የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 12/15 ገጽ 14-19
  • የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን መማር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን መማር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል
  • በስብሰባዎቻችን ላይ የይሖዋን ፈቃድ መማር
  • አምላካዊ አክብሮት ካላቸው ወላጆች የይሖዋን ፈቃድ መማር
  • ማፍቀርንና ውጊያን መማር
  • ራሳችንን እንድንጠቅም የሚሰጠን ትምህርት
  • እስከ ዘመናችን ድረስ ከይሖዋ መማር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • አስተማሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • “ምሳሌ ትቼላችኋለሁ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1996
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 12/15 ገጽ 14-19

የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን መማር

“አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ።”—መዝሙር 143:10

1, 2. (ሀ) መማር የሚኖርብን መቼ ነው? ሊኖረን የሚገባውስ ሊጨበጥ የሚችል ግብ ምንድን ነው? (ለ) ከይሖዋ መማራችን የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አንድ ሰው ሕያው ሆኖና እየተንቀሳቀሰ በሚያሳልፈው በእያንዳንዱ ዕለት ጠቃሚ የሆነ ነገር መማር ይችላል። ይህ አባባል ለአንተም ሆነ ለሌላው ሰው ይሠራል። ይሁን እንጂ ሰውዬው ሲሞትስ? ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት ነገር መማር አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን አንዳች አያውቁም” ሲል በግልጽ ይናገራል። የሰው ልጅ የጋራ መቃብር በሆነው በሲኦል ውስጥ ምንም ዓይነት እውቀት የለም። (መክብብ 9:5, 10) ይህ ማለት ግን መማራችን ማለትም እውቀት ማካበታችን ሁሉ ከንቱ ነው ማለት ነውን? ይህ በምንማረው የትምህርት ዓይነትና በትምህርቱ አጠቃቀም ላይ የተመካ ነው።

2 የቀሰምነው ዓለማዊ ትምህርት ብቻ ከሆነ ምንም ዘላቂ ተስፋ አይኖረንም። የሚያስደስተው ግን ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይዘው መለኮታዊውን ፈቃድ በመማር ላይ ናቸው። የዚህ ተስፋ መሠረቱ የሕይወት ሰጭ እውቀት ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ መማር ነው።—መዝሙር 94:9-12

3. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክ የመጀመሪያ ተማሪ ነበር ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ሰዎች ከይሖዋ ሊማሩ እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለን? ውጤቱስ ምን ይሆናል?

3 የአምላክ የበኩር ልጅ የይሖዋ የመጀመሪያ ተማሪ በመሆን የአባቱን ፈቃድ ማድረግን ተምሯል። (ምሳሌ 8:22-30፤ ዮሐንስ 8:28) ኢየሱስም ራሱ እልፍ አእላፍ የሰው ልጆች ከአባቱ እንደሚማሩ ተናግሯል። ከአምላክ ለተማርነው ሰዎች ከፊታችን ምን ምን ተስፋዎች ይጠብቁናል? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። . . . እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።”—ዮሐንስ 6:45-47

4. መለኮታዊ ትምህርት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የለወጠው እንዴት ነው? ምን ተስፋስ አላቸው?

4 ኢየሱስ ይህን የተናገረው የአምላክ ምሳሌያዊ ሴት ስለ ሆነችው ስለ ሰማያዊቷ ጽዮን ከሚናገረው ከኢሳይያስ 54:13 በመጥቀስ ነበር። ይህ ትንቢት በተለይ የሚያመለክተው በመንፈስ የተቀቡትን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ማለትም 144,000 ልጆቿን ነው። የእነዚህ መንፈሳዊ ልጆች ቀሪዎች በዛሬው ጊዜ ምድር አቀፉን የትምህርት መርሐ ግብር በግንባር ቀደምትነት በመምራት ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ ‘እጅግ ብዙ ሰዎችም’ ከይሖዋ በመማር እየተጠቀሙ ነው። የመማር ሂደቱን ሞት ሳያስተጓጉልባቸው የመቀጠል ልዩ ተስፋ አግኝተዋል። እንዴት? ወደ እኛ በፍጥነት እየገሰገሰ ያለውን “ታላቅ መከራ” በሕይወት አልፈው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እየተጠባበቁ ስለሆነ ነው።—ራእይ 7:9, 10, 13-17

የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል

5. (ሀ) የ1997 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? (ለ) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስለመገኘት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

5 በዓለም ዙሪያ ከ80,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች “ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ” የሚሉትን የመዝሙር 143:10 የመክፈቻ ቃላት በ1997 በሙሉ ያስቡባቸዋል። የ1997 የዓመት ጥቅስ ይህ ይሆናል። እነዚህ ቃላት በየመንግሥት አዳራሾቹ በጉልሕ ተጽፈው ሲታዩ ቀጣይ ከሆነው የትምህርት መርሐ ግብር ተካፋይ የምንሆንባቸው የጉባኤ ስብሰባዎች መለኮታዊ ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችሉ ዋነኛ ቦታ መሆናቸውን የሚያስታውሰን ይሆናል። ከታላቁ አስተማሪያችን ለመማር ከወንድሞቻችን ጋር በስብሰባዎች ላይ በምንገናኝበት ጊዜ “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” ሲል እንደጻፈው መዝሙራዊ ሊሰማን ይችላል።—መዝሙር 122:1፤ ኢሳይያስ 30:20

6. ከየትኛው የዳዊት አባባል ጋር እንስማማለን?

6 አዎን፣ ከባላጋራችን ከዲያብሎስ ወይም ደግሞ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ፈቃድ ይልቅ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ መማር እንመርጣለን። በመሆኑም ልክ እንደ ዳዊት እኛም የምናመልከውንና የምናገለግለውን አምላክ “አምላኬ ነህና . . . ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ መንገድ ይምራኝ” እንለዋለን። (መዝሙር 143:10) ዳዊት ከሐሰተኞች ጋር ከመቀመጥ ይልቅ የይሖዋ አምልኮ በሚካሄድበት ቦታ መገኘትን መርጦ ነበር። (መዝሙር 26:4-6) ዳዊት እርምጃውን በሚመራለት የአምላክ መንፈስ በመታገዝ በጽድቅ መንገድ መጓዝ ችሎ ነበር።—መዝሙር 17:5፤ 23:3

7. የአምላክ መንፈስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በምን መንገድ አገልግሏል?

7 ታላቁ ዳዊት ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር እንደሚያስተምራቸውና እርሱ የነገራቸውንም ሁሉ እንደሚያስታውሳቸው ለሐዋርያቱ አረጋግጦላቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:26) ይሖዋ ከጰንጠቆስጤ ዕለት ወዲህ በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ‘የአምላክ ጥልቅ ነገር’ ደረጃ በደረጃ ሲገልጽ ቆይቷል። (1 ቆሮንቶስ 2:10-13) ይህንንም ያደረገው ኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሲል በጠራው ምድራዊ የመገናኛ መስመር አማካኝነት ነው። ይህ ባሪያ በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች በጉባኤዎች የትምህርት መርሐ ግብር አማካኝነት የሚያጠኑትን መንፈሳዊ ምግብ ያዘጋጃል።—ማቴዎስ 24:45-47

