አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም
ከጥር ወር ጀምሮ የሚካሄደው አዲስ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም ጭብጥ “ለምሥራቹ ስትሉ ሁሉን አድርጉ” የሚል ነው። (1 ቆሮ. 9:23) የመንግሥቱ ምሥራች በዛሬው ጊዜ እየተነገረ ያለ ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ መልእክት ነው። ፕሮግራሙ የዚህ አስደሳች የምሥራች መልእክተኞች በመሆናችን ያገኘነውን ልዩ መብት እንድናደንቅ ይረዳናል። በተጨማሪም ያለማሰለስ ምሥራቹን ማወጃችንን እንድንቀጥል ድፍረት ይሰጠናል።—ሥራ 5:42
በአገልግሎቱ የተሻለ ነገር ማከናወን እንችል ዘንድ፣ የሚሰጡንን ቲኦክራሲያዊ ስልጠናዎች እንዴት ሙሉ በሙሉ ልንጠቀምባቸው እንደምንችልም ከፕሮግራሙ እንማራለን። ምሥራቹን ለማስፋፋት ሲሉ ሁለንተናቸውን የሰጡ ወጣቶችን ጨምሮ አንዳንዶች አገልግሎታቸውን ለማስፋት ምን ማስተካከያዎችን እንዳደረጉ ተሞክሯቸውን እንሰማለን።—ከፊልጵስዩስ 2:22 ጋር አወዳድር።
በጎብኚ ተናጋሪው የሚቀርበው ዋናው ንግግር ‘ምሥራቹን በአደራ ለመቀበል ብቁ ሆኖ’ የመቀጠልን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጽልናል። (1 ተሰ. 2:4) ምሥራቹን ለሌሎች የማካፈል መብታችንን ይዘን ለመቀጠል እንድንችል በአስተሳሰባችንና በጠባያችን ሁልጊዜ የአምላክን ብቃቶችና የአቋም ደረጃዎች አሟልተን መገኘት እንደሚኖርብን እንድንገነዘብ የሚረዳ ሐሳብም እናገኛለን። ይህንን በማድረጋችን የምናገኘው በረከትም ጎላ ተደርጎ ይገለጻል።
ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነ ፕሮግራም አያምልጥህ። በዚህ የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም ላይ ለመጠመቅ የሚፈልጉ በቅርቡ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አዳዲሶች ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ አሁኑኑ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናቸው ሁሉ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ጋብዛቸው። ከአርማጌዶን በፊት ሊጠናቀቅ የሚገባውን ታላቅ ሥራ ማከናወን እንችል ዘንድ ይሖዋ ለምሥራቹ ስንል ሁሉን በማድረግ ረገድ እንዲያጠናክረን እንፍቀድለት።