ወደ ነፃነት የሚወስደው ጠባብ መንገድ
ማንኛውም የማሰብ ችሎታ ያለው ሰው አጽናፈ ዓለሙ በተፈጥሮ ሕጎች መመራቱን አያስተባብልም። እነዚህ ሕግጋት ትናንሽ ከሆኑት አተሞች ጀምሮ በቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን እስከያዙት ግዙፍ ጋላክሲዎች ድረስ ሁሉንም ነገር ይቆጣጠራሉ። እንዲህ ባይሆን ኖሮ እቅድ ማውጣትና ነገሮችን መረዳት ሊኖር አይችልም ነበር፤ ሕይወት ራሱ ሊኖር አይችልም ነበር። ሰው የተፈጥሮ ሕጎችን በማስተዋልና ከእነርሱ ጋር በመስማማት በጨረቃ ላይ መራመድና ከየትኛውም የምድር ክፍል ሌላው ቀርቶ ከመሬት ከባቢ አየር ውጪ በመሆን ባለ ቀለም ምስሎችን ቤታችን ውስጥ ወዳለው ቴሌቪዥን ማስተላለፍ የመሳሰሉ አስደናቂ ተግባራትን ማከናወን ችሏል።
ነገር ግን የሥነ ምግባር ሕግጋትን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ከእነርሱ ጋር መጣበቅ ልክ እንደዚሁ ጠቃሚና ፍሬያማ ነውን? ብዙዎች የሥነ ምግባር ሕግጋት እንደሌሉ የሚሰማቸው ይመስላል፤ እንዲሁም ከራሳቸው ፍላጎት ጋር የሚስማማ ልል የሆነ ፍልስፍና ወይም ሃይማኖት መርጠዋል።
ነገር ግን ከዚህ የተለየ መንገድ የመረጡ ጥቂት ሰዎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን መንገድ ‘ወደ ሕይወት የሚወስድ ጠባብ መንገድ’ ብሎ ይገልጸዋል። ኢየሱስ ስለ ጠባቡ መንገድ ሲናገር “የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ስላለ በዚህ መንገድ ላይ ለመጓዝ የሚፈልጉ ጥቂቶች ብቻ መሆናቸው ሊያስደንቀን አይገባም። (ማቴዎስ 7:14) ጥቂቶች ብቻ የሆኑት ለምንድን ነው?
ምክንያቱም ጠባቡ መንገድ በአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች የተገደበ ስለሆነ ነው። ይህ መንገድ የሚያስደስተው ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ልባዊ ፍላጎት ላለው ሰው ብቻ ነው። ነፃነት የሚያስገኝ ከሚመስለው ነገር ግን ባሪያ ከሚያደርገው ሰፊው መንገድ ጋር ሲነጻጸር የማያፈናፍን የሚመስለው ጠባቡ መንገድ አንድን ሰው ከማንኛውም ጎጂ ተጽዕኖ ነፃ ያወጣዋል። ወሰኖቹ ‘ነፃ በሚያወጣው ፍጹሙ ሕግ’ የተከለሉ ናቸው።—ያዕቆብ 1:25
ጠባቡ መንገድ ነፃ የሚያወጣው እንዴት ነው?
በጠባቡ መንገድ ላይ መቆየት ሁልጊዜ ቀላል አለመሆኑ አይካድም። ሰው ሁሉ ፍጽምና የሌለው ሲሆን መጥፎ ድርጊት ለመፈጸም የሚገፋፋው የወረሰው ባሕርይ አለው። ስለዚህ አንድ ሰው በተወሰነ መጠን ልቅ ወደ መሆን ሊያዘነብል ይችላል። ነገር ግን አምላክ ‘የሚያስተምረን ለራሳችን ጥቅም’ ስለሆነ ‘በቀጠነው መንገድ’ መጓዛችንን መቀጠላችን የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ስንመለከት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ራሳችንን በራሳችን መገሠጹ ወይም እርማቶችን መቀበሉ የሚገባ ነው።—ኢሳይያስ 48:17፤ ሮሜ 3:23
በምሳሌ ለማስረዳት፦ ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥብቅ የሆነ የምግብ ፕሮግራም ያወጣሉ። ይህም አንዳንድ ጊዜ በምግብ ሰዓቶች ጥብቅ መሆን ማለት ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ልጆች ካደጉ በኋላ የወላጆቻቸውን ፍቅር የተሞላበት ማሰልጠኛ ያደንቃሉ። አዋቂዎች ሲሆኑ ሰውነትን የሚገነባ ምግብ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ አይቸገሩም። ከዚህ በላይ ተትረፍርፎ የሚቀርበው የተለያየ ተመጣጣኝ ምግብ ምንም ዓይነት የጭቆና ስሜት እንዳይሰማቸው ያደርጋል።
