የማስተዋል ችሎታችሁን አዳብሩ
1 ይህ የምንኖርበት አስጨናቂ የሆነ የመጨረሻው ዘመን በየትም ስፍራ በሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የሚሄዱ ተጽዕኖዎችን እንዲሁም የተለያዩ ከባድ ፈተናዎችን በማስከተል ላይ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5) ሁላችንም በእምነት ጸንተን እንድንኖር ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልገናል። (1 ቆሮ. 16:13) አምላክ በሚሰጠን እርዳታ ማለትም ቃሉን አዘውትረን በመመገብ፣ በመንፈሱ በመታመንና ድርጅቱን የሙጥኝ ብለን በመኖር ጸንተን መቆም እንችላለን።—መዝ. 37:28፤ ሮሜ 8:38, 39፤ ራእይ 2:10
2 ባለፈው ዓመት በተደረገው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም ላይ “በማስተዋል ችሎታችሁ የጎለመሳችሁ ሁኑ” የሚል ጭብጥ መቅረቡ በእርግጥም የተገባ ነበር። ይህ ጭብጥ “ወንድሞች ሆይ፣ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በማስተዋል ችሎታችሁ ሕፃናት አትሁኑ፤ በማስተዋል ችሎታችሁ ግን የጎለመሳችሁ ሁኑ” በሚለው በ1 ቆሮንቶስ 14:20 [NW ] ላይ በሚገኙት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ላይ የተመሠረተ ነበር። ስብሰባውን እንዴት አገኘኸው?
3 “እንዴት የሚያበረታታ ነው!” “የሚያስፈልገን እንዲህ ዓይነት ትምህርት ነበር!” እነዚህ ስለ ስብሰባው ከተሰጡት አስተያየቶች ውስጥ ሁለቱ ብቻ ናቸው። የ12 ዓመት ልጁ ስትጠመቅ ለማየት በልዩ ስብሰባው ላይ የተገኘ አንድ የይሖዋ ምስክር ያልሆነ ሰው እንኳን በፕሮግራሙ እንደተደነቀና ለቤተሰቡ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ መገንዘብ እንደቻለ ተናግሯል። አንተም እንደዚህ ይሰማሃል? እስቲ በፕሮግራሙ ላይ ከቀረቡት ዋና ዋና ነጥቦች ውስጥ አንዳንዶቹን እንከልስ።
4 የማስተዋል ችሎታን ለማዳበር ትክክለኛ እውቀት አስፈላጊ ነው:- “ዛሬውኑ የማስተዋል ችሎታችሁን አዳብሩ” በሚለው የመክፈቻ ንግግር ላይ ተናጋሪው በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመቋቋም ምን ነገር አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል? የአእምሮ ችሎታ ብቻውን በቂ አይደለም። በዙሪያችን ባለው ክፋት እንዳንሸነፍ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተዋል ችሎታችን እንዲዳብርና ጥልቀት እንዲኖረው ማድረግ አለብን። ይህ ደግሞ መለኮታዊ መመሪያ ማግኘትን ይጠይቃል። ሕግጋቱንና ማሳሰቢያዎቹን በማስተዋል በሙሉ ልብ ማገልገል እንድንችል እንደ መዝሙራዊው ይሖዋን በጸሎት መጠየቅ አለብን።—መዝ. 119:1, 2, 34
5 የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ቀጥሎ ባቀረበው ንግግር ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ በኩል “መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል ረገድ የጎለመሱ ለመሆን የሚረዱ ዝግጅቶች” እንደሚያቀርብልን ገልጿል። ማስተዋል “አንድን ነገር በጥልቀት የመመልከትና የተለያዩ ክፍሎቹ እርስ በርስ ያላቸውን ዝምድና አውቆ አጠቃላዩን ይዘት በመረዳት ምንነቱን የመገንዘብ ችሎታ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህን ችሎታ እንድናዳብር ማን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ የሚረዱንን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ሰጥቶናል። (ኤፌ. 4:11, 12) ምድራዊ ድርጅቱ የአምላክን ቃል በየዕለቱ እንድናነብና በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን እንድንገኝ አጥብቆ ያሳስበናል። (መዝ. 1:2) መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን በግልና በቤተሰብ ጥናት እንዲሁም ለጉባኤ ስብሰባዎችና ለመስክ አገልግሎት በምናደርገው ዝግጅት እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ተምረናል። በእነዚህ ዝግጅቶች በሙሉ እየተጠቀምክ ነው? ቋሚ የሆነ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም አለህ? በዓለማዊ ዝንባሌዎች፣ ፋሽኖች፣ ፍልስፍናዎችና የሚያባብሉ ተጽዕኖዎች ከመሸነፍ ልንጠበቅ የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።—ቆላ. 2:6-8