በስብሰባዎቻችን ላይ የይሖዋን ፈቃድ መማር

8. በመጠበቂያ ግንብ ጥናት መካፈላችን በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

8 በሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት የሚቀርበው ትምህርት ብዙ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ መሆን ስለሚችሉበት መንገድ የሚገልጽ ነው። ይህ ትምህርት የኑሮ ጭንቀቶችን ለማሸነፍ እንደሚረዳን ምንም አያጠራጥርም። በሌሎች ጥናቶች ላይ ደግሞ ጥልቀት ያላቸው መንፈሳዊ እውነቶች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ይጠናሉ። በእነዚህ ጥናቶች ወቅት በጣም ብዙ ነገሮችን እንማራለን! በብዙ አገሮች ውስጥ በእነዚህ ስብሰባዎች ወቅት የመንግሥት አዳራሾቹ ጢም ብለው ይሞላሉ። ይሁንና በአንዳንድ አገሮች የተሰብሳቢዎች ቁጥር ቀንሷል። ለምን ይመስላችኋል? ምናልባት አንዳንዶች ሰብዓዊ ሥራቸው ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለመነቃቃት’ ዘወትር እንዳይሰበሰቡ እንቅፋት እንዲሆንባቸው ፈቅደውለት ይሆን? ወይስ በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ወይም ቴሌቪዥን በመመልከት ብዙ ሰዓታት ስለሚያጠፉ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ፕሮግራማቸው እንደተጣበበ ሆኖ ተሰምቷቸው ይሆን? በዕብራውያን 10:23-25 ላይ በመንፈስ አነሣሽነት የተሰጠውን ትእዛዝ አስታውሱ። በተለይ ዛሬ ‘መጨረሻው ሲቀርብ እያየን’ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት መሰብሰባችን ይበልጥ አንገብጋቢ አይደለምን?

9. (ሀ) የአገልግሎት ስብሰባ ለመስክ አገልግሎት ሊያስታጥቀን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ስለ ምሥክርነቱ ሥራ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

9 ቀዳሚውን ስፍራ ከምንሰጣቸው ኃላፊነቶቻችን አንዱ የአምላክ አገልጋዮች ሆኖ መሥራት ነው። የአገልግሎት ስብሰባ የተዘጋጀው ይህንን ኃላፊነታችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንድንችል ለማስተማር ነው። ሰዎችን እንዴት መቅረብ እንደምንችል፣ ምን ብለን እንደምናነጋግራቸው፣ ጥሩ ምላሽ በሚያሳዩበት ጊዜ ምን እንደምናደርግና መልእክታችንን ለመቀበል አሻፈረኝ በሚሉበት ጊዜ አንኳ ሳይቀር ምን ማድረግ እንዳለብን እንማራለን። (ሉቃስ 10:1-11) በዚህ ሳምንታዊ ስብሰባ ላይ ውጤታማ ሆነው የተገኙ ዘዴዎች በውይይትና በሠርቶ ማሣያ መልክ ስለሚቀርቡ ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ብቻ ሳይሆን በመንገድ ላይ፣ በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች፣ በሕዝብ ማመላለሻዎች ውስጥ፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በገበያ ቦታዎች ወይም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰዎችን በተሻለ መንገድ ለማነጋገር ይበልጥ የታጠቅን እንሆናለን። “ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ” ከሚለው ልመናችን ጋር በመስማማት ጌታችን “በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ሲል የሰጠውን ምክር ለመፈጸም ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ ለመጠቀም መጣር ይኖርብናል።—ማቴዎስ 5:16

10. ‘የሚገባቸውን’ ሰዎች ከልብ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

10 እነዚህን በመሳሰሉት የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሌሎች ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ስለ ማድረግም እንማራለን። ግለሰቡ ፍላጎት ካሳየ ወይም ጽሑፍ ከተበረከተለት ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበት ጊዜ ግባችን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ነው። ይህም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ያዘዛቸውን ነገር ለማስተማር ሲሉ ‘በሚገባቸው ሰዎች ቤት ከመቀመጣቸው’ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ማቴዎስ 10:11፤ 28:19, 20) ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ የመሳሰሉ ግሩም አጋዥ መሣሪያዎች በማግኘታችን አገልግሎታችንን በጥራት ለማከናወን በሚገባ ታጥቀናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:5) በየሳምንቱ በአገልግሎት ስብሰባና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ስብሰባዎች ላይ ስትገኝ ፈቃዱን የምታደርግና በሚገባ የታጠቅህ የአምላክ አገልጋይ ለመሆን የሚያበቁህን ጠቃሚ ነጥቦች ለማስታወስና በሥራ ለመተርጎም ሞክር።—2 ቆሮንቶስ 3:3, 5፤ 4:1, 2

