‘መንፈሳቸው ለተሰበረ’ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ
በዛሬው ጊዜ የሰይጣን ዓለም “ማንኛውም ዓይነት የሥነ ምግባር ስሜት ጠፍቶበታል።” (ኤፌሶን 4:19 አዓት ፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ምንዝርና ዝሙት በየትኛውም ቦታ የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። በብዙ አገሮች ውስጥ 50 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑት ጋብቻዎች በፍቺ ያከትማሉ። ግብረ ሰዶም በሰፊው ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። አስገድዶ ስለ መድፈር ማለትም በኃይል ተጠቅሞ ስለሚፈጸም የጾታ ግንኙነት በተደጋጋሚ ጊዜያት በዜና ማሰራጫዎች ሲነገር ይሰማል። የብልግና ጽሑፎችና ፊልሞች በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር የሚዛቅባቸው የንግድ ዓይነቶች ሆነዋል።—ሮሜ 1:26, 27
በጣም አስጸያፊ ከሆኑት የብልግና ድርጊቶች መካከል ምንም የማያውቁ ልጆችን በጾታ ማስነወር ይገኝበታል። የሰይጣን ዓለም ጥበብ ‘እንስሳዊና አጋንንታዊ’ እንደ ሆነ ሁሉ ልጆችን በጾታ ማስነወርም እንደዚሁ ነው። (ያዕቆብ 3:15) ታይም መጽሔት እንደዘገበው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ “በየዓመቱ አስተማሪዎችና ዶክተሮች የሚፈጽሟቸው ከ400,000 በላይ የሆኑ በማስረጃ ሊረጋገጡ የሚችሉ የጾታ ጥቃት ሪፖርቶች በባለ ሥልጣናት ይመዘገባሉ።” የዚህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት ሰለባዎች ወደ አዋቂነት ዕድሜ ሲደርሱም እንኳ ባልሻሩት የስሜት ቁስሎች ይሠቃያሉ። እነዚህ ጥቃቶች በእርግጥም የስሜት ቁስል የሚያስከትሉ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የአንድ ሰው መንፈስ [የአእምሮ ዝንባሌው፣ ውስጣዊ ስሜቶቹና አስተሳሰቡ] ሥቃዩን እንዲችል ይረዳዋል፤ የተሰበረን [የተጎዳን፣ የተጨነቀን] መንፈስ ግን ማን ይቋቋማል?” ይላል።—ምሳሌ 18:14 አዓት
የአምላክ መንግሥት ምሥራች ‘ቅስማቸው የተሰበረውን’ እና ‘በሐዘን መንፈስ’ የተዋጡትን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይማርካል። (ኢሳይያስ 61:1–4) “የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” ለሚለው ጥሪ ብዙ የስሜት ሥቃይ ያለባቸው ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው ምንም አያስደንቅም። (ራእይ 22:17) እነዚህ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መጽናናትን ሊያገኙ ይችላሉ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሥቃይ የተረሳ ነገር እንደሚሆን መማራቸው ያስደስታቸዋል። (ኢሳይያስ 65:17) እስከዚያው ድረስ ግን ‘እንዲጽናኑ’ እና ቁስላቸው ‘እንዲጠግ’ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። ጳውሎስ “የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል ተናገሯቸው፣ ደካሞችን እርዷቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ” ሲል ክርስቲያኖችን መምከሩ ተገቢ ነው።—1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት
“የማይፈለጉ ትዝታዎች”
አንዳንዶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሌሎች በቀላሉ ሊረዷቸው ባልቻሏቸው ችግሮች ሳቢያ ‘ቅስማቸው ተሰብሯል።’ እነዚህ በልጅነታቸው በጾታ እንደ ተነወሩ የሚናገሩ ሰዎች በአእምሯቸው ውስጥ “የማይፈለጉ ትዝታዎች” የተቀረጹባቸው ትላልቅ ሰዎች ናቸው።a አንዳንዶች ቀደም ሲል ያጋጠማቸው ነገር ወይም በልጅነታቸው ያስነወራቸው በጉልምስና ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሰው (ወይም በጉልምስና ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች) “ትዝታ” በአእምሯቸው ውስጥ የተወው የስሜት ጠባሳ አንድ ቀን በድንገት ቁልጭ ብሎ እስኪታያቸው ድረስ ይህ አስነዋሪ ነገር በእነሱ ላይ ስለ መፈጸሙ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉ ሰዎች መካከል እንዲህ ዓይነቱ የሚረብሽ ሐሳብ የሚመጣበት ሰው ይኖራልን? በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ይህ ሁኔታ ያጋጥማል። እነዚህ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ከባድ የመንፈስ ጭንቀት፣ ንዴት፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ሐፍረት ወይም ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል። እንደ ዳዊት አምላክ እንደተዋቸው ሊሰማቸውና “አቤቱ፣ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሰወራለህ?” ብለው ሊጮኹ ይችላሉ።—መዝሙር 10:1
እነዚህ “ትዝታዎች” ያሏቸውን አያሌ ገጽታዎች የአእምሮ ሕክምና ባለ ሙያዎች በሚገባ ሊረዷቸው አልቻሉም። ቢሆንም እነዚህ “ትዝታዎች” ለአምላክ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖችን መንፈሳዊነት ሊነኩ ይችላሉ። ስለዚህ እነዚህን “ትዝታዎች” በመቋቋም ረገድ መመሪያ ለማግኘት በትምክህት ወደ አምላክ ቃል ዘወር ልንል እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “በነገር ሁሉ ማስተዋልን” ይሰጣል። (2 ጢሞቴዎስ 2:7፤ 3:16) በተጨማሪም ‘በመከራችን ሁሉ በሚያጽናናን የርኅራኄ አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ በሆነው በይሖዋ ላይ እምነት መጣል በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ይረዳናል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
ድርጊቱ በእርግጥ ተፈጽሟልን?
በዓለም ውስጥ ስለ እነዚህ “ትዝታዎች” ምንነትና ምን ያህል በእርግጥ የተፈጸሙ ነገሮችን እንደሚያሳዩ ብዙ ውዝግብ አለ። የይሖዋ ምሥክሮች ‘የዚህ ዓለም ክፍል ስላልሆኑ’ በዚህ ውዝግብ ውስጥ አይገቡም። (ዮሐንስ 17:16) አንዳንድ ጽሑፎች እንደዘገቡት አንዳንድ ጊዜ እነዚህ “ትዝታዎች” በትክክል የተፈጸሙ ነገሮች ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል የኢንሹራንስ ወኪል የሆነው ፍራንክ ፊትስፓትሪክ አንድ ቄስ እንዳስነወረው “ካስታወሰ” በኋላ ሌሎች ወደ መቶ የሚጠጉ ሰዎች በዚሁ ቄስ ተነውረው እንደ ነበረ ለመግለጽ መጥተዋል። ቄሱ የማስነወር ድርጊቱን መፈጸሙን እንዳመነ ተገልጿል።
ሆኖም ብዙ ግለሰቦች “ትዝታዎቻቸው” እውነተኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደተሳናቸው ሊስተዋል ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የተፈጸመባቸው አንዳንድ ሰዎች በሩካቤ ሥጋ ያስነወሯቸው ሰዎች ወይም ድርጊቱ የተፈጸመበት የተወሰነ ቦታ ቁልጭ ብሎ ይታያቸዋል። ሆኖም በሌላ ጊዜ እውነተኛ የሆነ ተቃራኒ ማስረጃ ሲገኝ በዝርዝር “ያስታወሷቸው” ነገሮች እውነት ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ ይሆናል።
