የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w20 የካቲት ገጽ 14-19
  • ምቀኝነትን በመዋጋት ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምቀኝነትን በመዋጋት ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የምቀኝነት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች
  • ትሑቶችና ባላችሁ ነገር የምትረኩ ሁኑ
  • “ሰላም የሚገኝበትን” ነገር አድርጉ
  • ቅናት አእምሯችንን ሊመርዝ የሚችል መጥፎ ባሕርይ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጉ ነገሮች
    ንቁ!—2014
  • ራስህን ከሌሎች ጋር ታወዳድራለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ምቀኛ ሰው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
w20 የካቲት ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 8

ምቀኝነትን በመዋጋት ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ

“ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።”—ሮም 14:19

መዝሙር 113 ከአምላክ ያገኘነው ሰላም

ማስተዋወቂያa

1. ምቀኝነት በዮሴፍ ቤተሰብ ላይ ምን ጉዳት አስከትሏል?

ያዕቆብ ሁሉንም ልጆቹን ይወዳቸው የነበረ ቢሆንም ለ17 ዓመቱ ዮሴፍ ለየት ያለ ፍቅር ነበረው። ታዲያ የዮሴፍ ወንድሞች ይህን ሲያዩ ምን ተሰማቸው? ዮሴፍን የተመቀኙት ሲሆን ይህ ደግሞ እንዲጠሉት አደረጋቸው። ዮሴፍ ወንድሞቹ እንዲጠሉት የሚያደርግ ምንም ነገር አላደረገም። ያም ቢሆን ዮሴፍን ለባርነት የሸጡት ከመሆኑም ሌላ ለአባታቸው የሚወደውን ልጁን አውሬ በልቶት እንደሞተ በመናገር ዋሹት። ምቀኛ መሆናቸው የቤተሰባቸው ሰላም እንዲደፈርስና የአባታቸው ልብ በሐዘን እንዲሰበር አድርጓል።—ዘፍ. 37:3, 4, 27-34

2. በገላትያ 5:19-21 መሠረት ምቀኝነት በጣም አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

2 በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ምቀኝነትb አንድ ሰው የአምላክን መንግሥት እንዳይወርስ ከሚያግዱና ወደ ሞት ከሚመሩ “የሥጋ ሥራዎች” መካከል ተጠቅሷል። (ገላትያ 5:19-21⁠ን አንብብ።) እንደ ጥላቻ፣ ጠብና በቁጣ መገንፈል ላሉት ጎጂ ባሕርያት ብዙውን ጊዜ መንስኤ የሚሆነው ምቀኝነት ነው።

3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

3 የዮሴፍ ወንድሞች ታሪክ እንደሚያሳየው ምቀኝነት ግንኙነትን የሚያሻክር ከመሆኑም ሌላ በቤተሰብ ውስጥ ያለውን ሰላም ያደፈርሳል። ማናችንም ብንሆን የዮሴፍ ወንድሞች ያደረጉትን ነገር አናደርግ ይሆናል፤ ያም ቢሆን የሁላችንም ልብ ኃጢአተኛና ከዳተኛ ነው። (ኤር. 17:9) በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ከምቀኝነት ዝንባሌ ጋር መታገል ቢያስፈልገን የሚያስገርም አይሆንም። እስቲ በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን እንመልከት፤ እነዚህ ምሳሌዎች የምቀኝነት ስሜት በልባችን እንዲያቆጠቁጥ የሚያደርጉ ምክንያቶችን ለማወቅ ያስችሉናል። ከዚያም ምቀኝነትን ለመዋጋትና ሰላምን ለማስፈን የሚረዱ አንዳንድ እርምጃዎችን እንመለከታለን።

የምቀኝነት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች

4. ፍልስጤማውያን ይስሐቅን የተመቀኙት ለምን ነበር?

