የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 3/8 ገጽ 3-5
  • “ረጅም ጊዜ የፈጀ ሥራ ተጠናቀቀ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ረጅም ጊዜ የፈጀ ሥራ ተጠናቀቀ”
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በርካታ አስተሳሰቦችን አዋህዶ አንድ አዋጅ ላይ መድረስ
  • ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት ነበር
  • ከሃያ ዘጠነኛው ፎቅ የተሰጠ አስተያየት
    ንቁ!—1999
  • ሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊ መብት ረገጣ በዛሬው ጊዜ
    ንቁ!—1999
  • የሁሉም ሰው ሰብዓዊ መብት የሚከበርበት ጊዜ ይመጣል!
    ንቁ!—1999
  • የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ያስገድዳሉ?
    ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 3/8 ገጽ 3-5

“ረጅም ጊዜ የፈጀ ሥራ ተጠናቀቀ”

ከሃምሳ ዓመት በፊት አንዲት አዛውንት ሴት ያቀረቡትን ንግግር መላው ዓለም አዳምጧል። ነገሩ የተፈጸመው በፓሪስ ከተማ ታኅሣሥ 10 ቀን 1948 ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ተቀምጦ በነበረበት በአዲሱ ፓሌ ሻይዮ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ሊቀ መንበር ንግግር ሊያሰሙ ተነሱ። የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት ባለቤት የነበሩት ኤሊኖር ሩዝቬልት ለጉባዔተኞቹ ባሰሙት ንግግር “ዛሬ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በሰው ልጆች ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ በሚያስገባ በር ላይ ቆመናል። ይህ በር የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ መጽደቅ ነው” አሉ።

የድንጋጌውን መግቢያና 30ዎቹን አንቀጾች ካነበቡ በኋላ ጠቅላላው ጉባዔ ሰነዱን አጸደቀ።a ከዚያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባሎች ሚስስ ሩዝቬልት ላሳዩት ከፍተኛ የሆነ የአመራር ብቃት አድናቆታቸውን ለመግለጽ “የዓለማችን ወይዘሮ” የሚል ተወዳጅነታቸውን የሚገልጽ መጠሪያ ለተሰጣቸው ለእኚህ ሴት ከመቀመጫቸው ተነስተው አጨበጨቡ። ሚስስ ሩዝቬልት የዚያን ቀን ሥራ እንዳጠናቀቁ “ረጅም ጊዜ የፈጀ ሥራ ተጠናቀቀ” የሚል ጽሑፍ በማስታወሻቸው ላይ አስፍረዋል።

በርካታ አስተሳሰቦችን አዋህዶ አንድ አዋጅ ላይ መድረስ

ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባሎች የሚስማሙበት አንድ የሰብዓዊ መብቶች ሰነድ ማዘጋጀት በጣም ከባድ ሥራ እንደሚሆን የታወቀው ከሁለት ዓመት በፊት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቋቋመው ኮሚሽን ሥራውን በጀመረበት በጥር 1947 ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በኮሚሽኑ 18 አባሎች መካከል በነበረው ከፍተኛ የሐሳብ ልዩነት ምክንያት ከፍተኛ ክርክር ይካሄድ ነበር። የቻይናው ልዑክ ሰነዱ የኮንፊዩሸስን ፍልስፍና ማካተት አለበት ሲሉ ካቶሊክ የነበሩ የኮሚሽኑ አባል ለቶማስ አክዊናስ ትምህርቶች ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ ለራሷ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ ጥብቅና ስትቆም ሶቪዬቶች ደግሞ የካርል ማርክስ ፍልስፍና መካተት ይኖርበታል ብለው ተከራክረዋል። እነዚህ በጊዜው ይንጸባረቁ ከነበሩት የከረሩ አስተሳሰቦች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው!

የኮሚሽኑ አባላት የማያባራ ጭቅጭቅ የሚስስ ሩዝቬልትን ትዕግሥት በእጅጉ ተፈታትኖት ነበር። በ1948 በፓሪስ ከተማ በሚገኘው ሶርቦን ባደረጉት ንግግር በርከት ያለ ቁጥር ያላቸውን የራሳቸውን ልጆች የማሳደግን ያህል ትዕግሥት የሚፈትን ነገር አይኖርም ብለው ያስቡ እንደነበረ ከገለጹ በኋላ “የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ስብሰባ መምራት ግን ከዚያ የበለጠ ትዕግሥት ጠይቆብኛል” በማለት አድማጮቻቸውን አስቀዋል።