11. አንዳንዶች በማቴዎስ 6:33 ላይ በሚገኙት ቃላት ላይ እምነት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

11 ‘አስቀድመን መንግሥቱንና ጽድቁን መፈለጋችንን መቀጠላችን’ የአምላክ ፈቃድ ነው። (ማቴዎስ 6:33) ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘መሥሪያ ቤቴ በስብሰባ ላይ ለመገኘት እንቅፋት ቢሆንብኝ [ወይም ለባለቤቴ ቢሆንባት] ይህን መሠረታዊ ሥርዓት እንዴት ልሠራበት እችላለሁ?’ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ብዙዎች ከአሠሪዎቻቸው ጋር ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር ይወስናሉ። አንዲት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንድትችል በየሳምንቱ የተወሰነ ሰዓት እረፍት ማግኘት እንደምትፈልግ ለአሠሪዋ አሳወቀች። ጥያቄዋን ተቀበላት። ይሁን እንጂ በስብሰባዎቹ ላይ ምን እንደሚካሄድ ለማወቅ ጉጉት ስላደረበት በዚያ ለመገኘት ጥያቄ አቀረበ። እዚያም በፊታቸው ሊደረግ ስለነበረው የአውራጃ ስብሰባ ማስታወቂያ ሲነገር ይሰማል። በዚህ ምክንያት አሠሪዋ አንድ ቀን ሙሉ በአውራጃ ስብሰባው ላይ ለመገኘት ዝግጅት አደረገ። ከዚህ ምሳሌ ምን ትማራለህ?

አምላካዊ አክብሮት ካላቸው ወላጆች የይሖዋን ፈቃድ መማር

12. ልጆች የይሖዋን ፈቃድ እንዲማሩ ክርስቲያን ወላጆች ትዕግሥተኛና ጥብቅ በመሆን ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?

12 ይሁን እንጂ የይሖዋን ፈቃድ የምንማርባቸው ዝግጅቶች የጉባኤና የአውራጃ ስብሰባዎች ብቻ አይደሉም። አምላካዊ አክብሮት ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያሰለጥኑ፣ ተግሣጽ እንዲሰጧቸው እንዲሁም ይሖዋን የሚያወድሱና ፈቃዱን የሚፈጽሙ ልጆች አድርገው ለማሳደግ እንዲጥሩ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። (መዝሙር 148:12, 13፤ ምሳሌ 22:6, 15) ይህ ‘ሕፃናት ልጆቻችንን ሊሰሙና ሊማሩ’ ወደሚችሉባቸው የጉባኤ ስብሰባዎች መውሰድን የሚጠይቅ ነው፤ ይሁን እንጂ በቤት ውስጥ ከቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ማስተማርስ ምን ማለት ይቻላል? (ዘዳግም 31:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15) ብዙ ቤተሰቦች ቋሚ የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያደርጉበት ፕሮግራም ያወጣሉ፤ ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ተረሳስቶና ችላ ተብሎ ይቀራል። እንደዚህ ያለ ነገር ገጥሟችሁ ያውቃልን? ቋሚ የጥናት ፕሮግራም ይኑራችሁ የሚለው ምክር ትክክል እንዳልሆነ ወይም ደግሞ የቤተሰባችሁ ሁኔታ የተለየ ስለሆነ ለእናንተ ሊሠራ እንደማይችል ሆኖ ይሰማችኋልን? ሁኔታችሁ ምንም ይሁን ምን እባካችሁ እናንተ ወላጆች በነሐሴ 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን “ውድ የሆነው መንፈሳዊ ቅርሳችን” እና “መንፈሰ ጠንካራነት የሚያስገኘው ዋጋ” የሚሉትን ርዕሶች ከልሱ።

13. ቤተሰቦች የዕለቱን ጥቅስ በመመርመር ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው?