4 ቁሳዊ ሀብት። ይስሐቅ ሀብታም ሰው በመሆኑ ፍልስጤማውያን ተመቅኝተውት ነበር። (ዘፍ. 26:12-14) በዚህም የተነሳ የይስሐቅ መንጎች የሚጠጡባቸውን የውኃ ጉድጓዶች ደፈኗቸው። (ዘፍ. 26:15, 16, 27) እንደ እነዚያ ፍልስጤማውያን ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ከእነሱ የበለጠ ቁሳዊ ሀብት ያላቸውን ሰዎች ይመቀኛሉ። የሰዎቹን ሀብት ከመመኘትም አልፈው እነዚያ ሰዎች ሀብታቸውን ቢያጡ ደስ ይላቸዋል።

5. የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን የተመቀኙት ለምን ነበር?

5 በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ መሆን። ኢየሱስ በተራው ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ስለነበረው የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተመቅኝተውታል። (ማቴ. 7:28, 29) ኢየሱስ የአምላክ ወኪል ከመሆኑም ሌላ እውነትን ያስተምር ነበር። ያም ቢሆን እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ስለ እሱ ውሸት በማሰራጨት ስሙን ለማጥፋት ጥረት አድርገዋል። (ማር. 15:10፤ ዮሐ. 11:47, 48፤ 12:12, 13, 19) ከዚህ ዘገባ ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት እናገኛለን? ባሏቸው መልካም ባሕርያት የተነሳ በጉባኤው ውስጥ ተወዳጅነት ያተረፉ ክርስቲያኖችን የመመቅኘት ዝንባሌ ጨርሶ በውስጣችን እንዳያድር መታገል ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ የእነሱን ጥሩ ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረግ አለብን።—1 ቆሮ. 11:1፤ 3 ዮሐ. 11

6. ዲዮጥራጢስ ወንድሞቹን እንደተመቀኘ የሚያሳየው ምንድን ነው?

6 ቲኦክራሲያዊ መብቶች። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ዲዮጥራጢስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንድሞችን ይመቀኝ ነበር። በጉባኤው ውስጥ “የመሪነት ቦታ መያዝ” ይፈልግ ነበር፤ በመሆኑም ስለ ሐዋርያው ዮሐንስና በኃላፊነት ቦታ ላይ ስለሚያገለግሉ ሌሎች ወንድሞች መጥፎ ወሬ በማናፈስ ጉባኤው ለእነሱ ያለውን አክብሮት እንዲያጣ ለማድረግ ሞክሯል። (3 ዮሐ. 9, 10) እንደ ዲዮጥራጢስ ዓይነት እርምጃ ባንወስድም እንኳ የምንጓጓለትን ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነት ያገኘን አንድ ክርስቲያን መመቅኘት ልንጀምር እንችላለን፤ በተለይ ደግሞ ይህን ኃላፊነት ለመቀበል የእሱን ያህል ብቁ እንደሆንን ከተሰማን ይህ ዝንባሌ ሊታገለን ይችላል።

ምስሎች፦ 1. በመልካም አፈር ውስጥ ሥር የሰደደ ጤናማ አበባ። 2. ይሄው አበባ አረም አንቆት። 3. በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሦስት እህቶች በደስታ ሲጨዋወቱ፤ ነጠል ብላ የቆመች ሌላ እህት ግን በስጨት ብላለች።

ልባችን እንደ አፈር፣ ያሉን መልካም ባሕርያት ደግሞ እንደሚያምሩ አበቦች ናቸው። ምቀኝነት ግን እንደ መርዛማ አረም ነው። ምቀኝነት እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና ደግነት ያሉትን ግሩም ባሕርያት አንቆ ሊያስቀራቸው ይችላል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. ምቀኝነት ምን ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል?

7 ምቀኝነት እንደ መርዛማ አረም ነው። በልባችን ውስጥ አንዴ ሥር መስደድ ከጀመረ ነቅለን ማውጣት ከባድ ነው። እንደ ቅናት፣ ኩራትና ራስ ወዳድነት ያሉት መጥፎ ባሕርያት ምቀኝነት ይበልጥ ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ሊያደርጉ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ምቀኝነት እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና ደግነት ያሉትን ግሩም ባሕርያት አንቆ ሊያስቀራቸው ይችላል። ምቀኝነት በልባችን ውስጥ ማቆጥቆጥ እንደጀመረ ካስተዋልን ወዲያውኑ ነቅለን ልናወጣው ይገባል። ታዲያ ምቀኝነትን መዋጋት የምንችለው እንዴት ነው?