በመንፈሳዊ ሁኔታም አምላክ ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብ መንገድ ላይ ለሚጓዙ ሰዎች እንዲሁ ያደርግላቸዋል። ገር በሆኑ ሰዎች ውስጥ ወደ ደስታና እውነተኛ ነፃነት የሚመራ ጤናማ ፍላጎት ያሳድጋል። ይህንን የሚያደርገው ቃሉ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በማቅረብ ነው። ከዚህም በተጨማሪ መንፈሱ እንዲረዳን በጸሎት እንድንጠይቀው ይጋብዘናል፤ እንዲሁም በጠባቡ መንገድ መጓዛችንን እንድንቀጥል ሊያበረታቱን ከሚችሉ መሰል ክርስቲያኖች ጋር እንድንሰባሰብ ያዘናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) አዎን፣ አምላክ ፍቅር ነው፤ ዓላማዎቹና ነገሮችን የሚያከናውንባቸው መንገዶች ሁሉ የተመሠረቱት በዚህ ከሁሉ በላቀ ጠባይ ላይ ነው።—1 ዮሐንስ 4:8
ፍቅር፣ ሰላም፣ ቸርነት፣ ራስን መግዛትና ሌሎች የመንፈስ ፍሬዎች ካሉ ጠባቡ መንገድ ጨቋኝ መስሎ አይታየንም። ቅዱስ ጽሑፉ እንደሚለው “እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።” (ገላትያ 5:22, 23) “የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ።” (2 ቆሮንቶስ 3:17) ሌላው ቀርቶ አሁን እንኳ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህንን ነፃነት እየቀመሱ ነው። ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን ከሚለውና ከአጉል እምነቶች ጋር በማያያዝ ሞትን መፍራት ከመሳሰሉት በዛሬው ጊዜ ሰዎችን ከሚያሠቃዩት አብዛኞቹ ፍርሃቶች ተገላግለዋል። ‘ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር አግዚአብሔርን በማወቅ ስለምትሞላበት’ ጊዜ ማሰላሰሉ ምንኛ የሚያስደስት ነው! (ኢሳይያስ 11:9) በዚያን ጊዜ የወንጀል ፍራቻ እንኳ አይኖርም። ቁልፎችና መስኮት ላይ የሚገጠሙ የሌባ መከላከያ የብረት ዘንጎች ለዘላለም ይወገዳሉ። ማታም ሆነ ቀን ቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጪ ሁሉም ሰው ነፃነትና ደህንነት ይሰማዋል። ነፃነት ማለት ይህ ነው!
አምላክ እንደሚረዳን አያጠራጥርም
ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምቶ መኖር ጥረት መጠየቁ የማይካድ ቢሆንም “ትእዛዛቱ” ፍጹም ላልሆኑ ሰዎች እንኳ ሳይቀር “ከባዶች አይደሉም።” (1 ዮሐንስ 5:3) ራሳችንን ከጠባቡ መንገድ ጋር ካስማማንና በዚህ መንገድ ላይ መጓዙ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ካወቅን በሰፊው መንገድ ላይ የሚጓዙ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁበትን ተግባርና አስተሳሰብ ይበልጥ እየጠላን እንሄዳለን። (መዝሙር 97:10) የአምላክን ሕግ መታዘዝ ከሁላችንም የተፈጥሮ ባሕርይ ጋር የሚስማማ ነው። በብዙዎች ላይ ከሚታየው ‘የልብ ኃዘን’ እና ‘የመንፈስ መሰበር’ እጅግ በተለየ ሁኔታ “እነሆ፣ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ” በማለት አምላክ ቃል ይገባል። አዎን፣ በይሖዋ የሰለጠነ ልብ ደስተኛና ነፃ ነው።—ኢሳይያስ 65:14
ኢየሱስ የሞተው ለእኛ እውነተኛ ነፃነት ለማስገኘት ብሎ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ በመሆን የዚህን መሥዋዕት ጥቅሞች እያቀረበ ነው። ሰፊው መንገድና በእሱ የሚጓዙ ሰዎች የሚጠፉበት “ታላቁ መከራ” ካበቃ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ታዛዥ የሰው ልጆችን በጠባቡ መንገድ ላይ ከቀሩት ሰዎች ጋር ወደ መንገዱ መጨረሻ ማለትም ወደ ፍጽምና መምራት ይጀምራል። (ራእይ 7:14–17፤ ማቴዎስ 24:21, 29–31) በመጨረሻ “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው” የሚለው ታላቅ ተስፋ ከግብ ሲደርስ እንመለከታለን። ይህንን ከአምላክ የሚገኝ ነፃነት ምንም ነገር አይተካከለውም። ሌላው ቀርቶ ሞት እንኳ አይኖርበትም።—ሮሜ 8:21፤ ራእይ 21:3, 4