13 ቤተሰቦች ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት አማካኝነት በዕለቱ ጥቅስ ላይ የመወያየት ልማድ እንዲያዳብሩ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል። ጥቅሱንና የተሰጠውን ሐሳብ ማንበቡ ራሱ ጥሩ ቢሆንም በጥቅሱ ላይ መወያየትና ሐሳቡን ተግባራዊ ማድረጉ ደግሞ ይበልጥ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል በኤፌሶን 5:15-17 ላይ የሚወያዩ ከሆነ የቤተሰቡ አባላት ለግል ጥናት፣ በአንድ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለመሳተፍና ለሌሎች ቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ‘ጊዜ መዋጀት’ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ሐሳብ ሊሰጡ ይችላሉ። አዎን፣ ቤተሰቡ በዕለቱ ጥቅስ ላይ መወያየቱ ከመካከላቸው አንዱ ወይም ከዚያ የሚበዙት ‘የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ በተሟላ ሁኔታ እንዲያስተውሉ’ ሊረዳቸው ይችላል።

14. ዘዳግም 6:6, 7 እንደሚጠቁመው ወላጆች ምን ዓይነት አስተማሪዎች መሆን ይገባቸዋል? ይህስ ምን ማድረግን ይጠይቃል?

14 ወላጆች የልጆቻቸው ትጉ አስተማሪዎች መሆን ይኖርባቸዋል። (ዘዳግም 6:6, 7) ይሁን እንጂ ይህ ለልጆቻቸው ተግሣጽ ወይም ትእዛዝ መስጠት ማለት ብቻ አይደለም። አባትና እናት ማዳመጥም ይኖርባቸዋል፤ እንዲህ ከሆነ ለልጆቻቸው ስለ ምን ነገር ግልጽ አድርገው ሊነግሯቸው፣ ሊያብራሩላቸው፣ በምሳሌ ሊያስረዷቸው ወይም የትኛውን ነገር ሊደግሙላቸው እንደሚገባ ሊያውቁ ይችላሉ። በአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ወላጆቹ ልጆቻቸው ያልገቧቸውን ወይም የሚያሳስቧቸውን ነገሮች እንዲጠይቁ በማበረታታት ነፃ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት እንዲሰፍን አድርገው ነበር። በዚህ ምክንያት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው አንዱ ልጃቸው ይሖዋ መጀመሪያ የለውም የሚለውን ሐሳብ ለመረዳት እንደከበደው ገባቸው። ወላጆቹ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ የወጡትን ማብራሪያዎች በመጠቀም ጊዜና ሕዋ ምንም መጨረሻ የላቸውም የሚለው ሐሳብ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ነገር መሆኑን ገለጹለት። የሰጡት ምሳሌ ነጥቡ ግልጽ እንዲሆንለት ስለረዳው ልጃቸው ባገኘው መልስ ረካ። እንግዲያውስ የልጆቻችሁን ጥያቄዎች ከቅዱሳን ጽሑፎች ግልጽ በሆነ መንገድ በመመለስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግን መማር በጣም አርኪ ሊሆንላቸው እንደሚችል እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጊዜ መድቡ። ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ዛሬ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ሌላስ ምን ነገር እየተማሩ ነው?

ማፍቀርንና ውጊያን መማር

15. የወንድማዊ ፍቅራችን እውነተኛነት የሚፈተነው መቼ ሊሆን ይችላል?