ትሑቶችና ባላችሁ ነገር የምትረኩ ሁኑ

ምስሎች፦ 1. በመልካም አፈር ውስጥ ሥር የሰደደ ጤናማ አበባ። 2. አንድ ሰው፣ አበባውን ያነቀውን አረም ሲነቅለው። 3. በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አራት እህቶች በደስታ ሲጨዋወቱ።

እንደ አረም የሆነውን ምቀኝነትን መዋጋት የምንችለው እንዴት ነው? በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ፣ ምቀኝነትን ነቅለን ማውጣት ብሎም ባለን የመርካትና የትሕትና ባሕርይን ማዳበር እንችላለን (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

8. ምቀኝነትን ለመዋጋት የሚረዱን የትኞቹ ባሕርያት ናቸው?

8 ትሑት ለመሆንና ባለን ነገር ረክተን ለመኖር ጥረት በማድረግ ምቀኝነትን መዋጋት እንችላለን። ልባችን በእነዚህ መልካም ባሕርያት ሲሞላ ምቀኝነት ቦታ አያገኝም። ትሕትና ስለ ራሳችን ከሚገባው በላይ እንዳናስብ ይረዳናል። ትሑት የሆነ ሰው ከሌሎች የበለጠ ማግኘት እንደሚገባው አይሰማውም። (ገላ. 6:3, 4) ባለው ነገር የሚረካ ሰው ደግሞ ራሱን ከሌሎች ጋር አያወዳድርም። (1 ጢሞ. 6:7, 8) ትሑት የሆነና ባለው ነገር የሚረካ ሰው ሌሎች ጥሩ ነገር ሲያገኙ ከእነሱ ጋር አብሮ ይደሰታል።

9. በገላትያ 5:16 እና በፊልጵስዩስ 2:3, 4 መሠረት መንፈስ ቅዱስ ምን እንድናደርግ ይረዳናል?

9 የሥጋ ሥራ የሆነውን ምቀኝነትን አስወግደን በምትኩ ትሕትናን እና ባለን የመርካት ባሕርይን ለማዳበር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል። (ገላትያ 5:16⁠ን እና ፊልጵስዩስ 2:3, 4⁠ን አንብብ።) የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ውስጣዊ ሐሳባችንን እና ዝንባሌያችንን ለመመርመር ሊረዳን ይችላል። በአምላክ እርዳታ፣ መጥፎ ሐሳቦችንና ስሜቶችን በሚያንጹ ነገሮች መተካት እንችላለን። (መዝ. 26:2፤ 51:10) ከዚህ ቀጥሎ፣ የምቀኝነት ስሜት እንዳያድርባቸው በማድረግ ረገድ የተሳካላቸውን የሙሴንና የጳውሎስን ምሳሌ እንመለከታለን።

ሙሴ፣ ኢያሱና የተወሰኑ እስራኤላውያን ሽማግሌዎች ከመገናኛ ድንኳኑ አጠገብ ቆመዋል። ኢያሱ እንደ ነቢያት የሆኑትን ሁለት ሰዎች እንዲከለክላቸው ሙሴን ሲጠይቀው።

አንድ ወጣት እስራኤላዊ ወደ ሙሴና ኢያሱ ሮጦ በመሄድ በሰፈሩ ውስጥ ያሉ ሁለት ወንዶች እንደ ነቢያት መሆን እንደጀመሩ ነገራቸው። ኢያሱ፣ ሰዎቹን እንዲከለክላቸው ሙሴን ጠየቀው፤ ሆኖም ሙሴ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲያውም ይሖዋ መንፈሱን ለሁለቱ ሰዎች በመስጠቱ እንደተደሰተ ለኢያሱ ነገረው። (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. ሙሴ ትሕትናውን የሚፈትን ምን ሁኔታ አጋጥሞታል? (ሽፋኑን ተመልከት።)