አንድ ሰው ጠባቡ መንገድ የሚያመራው ወዴት እንደሆነ በግልጽ ማስተዋሉና መረዳቱ ይህንን መንገድ እንዲመርጥና በዚህ መንገድ ላይ እስከመጨረሻው እንዲጓዝ ያስችለዋል። በተለይ ወጣቶች የአምላክ የአቋም ደረጃዎች የሚጥሉትን ገደብ በተመለከተ አርቆ አስተዋይ እንዲሆኑና ትዕግሥት እንዳያጡ እርዳታ ይቀርብላቸዋል። እነዚህ ነገሮች የአምላክ ፍቅር መግለጫና በሰፊው መንገድ ላይ ከሚገኙ መጥፎ ነገሮች የሚጠብቁ እንደሆኑ አድርገው እንዲመለከቷቸው ይማራሉ። (ዕብራውያን 12:5, 6) ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ ጥሩ ፍሬ ለማፍራት ጊዜ እንደሚወስድበት ሁሉ አንድ ሰው አምላካዊ ጠባዮችንና ፍላጎቶችን ለማሳደግ ጊዜ እንደሚወስድበት በማስታወስ ትዕግሥተኛ መሆን እንዳለበት የታወቀ ነው። ቢሆንም ዛፉ እንክብካቤ ከተደረገለትና ውኃ ከጠጣ ያፈራል።
ስለዚህ የአምላክን ቃል አጥና፣ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ተሰብሰብ፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት ‘ሳታቋርጥ ጸልይ።’ (1 ተሰሎንቄ 5:17) አምላክ ‘ጎዳናህን ለማቃናት’ እንደሚረዳህ እምነት ጣልበት። (ምሳሌ 3:5, 6) ነገር ግን ይህ ሁሉ ተግባራዊ መሆን የሚችል ነውን? በእርግጥ የሚሠራ ነውን? አዎን፣ ባለፈው ርዕስ ላይ ለተጠቀሱት ለቶምና ለማሪ ሠርቶላቸዋል።
በሰፊው መንገድ ላይ መጓዛቸውን አቆሙ
ቶም እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “በሰባዎቹ ዕድሜዬ አጋማሽ ላይ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤቴ ከመጣ በኋላ ከምሥክሮቹ ጋር ግንኙነት ጀመርን። ውይይቱ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ማጥናት አመራ። ቀስ በቀስ ሕይወቴን ማስተካከል ጀመርኩ። በ1982 ተጠመቅሁ፤ በአሁኑ ጊዜ በጉባኤያችን ውስጥ እያገለገልኩ ነው። ወንድ ልጃችንም ተጠምቋል። እውነትን ከማወቄ በፊት ባሉት በእነዚያ ዓመታት ሁሉ ባለቤቴ በትዕግሥት ስለያዘችኝ አመሰግናታለሁ። እንዲሁም ስላደረጉልን ነገር ሁሉና ስለ ወደፊቱ ተስፋችን ከሁሉ በላይ ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰግናቸዋለሁ።”
ማሪስ እንዴት ሆና ይሆን? አምላክ ፈጽሞ ይቅር እንደማይላት ቢሰማትም ለልጆችዋ ስትል ስለ አምላክ ለመማር ፈለገች። የይሖዋ ምሥክሮች ጎረቤትዋን መጽሐፍ ቅዱስ እያስተማሯት እንደሆነ ስትሰማ እርሷንም እንዲረዷት ጠየቀቻቸው። ቢሆንም የተጠናወቷት መጥፎ ዓመሎች እድገት እንዳታደርግ እንቅፋት ሆኑባት። በጥናቷ ወቅት አንድ ጊዜ ትበረታ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደነበረችበት ትመለስ ነበር። ቢሆንም ትንሿ የሰባት ዓመት ልጅዋ “አይዞሽ እማማ። ለውጥ ማድረግ ትቺያለሽ!” እያለች ሁልጊዜ ታበረታታት ነበር። ከዚያም ማሪ ከፍተኛ ጥረት አደረገች።
የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ የሆነው በሕግ ሳያገባት አብሯት የሚኖረው ሰው ወደ ቤት ሲመለስ እርሱም ጥናት ጀመረ። በመጨረሻ ሁለቱም በመጥፎ ልማዶቻቸው ላይ ድል ተቀዳጁ። ጋብቻቸውን ሕጋዊ ካደረጉና ከተጠመቁ በኋላ ታላቅ ደስታ ከማግኘታቸውም በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ቤተሰብ እንደሆኑ ተሰማቸው። የሚያሳዝነው ማሪ በመጨረሻ በኤድስ በሽታ ሞተች፤ ቢሆንም ስለትንሣኤና አደገኛው ሰፊ መንገድ ፈጽሞ በማይኖርባት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚኖረው ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ አጥብቃ ይዛ ነው የሞተችው።
አዎን፣ ወደ ጥፋት ከሚወስደው ሰፊና ትልቅ መንገድ መውጣት ይቻላል። ኢየሱስ ክርስቶስ “የዘላለም ሕይወትም፣ ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም) ወደ ሕይወት በሚመራው ጠባብ መንገድ ላይ ለመጓዝ ለምን አትወስንም? ከአምላክ ቃል የተማርከውን ነገር በልብህ በመጻፍና በሥራ ላይ በማዋል “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” የሚለውን አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አንተም በግልህ ልትቀምሰው ትችላለህ።—ዮሐንስ 8:32