የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የቀድሞዎቹ ባላንጣዎች አንድ ላይ ሆነው ይሖዋን ማገልገል ጀመሩ
ብራንኮ “ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ቦስኒያ ውስጥ ታጣቂ ዘብ በነበርኩበት ጊዜ ነው” በማለት ይናገራል።a
ብራንኮ ቁስለኞች በሚታከሙበት አንድ ሆስፒታል በጥበቃ ተረኝነት ላይ ነበር። ከዶክተሮቹ አንዱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና ስለነበር አንድ ቀን የሌሊት ተረኛ ሳለ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማረውን አብዛኛውን ነገር ለብራንኮ ነገረው።
ብራንኮ በዚያ ምሽት የሰማው ነገር በጣም ስለነካው የነበሩትን የጦር መሣሪያዎች አስረከበ። ይበልጥ ለመማር ስለፈለገ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ጀመረ። ብራንኮ ከጊዜ በኋላ ወደ ሌላ የአውሮፓ አገር ሄደ። እዚያም የመንግሥት አዳራሽ ፈለገና የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በዩጎዝላቪያ ቋንቋ በሚደረግበት አንድ ስብሰባ ላይ ተገኘ። እዚያም ስሎቦዳን ከሚባል ሰው ጋር ተገናኘ።
ስሎቦዳንም የመጣው ከቦስኒያ ሲሆን ብራንኮ በተካፈለበት ጦርነት ላይ በተቃራኒው ጎራ በወዶ ዘማችነት አገልግሏል። ስሎቦዳን በሰርቦች ጎን በመሆን ከክሮአቶች ጋር ተዋግቶ ነበር። ሁለቱ በተገናኙበት ጊዜ ስሎቦዳን የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ነበር። ስሎቦዳን መጽሐፍ ቅዱስ አብረው እንዲያጠኑ የቀድሞ ባላንጣው ለሆነው ለብራንኮ ግብዣ አቀረበለት። ብራንኮ በጥናቱ እየገፋ ሲሄድ ስለ ይሖዋ ብዙ ከማወቁም በላይ ለአምላክ የነበረው ፍቅር እያደገ መጣ። ይህም ሕይወቱን ለፈጣሪ እንዲወስን ገፋፋው። ጥቅምት 1993 ራሱን ለአምላክ መወሰኑን በውኃ ጥምቀት አሳየ።
ስሎቦዳን የይሖዋ ምሥክር የሆነው እንዴት ነው? ስሎቦዳን ቦስኒያ ውስጥ የሚገኘውን የጦርነት ቀጠና ከለቀቀ ትንሽ ቆየት ብሎ ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ አንዳንድ ጽሑፎችን ያነብ የነበረ ሲሆን በ1992 መጀመሪያ ላይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቱ መጥተው ሲያነጋገሩት የአምላክን ቃል ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት አደረበት። ስሎቦዳንን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናው ማን ነበር? ከቦስኒያ የመጣው ሙዮ ነው። ሙዮ ደግሞ ከልጅነቱ ጀምሮ እስላም ነበር። ከጊዜ በፊት ባላንጣዎች የነበሩት ሙዮ እና ስሎቦዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ እየገፋ ሲሄድ አንዱ የሌላውን እምነት ለማጠንከር በየዕለቱ የተወሰነ ጊዜ ያሳልፉ ነበር።
በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የሚደረገው ጦርነት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ነገር ግን ብራንኮ፣ ስሎቦዳን እና ሙዮ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ ሰባኪዎች በመሆን እያገለገሉ ናቸው። በመካከላቸው የጎሣና የዘር ግጭት ካለመኖሩም በተጨማሪ ራሳቸውን ለፈጣሪያቸው ለይሖዋ በማስገዛት ሰላማውያን ሆነው ይኖራሉ።
ነገር ግን እነዚህን ለውጦች ያስከተለው ምንድን ነው? ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር፣ መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድርገው መመልከታቸውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን እውነቶች በሕይወታቸው ለመተግበር ያላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚሉት “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም . . . ነው፣ . . . የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።”—ዕብራውያን 4:12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የብዕር ስሞች ተጠቅመናል።