ቢሆንም በእናትነታቸው ያካበቱት ተሞክሮ በጣም ጠቅሟቸዋል። በጊዜው የነበረ አንድ ጋዜጠኛ ሚስስ ሩዝቬልት ለኮሚሽኑ አባላት ያሳዩ የነበረው አያያዝ አንዲት እናት የምታደርገውን እንዳስታወሰው ጽፏል። “ብዙ ጊዜ የሚንጫጩ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ሕገ ወጥ የሚሆኑ፣ በመሠረቱ ግን ጥሩ ልብ ያላቸውና አሁንም፣ አሁንም ተግሣጽና ምክር የሚያስፈልጋቸው ብዙ ልጆች የሚያስተዳድሩ ይመስሉ ነበር።” (ኤሊኖር ሩዝቬልት፣ ኤ ፐርሰናል ኤንድ ፐብሊክ ላይፍ) በጥብቅነታቸው ላይ ጨዋነትንና ደግነትን በመጨመር የተቃዋሚዎቻቸውን ባላጋራነት ሳያተርፉ የፈለጉትን ነጥብ ለማሳመን ችለዋል።

በመጨረሻ፣ ከሁለት ዓመት ስብሰባ፣ በመቶ ከሚቆጠሩ ማስተካከያዎች፣ በሺህ ከሚቆጠሩ መግለጫዎችና በእያንዳንዱ ቃልና በእያንዳንዱ ሐረግ ላይ ማለት ይቻላል 1,400 ጊዜ ድምፅ ከተሰጠ በኋላ ኮሚሽኑ በየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች በሙሉ ሊከበሩላቸው ይገባል ብሎ ያመነባቸውን ሰብዓዊ መብቶች የሚዘረዝረውን ሰነድ አወጣ። ይህ ሰነድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የሚል ስያሜ ተሰጠው። በአንዳንድ ወቅቶች ተስፋ አስቆራጭ እስከመሆን ደርሶ የነበረው ይህ ተልዕኮ በዚህ ሁኔታ ተጠናቀቀ።

ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት ነበር

እርግጥ፣ የዚህ ድንጋጌ ጥሩንባ እንደተሰማ ወዲያው ማንኛውም የጭቆና ግንብ ይናዳል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም። ቢሆንም የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መጽደቅ ከፍተኛ ተስፋ አሳድሮ እንደነበረ አይካድም። የወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት የነበሩት አውስትራሊያዊው ዶክተር ኸርበርት ቪ ኤቫት “ይህ ሰነድ ከፓሪስና ከኒው ዮርክ ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀው የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ የመላው ዓለም ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት እርዳታ፣ መመሪያና ሐሳብ የሚያገኙበት ይሆናል” ብለው ነበር።

ዶክተር ኤቫት እነዚህን ቃላት ከተናገሩ ሃምሳ ዓመታት አልፈዋል። በዚያ ዘመን ይህን ድንጋጌ እንደ መመሪያቸው አድርገው ይመለከቱ የነበሩና በመላው ዓለም ለሚታየው የሰብዓዊ መብቶች አከባበር እንደ መመዘኛ አድርገው የተጠቀሙበት ብዙዎች ነበሩ። ታዲያ ምን ሊገነዘቡ ችለዋል? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ይህን መመዘኛ አሟልተው ተገኝተዋል? በዛሬው ዓለም ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አርባ ስምንት አገሮች የድጋፍ ድምፅ ሲሰጡ አንድም ተቃዋሚ አልነበረም። ዛሬ ግን በ1948 ድምፀ ተአቅቦ አድርገው የነበሩትን አገሮች ጨምሮ 185 የሚያክሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባሎች በሙሉ ይህን አዋጅ ተቀብለዋል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሰብዓዊ መብቶች ምንድን ናቸው?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሰብዓዊ መብቶች “በተፈጥሮ ያሉና ሰብዓዊ ፍጡር ሆኖ ለመኖር የግድ አስፈላጊ የሆኑ መብቶች” የሚል ፍቺ ሰጥቷል። በተጨማሪም ሰብዓዊ መብቶች “የመላው ሰብዓዊ ዘር የጋራ ቋንቋ” ተብለዋል። ይህም ተገቢ አባባል ነው። ቋንቋ የመናገር ችሎታ በተፈጥሮ የምናገኘውና ሰው የሚያሰኘን ባሕርይ እንደሆነ ሁሉ በምድር ላይ ከሚኖሩ ሌሎች ፍጥረታት ልዩ የሚያደርጉን ሌሎች የተፈጥሮ ፍላጎቶችና ባሕርያት አሉን። ለምሳሌ ያህል ሰብዓውያን ፍጥረታት የማወቅ፣ የሥነ ጥበብና የመንፈሳዊነት ፍላጎት አላቸው። እነዚህን መሠረታዊ ፍላጎቶች የተነፈገ ሰው ከሰብዓዊ ደረጃ ዝቅ ያለ ኑሮ እንዲኖር ይገደዳል ማለት ነው። አንዲት የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ የሰው ልጆች እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች እንዳይነፈጉ ለመከላከል ስንል “‘ሰብዓዊ ፍላጎቶች’ ከማለት ይልቅ ‘ሰብዓዊ መብቶች’ በሚል ሐረግ እንጠቀማለን። ምክንያቱም ከሕግ አንጻር ‘ፍላጎት’ የሚለው ቃል ‘መብት’ የማለትን ያህል ጥንካሬ የለውም። ‘መብት’ በማለታችን እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር ሰብዓዊ ፍላጎቶቹ እንዲረኩለት ሥነ ምግባራዊም ሆነ ሕጋዊ መብት እንዳለው እናረጋግጣለን” ብለዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ

ደራሲና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት አሌክሳንደር ሶልዠኒትሰን ተመድ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን ድንጋጌ የመሰለ “ጥሩ ሰነድ” አውጥቶ አያውቅም ብለው ነበር። የሰነዱን ይዘት በአጭሩ ብንመለከት ብዙ ሰዎች በዚህ አባባል ለምን እንደሚስማሙ መገንዘብ እንችላለን።

ድንጋጌው የተመሠረተበት መሠረታዊ ፍልስፍና በአንቀጽ 1 ላይ ተገልጿል:- “ሁሉም ሰብዓዊ ፍጥረታት ነጻ ሆነው የተወለዱ ሲሆን በክብርና በመብት እኩል ናቸው። በደንብ የማገናዘብ ችሎታና ሕሊና ያላቸው ሲሆኑ እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ መተያየት ይኖርባቸዋል።”

የድንጋጌው አርቃቂዎች ይህን መሠረታዊ ሐሳብ በመመርኮዝ በሁለት ምድብ የተከፈሉ ሰብዓዊ መብቶችን ደንግገዋል። የመጀመሪያ ምድብ በአንቀጽ 3 ላይ የሚገኘው ሲሆን “ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር፣ ነጻነት የማግኘትና አካላዊ ጥበቃ የማግኘት መብት አለው” ይላል። ከአንቀጽ 4 እስከ 21 ለተደነገጉት የሰው ልጅ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች መሠረት የሆነው ይህ አንቀጽ ነው። ሁለተኛው ምድብ በአንቀጽ 22 ላይ የተመሠረተ ሲሆን ይህ አንቀጽ በከፊል ማንኛውም ሰው “ለክብሩና ለስብዕናው መዳበር አስፈላጊ የሆኑትን” መብቶች በሙሉ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል። የሰውን ልጅ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባሕላዊ መብቶች ለሚደነግጉት ከቁጥር 23 እስከ 27 ለሚገኙት አንቀጾች ድጋፍ የሆነው ይህ 22ኛው አንቀጽ ነው። እነዚህ በሁለተኛው ምድብ የተጠቃለሉት መብቶች በመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና የሰጠው ይህ ዓለም አቀፋዊ ሰነድ ነው። “ሰብዓዊ መብቶች” በሚለው ሐረግ በመጠቀም ረገድም የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ሰነድ ይኸው ድንጋጌ ነው።

ሩት ሮሽ የተባሉት ብራዚላዊት ሶስዮሎጂስት ዓለም አቀፋዊው የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የሚነግረንን ነገር ለተራ ሰው በሚገባ ቋንቋ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ዘርህ ምንም ሆነ ምን፣ ወንድም ሆንክ ሴት፣ የትኛውንም ቋንቋ ተናገር፣ የትኛውንም ሃይማኖት ተከተል፣ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ይኑርህ፣ የየትኛውም አገር ወይም ቤተሰብ ተወላጅ ሁን፣ ባለጠጋም ሁን ድሃ፣ አገርህ በንጉሥ የሚተዳደርም ይሁን ሪፑብሊክ የእነዚህ መብቶችና ነጻነቶች ሙሉ ተጠቃሚ ነህ ማለት ነው።”

ዓለም አቀፋዊው ድንጋጌ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ሲተረጎም በብዙ አገሮች ሕግጋተ መንግሥት ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ድንጋጌው መታረም እንደሚያስፈልገው የሚሰማቸው መሪዎች አሉ። የተመድ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን ግን በዚህ አይስማሙም። አንድ የተመድ ባለ ሥልጣን እሳቸው የተናገሩትን በመጥቀስ እንዲህ ብለዋል:- “መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ ቁርዓንን ማረምና እንደገና መጻፍ አስፈላጊ እንዳልሆነ ሁሉ ይህንንም ድንጋጌ ማረም አያስፈልግም። መታረምና መስተካከል የሚያስፈልገው ዓለም አቀፋዊው ድንጋጌ ሳይሆን የድንጋጌው አማኞች ባሕርይ ነው።”

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን

[ምንጭ]

UN/DPI photo by Evan Schneider (Feb97)

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚስስ ሩዝቬልት የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን ድንጋጌ እንደያዙ

[ምንጭ]

ሚስስ ሩዝቬልትና በገጽ 3፣ 5 እና 7 ላይ ያለው አርማ:- UN photo

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