10 ሙሴ በአምላክ ሕዝብ ላይ ትልቅ ሥልጣን ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ሌሎች ይህን መብት እንዳያገኙ ለመከላከል አልሞከረም። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ይሖዋ ለሙሴ ከሰጠው መንፈስ ቅዱስ ወስዶ በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ለቆሙት እስራኤላውያን ሽማግሌዎች ሰጥቷቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሙሴ፣ ወደ መገናኛው ድንኳን ያልመጡ ሁለት ሽማግሌዎችም መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉና እንደ ነቢያት እንደሆኑ ሰማ። ታዲያ እነዚህን ሁለት ሽማግሌዎች እንዲከለክላቸው ኢያሱ ሲጠይቀው ሙሴ ምን አደረገ? ሙሴ፣ ይሖዋ ለእነዚህ ሁለት ሰዎች ባደረገው ነገር አልተመቀኘም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያለ መብት በማግኘታቸው አብሯቸው በመደሰት ትሕትና አሳይቷል። (ዘኁ. 11:24-29) ከሙሴ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ምስሎች፦ 1. የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የሚመራ አንድ በዕድሜ የገፋ ወንድም፣ በዕድሜ ከእሱ የሚያንስን አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ለዚህ ኃላፊነት እንዲያሠለጥነው የሽማግሌዎች አካል በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ተጠየቀ። 2. በዕድሜ የሚያንሰው ወንድም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እየመራ ሳለ በዕድሜ የገፋው ወንድም ቁጭ ብሎ በትኩረት ይከታተላል። 3. በዕድሜ የገፋው ወንድም በዕድሜ የሚያንሰውን ወንድም ሄዶ በመጨበጥ አድናቆቱን ይገልጽለታል።

ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንደ ሙሴ ትሑት መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት)c

11. ሽማግሌዎች የሙሴን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

11 የጉባኤ ሽማግሌ ከሆንክ በጣም የምትወደውን አንድ የጉባኤ ኃላፊነት ሌላ ሰው እንዲያከናውነው እንድታሠለጥን ተጠይቀህ ታውቃለህ? ለምሳሌ ያህል፣ በየሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መምራት ያስደስትህ ይሆናል። ሆኖም እንደ ሙሴ ትሑት ከሆንክ በጊዜ ሂደት ይህን ኃላፊነት መረከብ እንዲችል አንድን ወንድም እንድታሠለጥን ብትጠየቅ ቦታዬን አጣለሁ የሚል ስጋት አያድርብህም። እንዲያውም ወንድምህን በደስታ ትረዳዋለህ።

12. በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ክርስቲያኖች ባላቸው እንደሚረኩና ትሑት እንደሆኑ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

12 በዕድሜ የገፉ በርካታ ወንድሞች እያጋጠማቸው ያለ ሌላ ሁኔታ ደግሞ እንመልከት። እነዚህ ወንድሞች ለበርካታ ዓመታት የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪዎች ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ዕድሜያቸው 80 ሲሞላ ግን ይህን ኃላፊነታቸውን በፈቃደኝነት ለሌሎች ያስረክባሉ። በተመሳሳይም 70 ዓመት የሆናቸው የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በዚህ አገልግሎት መካፈላቸውን አቁመው በሌላ የአገልግሎት ምድብ እንዲሰማሩ የሚቀርብላቸውን ግብዣ በትሕትና ይቀበላሉ። በቅርቡ ደግሞ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ የቤቴል ቤተሰብ አባላት መስኩ ላይ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። እነዚህ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ቀደም ሲል ያከናውኑት የነበረውን ኃላፊነት በተረከቡት ወንድሞች ቅር አይሰኙም።

13. ጳውሎስ 12ቱን ሐዋርያት ለመመቅኘት ሊፈተን የሚችለው ለምን ነበር?

