የሁሉም ሰው ሰብዓዊ መብት የሚከበርበት ጊዜ ይመጣል!
“ለሰብዓዊ መብቶች መረገጥ ዋነኛው መንስዔ ምንድን ነው?” ለአንዲት የበርካታ ዓመት የሥራ ልምድ ላላቸው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የቀረበ ጥያቄ ነበር። እኚህ የሕግ ባለ ሞያ “ስግብግብነት” ሲሉ መልሰዋል። “ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ ሥልጣን መስገብገብ።” ስግብግብነት ደግሞ የሚመነጨው ከሰው አእምሮ ስለሆነ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ የሰዎች የአእምሮ ሁኔታ ነጸብራቅ ነው ማለት ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ብሔረተኝነት ነው። አገሬ ከማንም፣ ከምንም ነገር መቅደም አለበት የሚለው ፍልስፍና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ያፋፍማል። ስለዚህ ሰብዓዊ መብት ሙሉ በሙሉ ሊከበር የሚችለው ‘አስገዳጅ እርምጃዎችን የመውሰድ አቅም ያለው አንድ የዓለም መንግሥት ሲቋቋም ነው’ ብለዋል ያን ቤርካወር የተባሉት ሆላንዳዊ የሕግና የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር።
በሌላ አነጋገር ሰብዓዊ መብቶች በመላው ምድር እንዲከበሩ ከተፈለገ ቢያንስ ሁለት ነገሮች በቅድሚያ መከናወን አለባቸው። የአእምሮ ለውጥና የመንግሥት ለውጥ ያስፈልጋል። ታዲያ እነዚህ ነገሮች ይፈጸማሉ ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው?
ባለ ሁለት ፈርጅ ለውጥ
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት አሥርተ ዓመት አምስተኛ ዓመቱን ሊጀምር የተቃረበ ቢሆንም ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲካሄድ የቆየና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስተሳሰብ ለመለወጥ የቻለ ዓለም አቀፋዊና መንግሥታዊ ያልሆነ የትምህርት ፕሮግራም አለ። ይህን ትምህርት የተቀበሉ ግለሰቦች ሌሎች ሰዎችን በአክብሮት የሚይዙ ሆነዋል። ይህ በይሖዋ ምሥክሮች የሚካሄደው የትምህርት ፕሮግራም ከ230 በሚበልጡ አገሮች ይካሄዳል። የተሳካ ውጤት ያስገኘው ለምንድን ነው?
አንደኛ ነገር ይህ ምድር አቀፍ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ሰዎች ስለ ሰው ልጅ መብቶች አመጣጥና ምንጭ ያላቸውን ግንዛቤ ያሰፋላቸዋል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የሰው ልጅ ባለ መብት የሆነው የሚያስብና የሥነ ምግባር ስሜት ያለው ፍጡር ስለሆነ እንደሆነ ያመለክታል።
የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታውንና ሕሊናውን ያገኘው ከራሱ በላይ ከሆነ ምንጭ መሆን ይኖርበታል። (በገጽ 13 ላይ የሚገኘውን “የሰብዓዊ መብቶች ምንጭ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይህን ከሰው በላይ የሆነውን መለኮታዊ ምንጭ ማወቅና መቀበል ሌሎች ሰዎችን ለማክበር ይገፋፋል። ስለዚህ ሕሊናህ ስለሚያነሳሳህ ብቻ ሳይሆን በይበልጥ ለፈጣሪ ያለህ ፍቅርና አክብሮት ስለሚገፋፋህ የእሱን ፍጡሮች በክብር ትይዛለህ ማለት ነው። ይህ ዓይነቱ ባለ ሁለት ፈርጅ አቀራረብ በሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት ላይ የተመሠረተ ነው:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” እና “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:37-39) ሰብዓዊ መብቶች በቀጥታ ከአምላክ የተገኙ የአምላክ ስጦታዎች በመሆናቸው ፈጣሪን በጥልቅ የሚያከብር ሰው የሌላውን ሰው መብቶች አይጋፋም። ሰብዓዊ መብቶችን የሚዳፈር ሰው የአምላክን ስጦታ ይነጥቃል ማለት ነው።
ለውጥ የሚያመጣ ትምህርት
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም የሰብዓዊ መብቶችን ረገጣ በመቀነስ ረገድ ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል? ይህን ለመመለስ ፕሮግራሙ ያስገኘውን ውጤት ከመቃኘት የተሻለ መንገድ አይኖርም። ኢየሱስ እንዳለው “የጥበብ ጻድቅነት የሚረጋገጠው በሥራዎቹ ነው።”—ማቴዎስ 11:19 NW
በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደባባይ አንድ በጣም የታወቀ የግድግዳ ላይ ጽሑፍ አለ። “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለመድረግ ይቀጠቅጣሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም። ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይማሩም” ይላል። ተመድ ይህን በኢሳይያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ከኪንግ ጀምስ ትርጉም በመጥቀስ በርካታ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ማስወገድ የሚቻልበትን አንድ ዋነኛ መንገድ ጠቅሷል:- ጦርነት ማጥፋት። አንድ የተመድ ጽሑፍ እንዳለው ጦርነት ‘የሰብዓዊ መብቶች ጸር ነው።’
የይሖዋ ምሥክሮች የትምህርት ፕሮግራም የኢሳይያስን ቃላት በግድግዳ ላይ በመጻፍ ብቻ አልተወሰነም። አንድ እርምጃ ወደፊት ሄዷል። የኢሳይያስን ቃላት በሰዎች ልብ ውስጥ “ይጽፋል።” (ከዕብራውያን 8:10 ጋር አወዳድር።) እንዴት? ፕሮግራሙ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘር ያለውን አመለካከት በማስተማር በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን የዘርና የጎሣ ድንበር ፍቆ ያጠፋል፣ የብሔረተኝነትን አጥሮች ያፈራርሳል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ በሙሉ አንድ ዘር እንደሆነ ያስተምራል። (ሥራ 17:26) በዚህ የትምህርት ፕሮግራም የሚሳተፉ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለሰው ፊት አያዳላም፣ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ ነው’ የሚልለትን አምላክ የመምሰል ፍላጎት ያድርባቸዋል።—ኤፌሶን 5:1፤ ሥራ 10:34, 35
ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ምክንያት ‘ጦርነት የማይማሩ’ ሆነዋል። አእምሮአቸውና ልባቸው ተለውጧል። ለውጡ ደግሞ ዘለቄታ ያለው ነው። (በገጽ 14 ላይ የሚገኘውን “ሰላም የሚያስገኝ ትምህርት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ በአማካይ ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጡትን መሠረታዊ ትምህርት አጠናቅቀው ከዚህ ዓለም አቀፋዊ የሰላም ኃይል ጋር ይቀላቀላሉ።
ይህ የአእምሮ ለውጥና በዚህ ለውጥ ሳቢያ በጦርነት ለመካፈል እምቢተኛ በመሆን ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር የሚደረግ ውሳኔ ምን ያህል ጠንካራና ሥር የሰደደ ነው? በጣም ጠንካራ ነው። አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዓመታት፣ በተለይ በናዚዎች ትተዳደር በነበረችው በጀርመን የይሖዋ ምሥክሮች ለሰብዓዊ መብቶች ያላቸው አክብሮት ጥልቀትና ጥንካሬ ከባድ ፈተና ደርሶበት ነበር። ብራያን ዱን የተባሉት የታሪክ ምሁር እንዲህ ብለዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ከናዚ ሥርዓት ጋር አልተጣጣሙም። የናዚዎችን ተቃውሞ ካስነሱት ነገሮች አንዱና ዋነኛው ለፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆናቸው ነው። ማንም አማኝ የጦር መሣሪያ አያነሳም ማለት ነው።” (ዘ ቸርችስ ሪስፖንስ ቱ ዘ ሆሎኮስት) ፖል ጆንሰን ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያኒቲ በተባለው መጽሐፋቸው “የውትድርና አገልግሎት አንሰጥም በማለታቸው ምክንያት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው . . . ወይም ወደ ዳካው የማጎሪያ ካምፕ ወይም ወደ አእምሮ በሽተኞች መታጎሪያ የተጣሉ በርካታ ናቸው” ብለዋል። እነዚህ ምሥክሮች በአቋማቸው የጸኑ ቢሆንም የማህበረሰብ ጥናት ምሁር የሆኑት አና ፓቨልሽንስካ “በፍርሐት በተንቀጠቀጠ ብሔር እቅፍ ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ የተቃውሞ ደሴቶች ነበሩ” ብለዋቸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ሰዎች ይህን የመሰለ አቋም ቢይዙና ‘ጦርነት ለመማር እምቢተኛ ቢሆኑ’ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ እንዴት ባለ ከፍተኛ መጠን ሊቀንስ እንደሚችል አስብ!