ጥበቃ ማግኘት
ሆኖም በእነዚህ “ትዝታዎች” ሳቢያ “መንፈሳቸው የተሰበሩትን” ሰዎች ማጽናናት የሚቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሰጠውን ምሳሌ አስታውስ። አንድ ሰው ወንበዴዎች አግኝተውት ደበደቡትና ንብረቱን ዘረፉት። አንድ ሳምራዊ ሰው በዚያ መንገድ ሲያልፍ ይህን ቁስለኛ አየውና አዘነለት። ምን አደረገለት? ስለ ድብደባው እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ ለማወቅ አጥብቆ ጠየቀውን? ወይስ ሳምራዊው ወንበዴዎቹ እንዴት ያሉ እንደነበሩ ከተረዳ በኋላ ጊዜ ሳያባክን ተከታተላቸው? እንደዚህ አላደረገም። ሰውዬው ተጎድቷል! ስለዚህ ሳምራዊው ቀስ ብሎ ቁስሎቹን በጨርቅ አሰረለትና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ሊያገግም ወደሚችልበት በአቅራቢያው ወደሚገኘው አንድ የእንግዶች ማደሪያ ወሰደው።—ሉቃስ 10:30–37
በልጅነት ጊዜ የተፈጸመ የጾታ መነወር በሚያስከትለው “የተሰበረ መንፈስ” እና በአካል ላይ በደረሰ ጉዳት መካከል ልዩነት እንዳለ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱም ቢሆኑ ከፍተኛ ሥቃይ ያስከትላሉ። ስለዚህ ሳምራዊው ሰው ለተጎዳው አይሁዳዊ ያደረገው ነገር አንድ መሰል ክርስቲያን ጉዳት ሲደርስበት እንዴት መርዳት እንደሚቻል ያሳያል። ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ፍቅራዊ ማጽናኛ መለገስና እንዲያገግም መርዳት ነው።
ዲያብሎስ በታማኙ ኢዮብ ላይ ጥቃቱን የሰነዘረው ስሜታዊ ወይም አካላዊ ሥቃይ ፍጹም አቋሙን እንዲያጎድፍ ያደርገዋል ብሎ አስቦ ሳይሆን አይቀርም። (ኢዮብ 1:11፤ 2:5) ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሰይጣን ብዙውን ጊዜ ራሱ በቀጥታ የሚያመጣውንም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያደርሰውን መከራ የአምላክ አገልጋዮችን እምነት ለማዳከም ሊጠቀምበት ሲሞክር ቆይቷል። (ከ2 ቆሮንቶስ 12:7–9 ጋር አወዳድር።) ዲያብሎስ በአሁኑ ጊዜ በልጅነት ወቅት የሚፈጸምን የጾታ መነወር እና ይህ ሁኔታ የደረሰባቸው (ወይም ይህ ነገር እንደደረሰባቸው በሚገልጹ “ትዝታዎች” የሚሠቃዩ) ትልልቅ ሰዎች የሚፈጠርባቸውን “በሐዘን የተደቆሰ መንፈስ” ተጠቅሞ የክርስቲያኖችን እምነት ለማዳከም እንደሚሞክር ልንጠራጠር እንችላለንን? ኢየሱስ ከሰይጣን ጥቃት በተሰነዘረበት ወቅት እንዳደረገው ሁሉ ሥቃይ እየደረሰበት በቆራጥነት ፍጹም አቋሙን የሚጠብቅ ክርስቲያንም “ሂድ አንተ ሰይጣን” ማለቱ ነው።—ማቴዎስ 4:10
መንፈሳዊ ጥንካሬያችሁን ጠብቁ
“ታማኝና ልባም ባሪያ” በልጅነት ወቅት በጾታ መነወር የሚያስከትለውን መንፈሳዊና ስሜታዊ ጉዳት ለመቋቋም የሚረዳ ትምህርት ሲያወጣ ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:45–47) በተሞክሮ እንደታየው ጉዳቱ የደረሰበት ሰው “የእግዚአብሔርን የጦር መሣሪያ በሙሉ” ለብሶ “በጌታና በእርሱ ታላቅ ኃይል” ከታመነ እርዳታ ሊያገኝ ይችላል። (ኤፌሶን 6:10–17 የ1980 ትርጉም) ይህ የጦር መሣሪያ ሰይጣን ቀንደኛ ጠላት እንደሆነ የሚያጋልጠውንና እሱና ደጋፊዎቹ የሚሠሩበትን ጨለማ የሚገላልጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ “እውነት” ይጨምራል። (ዮሐንስ 3:19) ከዚህም በተጨማሪ “የጽድቅ ጥሩር” አለ። ችግሩ የደረሰበት ግለሰብ የጽድቅ ደረጃዎችን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ራሳቸውን ለመጉዳት ወይም የጾታ ብልግና ለመፈጸም ጠንካራ ምኞት ያድርባቸዋል። ይህን ምኞት በተቋቋሙ መጠን ድል ይቀዳጃሉ!
