ዓመፅ በየትኛውም ስፍራ ተስፋፍቷል
ሹፌሩ መኪናው ውስጥ ተቀምጦ የትራፊክ መብራቱ እስኪለወጥ ድረስ በመጠባበቅ ላይ ሳለ ከየት መጣ ሳይባል በድንገት አንድ ግዙፍ ሰው እየተሳደበና እጁን ጨብጦ እያወዛወዘ ወደ እርሱ ሲመጣ ተመለከተ። ሹፈሩ ቶሎ ብሎ በሮቹን ቆላለፈና መስኮቶቹን ዘጋ። ሆኖም ግዙፉ ሰውዬ አሁንም ወደ እርሱ በመምጣት ላይ ነበር። ሰውዬው አጠገቡ ሲደርስ መኪናዋን በኃይል አነቃነቃት። በሩን ለመክፈትም ታገለ። በመጨረሻ በጣም ተበሳጭቶ የመኪናውን የፊት መስታወት በቡጢ መቶት ብትንትኑን አወጣው።
ይህ ሁኔታ ከአንድ ፊልም ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነውን? በፍጹም አይደለም! ነገሩ ጸጥታና የተረጋጋ ሁኔታ የሰፈነባት አገር ናት በምትባለው የሐዋይ ደሴት በሆነችው በኦሁ ውስጥ በተሽከርካሪዎች መጨናነቅ የተነሣ የተፈጠረ ጠብ ነበር።
ይህ ሁኔታ መከሰቱ አያስገርምም። የበር ቁልፎች፣ በመስኮቶች ላይ የሚገጠሙ የሌባ መከላከያ የብረት ዘንጎች፣ ሕንፃዎችን የሚጠብቁ የደኅንነት ሠራተኞች ሌላው ቀርቶ በአውቶቡሶች ላይ ተለጥፈው የሚታዩ “ሹፌር ገንዘብ አይዝም” የሚሉ ማስታወቂያዎች እንኳ አንድ የሚጠቁሙት ነገር አለ። ዓመፅ በየትኛውም ስፍራ እንደተስፋፋ ያሳያሉ!
በቤት ውስጥ የሚፈጸም ዓመፅ
ቤት ለረጅም ዘመናት ግለሰቦች ሰላምና ደኅንነት የሚያገኙበት ተወዳጅ ቦታ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል። ሆኖም ይህ አመለካከት በፍጥነት በመለወጥ ላይ ነው። በሕፃናት ላይ የሚፈጸመውን ግፍ፣ የትዳር ጓደኛን መደብደብንና ነፍስ ግድያን የሚጨምረው በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸመው ዓመፅ የመላው ዓለም ዜና ማሰራጫዎች ዋና ርዕስ ሆኗል።
ለምሳሌ ያህል “በብሪታንያ ቢያንስ 750,000 ልጆች በቤት ውስጥ ለሚፈጸም ዓመፅ የተጋለጡ በመሆናቸው ምክንያት በሥነ ልቦና ቀውስ ለረጅም ጊዜ ሊሠቃዩ ይችላሉ” በማለት ማንቸስተር ጋርዲያን ዊክሊ የተባለው መጽሔት ተናግሯል። ዘገባው በአንድ ጥናት ላይ የተመረኮዘ ነበር፤ “ጥያቄ ከቀረበላቸው አራት ሴቶች መካከል ሦስቱ ልጆቻቸው የዓመፅ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንደሚመለከቱና ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ልጆች ደግሞ እናቶቻቸው ሲደበደቡ እንደሚያዩ ገልጸዋል።” በተመሳሳይም ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት የተባለው መጽሔት እንክብካቤ የተነፈጋቸውና ግፍ የሚፈጸምባቸውን ሕፃናት በተመለከተ በጥናት ላይ የተመረኮዘ ምክር የሚሰጠው በአሜሪካ የሚገኘው የአማካሪዎች ቡድን “በየዓመቱ በአብዛኛው ከ4 ዓመት ዕድሜ በታች ያላቸው 2,000 የሚሆኑ ልጆች በወላጆች ወይም በሞግዚቶች ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ምክንያት ይሞታሉ” ሲል ገምቷል። ዘገባው ይህ ቁጥር በትራፊክ አደጋዎች፣ ወድቀው ወይም ውኃ ውስጥ ሰጥመው ከሚሞቱት ሕፃናት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይበልጣል ይላል።
በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ የዓመፅ ድርጊቶች በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ይጨምራሉ። ይህም ከመገፍተር አንሥቶ በጥፊ መምታት፣ በእርግጫ መምታት፣ ማነቅ፣ መደብደብ፣ በስለት ወይም በሽጉጥ ማስፈራራት ይባስ ብሎም መግደልን ይጨምራል። በአሁኑ ጊዜ ይህ ዓይነቱ ዓመፅ በወንድየውም ሆነ በሴትየዋ ላይ ይፈጸማል። የአንድ ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው በትዳር ጓደኛሞች መካከል እንደ ተፈጸሙ ከተዘገቡት ዓመፆች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት በወንዶች ቆስቋሽነት ሲሆን በአንፃሩ አንድ አራተኛ የሚሆኑት ዓመፆች ደግሞ በሴቶች ቆስቋሽነት የተፈጸሙ ናቸው። ቀሪዎቹ ደግሞ ሁለቱም በጥፋተኝነት የሚጠየቁባቸው ግጭቶች እንደሆኑ ተደርገው ሊገለጹ ይችላሉ።
