችን ይጨምራል።

17. (ሀ) ሕዝባዊ ስብሰባ የተዘጋጀው በተለይ ለምን ዓላማ ነው? (ለ) የሕዝብ ንግግር አቅራቢዎች በአእምሯቸው ሊይዟቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

17 ሕዝባዊ ስብሰባ ሌላው የማስተማር መርሐ ግብር ገጽታ ነው። ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ ስብሰባ በተለይ የተቋቋመው የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችን መሠረታዊ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ለማስተዋወቅ ሲባል ነው። ስለዚህ ንግግር የሚሰጠው ወንድም መልእክቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያዳምጡ ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ማቅረብ አለበት። ይህም እንደ “ሌሎች በጎች”፣ “ወንድሞች” እና “ቀሪዎች” የመሳሰሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎች የማይረዷቸውን ቃላት ማብራራትን ይጠይቃል። በአሁኑ ወቅት ባለው ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ቢሆኑም እንኳ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚቃረኑ እምነቶች ወይም አኗኗር ያላቸው ሰዎች በሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ሊገኙ ስለሚችሉ ተናጋሪው ምን ጊዜም ቢሆን ዘዴኛ መሆንና በእነዚህ እምነቶች ወይም አኗኗሮች ከማሾፍ መቆጠብ ይኖርበታል።—ከ1 ቆሮንቶስ 9:19–23 ጋር አወዳድር።

18. ሌሎቹ ሳምንታዊ ስብሰባዎች የትኞቹ ናቸው? ለምንስ ዓላማ ያገለግላሉ?

18 የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት በየሳምንቱ በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት የተዘጋጁ ጽሑፎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጠኑበት ስብሰባ ነው። በአሁኑ ወቅት በብዙ አገሮች እየተጠና ያለው መጽሐፍ ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለው መጽሐፍ ነው። የአገልግሎት ስብሰባ የተዘጋጀው የይሖዋ ሕዝቦች የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስታጠቅ ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ማርቆስ 13:10

በትልልቅ ስብሰባዎች መማር

19. ‘ባሪያው’ በየዓመቱ የትኞቹን ትልልቅ ስብሰባዎች ያዘጋጃል?

19 ይህ ‘ታማኝ ባሪያ’ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለማስተማርና ልዩ ማበረታቻ ለመስጠት ትልልቅ ስብሰባዎችን ከመቶ ዓመት በላይ ሲያዘጋጅ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ ትልልቅ ስብሰባዎች ሦስቱ በየዓመቱ ይደረጋሉ። የተለያዩ ጉባኤዎች በአንድ ወረዳ ውስጥ ተጠቃለው የሚያደርጉት የአንድ ቀን ስብሰባ አለ። በተጨማሪም በዓመቱ የተወሰነ ወቅት እያንዳንዱ ወረዳ የወረዳ ስብሰባ የሚባል የሁለት ቀን ስብሰባ ያደርጋል። ከዚህም በላይ በርካታ ወረዳዎች ተሰባስበው የሚያደርጉት የአውራጃ ስብሰባ የሚባል ስብሰባም አለ። አልፎ አልፎ ደግሞ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። እነዚህ ከሌሎች አገሮች ከመጡ እንግዶች ጋር የሚደረጉ ትልልቅ ስብሰባዎች የይሖዋ ሕዝቦችን እምነት እንደሚያጠነክሩ የተረጋገጠ ነው!—ከዘዳግም 16:16 ጋር አወዳድር።

20. በይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ የጎላው ምንድን ነው?

