የአንባብያን ጥያቄዎች
አንደኛ ዮሐንስ 4:18 “ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም” በማለት ይነግረናል። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ “ወንድሞችን ውደዱ፣ እግዚአብሔርን ፍሩ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:17) እነዚህን ሁለት ጥቅሶች ማስማማት የምንችለው እንዴት ነው?
ጴጥሮስም ሆነ ዮሐንስ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀጥታ የተማሩ ሐዋርያት ነበሩ። ስለዚህ የጻፉት ነገር እርስ በርሱ እንደሚስማማ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሶች ለመረዳት ቁልፉ ሁለቱ ሐዋርያት እየተናገሩ ያሉት ስለ ተለያዩ የፍርሃት ዓይነቶች መሆኑን መገንዘብ ነው።
በመጀመሪያ የጴጥሮስን ምክር እንመልከት። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ጴጥሮስ መሰል ክርስቲያኖች በሥልጣን ላይ ላሉት ሰዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው አመለካከት በመንፈስ ተነሣስቶ ምክር እየሰጣቸው ነበር። በሌላ አነጋገር በአንዳንድ መስኮች ስለ መገዛት ተገቢ አመለካከት እንዲኖራቸው እያብራራላቸው ነበር። ስለዚህ በሰብዓዊ መንግሥታት ውስጥ በሥልጣን ላይ ላሉት ማለትም እንደ ነገሥታት ወይም ገዥዎች ላሉት ሰዎች እንዲገዙ ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:13, 14) ከዚህ በመቀጠልም ጴጥሮስ “ሁሉን አክብሩ፣ ወንድሞችን ውደዱ፣ እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ንጉሥን አክብሩ” በማለት ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 2:17
በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ስንመረምር ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ‘እግዚአብሔርን መፍራት’ አለባቸው ሲል የመጨረሻ ባለ ሥልጣን የሆነውን አምላክ ላለማሳዘን በመፍራት ለእሱ የጠለቀ አክብሮት ሊኖረን ይገባል ማለቱ እንደነበር ግልጽ ነው።—ከዕብራውያን 11:7 ጋር አወዳድር።
ስለ ሐዋርያው ዮሐንስ ምክርስ ምን ለማለት ይቻላል? ቀደም ሲል ሐዋርያው በ1 ዮሐንስ ምዕራፍ 4 ላይ ከሐሰተኛ ነቢያት የሚመጡ “በመንፈስ የተነገሩ ቃላት”ን የመመርመርን አስፈላጊነት ገልጿል። እነዚህ ቃላት ከይሖዋ አምላክ እንደማይመጡ የተረጋገጠ ነው፤ ከክፉው ዓለም የሚመጡ ወይም ክፉውን ዓለም የሚያንጸባርቁ ናቸው።
ከዚህ በተቃራኒ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ከእግዚአብሔር” ናቸው። (1 ዮሐንስ 4:1–6) በዚህም ምክንያት ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፣ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ፣ . . . እርስ በርሳችን እንዋደድ” በማለት በጥብቅ አሳስቧቸዋል። አምላክ ፍቅር በማሳየት ረገድ ቀዳሚ ሆኖ እርምጃ በመውሰድ ‘ስለ ኃጢአታችን ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን ልኮታል።’ (1 ዮሐንስ 4:7–10) እኛስ ለዚህ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ነው?
ከአፍቃሪው አምላካችን ጋር መጣበቅ እንዳለብን ግልጽ ነው። በፊቱ መሸበርም ሆነ በጸሎት ወደ እሱ ስንቀርብ መንቀጥቀጥ የለብንም። ቀደም ሲል ዮሐንስ “ኅሊናችን የማይወቅሰን ከሆነ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሙሉ መተማመን ይኖረናል። የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምንፈጽምና እርሱን ደስ የሚያሰኘውንም የምናደርግ ስለሆንን፤ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን” በማለት ምክሩን ለግሶ ነበር። (1 ዮሐንስ 3:21, 22 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ ንጹሕ ሕሊና በፍርሃት ሳንሽመደመድ ወይም ፍርሃት ሳያግደን አምላክን ለመቅረብ ነፃ ያደርገናል። ከፍቅር የተነሣ ይሖዋን በጸሎት ለማነጋገር ወይም ለመቅረብ ነፃነት ይሰማናል። በዚህ በኩል “በፍቅር ፍርሃት የለም።”
እስቲ እነዚህን ሁለት የፍርሃት ዓይነቶች አንድ ላይ እንመልከታቸው። አንድ ክርስቲያን ለሥልጣኑ፣ ለኃይሉና ለፍትሑ ካለው የጠለቀ አክብሮት የተነሣ ዘወትር ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት ሊኖረው ይገባል። ይሁን እንጂ አምላክን እንደ አባታችን አድርገን እናፈቅረዋለን፤ ከእሱ ጋር እንደተቀራረብንና ወደ እሱ ለመቅረብ ነፃነት እንዳለን ይሰማናል። በምንም ዓይነት መልኩ ፍርሃት ወደ እሱ ከመቅረብ እንዲያግደን ከማድረግ ይልቅ አንድ ልጅ አፍቃሪ ወላጁን ለመቅረብ ነፃነት እንደሚሰማው ሁሉ እኛም ይሖዋን ለመቅረብ እንደምንችል እንተማመናለን።—ያዕቆብ 4:8