ምቀኛ ሰው
የዕብራይስጥ ቋንቋ “ቅናት” ለሚለው ቃል የሚጠቀምበት መሠረታዊ ቃል አንድ ብቻ ነው። ይህ የዕብራይስጥ ቃል ኃጢአተኛ ሰዎችን ለመግለጽ ሲጠቀስ “ምቀኝነት” ወይም “መቀናቀን” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። (ዘፍጥረት 26:14፤ መክብብ 4:4) ሆኖም የግሪክ ቋንቋ “ቅናት”ን ለመግለጽ ከአንድ በላይ ቃል ይጠቀማል። ዜሎስ የተባለው የግሪክኛ ቃል አቻው እንደሆነው የዕብራይስጥ ቃል ሁሉ ጥሩውንም ሆነ መጥፎውን ቅናት ሊያመለክት ይችላል። ሌላው ፍትሆነስ የተባለው ቃል መጥፎውን ቅናት ብቻ የሚያመለክት ነው። ይህ ቃል በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ በሁሉም ቦታ ላይ “ምቀኝነት” ተብሎ ተተርጉሟል።
በጥንቷ ግሪክ ፍትሆነስ የተባለው ቃል የሚሠራበት እንዴት ነበር? ዘ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ከስግብግብ ሰው በተለየ መንገድ ፍትሆነስ ያለበት ሰው ሌላው ሰው ስላለው ቅር የተሰኘበትን ንብረት የግድ ላይፈልግ ይችላል፤ በቀላሉ ለመናገር ያህል፣ ሌላ ሰው ያ ነገር እንዲኖረው አይፈልግም። ከተፎካካሪ ሰው የሚለየው ዓላማው ተፎካክሮ ማሸነፍ ሳይሆን ሌሎች እንዳያሸንፉ ማድረግ በመሆኑ ነው።”
ብዙውን ጊዜ ምቀኛ ሰው ለሚደርሱበት ችግሮች ዋነኛ መንስኤ የራሱ ዝንባሌ መሆኑን አያውቅም። ይኸው መዝገበ ቃላት እንዲህ በማለት ማብራሪያ ይሰጣል፦ “ፍትሆነስን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ሰውዬው ራሱን አለማወቁ ነው። ፍትሆነስ ያደረበት ሰው ለምን እንዲህ ዓይነት ባሕርይ እንደሚያሳይ ቢጠየቅ የሚነቅፈው ሰው ሊነቀፍ የሚገባው እንደሆነና ድርጊቱ አግባብነት የሌለው መሆኑ ለትችት እንደገፋፋው ለራሱም ሆነ ለሌሎች መናገሩ የማይቀር ነው። ስለ ጓደኛው እንደዚያ ያለ ነገር ለምን እንደሚናገር ቢጠየቅ ትችቶቹን ያቀረበው ጓደኛውን ለመጥቀም ብሎ እንደሆነም ሊናገር ይችላል።”
የወንጌል ጸሐፊዎች የሆኑት ማቴዎስና ማርቆስ ኢየሱስ እንዲገደል ያደረጉት ሰዎች የነበራቸውን ዝንባሌ ለመግለጽ ፍትሆነስ በተባለው የግሪክኛ ቃል ተጠቅመዋል። (ማቴዎስ 27:18፤ ማርቆስ 15:10) አዎን፣ ያን ሁሉ ለማድረግ የገፋፋቸው ምቀኝነት ነበር። ከሐዲዎችም ወንድሞቻቸው የነበሩትን እንዲጠሉ ያደረጋቸው ይኸው መጥፎ ስሜት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:3–5) ምቀኞች ወደ አምላክ መንግሥት እንዳይገቡ መከልከላቸው ምንም አያስደንቅም! ይሖዋ አምላክ ‘በምቀኝነት እንደተሞሉ’ የሚቀጥሉ ሰዎች ‘ሞት ይገባቸዋል’ ብሎ ደንግጓል።—ሮሜ 1:29, 32 የ1980 ትርጉም፤ ገላትያ 5:21
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ምቀኝነት ሕይወትህን እንዲያበላሽ አትፍቀድለት