6 የማስተዋል ችሎታችንን ማሰልጠን አለብን:- ጎብኚ ተናጋሪው “የማስተዋል ችሎታችሁን በማሰልጠን መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ” የሚል ርዕስ ባለው የመጀመሪያ ንግግሩ በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች መልካሙንና ክፉውን መለየት እንደማይችሉ ገልጾ ነበር። (ኢሳ. 5:20, 21) ይህ የሆነበት ምክንያት አምላክ ያወጣቸውን የጽድቅ የአቋም መሥፈርቶች ለመቀበልና ለመከተል እምቢተኞች በመሆናቸው ነው። በተቃራኒው ደግሞ ከይሖዋ ድርጅት መንፈሳዊ ማሠልጠኛ ያገኘን ሰዎች እንደመሆናችን ድርጊታችንንና አኗኗራችንን ለመምራት የሚያገለግሉንን የአምላክ የአቋም ደረጃዎች አስፈላጊነት አምነን እንቀበላለን። በመሆኑም በእርሱ ፊት በጎና ደስ የሚያሰኘውን እንዲሁም ፍጹም ከሆነው ፈቃዱ ጋር የሚስማማው ነገር ምን እንደሆነ ፈትነን ማወቅ እንችላለን።—ሮሜ 12:2
7 ግራ ከሚያጋባው የዓለም አስተሳሰብና ይህም ከሚያስከትለው መጥፎ ውጤት ራሳችንን ለመከላከል ያለማቋረጥ የማስተዋል ችሎታችንን ማሰልጠን አለብን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በዕብራውያን 5:12-14 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የቃሉን ወተት’ በመመገብ ብቻ መርካት በቂ አለመሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል። የዳንኤልን ትንቢት በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ስናጠና እንዳገኘነው ያለ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገናል። ከዚያም የተማርነውን በሕይወታችን ውስጥ ወዲያውኑ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። እንዲህ ስናደርግ የይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶችና የአቋም ደረጃዎች ትክክል ስለመሆናቸው እምነት ያድርብናል። ይህም ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች መለየት እንድንችል የማስተዋል ችሎታችንን ያሰለጥነዋል።
8 የሚያሳዝነው አንዳንዶች በመንፈሳዊ ተሰናክለዋል። ለምን? ትኩረታቸውን በይሖዋ ዓይን መልካምና ቅን በሆነው ነገር ላይ እንዲያተኩር ባለማድረጋቸው ነው። በዚህም ምክንያት በመንፈሳዊ አጠያያቂ የሆነ ሐሳብ ለሚተላለፍባቸው የቴሌቪዥንና የራዲዮ ፕሮግራሞች፣ ለወራዳ ሙዚቃ ወይም በመረጃ መረብ የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግባቸው የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ለሚያሳድሩት መጥፎ ተጽእኖ ተጋልጠዋል። በጥበብ በመመላለስ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሰነፍ ወይም ክፉ ሰዎች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብን እንከላከላለን።—ምሳሌ 13:20፤ ገላ. 5:7፤ 1 ጢሞ. 6:20, 21
9 ወጣቶች “ለክፋት ነገር ሕፃናት መሆን” አለባቸው:- የስብሰባው ፕሮግራም ወጣቶች የማስተዋል ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያበረታቱ ሁለት ክፍሎች ነበሩት። ተናጋሪዎቹ “ለክፋት ነገር ሕፃናት” መሆን በይሖዋ ፊት ርኩስ ለሆኑ ነገሮች አላዋቂ ማለትም እንደ ሕፃናት ምንም የማያውቁ መሆን ማለት እንደሆነ አብራርተዋል። (1 ቆሮ. 14:20) ሁላችንም ለማንኛውም ዓይነት ክፋት እንዳንጋለጥ ለመከላከልና በዚህ እንዳንበከል ራሳችንን ለመጠበቅ በጊዜ አጠቃቀም ረገድ ጠንቃቆች እንድንሆን ተበረታተናል። (ኤፌ. 5:15-17) መንፈሳዊ ነገሮችን በማስተዋል ረገድ ለምናደርገው እድገት አንዳችም ፋይዳ የሌለውን ጽሑፍ በማንበብ ምን ያህል ጊዜ እንደምናጠፋ እንድናሰላ ማበረታቻ ተሰጥቶን ነበር። ይህን አድርገህ ነበር? በውጤቱ ምን ተገነዘብክ? ከዕለታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ በተጨማሪ የይሖዋ ድርጅት የሚያቀርብልንን ጽሑፎች ተከታትለህ ለማንበብ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ይህን ማድረግ ወጣቶችን ጨምሮ ሁላችንም ‘ማስተዋልን እንድናተርፍ’ ይረዳናል።—ምሳሌ 4:7-9
10 “የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች አስተውላችሁ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቀሙ”:- ይህ የልዩ ስብሰባው ቀን ፕሮግራም የመደምደሚያ ንግግሩ ርዕስ ነበር። ጐብኚ ተናጋሪው ይሖዋ ሰብአዊ ፍጡራን ሁሉ ካላቸው በጣም የሚልቅ ሕይወት ሰጪ ማስተዋል እንዳለው አብራራ። ከዚህ የይሖዋ ማስተዋል መቅዳት መቻል ምን ያህል ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነ እስቲ አስብ! ይሖዋ ይህን ማስተዋል ለማግኘት ከልብ ለሚፈልጉና እንዲሰጣቸው በእምነት ለሚጠይቁት ሁሉ በለጋስነት ይሰጣል። (ምሳሌ 2:3-5, 9፤ 28:5) ከዚህ ግብዣ ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምህ ነውን?
