አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
ከጥር 2001 ጀምሮ የሚካሄደው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም ርዕስ “በማስተዋል ችሎታችሁ የጎለመሳችሁ ሁኑ” የሚል ይሆናል። (1 ቆሮ. 14:20 NW ) በስብሰባው ላይ መገኘታችን ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? የምንኖረው በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው። ይህንን ለመቋቋምና ክፉውን በመልካም ለማሸነፍ መንፈሳዊ የማስተዋል ችሎታችንን ማጎልበት ይገባናል። የልዩ ስብሰባው ቀን ፕሮግራም ይህን እንድናደርግ ይረዳናል።
በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ “መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል ረገድ የጎለመሱ ለመሆን የሚረዱ ዝግጅቶች” በሚል ርዕስ ንግግር ያቀርብልናል። በክርስቲያናዊ እምነታችን ጸንተን መቆም የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁመናል። ጎብኚ ተናጋሪው “የማስተዋል ችሎታችሁን በማሰልጠን መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ” በሚል ርዕስ በሚያቀርበው ንግግር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መጠቀም ወይም ተግባራዊ ማድረግ ንቁ የማመዛዘን ችሎታ ለማዳበር ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ያጎላል።
ወጣቶችም የማመዛዘን ችሎታቸውን ማዳበር ይገባቸዋል። “ለክፋት ሕፃናት መሆን ያለብን ለምንድን ነው?” እና “ከልጅነታቸው ጀምረው ማስተዋልን ያገኙ ወጣቶች” በሚሉት ክፍሎች ይህ ጉዳይ ይብራራል። ወጣቶች በዓለም ውስጥ የሚፈጸሙትን የክፋት ድርጊቶች በተመለከተ የሚመጣባቸውን ማንኛውንም የማወቅ ጉጉት መቆጣጠርና ከችግር መራቅ ይችሉ ዘንድ ራሳቸውን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ምን እንደሚያደርጉ ሲናገሩ አዳምጡ።
ከሕይወት የላቀ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ጎብኚ ተናጋሪው “የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በማስተዋል ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች” በሚል ርዕስ በሚያቀርበው የመደምደሚያ ንግግር ይህንን ያብራራል። የአምላክን ቃል በሥራ ላይ ማዋል ችግሮችን ለማሸነፍ፣ ውሳኔ ለማድረግና ይሖዋ ከሚያስተምረን ነገሮች ጥቅም ለማግኘት እንዴት እንደሚረዳ የሚያሳዩ ተግባራዊ ምሳሌዎችን ይጠቅሳል።
ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት ማሳየት የሚፈልጉ ሁሉ ስማቸውን ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ሳይዘገዩ መስጠት ይኖርባቸዋል። ልዩ ስብሰባው የሚደረግበት ቀን በማስታወቂያ እንደተነገረ በማስታወሻህ ላይ መዝግበህ በመያዝ እውቀት ሰጪ ከሆነው ከዚህ ፕሮግራም ጥቅም ለማግኘት ቁርጥ ያለ እቅድ አውጣ። የልዩ ስብሰባው የትኛውም ክፍል አያምልጥህ! ይህን ክፉ ሥርዓት በጽናት እንድትቋቋምና ለይሖዋ ታማኝ ሆነህ እንድትቀጥል ያጠነክርሃል።