ከዚህም ሌላ ይህ መንፈሳዊ የጦር መሣሪያ “የሰላምን ወንጌል” ይጨምራል። ለሌሎች ስለ ይሖዋ ዓላማዎች መናገር ተናጋሪውንም ሆነ አዳማጩን ያጠነክራል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ‘መንፈስህ በመሰበሩ’ ምክንያት ስለ ምሥራቹ መናገር ካስቸገረህ አንድ ክርስቲያን ይህን በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ ሲሠራ አብረኸው ለማገልገል ጥረት አድርግ። ከዚህም በተጨማሪ “የእምነት ጋሻ” መያዝን አትዘንጋ። ይሖዋ እንደሚወድህና አሁን ያጣኸውን ነገር ሁሉ መልሰህ እንድታገኝ እንደሚያደርግ እምነት ይኑርህ። ኢየሱስም እንደሚወድህና ይህን ፍቅር ለአንተ በመሞት እንዳሳየ አንዳች አትጠራጠር። (ዮሐንስ 3:16) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ እንደማያስብ ሰይጣን ሁልጊዜ በሐሰት ይናገራል። ይህም እሱ ከሚናገራቸው ከባድና ተንኮል የተሞላባቸው ውሸቶች አንዱ ብቻ ነው።—ዮሐንስ 8:44፤ ከኢዮብ 4:1, 15–18፤ 42:10–15 ጋር አወዳድር።
ልብህ መደቆሱ ይሖዋ ለአንተ እንደሚያስብልህ እንዳታምን ካደረገህ እሱ ለእኛ እንደሚያስብልን አጥብቀው ከሚያምኑ ሌሎች ሰዎች ጋር መቀራረብ ሊረዳህ ይችላል። (መዝሙር 119:107, 111፤ ምሳሌ 18:1፤ ዕብራውያን 10:23–25) ሰይጣን የሕይወትን ሽልማት እንዲነጥቅህ አትፍቀድለት። “የመዳን ራስ ቁር” የጦር መሣሪያው ክፍል እንደሆነ አትርሳ፤ “የመንፈስ ሰይፍ”ም እንደዚሁ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ሊቋቋመው በማይችለው በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ ዕብራውያን 4:12) ፈዋሽ ቃላቶቹ የስሜት ሥቃይን ሊያስታግሡ ይችላሉ።—ከመዝሙር 107:20 ጋር አወዳድር፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4, 5
በመጨረሻም ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬ ለማግኘት ሳታቋርጥ ጸልይ። (ሮሜ 12:12፤ ኤፌሶን 6:18) ኢየሱስ ያደረገው ልባዊ ጸሎት ከባድ የስሜት ሥቃይን እንዲቋቋም ረድቶታል። እንዲህ ዓይነቱ ጸሎት አንተንም ጭምር ሊረዳህ ይችላል። (ሉቃስ 22:41–43) መጸለይ ያስቸግርሃልን? ሌሎች ሰዎችን ከአንተ ጋር ሆነው እንዲጸልዩና ስለ አንተ እንዲጸልዩ ጠይቃቸው። (ቆላስይስ 1:3፤ ያዕቆብ 5:14) ስትጸልይ መንፈስ ቅዱስ ይረዳሃል። (ከሮሜ 8:26, 27 ጋር አወዳድር።) ከባድ የሆነ የአካል ሕመም ሙሉ በሙሉ እንደማይፈወስ ሁሉ አንዳንድ ከባድ ስሜታዊ ቁስሎችም በዚህ ሥርዓት ውስጥ ላይፈወሱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በይሖዋ እርዳታ ልንጸና እንችላለን፤ መጽናት ደግሞ በኢየሱስ ሁኔታ ላይ እንደታየው ድል ነው። (ዮሐንስ 16:33) “የሕዝብ ማኅበር ሁላችሁ፣ በእርሱ [“በይሖዋ” አዓት] ታመኑ፣ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር ረዳታችን ነው።”—መዝሙር 62:8
አስነውሯል ስለ ተባለው ሰው ምን ሊባል ይቻላል?