13 ባለው በመርካትና ትሑት በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሌላው ሰው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ጳውሎስ ምቀኝነት እንዲያድርበት አልፈቀደም። በአገልግሎት በትጋት ይካፈል የነበረ ቢሆንም “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ” በማለት በትሕትና ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:9, 10) አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት አብረውት ነበሩ፤ ጳውሎስ ግን ክርስቲያን የሆነው ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ነው። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ‘ለአሕዛብ የተላከ ሐዋርያ’ ሆኖ ቢሾምም ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የመሆን ልዩ መብት አላገኘም። (ሮም 11:13፤ ሥራ 1:21-26) ጳውሎስ እነዚህን 12 ሐዋርያት ባገኙት መብትና ከኢየሱስ ጋር በነበራቸው የጠበቀ ቅርርብ ከመመቅኘት ይልቅ ባለው ረክቶ ኖሯል።

14. ባለን የምንረካና ትሑት ከሆንን ምን እናደርጋለን?

14 ባለን የምንረካና ትሑት ከሆንን እንደ ጳውሎስ፣ ይሖዋ ኃላፊነት የሰጣቸውን ሰዎች እናከብራለን። (ሥራ 21:20-26) ይሖዋ የተሾሙ ወንድሞች የክርስቲያን ጉባኤን እንዲመሩ ዝግጅት አድርጓል። እነዚህ ወንድሞች ፍጹማን ባይሆኑም ይሖዋ እንደ “ስጦታ” አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ኤፌ. 4:8, 11) እነዚህን የተሾሙ ወንድሞች ስናከብርና የሚሰጡንን መመሪያ በትሕትና ስንታዘዝ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ጠብቀን መኖር እንችላለን።

“ሰላም የሚገኝበትን” ነገር አድርጉ

15. ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 ምቀኝነት ሥር እንዲሰድ ከፈቀድን ሰላም አይኖርም። ምቀኝነትን ከልባችን ነቅለን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲፈጠርባቸው ላለማድረግ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይሖዋ የሰጠንን የሚከተለውን ትእዛዝ ማክበር የምንችለው እነዚህን አስፈላጊ እርምጃዎች ከወሰድን ብቻ ነው፦ “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።” (ሮም 14:19) ታዲያ ሌሎች ምቀኝነት እንዳያድርባቸው የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን? ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

16. ሌሎች ምቀኝነት እንዳያድርባቸው መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?

16 አመለካከታችንና ድርጊታችን በሌሎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ዓለም፣ ያለኝ ነገር “ይታይልኝ” የሚል መንፈስ እንድናንጸባርቅ ያበረታታናል። (1 ዮሐ. 2:16) ይሁንና እንዲህ ያለው መንፈስ ሌሎች ምቀኝነት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ስላሉን ወይም ልንገዛቸው ስላሰብናቸው ነገሮች ሁልጊዜ ባለማውራት ሌሎች ምቀኝነት እንዳያድርባቸው ማድረግ እንችላለን። ሌሎች ምቀኝነት እንዳያድርባቸው መከላከል የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያሉንን ኃላፊነቶች በተመለከተ ትሑት መሆን ነው። ስላገኘናቸው መብቶች ለሌሎች ብዙ የምናወራ ከሆነ በውስጣቸው ምቀኝነት ሥር እንዲሰድ መንገድ እንከፍታለን። ከዚህ በተቃራኒ ለሌሎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት የምንሰጥ እንዲሁም ያከናወኑትን መልካም ሥራ ጠቅሰን የምናመሰግናቸው ከሆነ ባላቸው ነገር እንዲረኩ እንረዳቸዋለን፤ ይህም በጉባኤ ውስጥ አንድነትና ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል።

17. የዮሴፍ ወንድሞች በቤተሰቡ ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ችለዋል? ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው?

