የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ—ሕንድ
ሕንድ! በዚህ ፕላኔት ላይ ከሚኖሩ ስድስት ሰዎች መካከል አንዱ በዚህች በጣም ሰፊ በሆነች አገር ውስጥ ይኖራል። የተለያዩ ሰዎች በሚኖሩባት በዚህች አገር ውስጥ በአጠቃላይ ከ1,000 የሚበልጡ ቋንቋዎች ሲነገሩ በእነዚህ ቋንቋዎች ውስጥ ደግሞ የተለያዩ የአነጋገር ዘይቤዎች አሉ። አብዛኛው ሕዝብ ማለትም 83 በመቶው ሂንዱዎች፣ 11 በመቶው እስላሞች ሲሆኑ የተቀሩት ሲኮች፣ ቡዲሂስቶች፣ ጃይኒስቶች እና ስመ ክርስቲያኖች ናቸው።
በቅርብ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ሕንድ ውስጥ መልካም ፍሬ እያገኙ ነው። ምንም እንኳ ተጽዕኖና ተቃውሞ ቢኖርባቸውም ከይሖዋ መንግሥት ጎን ለመቆም የሚያስችላቸውን ጽኑ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆኑ በግ መሰል ሰዎች አግኝተዋል።
ለምሳሌ ያህል ቤተሰቦቿ የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆኑ አንዲት ልጃገረድ ከልጅነቷ ጀምሮ በልጅነት ልምሻ ሽባ ሆና ነበር። ያለባት በሽታ ስለ አምላክና ስለ ሕይወት ዓላማ እንድታስብ አደረጋት። ስለዚህ ጉዳይ ለማወቅ ብዙ ሃይማኖቶችን ብትመረምርም ምንም ማጽናኛ አላገኘችም። ከዚህ የተነሳ በሃይማኖት ላይ የነበራትን እምነት አጣች፤ ይሁንና በአምላክ ማመኗን አላቆመችም።
በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለች ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ ከዚህች ልጅ ጋር ተገናኙ። “ራእይ 21:4ን ሲያነቡልኝ እንባዬ መጣ” በማለት ታስታውሳለች። ብዙ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን ከመውሰዷም በላይ ምንም እንኳ እናቷ ቢቃወሟትም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ይህች ሴት በሕይወቷ ውስጥ ብዙ ለውጦችን አደረገች፣ ከዘመዶቿ የሚደርስባትን ተቃውሞ በድፍረት ከመቋቋሟም በተጨማሪ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። “በሕይወቴ ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፌአለሁ። ቢሆንም ይሖዋ አምላክ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር በመሆን ታላቅ ሰላምና ደስታ ሰጥቶኛል” ብላለች።
በትምህርት ቤት ውስጥ ለንጹሕ አምልኮ የጸና አቋም መያዝ
አንዲት ወጣት እህት ከተቀሩት የክፍል ተማሪዎች ጋር በመሆን ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንድትሄድ አስተማሪዋ አዘዘቻት። እህት የይሖዋ ምሥክር እንደሆነችና ከይሖዋ ሌላ ማንንም ወይም ምንም ነገር እንደማታመልክ በመናገር እንደማትሄድ በትሕትና ተናገረች። ሌሎቹ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲሄዱ እርሷም መሄድ እንዳለባት አስተማሪዋ ነገረቻት። ተማሪዎቹ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ወደ ይሖዋ ስለማይጸልዩ ከእነርሱ ጋር በዚያ የምትገኝበት ምክንያት ፈጽሞ ሊገባት እንደማይችል በመግለጽ እህት በአቋሟ ጸናች።
ይህች ልጅ ባሳየችው ጽኑ አቋም አስተማሪዋ ስለ እምነትዋ ይበልጥ ለማወቅ ፈለገች። ስለዚህ በማግሥቱ ስለ ይሖዋ አምልኮ የሚናገር ርዕስ ያለበት መጠበቂያ ግንብ ሰጠቻት። አስተማሪዋ ባነበበችው ነገር በመደሰት በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከሚከናወነው ማንኛውም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነፃ እንድትሆን አደረገቻት። እህት ለእርሷና ለሌሎች አስተማሪዎች አሥር መጽሔቶች አበረከተች።
ስለ ደም የሚናገረውን የአምላክ ሕግ ማክበር የታማኝነት ዋጋ አስገኘ
በቅርቡ በቫይረስ የሚመጣ ወረርሽኝ በሽታ በኬረለ ክፍለ ሀገር በአንዳንድ ክፍሎች ተዛምቶ ነበር። ይህ በሽታ ኩላሊትን በጣም ስለሚጎዳ በዚህ በሽታ የተያዘ ሰው ዲያሊሲስ የተባለ ሕክምና ማድረግ ያስፈልገዋል። ለሕክምና ደም መስጠት የተለመደ ነበር። በአንድ ከተማ 14 ሰዎች በዚህ በሽታ ተይዘው ሆስፒታል ገቡ። ከእነዚህ በሽተኞች አንዱ የአካባቢው ጉባኤ ሽማግሌ የሆነ የይሖዋ ምሥክር ነበር። ደም መውሰድ አማራጭ የሌለው ሕክምና እንደሆነ ተነገረው። ሽማግሌው ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለውን እምነቱን ካብራራ በኋላ በፍጹም ደም እንደማይወስድ ገለጸ። (ሥራ 15:28, 29) ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ደም አልወስድም ስላለ እንደሚሞት ሐኪሞቹ ተናገሩ።
ሌሎቹ 13 በሽተኞች ደም ወሰዱ። የሚያሳዝነው ግን ሁሉም በጥቂት ቀናት ውስጥ ሞቱ። በሕይወት የተረፈው ወንድም ብቻ ነበር! የሆስፒታሉ ባለሥልጣናት በጣም ተገረሙ። የጉባኤው አባላት ያለማቋረጥ እየመጡ ወንድምን መጠየቃቸው የሕክምና ሠራተኞቹን በኃይል አስገርሟቸው ነበር። ወንድም ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ አንድ ቀን ዶክተሮቹን ሊያመሰግናቸው ወደ ሆስፒታሉ ሄዶ ነበር፤ ዶክተሮቹ ግን “እኛን የምታመሰግነን ለምንድን ነው? አምላክህን ይሖዋን አመስግነው። ያዳነህ እርሱ ነው። እባክህ ለእኛም ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ጸልይልን” አሉት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአገሪቱ ሪፖርት መግለጫ
የ1994 የአገልግሎት ዓመት
የምሥክሮቹ ከፍተኛ ቁጥር፦14,271
ከሕዝቡ ብዛት ጋር ሲነጻጸር፦1 ምሥክር ለ65,266
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች፦38,192
የአቅኚዎች ብዛት በአማካይ፦1,780
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በአማካይ፦12,453
የተጠማቂዎች ቁጥር፦1,312
የጉባኤዎች ብዛት፦410
ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት ቦታ፦ሎናቭላ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሎናቭላ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1963 የተካሄደውን “የዘላለም ምሥራች” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባ አስመልክቶ የተሰጠ ምሥክርነት
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በደልሂ ከሬድ ፎርት ውጪ ለአንድ ሱቅ በደረቴ ሲመሰከርለት