20 በሴዳር ፖይንት ኦሃዩ ዩ ኤስ ኤ በተደረገው ስብሰባ ላይ 10,000 የሚያህሉ ሰዎች በተገኙበት በ1922 ለስብሰባ የመጡ እንግዶች ተናጋሪው እንዲህ በማለት በሰጣቸው ማበረታቻ ተነቃቅተዋል፦ “ይህ የቀኖች ሁሉ ቀን ነው። እነሆ! ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው! እናንተ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።” እንደነዚህ ያሉት ትልልቅ ስብሰባዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት በስብከቱ ሥራ ላይ አተኩረዋል። ለምሳሌ ያህል በ1953 ኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ በሁሉም ጉባኤዎች ውስጥ ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው አገልግሎት ሥልጠና ሊደረግ እንደታቀደ ተገልጾ ነበር። ይህ መከናወኑ በብዙ አገሮች ውስጥ በሚካሄደው የመንግሥቱ ስብከት ላይ በጣም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።

ለማስተማር ከአምላክ መማር

21. ዓላማውን ሳንስት መቀበል የምንፈልገው መብት የትኛው ነው?

21 በእርግጥም ይሖዋ በአሁኑ ወቅት በምድር ላይ አስደናቂ የማስተማሪያ ዝግጅት አለው! ከዚህ ዝግጅት የሚጠቀሙ ሁሉ ከአምላክ መማር ይችላሉ፤ አዎን ‘የተማሩት ምላስ’ ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል ሊሆኑ ይችላሉ። በምሳሌያዊ አነጋገር በአምላክ ትምህርት ቤት ውስጥ መማር እንዴት ያለ መብት ነው! ሆኖም ይህን መብት ስንቀበል ትምህርት ቤቱ የተቋቋመበትን ዓላማ መሳት የለብንም። ይሖዋ ኢየሱስን ያስተማረው ሌሎችን ለማስተማር እንዲችል ነው፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማራቸው ተመሳሳይ ሥራ እንዲሠሩ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በበለጠ ደረጃ እንዲሠሩ ነው። በተመሳሳይም በአሁኑ ወቅት በይሖዋ ታላቅ የማስተማር መርሐ ግብር የምንሠለጥነው ሌሎችን ለማስተማር እንድንችል ነው።—ዮሐንስ 6:45፤ 14:12፤ 2 ቆሮንቶስ 5:20, 21፤ 6:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:2

22. (ሀ) ሙሴና ኤርምያስ ምን ችግር ነበረባቸው? ችግሩ የተፈታው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ የመንግሥቱን ስብከት ወደ ፍጻሜው እንደሚያመጣው ምን ማረጋገጫ ሊኖረን ይችላል?

22 እንደ ሙሴ “አጥርቶ የመናገር ችሎታ የለኝም” ወይም እንደ ኤርምያስ “እናገር ዘንድ አላውቅም” ትላለህን? ይሖዋ እነሱን እንደረዳቸው ሁሉ አንተንም ይረዳሃል። ሙሴን “ከአፍህ ጋር እሆናለሁ” ብሎታል። ኤርምያስን ደግሞ “ከአንተ ጋር ነኝና . . . አትፍራ” ብሎታል። (ዘጸአት 4:10–12 አዓት ፤ ኤርምያስ 1:6–8) የሃይማኖት መሪዎች ደቀ መዛሙርቱን ዝም ሊያሰኟቸው ሲፈልጉ ኢየሱስ “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ብሏል። (ሉቃስ 19:40) ይሁን እንጂ ይሖዋ የመንግሥቱን መልእክት እንዲያደርሱ ባስተማራቸው ሰዎች ምላስ እየተጠቀመ ስለሆነ ድንጋዮች መጮህ አያስፈልጋቸውም።

ልትመልስ ትችላለህን?

◻ በኢሳይያስ ምዕራፍ 50 ላይ የጎላው ምን አስደሳች የአስተማሪና የተማሪ ግንኙነት ነው?

◻ ይሖዋ ከፍተኛ የማስተማር መርሐ ግብር ማካሄዱን የቀጠለው እንዴት ነው?

◻ በይሖዋ የማስተማር መርሐ ግብር ውስጥ የተካተቱት አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

◻ በይሖዋ የማስተማር መርሐ ግብር ውስጥ መካፈል ታላቅ መብት የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች የሚሰጧቸው ከልብ የመነጩ ሐሳቦች ብዙውን ጊዜ አዋቂዎችን ያበረታታሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