የዓለም መንግሥት—‘ተምኔታዊ ነው’?
አንዲት የተመድ ሠራተኛ ‘የሰዎችን አእምሮ መለወጥ ከባድ ሥራ ሲሆን የዓለም መንግሥት ማቋቋም ግን ተምኔታዊ ነው’ ብለዋል። በእርግጥም ብሔራት የየራሳቸውን ሉዓላዊነት ለተመድ ወይም ለማንኛውም ሌላ ድርጅት አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው የዚህን አባባል ትክክለኛነት ያሳያል። ይሁን እንጂ አንድ የዓለም መንግሥት ማስፈለጉን የማይቀበሉ ሁሉ ፕሮፌሰር ቤርካወር እንዳሉት “የዓለምን ችግሮች ለመፍታት የሚቻልባቸውን ሌሎች መንገዶች የመጠቆም የሞራል ግዴታ አለባቸው። አማራጭ መፍትሔዎች ግን የሉም።” ከሰዎች ሊገኙ የሚችሉትን መፍትሔዎች ማለታቸው ነው። ይሁን እንጂ ከሰው የበለጠ ኃይል ካለው ምንጭ የሚመጣ መፍትሔ አለ። ይህ መፍትሔ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለሰብዓዊ መብቶች መሠረት የሆኑት ባሕርያት ምንጭ ፈጣሪ መሆኑን እንደሚያመለክት ሁሉ እነዚህን መብቶች የሚያስከብረው የዓለም መንግሥት ምንጭም ይኸው ፈጣሪ እንደሆነ ይነግረናል። ይህ ሰማያዊ መንግሥት የማይታይ ቢሆንም እውን የሆነ መንግሥት ነው። እንዲያውም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገብቷቸውም ሆነ ሳይገባቸው “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው በተለምዶ የጌታ ጸሎት የሚባለውን ጸሎት በሚጸልዩበት ጊዜ ይህ የዓለም መንግሥት እንዲመጣ መጸለያቸው ነው። (ማቴዎስ 6:10) የዚህ ንጉሣዊ መንግሥት መሪ እንዲሆን አምላክ የሾመው የሰላም መስፍን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።—ኢሳይያስ 9:6
ይህ የዓለም መንግሥት ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ጦርነትን ለዘላለም በማጥፋት እውነተኛ የሆነ ምድር አቀፍና ዘላቂነት ያለው ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር ባሕል እንዲፈጠር ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “[ፈጣሪ] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፣ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቆርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል” ሲል ተንብዮአል።—መዝሙር 46:9
ይህ በመላው ምድር ላይ የሚፈጸመው መቼ ነው? የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ይሰጣል። ከዚህ ፕሮግራም ጋር እንድትተዋወቅ እናበረታታሃለን።a የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ የሚያሳስብህ ሰው ከሆንክ በፕሮግራሙ መደሰትህ አይቀርም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለግህ ከዚህ መጽሔት አዘጋጆች ወይም በአካባቢህ ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት ለማድረግ ሞክር። ፕሮግራሙ የሚሰጠው አለምንም ክፍያ ነው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሰብዓዊ መብቶች ምንጭ
የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 1 “ሁሉም ሰብዓዊ ፍጥረታት ነጻ ሆነው የተወለዱ ሲሆን በክብርና በመብት እኩል ናቸው” ይላል። ስለዚህ ሰብዓዊ መብት በአንድ ወንዝ ዳርቻዎች ላሉ ተክሎች በሙሉ እንደሚዳረስ ውኃ ከወላጆች ወደ ልጆች የሚተላለፍ በመወለድ ብቻ የሚገኝ መብት ነው ማለት ነው። ታዲያ ይህ የሰብዓዊ መብቶች ወንዝ የመነጨው ከየት ነው?