አንድን ልጅ በጾታ ያስነወረ ሰው አስገድዶ እንደ ደፈረ ሰው ተደርጎ መታየት ይኖርበታል። የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆነ ግለሰብ ያስነወረውን ሰው የመክሰስ መብት አለው። ያም ሆኖ ግን ጉዳዩ “በማይፈለጉ ትዝታዎች” ላይ ብቻ የተመሠረተ ከሆነ ክሱ በችኮላ መደረግ የለበትም። በዚህ ረገድ ጉዳቱ ለደረሰበት ሰው በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር በጥቂቱም ቢሆን የስሜት ሚዛኑን ለመጠበቅ መቻሉ ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ትዝታዎቹን” ለማመዛዘንና ምን ማድረግ እንዳለበት ለመወሰን የተሻለ ሁኔታ ሊኖረው ይችላል።
የዶናን ሁኔታ እንውሰድ። የምግብ ፍላጎቷ ተዛብቷል ተብሎ ወደ አንድ አማካሪ ሄደች። ይህ ጥርጣሬ እንዲያድርባት ካደረጉት ነገሮች አንዱ ሳይሆን አይቀርም። ብዙም ሳይቆይ አባቷን የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንደፈጸመባት ትከሰውና ፍርድ ቤት ይቀርባል። ዳኞች ስምምነት ላይ ሊደርሱ ባለመቻላቸው አባትየው ባይታሰርም ለፍርድ ቤቱ ወጪ የሆነውን 100,000 ዶላር እንዲከፍል ተፈረደበት። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ዶና የማስነወሩ ድርጊት ተፈጽሟል ብላ እንደማታምን ለወላጆቿ ነገረቻቸው።
ሰሎሞን “ለክርክር [“ለክስ” አዓት] ፈጥነህ አትውጣ” በማለት በጥበብ ተናግሯል። (ምሳሌ 25:8) ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለው ሰው አሁንም ልጆችን እንደሚያስነውር ለመጠርጠር የሚያስችል በቂ ምክንያት ካለ ማስጠንቀቂያ መስጠት ሊያስፈልግ ይችላል። በዚህ ረገድ የጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ ሊሰጡ ይችላሉ። አለበለዚያ አትቸኩል። የኋላ ኋላ ጉዳዩን ለመተው ትፈልግ ይሆናል። ሆኖም ድርጊቱን ፈጽሟል ከተባለው ሰው ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ከፈለግህ (በመጀመሪያ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ሁኔታዎች ምን እንደሚሰማህ በጥንቃቄ ካመዛዘንክ በኋላ) ይህን ለማድረግ መብት አለህ።
እንዲህ ዓይነት “ትዝታዎች” ያሉበት ሰው ነገሩን ለመተው በሚሞክርበት ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ግለሰብ በየዕለቱ የሚያየው አንድ ሰው በጾታ ሲያስነውረው በዓይነ ሕሊናው ቁልጭ ብሎ ሊታየው ይችላል። ይህን ሁኔታ ለመቋቋም አንድ የተወሰነ ደንብ ማውጣት አይቻልም። “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።” (ገላትያ 6:5) አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ዘመዱ ወይም የቅርብ የቤተሰብ አባሉ ይህን ድርጊት እንደፈጸመበት ሊሰማው ይችላል። ድርጊቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረውን ሰው ለይቶ በማወቅ ረገድ “የማይፈለጉ ትዝታዎች” ምን ያህል አጠያያቂ እንደሆኑ አስታውስ። በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች ጉዳዩ በትክክል እስካልተረጋገጠ ድረስ ቢያንስ አልፎ አልፎ በመጠየቅ፣ በደብዳቤ ወይም በስልክ ከቤተሰቡ ጋር ያለህን ግንኙነት መቀጠልህ ቅዱስ ጽሑፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ጥረት እያደረክ እንደ ሆነ ያሳያል።—ከኤፌሶን 6:1–3 ጋር አወዳድር።
ሽማግሌዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
ሽማግሌዎች በልጅነት ወቅት በተከሰተ የጾታ መነወር ትውስታዎች ወይም “በማይፈለጉ ትዝታዎች” የሚሠቃይ አንድ የጉባኤ አባል ሲያጋጥማቸው ብዙውን ጊዜ ሁለት ሆነው እንዲረዱት ይመደባሉ። እነዚህ ሽማግሌዎች ጉዳቱ የደረሰበት ግለሰብ ለጊዜው ስሜታዊ ጭንቀቱን ለመቋቋም በመጣሩ ተግባር ላይ እንዲያተኩር በደግነት ሊያበረታቱት ይገባል። በማስነወሩ ድርጊት ተካፍለዋል ተብለው “የሚታወሱ” ሰዎች ስም በምሥጢር መያዝ ይኖርበታል።
የሽማግሌዎች ተቀዳሚ ኃላፊነት እንደ እረኛ ሆኖ ማገልገል ነው። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3) በተለይም “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን ትዕግሥትን” ለመልበስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ቆላስይስ 3:12) በደግነት ካዳመጧቸው በኋላ ከቅዱሳን ጽሑፎች የሚፈውሱ ቃላትን በመጥቀስ ያጽናኗቸው። (ምሳሌ 12:18) ሥቃይ የሚያስከትሉ “ትዝታዎች” ያጋጠማቸው አንዳንድ ሰዎች ሽማግሌዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ዘወትር ስለጠየቋቸው፣ እንዲያውም ስልክ ስለደወሉላቸው እንኳ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። እንደዚህ ያሉትን ግንኙነቶች ለማድረግ የግድ ብዙ ጊዜ ማጥፋት ባያስፈልግም ይህን ማድረጉ የይሖዋ ድርጅት ያላትን አሳቢነት ያሳያል። ጉዳቱ የደረሰበት ግለሰብ ክርስቲያን ወንድሞቹ ለእሱ ልባዊ ፍቅር እንዳላቸው ሲገነዘብ በተወሰነ ደረጃ የስሜት ሚዛኑን መልሶ ሊያገኝ ይችላል።
ጉዳቱ የደረሰበት ግለሰብ ክስ ለመመሥረት ቢፈልግስ?b በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሽማግሌዎች ከማቴዎስ 18:15 ጋር በሚስማማ መንገድ ተከሳሹን ስለ ጉዳዩ በግል ማነጋገር እንዳለበት ሊመክሩት ይችላሉ። ከሳሹ ስሜቱ ስለ ተጎዳ ከሰውዬው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገር ካልቻለ ስልክ መደወል ወይም ደብዳቤ መጻፍ ይችላል። በዚህ መንገድ ተከሳሹ ረጋ ብሎ በይሖዋ ፊት ለክሱ መልስ ለመስጠት አጋጣሚ ያገኛል። ምናልባት የማስነወሩን ድርጊት እንዳልፈጸመ ማስረጃ ሊያቀርብ ይችላል። ወይም ተከሳሹ ጥፋቱን አምኖ እርቅ ሊደረግ ይችላል። ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው! ሰውዬው ከተናዘዘ ሁለቱ ሽማግሌዎች ጉዳዩን ቅዱስ ጽሑፋዊ ከሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንፃር ይይዙታል።
ክሱ የቀረበበት ሰው ከካደ ሽማግሌዎች በፍርድ ደረጃ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ለከሳሹ መግለጽ ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ ጉባኤው ተከሳሹን እንደ ንጹሕ ሰው አድርጎ መመልከቱን ይቀጥላል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ የፍርድ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች መኖር እንዳለባቸው ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 13:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:19) በርካታ ሰዎች አንድ ግለሰብ እንዳስነወራቸው “ቢያስታውሱ”ም እንኳን ሌላ ማስረጃ እስካልተገኘ ድረስ የእነዚህ ትዝታዎች ሁኔታ የፍርድ ውሳኔዎችን ለመስጠት አስተማማኝ አይሆንም። ይህ ማለት ግን እነዚህ “ትዝታዎች” እንደ ሐሰት ተደርገው (ወይም እንደ እውነት ተደርገው) ይታያሉ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ጉዳዩን በፍርድ ደረጃ ለማየት የመጽሐፍ ቅዱስን ሥርዓቶች መከተል ያስፈልጋል።
ሆኖም ተከሳሹ ጥፋቱን ቢክድም እንኳ ጥፋተኛ ቢሆንስ? “ከቅጣቱ ያመልጣልን?” በፍጹም አያመልጥም! ጥፋተኛ ወይም ንጹሕ የመሆኑ ጉዳይ ለይሖዋ ሊተው ይችላል። “የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፣ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል።” (1 ጢሞቴዎስ 5:24፤ ሮሜ 12:19፤ 14:12) የምሳሌ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የጻድቅ አለኝታ ደስታ ነው፤ የኀጥአን ተስፋ ግን ይጠፋል። ኀጥእ በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቆረጣል።” (ምሳሌ 10:28፤ 11:7) በመጨረሻ፣ ይሖዋ አምላክና ክርስቶስ ኢየሱስ ፍትሐዊ የሆነ ዘላለማዊ ፍርድ ይሰጣሉ።—1 ቆሮንቶስ 4:5
ዲያብሎስን መቃወም
ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ከባድ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሥቃይ እየደረሰባቸውም እንኳ መጽናታቸው ውስጣዊ ጥንካሬያቸውንና ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ እንዴት ያለ ማረጋገጫ ነው! በተጨማሪም እነሱ መጽናታቸው የይሖዋ መንፈስ ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያስመሰክራል።—ከ2 ቆሮንቶስ 4:7 ጋር አወዳድር።
“[ሰይጣንን] በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” በማለት ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት እንደዚህ ላሉት ሰዎች ይሠራሉ። (1 ጴጥሮስ 5:9) ይህን ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በትክክልና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሰብ እንኳ ሊያዳግት ይችላል። ይሁን እንጂ ተስፋ አትቁረጡ! በቅርቡ ሰይጣንና የተንኮል ዘዴዎቹ ይጠፋሉ። በእርግጥም “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ . . . እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአል” የሚለው ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ እንናፍቃለን።—ራእይ 21:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “የማይፈለጉ ትዝታዎች” እና ሌሎች ተመሳሳይ አገላለጾች በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ የገቡት ሁላችንም ካሉን በአብዛኛው ተመሳሳይ ከሆኑ ትዝታዎች ለመለየት ነው።
b በተጨማሪም ጉባኤው ጉዳዩን በደምብ የሚያውቀው ከሆነ በዚህ አንቀጽ ውስጥ የቀረበውን እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።