በሥራ ቦታ የሚፈጸም ዓመፅ
ሰዎች ከቤታቸው ውጪ በሥራ ቦታቸው ሥርዓት፣ አክብሮትና ትሕትና የታከለበት ባሕርይ ማየታቸው የተለመደ ነገር ነበር። አሁን ግን ይህ ሁኔታ የሚታይ አይመስልም። ለምሳሌ ያህል የአሜሪካ የፍትሕ ቢሮ ያወጣው አሃዝ እንደሚያሳየው በሥራ ቦታ በየዓመቱ 970,000 ሰዎች ከባድ ወንጀል ይፈጸምባቸዋል። ነገሩን በሌላ መንገድ ለመግለጽ ፕሮፌሽናል ሴፍቲ—ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን ሶሳይቲ ኦቭ ሴፍቲ ኢንጂነርስ የተባለው መጽሔት እንደተናገረው “ከአራት ሠራተኞች አንዱ በሥራ ቦታው በዓመፅ ድርጊት የመጠቃት አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል።”
በሥራ ቦታ የሚፈጸመውን ዓመፅ ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርገው ጸቡ በመጯጯህና በስድብ የማያበቃ መሆኑ ነው። ይኸው ዘገባ “በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ በተለይ ሠራተኞች በአሠሪዎችና በሌሎች ሠራተኞች ላይ በሚፈጽሙት የዓመፅ ድርጊት የሚገደሉት ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል” ብሏል። በ1992 ከሥራ ጋር በተያያዘ ከተከሰቱት 6 የሞት አደጋዎች መካከል አንዱ ነፍስ ግድያ ነበር፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከ2 ሴቶች መካከል አንዷ የምትሞተው በነፍስ ግድያ ነው። በአንድ ወቅት ሥርዓታማ የነበሩትን የሥራ ቦታዎች የዓመፅ ማዕበል እንዳጥለቀለቃቸው አይካድም።
በስፖርትና በመዝናኛ መስክ የሚፈጸም ዓመፅ
ሰዎች ከባድ ሥራ ከሠሩ በኋላ ለለውጥ ያህልና ለመዝናናት ስፖርትና መዝናኛዎችን ሲከታተሉ ቆይተዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን መዝናኛ ብዙ ቢልዮን ብር የሚያስገኝ ሥራ ሆኗል። መዝናኛውን የሚያቀርቡት ሰዎች ከዚህ አትራፊ ንግድ የተቻላቸውን ያህል ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት ማናቸውንም ዘዴ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም። ከእነዚህ ዘዴዎች አንዱ ደግሞ ዓመፅ ነው።
ለምሳሌ ያህል ፎርብስ የተባለ የንግድ መጽሔት እንደዘገበው አንድ የቪዲዮ ጨዋታዎች አምራች ኩባንያ ጦረኛው የባላጋራውን ጭንቅላት ሲተረክከው ተመልካቾች “ግደለው! ግደለው!” እያሉ ሲጮኹ የሚያሳይ ተወዳጅ የሆነ የጦርነት ጨዋታ አውጥቶ ነበር። ሆኖም ሌላ የቪዲዮ ጨዋታዎችን የሚያመርት ኩባንያ ደም መፋሰስ የማያሳይ ተመሳሳይ ጨዋታ አወጣ። ውጤቱ ምን ሆነ? ይበልጥ ዓመፅ የተሞላበት ጨዋታ ያወጣው ኩባንያ ከተፎካካሪው ኩባንያ በሦስት ሁለተኛ እጅ አስበልጦ ለመሸጥ ችሏል። ይህ ጨዋታ ብዙ ገንዘብ አስገኘ። እነዚህ ጨዋታዎች እቤት ውስጥ ለመታየት እንደሚችሉ ሆነው ተዘጋጅተው በገበያ ላይ መዋል ሲጀምሩ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ብቻ ኩባንያዎቹ 65 ሚልዮን ዶላር አካበቱ! የንግድ ሥራ የሚያካሂዱ ሰዎች ትርፍ የሚያስገኝላቸው ከሆነ ተጠቃሚዎችን ለመሳብ ዓመፅን መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል።
