ደስታ በሌለው ዓለም ውስጥ ደስተኛ መሆን
የጥር 26, 1995 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ርዕስ አንቀጽ “ያለንበት ዘመን የሰይጣን መቶ ዘመን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም” በማለት ይጀምራል። በመቀጠልም “ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በመደብ ልዩነት የተነሳ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመጨፍጨፍ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ዝንባሌና ፍላጎት ያሳዩበት ጊዜ የለም” ብሏል።
ሰው ወደ ሞት በሚነዳባቸው የናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስረው የነበሩ ንጹሐን ሰዎች ነፃ የወጡበት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል የተለያዩ ርዕሰ አንቀጾች ከላይ እንደተገለጸው ያለ ነገር እንዲያሰፍሩ ገፋፍቷቸዋል። ቢሆንም በተለያዩ የአፍሪካና የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች አሁንም ያንን የመሰለ ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው።
የጭፍጨፋ ዘመቻ፣ የጎሳ ምንጠራ፣ የእርስ በርስ እልቂት በማለት የትኛውንም ዓይነት ስያሜ ቢሰጧቸው እነዚህ ጭፍጨፋዎች ይህ ነው የማይባል ሐዘን አስከትለዋል። ሆኖም በዚህ ምስቅልቅሉ በወጣ ዓለም ውስጥ ደስተኛ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ በ1930ዎቹ ጀርመን ውስጥ የነበረውን ሁኔታ እንመልከት።
ሚያዝያ 1935 የይሖዋ ምሥክሮች በሂትለርና እርሱ ባቋቋመው የናዚ ፓርቲ አማካኝነት ከማንኛውም የመንግሥት ሥራ ታገዱ። በተጨማሪም ምሥክሮቹ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን ስለጠበቁ ተይዘዋል፣ ታስረዋል እንዲሁም ወደ ማጎሪያ ካምፖች ተልከዋል። (ዮሐንስ 17:16) በ1936 ነሐሴ ማብቂያ ላይ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ታፈሱ። በሺህ የሚቆጠሩት ወደ ማጎሪያ ካምፖች የተላኩ ሲሆን ከሞቱት በስተቀር አብዛኞቹ እስከ 1945 እዚያው ቆይተዋል። ምሥክሮቹ በካምፖቹ ውስጥ ይደርስባቸው የነበረውን ኢሰብዓዊ ቅጣት የተወጡት እንዴት ነበር? ሁኔታው ሊያስገርም ቢችልም ደስታ በሌላቸው ሰዎች መሃል ደስተኛ ሆነው ይኖሩ ነበር።
“በጭቃ ውስጥ እንዳለ የመረማመጃ ድንጋይ”
ክርስቲን ኪንግ የተባሉ እንግሊዛዊት ታሪክ ጸሐፊ በካምፖቹ ውስጥ ለነበረች አንዲት ካቶሊክ ሴት ቃለ መጠይቅ አድርገውላት ነበር። ዶክተር ኪንግ እንዲህ አሉ፦ “ፈጽሞ የማይረሳኝ አንድ አባባል ነግራኛለች። በዚያ ውስጥ የሚፈጸመው ነገር ምን ያህል የሚዘገንን እንደነበረና ስላሳለፈችው አስከፊ ሁኔታ አንድ በአንድ ነግራኛለች፤ የይሖዋ ምሥክሮችን እንደምታውቃቸውና በጭቃ ውስጥ እንዳለ የመረማመጃ ድንጋይ እንደነበሩ ተናግራለች። በዚያ የቦካ ጭቃ ውስጥ ልክ እንደ ደረቅ ቦታ ነበሩ። ጠባቂዎች ካለፉ በኋላ ምራቃቸውን በጥላቻ የማይተፉ እነርሱ ብቻ እንደነበሩ ተናግራለች። በካምፑ ውስጥ የሚደርስባቸውን ሁሉ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅርና በተስፋ ተቋቁመው ያለፉ እንዲሁም ዓላማ እንዳላቸው የሚሰማቸው እነርሱ ብቻ ነበሩ።”
የይሖዋ ምሥክሮች ‘በጭቃ ውስጥ እንዳሉ የመረማመጃ ድንጋዮች’ ለመሆን ያስቻላቸው ምንድን ነው? በይሖዋ አምላክና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸው የማይናወጥ እምነት ነው። በዚህ የተነሳ የሂትለር ጥረት ክርስቲያናዊ ፍቅራቸውንና ደስታቸውን ሊገታው አልቻለም።
የደረሰባቸውን የእምነት ፈተና በተሳካ ሁኔታ ተወጥተው ከካምፑ በሕይወት የተረፉ ሁለት ሰዎች ከአምስት አሥርተ ዓመታት በኋላ ትዝታቸውን ሲናገሩ ተመልከት። አንደኛዋ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ለይሖዋ ያለኝን ፍቅርና ምስጋና የማሳየት ልዩ መብት እንደነበረኝ ስገነዘብ በደስታ እፈነድቃለሁ። ይህንን እንዳደርግ ያስገደደኝ የለም! ከዚህ ይልቅ አምላክን ሳይሆን ሂትለርን እንድንታዘዝ ለማድረግ በኃይል በማስፈራራት ሊያስገድዱን ይሞክሩ የነበሩት ጠላቶቻችን ነበሩ። ነገር ግን አልተሳካላቸውም! ባለኝ ጥሩ ሕሊና የተነሳ ደስታ ማግኘት የጀመርኩት አሁን ሳይሆን ገና እስር ቤት ሳለሁ ነበር።”—የ94 ዓመቷ ማሪያ ሆምባክ
ሌላኛው ምሥክር ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “በእስር ቤት ያሳለፍኳቸውን ጊዜያት ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስታውስ እርካታና ደስታ ይሰማኛል። በሂትለር ጊዜ በእስር ቤትና በማጎሪያ ካምፖች ያሳለፍኳቸው ዓመታት አስቸጋሪና በመከራ የተሞሉ ነበሩ። ሆኖም እነዚህ ዓመታት በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድታመን ስላደረጉኝ እንኳን አላመለጡኝ እላለሁ።”—የ91 ዓመቱ ዮሐንስ ኒዎቤከር።
“በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን።” የይሖዋ ምሥክሮች ደስተኛ የሆኑበት ቁልፉ ይህ ነው። በዚህ የተነሳ ደስታ በሌለው ዓለም ውስጥ ቢኖሩም ደስተኞች ናቸው። ባለፉት ወራት የተደረጉት “ደስተኛ አወዳሾች” የአውራጃ ስብሰባዎች ደስታቸውን የሚያንፀባርቁ ነበሩ። እስቲ ይህንን አስደሳች ስብሰባ በአጭሩ እንከልስ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማሪያ ሆምባክ