11 መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለይተን ለማወቅ እንድንጥር ተበረታተን ነበር። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ይሖዋ ምን እያለ እንዳለ ለማስተዋል እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥንቃቄ አጥኗቸው። በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ጊዜ ወስዳችሁ በማሰላሰል በአእምሮአችሁና በልባችሁ ውስጥ እንዲቀረጹ አድርጉ። ይህም በሕይወታችሁ ውስጥ ውሳኔ በምታደርጉበት ጊዜ ስኬታማ መሆን ትችሉ ዘንድ የማስተዋል ችሎታችሁን ያሰለጥነዋል። (ኢያሱ 1:8) እስቲ ብዙዎችን ከሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች መካከል ጥቂቶቹን እንውሰድና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ እንዴት ሊረዳን እንደሚችል እንመልከት።
12 ‘በአለባበስ እና በአበጣጠር ፋሽን መከተል አለብኝን?’ ዓለም የሚከተለው ዘመን አመጣሽ የሆነ አለባበስና የጠጉር አበጣጠር የሥርዓት አልበኝነትን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ ዓይነቱ መንፈስ ሰዎች የተዝረከረከና ቅጥ ያጣ ወይም እርቃንን የሚያሳይ ልብስ እንዲለብሱ ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል። እንዲህ ካለው ዝንባሌ ራሳችንን እንድንጠብቅ የሚረዱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው? የማስተዋል ችሎታችን የሰለጠነ ከሆነ በ1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 ላይ የሚገኘውን “ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር . . . እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት [ሰዎች] እንደሚገባ” እንድንለብስ የሚናገረውን መሠረታዊ ሥርዓት ግምት ውስጥ እናስገባለን። በ2 ቆሮንቶስ 6:3 ላይ እና በቆላስይስ 3:18, 20 የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶችም ሊረዱን ይችላሉ።
13 ‘በቤተሰቤ መካከል ያለው አንድነት የጠበቀ እንዲሆን ምን ማድረግ እችላለሁ?’ በቤተሰብ አባላት መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት መኖሩ አስፈላጊ ነው። ያዕቆብ 1:19 “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቊጣም የዘገየ ይሁን” በማለት ይነግረናል። በቤተሰብ ውስጥ ያለው የሐሳብ ግንኙነት የሁለት ወገን ተሳትፎ የሚጠይቅ ስለሆነ የቤተሰብ አባላት መደማመጥና ሐሳብ መለዋወጥ ያስፈልጋቸዋል። የምንናገረው ነገር ትክክል ቢሆንም እንኳ ሸካራ ቃል በመጠቀም፣ በኩራት ወይም ለሌላው ስሜት ደንታ እንደሌለን በሚያሳይ መንገድ የሚነገር ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ስለዚህ ባልም ሆንን ሚስት፣ ወላጅም ሆንን ልጅ ንግግራችን “ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ” እንዲሆን ማድረግ አለብን።—ቆላ. 4:6
14 ‘ፍቅረ ነዋይ ተጽዕኖ እያሳደረብኝ ነው?’ ፍቅረ ነዋይ የአንድን ሰው ሕይወት የሚያወሳስብ ዓለማዊ ተጽዕኖ እንጂ ወደ ደስታ የሚያስገባ ቁልፍ አይደለም። (መክ. 5:10፤ ሉቃስ 12:15፤ 1 ጢሞ. 6:9, 10) ከፍቅረ ነዋይ ወጥመድ እንድንርቅ ለመርዳት ኢየሱስ ‘ዓይናችሁ ቀና ይሁን’ የሚለውን ወሳኝ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓት አስተምሮናል። ሚዛናዊ የሆነና ያልተወሳሰበ ሕይወት መኖር ዓይናችንን የመንግሥቱን ጥቅሞች በማስቀደም ላይ እንዲያተኩር ማድረግንና የቀረውን ነገር ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ መመልከትን ይጨምራል።—ማቴ. 6:22, 23, 33
15 ግባችን ምን መሆን አለበት:- ውሳኔዎችን ለማድረግ መመሪያ የሚሆኑንን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች የያዘ አስተማማኝ ምንጭ በአምላክ ቃል ውስጥ እናገኛለን። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች መማር፣ በእነሱ ላይ ማሰላሰልና በሕይወታችን ውስጥ እንዴት እንደምንጠቀምባቸው መገንዘብ ያስፈልገናል። በዚህ መንገድ የማስተዋል ችሎታችን “መልካሙንና ክፉውን ለመለየት” እንዲችል በማሰልጠን ራሳችንን እንጠቅማለን፣ ይሖዋንም እናስከብራለን።—ዕብ. 5:14