በስፖርቱ መስክ የሚፈጸመው ዓመፅ ደግሞ አንድ ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው። ብዙውን ጊዜ ተጫዋቾች በሌሎች ተጫዋቾች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት ይኩራራሉ። ለምሳሌ ያህል በ1990 በተደረገ አንድ የገና ጨዋታ ላይ ለተጫዋቾቹ 86 ጊዜ ቅጣት የተሰጠ ሲሆን ይህን ያህል ቅጣት ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው ነበር። ጨዋታው ሦስት ሰዓት ተኩል በፈጀ ብጥብጥ ተቋረጠ። የአንድ ተጫዋች የፊቱ አጥንት ተሰበረ፣ ዓይኑ ላይ ጉዳት ደረሰበት እንዲሁም ፊቱ ተሰነጠቀ። ይህ ሁሉ ዓመፅ የተፈጸመው ለምን ነበር? አንድ ተጫዋች እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “እልህና ጠብ የሞላበት ጨዋታ ተጫውተህ ካሸነፍክ በኋላ ወደ ቤትህ ስትሄድ ከቡድንህ አባሎች ጋር በስሜት በይበልጥ እንደ ተቀራረብክ ይሰማሃል። ሽኩቻው ጨዋታውን እልህ የተቀላቀለበት እንዲሆን ያደርገዋል።” በአሁኑ ጊዜ በአብዛኞቹ ስፖርቶች ዓመፅ አስፈላጊውን ውጤት ለማግኘት የሚጠቀሙበት ዘዴ ከመሆኑም በተጨማሪ ዓመፅ ራሱ ተፈላጊ ውጤት ሆኗል።
በትምህርት ቤት ውስጥ የሚፈጸም ዓመፅ
ትምህርት ቤት ብዙውን ጊዜ ወጣቶች አሳባቸውን ሁሉ እርግፍ አድርገው ትተው አእምሯቸውንና አካላቸውን ለማዳበር በሚያደርጉት ጥረት ላይ ብቻ የሚያተኩሩበት ቦታ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ዛሬ ግን ትምህርት ቤት ከአደጋ ነፃ የሆነ ቦታ አይደለም። በ1994 የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ዓመፅና ውንብድና ዋንኛ ችግር ሆኖ ከመገኘቱም በላይ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ አስከትሏል። ባለፈው ዓመት ከሁሉ የበለጠ ከፍተኛ ወጪ ያስከተለው ነገር ይህ ሆኖ ተገኝቷል። ሁኔታው ምን ያህል አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል?
በአንድ ወቅት በተካሄደ ጥናት “ትምህርት ቤት ውስጥ ወይም በትምህርት ቤት አካባቢ የዓመፅ ድርጊት ተፈጽሞብህ ያውቃልን?” የሚል ጥያቄ ከቀረበላቸው ተማሪዎች መካከል ከአራቱ አንዱ አዎን የሚል መልስ ሰጥተዋል። በተጨማሪም ከአስተማሪዎቹ መካከል ከአንድ አሥረኛ በላይ የሚሆኑት አዎን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይኸው ጥናት እንዳረጋገጠው ከተማሪዎቹ መካከል 13 በመቶ የሚሆኑት ወንዶችና ሴቶች የጦር መሣሪያ ወደ ትምህርት ቤት ይዘው ሄደው እንደሚያውቁ አምነዋል። አብዛኞቹ ይህን የሚያደርጉት ሌሎች እንዲፈሯቸው ወይም ራሳቸውን ለመጠበቅ ሲሉ እንደሆነ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አንድ የ17 ዓመት ተማሪ አስተማሪው ሽጉጡን ሊነጥቀው ሲሞክር ተኩሶ ደረቱ ላይ መትቶታል።
ዓመፅ የተለመደ ሆኗል
በአሁኑ ጊዜ ዓመፅ በየትኛውም ስፍራ እንደ ተስፋፋ የማይካድ ነው። በቤት ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትና በመዝናኛ ዓመፅ ያጋጥመናል። ብዙዎች በየዕለቱ የዓመፅ ድርጊቶችን ስለሚመለከቱ ራሳቸው የጥቃቱ ሰለባ እስኪሆኑ ድረስ ዓመፅን እንደ ተለመደ ነገር አድርገው ይመለከቱታል። በራሳቸው ላይ ሲደርስ ግን ዓመፅ የሚወገድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? በማለት ይጠይቃሉ። መልሱን ለማወቅ ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ እባክህ የሚቀጥለውን ርዕስ አንብብ።