15 ኢየሱስ ከሰጠው አዲስ ትእዛዝ ጋር በሚስማማ መንገድ ‘እርስ በርስ መዋደድን ከአምላክ ተምረናል።’ (1 ተሰሎንቄ 4:9) ምንም ችግር በማይኖርበት ጊዜ ሁሉንም ወንድሞች እንደምንወዳቸው ሆኖ ይሰማን ይሆናል። ይሁንና የግል አለመጣጣም ቢፈጠር ወይም አንድ ክርስቲያን የተናገረው አለዚያም የሠራው ነገር ቢጎዳን ምን እናደርጋለን? በዚህ ጊዜ የፍቅራችን እውነተኝነት ይፈተን ይሆናል። (ከ2 ቆሮንቶስ 8:8 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ምን እንድናደርግ ያስተምረናል? ማድረግ ያለብን አንዱ ነገር ልባዊ ፍቅር ማሳየት ነው። (1 ጴጥሮስ 4:8) በጥቃቅን ስህተቶች በመበሳጨት የራሳችንን ጥቅም ከመፈለግ ወይም በደልን ከመቁጠር ይልቅ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት እንዲሸፍን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 13:5) ቃሉም የሚያስተምረን ይኸንኑ ስለሆነ እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ እናውቃለን።

16. (ሀ) ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ውጊያ ተምረዋል? (ለ) ለዚህስ አስፈላጊውን ትጥቅ ያገኘነው እንዴት ነው?

16 ብዙዎች ፍቅርንና ውጊያን ምን አዛመዳቸው ብለው ሊያስቡ ቢችሉም ሌላው የምንማረው ነገር ውጊያ ነው፤ ይሁን እንጂ ይህ ውጊያ ዓይነቱ ለየት ያለ ነው። በዳዊት ዘመን የነበረው ውጊያ ቃል በቃል ከእስራኤል ጠላቶች ጋር መፋለምን የሚጨምር ቢሆንም ውጊያውን እንዴት እንደሚያካሂድ እንዲያስተምረው በይሖዋ ላይ መመካት እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። (1 ሳሙኤል 17:45-51፤ 19:8፤ 1 ነገሥት 5:3፤ መዝሙር 144:1) ዛሬ ስላለብን ውጊያስ ምን ማለት ይቻላል? የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉም። (2 ቆሮንቶስ 10:4) ውጊያችን መንፈሳዊ ትጥቅ የሚጠይቅ መንፈሳዊ ውጊያ ነው። (ኤፌሶን 6:10-13) ይሖዋ በቃሉና በጉባኤ በተደራጁት ሕዝቦቹ አማካኝነት የተሳካ መንፈሳዊ ውጊያ ማድረግ እንድንችል ያስተምረናል።

17. (ሀ) ዲያብሎስ እኛን ከያዝነው ጎዳና ፈቀቅ ለማድረግ ምን ዘዴ ይጠቀማል? (ለ) ከምን ነገርስ መራቃችን ጥበብ ነው?

17 ዲያብሎስ አታላይና ረቂቅ በሆነ መንገድ ተጠቅሞ እኛን አስፈላጊ ወዳልሆኑ ነገሮች ዞር ለማድረግ ሲል በዓለም ውስጥ ባሉ ማባበያዎች፣ በከሃዲዎች እንዲሁም እውነትን በሚቃወሙ ሌሎች ሰዎች ይጠቀማል። (1 ጢሞቴዎስ 6:3-5, 11፤ ቲቶ 3:9-11) ፊት ለፊት ጥቃት ቢከፍት የሚያሸንፍበት አጋጣሚ በጣም ጠባብ መሆኑን ስለሚያይ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ጠቀሜታ የሌላቸውን ጉዳዮች ወይም አስተዋይነት የጎደላቸው ጥያቄዎች እንድናነሣ በማድረግ ሊያጠምደን ይሞክራል። ጀግና ተዋጊዎች እንደመሆናችን መጠን ፊት ለፊት የሚመጣውን ጥቃት እንደምንመክት ሁሉ ይህንንም ለመመከት ንቁዎች መሆን ይገባናል።—1 ጢሞቴዎስ 1:3, 4

18. ከእንግዲህ ለራሳችን አንኖርም ማለት ምን ነገሮችን ይጨምራል?

