የታሸገ ምግብ ምሥክርነት ሰጠ
ባለፈው ጥር ኮቤ ተብላ በምትጠራው የጃፓን ከተማ ከደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ባሉት ቀናት ጉዳት በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምግብ ለማግኘት ተቸግረው ነበር። መሬት መንቀጥቀጡ ከደረሰ ሳምንታት ካለፉ በኋላ እንኳ ሱቆች አልተከፈቱም ነበር። ያለ ጋዝና ውኃ ምግብ ማብሰል ስለማይቻል ብዙዎች በቂ ምግብ አላገኙም ነበር። ቢሆንም በዚያ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በጓደኞቻቸው ደግነት የተሞላበት እርዳታ የተነሳ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ አላጡም። ከመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ ለነበሩት ሁለት ወይም ሦስት ቀናት በአቅራቢያው የሚገኙ ጉባኤዎች የሩዝ ዳቦ ላኩ። ወዲያውኑ አሳቢ የሆኑ ጓደኞቻቸው እንደ አትክልት፣ ዓሳ፣ ሥጋና ሰላጣ ያሉ ተመጣጣኝ ምግብ የያዙ የታሸጉ ምግቦች ላኩ። ብዙዎች ከታሸጉት ምግቦች ጋር አያይዘው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ያላቸውን አሳቢነት የሚያሳዩ ማስታወሻዎች ጽፈው ነበር። ምግቡን የተቀበሉ ወንድሞች ማስታወሻውን ሲያነቡ ዕንባቸውን መቆጣጠር ስለሚያቅታቸው እያንዳንዱን ምግብ “ከዕንባ ጋር” ይበሉ እንደነበር ተናግረዋል። በእርግጥም ከምግቦቹ ጋር ፍቅራቸውንም አሽገው ልከውላቸው ነበር።
የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ምግብ በችግር ላይ ከነበሩ ሌሎች ሰዎች ጋር ተካፍለዋል። አንድ የይሖዋ ምሥክር የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ የሥራ ባልደረባው ጋር በመኪና እየተጓዘ ሳለ ምሳውን ይበላ ነበር። ይህ ወንድም ከይሖዋ ምሥክሮች የእርዳታ ዝግጅት ካገኛቸው የታሸጉ ምግቦች አንዱን አብሮት ለነበረው ሰው አካፈለው።
“ይህንን የታሸገ ምሳ ከየት ነው የገዛኸው?” በማለት የሥራ ባልደረባው ጠየቀው። ወንድም የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን የእርዳታ ሥራ ገለጸለት። “አትክልት ከበላሁ ብዙ ቀናት ሆኖኛል። ጥቂት አስተርፌ ወደ ቤት እወስድና ለቤተሰቤ እሰጣቸዋለሁ” በማለት አመስጋኝነቱን ገለጸና የተሰጠውን የታሸገ ሰላጣ ወደ ቤቱ ይዞ ሄደ።
ሰውዬው ለሦስተኛ ጊዜ ምግብ ሲወስድ ለወንድም 3,000 የን (ወደ 35 የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር) ሰጠውና እንዲህ አለ፦ “ይህ ገንዘብ ለወሰድኩት ምግብ ክፍያ ሳይሆን የምትሠሯቸውን ሥራዎች በደንብ ስላወቅሁ ነው። እባክህ ለሥራችሁ ያደረግሁትን የገንዘብ እርዳታ ተቀበለኝ። ምሳህን ስላካፈልከኝ አመሰግንሃለሁ። ጓደኞችህ በአጠቃላይ ጥሩ ሰዎች ናቸው።”