አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
1 በአንዳንድ አካባቢዎች ከጥር ወር ጀምሮ የሚደረገው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም “ከይሖዋ የተማራችሁ ሁኑ” የሚል ጭብጥ ይኖረዋል። (ዮሐ. 6:45) ይሖዋ የሚሰጠው መለኮታዊ ትምህርት እርካታ የሞላበት ኑሮ እንድንኖር ረድቶናል። ላገኘነው መንፈሳዊ ቅርስ በውስጣችን ከፍ ያለ አድናቆት ያሳድርብናል። ሌሎች ምሥራቹን እንዲሰሙ ለመርዳት መጣራችን የማኅበረሰቡ ጠቃሚ አባላት ያደርገናል። ይህ ልዩ የስብሰባ ቀን ከይሖዋ የተማሩ ሰዎች ያገኙትን በረከት ጎላ አድርጎ ይገልጻል።
2 ፕሮግራሙ መለኮታዊ ትምህርት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ዓለማዊ ትምህርቶች ካላቸው አደጋ ጋር ያነፃፅራል። ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ከሁሉ የበለጠውን ትምህርት የሚያቀርበው እንዴት እንደሆነ ግልጽ በሆነ መንገድ እንማራለን። ከአምላክ የተማርን በመሆናችን ምክንያት ደስታ ያስገኙልንን ሦስት የአምልኮ መስኮች አጽንኦት ይደረግባቸዋል። በተጨማሪም ወጣቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ዳዊትንና ጢሞቴዎስን የመሰሉ ተወዳዳሪ የማይገኝላቸውን ሰዎች ምሳሌ እንዲከተሉና አኗኗራቸውን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ እንዲገነቡ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል። በዕድሜ የገፉት ያሳዩት ታማኝነት ጎላ ተደርጎ ሲገለጽ እምነታችን የበለጠ ይጠናከራል። ብቃቱን አሟልተው ራሳቸውን የወሰኑ አዳዲስ ሰዎችም መጠመቅ ይችላሉ። ከስብሰባው ቀን በፊት ጥሩ ዝግጅት አድርገው ለመጠመቅ ያላቸውን ፍላጎት ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ መንገር ይኖርባቸዋል።
3 በልዩ ስብሰባው ቀን የሚቀርበው ዋነኛው ንግግር “ይሖዋ ፈቃዱን እንዲያደርጉ ያስተማራቸው ሰዎች” የሚል ርዕስ አለው። ንግግሩ ሁላችንም መማራችንን መቀጠል፣ በእምነት ጽኑ መሆንና እድገት ማድረጋችንን መቀጠል የሚገባን ለምን እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውነት ለሌሎች በማስተማር ይሖዋን እንድንመስል ማበረታቻ ይሰጠናል። ብዙ ሰዎች ከይሖዋ የተማሩ እንዲሆኑ የማኅበሩ ጽሑፎች እንዴት እንደረዷቸው የሚያሳዩ ገንቢ የሆኑ ተሞክሮዎችም ይቀርባሉ። በዓለም ዙሪያ የሚሰጠው የይሖዋ የትምህርት ፕሮግራም ያስገኘው ጠቃሚ የሥራ ውጤት ጎላ ተደርጎ ይብራራል።
4 በስብሰባው ላይ ለመገኘት ቁርጥ ያለ እቅድ አውጣ። ፍላጎት ያላቸው አዲሶች ሁሉ እንዲገኙ አበረታታ። በታላቁ አስተማሪያችን አማካኝነት ብዙ ጥሩ ነገሮች ለመማር ስብሰባውን በጉጉት ተጠባበቅ።— ኢሳ. 30:20