አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
“ለአምላክ ተገዙ—ዲያብሎስን ተቃወሙ” የሚለው የአዲሱ የአገልግሎት ዓመት የልዩ ስብሰባ ፕሮግራም ጭብጥ ጠንካራ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አለው። (ያዕ. 4:7) ለዚህ ላለንበት ፈታኝ ወቅት ይህ በጣም አስፈላጊ መመሪያ ነው! የአምላክን ትእዛዛት ማክበራችን ከሰይጣን ጋር በቀጥታ ያጋጨናል። ፕሮግራሙ ዲያብሎስ በእምነታችን ላይ የሚሰነዝረውን ስውር ጥቃት እንዴት በጽናት መመከት እንደምንችል ያስተምረናል። በዚህ ስብሰባ ላይ ከምናገኛቸው መንፈሳዊ ውድ ማዕድናት መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
የወረዳ የበላይ ተመልካቹ “በቤተሰብ ውስጥ አምላካዊ ተገዥነትን ማንጸባረቅ” ቤተሰቡ የዓለምን ተጽዕኖዎች እንዲቋቋም እንዴት እንደሚያጠነክረው ያብራራል። “ዲያብሎስን መቃወም ማለት ምን ማለት ነው” የሚለው የጎብኚ ተናጋሪው የዕለቱ የመጀመሪያ ንግግር ሰይጣን መንፈሳዊነታችንን ለማበላሸት ያለውን ዓላማ ለመግታት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ያለብን ለምንና እንዴት እንደሆነ ያስረዳል። የዲያብሎስን የተንኮል ዘዴዎች በተመለከተ ንቁ መሆን ለሚያስፈልጋቸው ለወጣቶች ጭምር ሁለት ክፍሎች ተዘጋጅተዋል። አሁን በጐልማሳነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ክርስቲያኖች ወጣት ሳሉ ከዓለም ፍላጎቶች ጋር ተስማምተው ለመጓዝ እምቢ ብለዋል። አንዳንዶቹ ተሞክሯቸውን ሲናገሩ እንሰማለን።
የሰብዓዊው ኅብረተሰብ ክፍል የሆኑ ሁሉ ለሥልጣን መገዛት ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም በጎብኚ ተናጋሪው የሚቀርበው የመደምደሚያ ንግግር አምላካዊ ተገዥነታችንን ማሳየት አስፈላጊ የሆነባቸውን አራት አቅጣጫዎች ያብራራል። (1) ለመንግሥታት፣ (2) በጉባኤ ውስጥ፣ (3) በሥራ ቦታ እና (4) በቤተሰብ ክልል ውስጥ። እንዴት ያለ ግሩም ፕሮግራም ነው!
በዚህ የልዩ ስብሰባ ቀን ለመጠመቅ የሚፈልጉ ሁሉ ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ አሁኑኑ ማሳወቅ አለባቸው። ሁላችንም የስብሰባውን ዕለት በቀን መቁጠሪያችን ላይ ምልክት በማድረግ ሙሉውን የስብሰባ ፕሮግራም ለመካፈል ከወዲሁ እቅድ ማውጣት ይኖርብናል። ምንጊዜም ራሳችንን ለይሖዋ የምናስገዛ ከሆነ ዘላለማዊ በረከቶችን እናገኛለን።