18 እኛ የምንኖረው የሰውን ምኞት ወይም የአሕዛብን ፈቃድ ለመፈጸም አይደለም። ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ አማካኝነት ከእንግዲህ ለራሳችን እንዳንኖር አስተምሮናል፤ ከዚህ ይልቅ የክርስቶስ ኢየሱስ ዓይነት አስተሳሰብ በመያዝ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ መኖር ይገባናል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ቀድሞ ውድ የሆነውን ጊዜያችንን ቅጥ ባጣና በአስረሽ ምችው አኗኗር ስናባክን ቆይተን ሊሆን ይችላል። ይህ ዓለም በፈንጠዝያ፣ ያለልክ በመጠጣትና በሥነ ምግባር ብልግና የታወቀ ነው። ዛሬ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ የምንማር ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ከዚህ ብልሹ ዓለም በመለየታችን ደስ አይለንምን? እንግዲያውስ በሚበክሉ ዓለማዊ ድርጊቶች ውስጥ እንዳንገባ ብርቱ መንፈሳዊ ተጋድሎ እናድርግ።—1 ጴጥሮስ 4:1-3

ራሳችንን እንድንጠቅም የሚሰጠን ትምህርት

19. የይሖዋን ፈቃድ መማርና ማድረግ ምን ጥቅሞችን ያስገኛል?

19 የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን መማር በእጅጉ እንደሚጠቅመን መገንዘብ ያስፈልገናል። ትምህርቱን በትኩረት በመከታተልና በልጁ፣ በቃሉ እና በተደራጁት ሕዝቦቹ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ በመከተል ረገድ የበኩላችንን ማድረግ እንዳለብን ግልጽ ነው። (ኢሳይያስ 48:17, 18፤ ዕብራውያን 2:1) እንዲህ ካደረግን ዛሬ ያለውን በመከራ የተሞላ ጊዜና ወደፊት ከፊታችን የሚመጡትን አስቸጋሪ ወቅቶች በጽናት መቋቋም እንችላለን። (ማቴዎስ 7:24-27) ዛሬም ቢሆን የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እርሱን ከማስደሰታችን በላይ ጸሎታችን መልስ እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 9:31፤ 1 ዮሐንስ 3:22) እውነተኛ ደስታም እናገኛለን።—ዮሐንስ 13:17

20. በ1997 በሙሉ የዓመቱን ጥቅስ ባየን ቁጥር ስለ ምን ነገር ማሰላሰላችን ጥሩ ይሆናል?

20 በ1997 በመዝሙር 143:10 ላይ የሚገኘውን “ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ” የሚለውን የዓመት ጥቅስ የምናነብበትና በጥቅሱ ላይ የምንወያይበት ብዙ አጋጣሚ ይኖረናል። ከእነዚህ አጋጣሚዎች መካከል አንዳንዶቹን ቀደም ሲል እንደተገለጸው አምላክ እኛን ለማስተማር ስላደረጋቸው ዝግጅቶች ለማሰላሰል እንጠቀምባቸው። ‘የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም እንደሚኖር’ ስለምናውቅ በእነዚህ ቃላት ላይ በዚህ መንገድ ማሰላሰላችን ከዚሁ ልመናችን ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለሳችንን ለመቀጠል የሚያስችለን እንዲሆን እንጣር።—1 ዮሐንስ 2:17

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ዛሬ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን እየተማሩ ያሉት እነማን ናቸው?

◻ በ1997 መዝሙር 143:10 እንዴት ሊነካን ይገባል?

◻ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን እየተማርን ያለነው እንዴት ነው?

◻ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን በማስተማር በኩል ምን እንዲያደርጉ ይፈለግባቸዋል?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