17 ምቀኝነትን ለማስወገድ በምናደርገው ጥረት ሊሳካልን ይችላል! የዮሴፍን ወንድሞች ታሪክ በድጋሚ እንመልከት። በዮሴፍ ላይ በደል ከፈጸሙ ከዓመታት በኋላ ግብፅ ውስጥ አገኙት። ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ከመግለጡ በፊት፣ ባሕርያቸው ተለውጦ እንደሆነ ለማየት ፈተናቸው። ምግብ እንዲቀርብ ካደረገ በኋላ ለታናሽ ወንድማቸው ለቢንያም ከእነሱ እጅግ የላቀ ድርሻ እንዲሰጠው አዘዘ። (ዘፍ. 43:33, 34) ያም ቢሆን ወንድሞቹ ቢንያምን እንደተመቀኙት የሚጠቁም ነገር የለም። እንዲያውም ለወንድማቸውና ለአባታቸው ለያዕቆብ ከልብ እንደሚያስቡ አሳይተዋል። (ዘፍ. 44:30-34) የዮሴፍ ወንድሞች ምቀኝነትን ማስወገድ ስለቻሉ የቤተሰቡ ሰላም ተመልሷል። (ዘፍ. 45:4, 15) እኛም በተመሳሳይ የምቀኝነት ዝንባሌን ከውስጣችን ነቅለን የምናስወግድ ከሆነ የቤተሰባችንንም ሆነ የጉባኤያችንን ሰላም መጠበቅ እንችላለን።

18. በያዕቆብ 3:17, 18 ላይ እንደተገለጸው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ለማድረግ መጣራችን ምን ውጤት አለው?

18 ይሖዋ ምቀኝነትን እንድንዋጋ እና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እንድንጥር ይፈልጋል። እነዚህን ሁለት ነገሮች ለማድረግ ጠንክረን መሥራት ያስፈልገናል። በዚህ ርዕስ ላይ እንደተብራራው ምቀኝነት ብዙ ጊዜ የሚታገለን ዝንባሌ ነው። (ያዕ. 4:5) በዚያ ላይ ደግሞ የምንኖረው የምቀኝነት ዝንባሌ እንድናዳብር በሚገፋፋ ዓለም ውስጥ ነው። ሆኖም ትሑት፣ ባለን የምንረካና አመስጋኝ ከሆንን ምቀኝነት ቦታ አያገኝም። ከዚህ ይልቅ የጽድቅ ፍሬ ለማፍራት የሚመች ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ እንችላለን።—ያዕቆብ 3:17, 18⁠ን አንብብ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • መንፈስ ቅዱስ ምቀኝነትን ለመዋጋት የሚረዳን እንዴት ነው?

  • ባለን መርካትና ትሕትናን ማዳበር ምቀኝነትን ለመዋጋት የሚረዳን እንዴት ነው?

  • ላሉን ነገሮች ትክክለኛ አመለካከት ማዳበራችን ሌሎችን የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

a የይሖዋ ድርጅት ሰላም የሰፈነበት ነው። ይሁንና በውስጣችን ምቀኝነት እንዲያድግ ከፈቀድን ይህ ሰላም ሊደፈርስ ይችላል። በዚህ ርዕስ ላይ፣ የምቀኝነት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን እንመለከታለን። በተጨማሪም ይህን ጎጂ ባሕርይ መዋጋትና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የምንችልበትን መንገድ እናያለን።

b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው ምቀኝነት ሌሎች ያሏቸውን ነገሮች ከመመኘት ባለፈ እነዚያን ነገሮች እንዲያጡ እስከመፈለግ የሚያደርስ ባሕርይ ነው።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የሚመራ አንድ በዕድሜ የገፋ ወንድም፣ በዕድሜ ከእሱ የሚያንስን አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ለዚህ ኃላፊነት እንዲያሠለጥነው የሽማግሌዎች አካል በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ተጠየቀ። በዕድሜ የገፋው ወንድም ይህን ኃላፊነቱን ቢወደውም የሽማግሌዎቹን ውሳኔ በሙሉ ልቡ በመደገፍ፣ ለሚያሠለጥነው ወንድም ጠቃሚ ሐሳቦችን ያካፍለዋል፤ እንዲሁም ከልቡ ያመሰግነዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