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እንደሚለው ሰብዓውያን ፍጥረታት የመብቶች ባለቤት የሆኑት “የማሰብ ችሎታና ሕሊና የተሰጣቸው” ስለሆኑ ነው። አንድ የተመድ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ሰው የማሰብ ችሎታና የሥነ ምግባር ስሜት ያለው ፍጡር በመሆኑ በምድር ላይ ከሚኖሩት ፍጥረታት በሙሉ የተለየ ነው፤ በዚህም ምክንያት ለሌሎች ፍጥረታት ያልተሰጡ መብቶችና ነጻነቶች ባለቤት ነው።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ስለዚህ የሰብዓዊ መብቶች ባለቤት ለመሆን መሠረቱ የማሰብ ችሎታና የሕሊና ባለቤት መሆን ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታና የሕሊናው ምንጭ የሰብዓዊ መብቶችም ምንጭ ነው ማለት ነው።
በስነ ሕይወታዊ አዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ለሚያምኑ የሰብዓዊ መብት አራማጆች ሰብዓዊ መብቶች ከማሰብ ችሎታና ከሕሊና ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አላቸው የሚለው አባባል መልስ የማይገኝለት ጥያቄ ይደቅንባቸዋል። የአዝጋሚ ለውጥ ንድፈ ሐሳብን የሚደግፈው ላይፍ አሴንዲንግ የተባለ መጽሐፍ “አንድ ሂደት [አዝጋሚ ለውጥ] . . . ውበትንና እውነትን እንደ ማፍቀር፣ እንደ ርኅራኄና እንደ ነጻነት ያሉትን ባሕርያት ከሁሉ በላይ ደግሞ በጣም ጥልቅ የሆነውን የሰብዓዊነት መንፈስ እንዴት ሊያስገኝ ይችላል ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ በጣም ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ እንወድቃለን” ይላል። በእርግጥም ትክክለኛ አባባል ነው። የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታና ሕሊና፣ ራሳቸው የማሰብ ችሎታም ሆነ ሕሊና ከሌላቸው ቅድመ አያቶች የተገኘ ነው ማለት ውኃ ከሌለው ጉድጓድ ትልቅ ወንዝ ፈለቀ የማለት ያህል ነው።
የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታና ሕሊና ከሰብዓዊ ፍጥረታት ካነሱ ምንጮች ሊገኙ የማይችሉ በመሆናቸው ከሰው ልጅ ከሚበልጥ ምንጭ የተገኙ መሆን አለባቸው ማለት ነው። ከሰብዓዊ መብቶች ጋር ዝምድና ያላቸው ባሕርያት ማለትም የማሰብ ችሎታና የሕሊና ባለቤት የሆነ ምድራዊ ፍጡር ሰው ብቻ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው በአምላክ “መልክ” የተፈጠሩት የሰው ልጆች ብቻ በመሆናቸው እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። (ዘፍጥረት 1:27) ስለዚህም ሂውማን ራይትስ፣ ኢሴይስ ኦን ጀስቲፊኬይሽን ኤንድ አፕሊኬይሽንስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው የሰው ልጆች የሞራል መብቶች ሊኖሯቸው የሚገባው ለምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ የምናገኘው አጥጋቢ መልስ “በተፈጥሮአቸው ያገኙት ዋጋ ወይም ክብር ስላላቸው፣ ወይም . . . የአምላክ ልጆች በመሆናቸው ነው” የሚል ነው።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ሰላም የሚያስገኝ ትምህርት
ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ የቦልካን አገሮች በጦርነት ይታመሱ በነበረበት ጊዜ ብራንኮ በክሮአቶች ይተዳደር በነበረው የቦስንያ ክፍል በአንድ ክሊኒክ ጥበቃ ላይ ተመድቦ የሚሠራ ታጣቂ ነበር።b በዚያ ክሊኒክ የሚሠራ አንድ ዶክተር መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠና ነበርና አንድ ቀን ምሽት ስለተማራቸው ነገሮች ለብራንኮ ይነግረዋል። ብራንኮ የሰማው ነገር የጦር ትጥቁን እንዲፈታ ገፋፋው። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ብራንኮ ወደ ሌላ የአውሮፓ አገር ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚያም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ከተገኘ በኋላ ከስሎቦዳን ጋር ተገናኘ።
ስሎቦዳንም ከቦስንያ የመጣ ሰው ነው። ብራንኮ ይዋጋ ከነበረበት ጦርነት በተቃራኒው ወገን ተሰልፎ ይዋጋ ነበር። ስሎቦዳን ከሰርቦች ጎን ተሰልፎ ክሮአቶችን ይወጋ ነበር። ሁለቱ ሰዎች በተገናኙበት ወቅት ስሎቦዳን የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ስለነበር የቀድሞ ጠላቱን ብራንኮን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ጠየቀው። ጥናቱ እየቀጠለ በሄደ መጠን ብራንኮ ለፈጣሪው ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወሰነ።c
ስሎቦዳን ራሱ የይሖዋ ምሥክር ሊሆን የቻለው የቀድሞ ጠላቱ በሰጠው እርዳታ ነው። እንዴት? ስሎቦዳን በቦስንያ ከነበረው የጦርነት ቀጠና ከወጣ በኋላ ሙዮ የሚባል ሰው ያነጋግረዋል። ሙዮም ከቦስንያ የመጣ ሰው ቢሆንም ከስሎቦዳን በጣም የተለየ ሃይማኖት የነበረው ሰው ነበር። አሁን ግን የይሖዋ ምሥክር ሆኗል። በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ ሰዎች ቢሆኑም ስሎቦዳን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ሙዮ ያቀረበለትን ጥያቄ ተቀበለ። በኋላም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ያስቻለውን እርምጃ ወሰደ።
እነዚህ ሰዎች በመካከላቸው የነበረውን ሥር የሰደደ የጎሣ ጥላቻ አስወግደው ከጠላትነት ወደ ወዳጅነት እንዲሸጋገሩ ያደረጋቸው ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው አማካኝነት ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር አሳድገዋል። ከዚያም በኋላ ‘እርስ በርሳቸው የሚዋደዱበትን መንገድ አምላክ እንዲያስተምራቸው ፈቅደዋል።’ (1 ተሰሎንቄ 4:9) ፕሮፌሰር ቮይቼክ ሞጄሌስኪ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በአጠቃላይ እንደተናገሩት “ሰላማዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ያስቻለው ቁልፍ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን መሠረታዊ ሥርዓቶች አሁኑኑ ሥራ ላይ ለማዋል መወሰናቸው ነው።”
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b በዚህ ሣጥን ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች በሙሉ የተለወጡ ናቸው።
c ብራንኮ በመጀመሪያ አነጋግሮት የነበረው ዶክተር የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ከጊዜ በኋላ ሲሰማ ተደስቷል።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአእምሮና የመንግሥት ለውጥ የሚመጣበት ጊዜ ይኖር ይሆን?
[ምንጭ]
U.S. National Archives photo
[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት በጎ የሆነ የአእምሮ ለውጥ በማምጣት ላይ ነው