ሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊ መብት ረገጣ በዛሬው ጊዜ
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ድሎች ተጎናጽፈዋል። በመጀመሪያ በ60 አገሮች የሚገኙ ከ1,000 በላይ ድርጅቶችን ፈንጂዎች እንዲታገዱ የማድረግ ዓለም አቀፍ ዘመቻ (ኢንተርናሽናል ካምፔይን ቱ ባን ላንድማይንስ) (አይ ሲ ቢ ኤል) በተባለ እንቅስቃሴ ለማስተባበር ችለዋል። ከዚያም እነዚህን መሣሪያዎች የሚያግድ ዓለም አቀፍ ውል እንዲተላለፍ አድርገዋል። በዚህ ምክንያት አይ ሲ ቢ ኤል እና አላንዳች መሰልቸት ይህን እንቅስቃሴ ሲመሩ የቆዩት አሜሪካዊቷ ጆዲ ዊልያምስ የ1997ን የኖቤል የሰላም ሽልማት አግኝተዋል።
ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት ድሎች እምብዛም የሚያስፈነድቁ አይደሉም። ሂውማን ራይትስ ዎች ወርልድ ሪፖርት 1998 እንዳስገነዘበው አሁንም በሁሉም አካባቢዎች ሰብዓዊ መብቶችን “ማስከበር አልተቻለም።” በዚህ ረገድ የሚወቀሱት ዝቅ ተደርገው የሚታዩት አምባገነኖች ብቻ አይደሉም። ሪፖርቱ እንዳለው “ዋነኞቹ ኃይሎችም ለኢኮኖሚያዊና ለስትራቴጂያዊ ጥቅሞቻቸው የማያመቹ ሆነው ካገኟቸው ሰብዓዊ መብቶችን ችላ የማለት አዝማሚያ ታይቶባቸዋል። ይህ ደግሞ በአውሮፓም ሆነ በዩናይትድ ስቴትስ በሰፊው የተዛመተ በሽታ ነው።”
በመላው ዓለም ለሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ችላ ሊባል ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። አሁንም መድልዎ፣ ድህነት፣ ረሐብ፣ ስደት፣ ተገድዶ መደፈር፣ ባርነት፣ በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ግፍና ኢሰብዓዊ ግድያ የዕለት ተዕለት ኑሯቸው ክፍሎች ናቸው። ለእነኚህ ጎስቋላ ሰዎች የሰብዓዊ መብት ውሎችና ድንጋጌዎች ምን ያህል ቢበዙ ምንም ዓይነት ስሜት አይሰጧቸውም ወይም የሚፈይዱላቸው ነገር የለም። እንዲያውም ለአብዛኛው የሰው ዘር ክፍል በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ 30 አንቀጾች ውስጥ የተዘረዘሩት መሠረታዊ መብቶች እንኳን ሊከበሩላቸው አልቻሉም። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት በዚህ ድንጋጌ ውስጥ ከተጠቀሱት ታላላቅ መብቶች አንዳንዶቹ በምን ዓይነት የተፈጻሚነት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ እንመልከት።
እኩልነት ለሁሉም?
ሁሉም ሰብዓዊ ፍጥረታት ነጻ ሆነው የተወለዱ ሲሆን በክብርና በመብት እኩል ናቸው።—አንቀጽ 1
ቀደም ሲል የተጻፈ የዚህ ድንጋጌ አንቀጽ 1 ረቂቅ “ሁሉም ሰው [በእንግሊዝኛ “ኦል ሜን”] ... እኩል ነው” ይላል። ይሁን እንጂ ይህ ቃል ሴቶችን የሚያገልል ትርጉም እንዳለው ሆኖ እንዳይወሰድ በአርቃቂ ኮሚሽኑ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች የቃል ለውጥ እንዲደረግ አጥብቀው አሳሰቡ። ማሳሰቢያቸው ተቀባይነት በማግኘቱም “ሁሉም ሰው ... እኩል ነው” የሚለው ሐረግ “ሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር ... እኩል ነው” በሚል ተተካ። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ይሁን እንጂ ይህ በአንቀጹ ቃላት ላይ የተደረገው ለውጥ በሴቶች ሁኔታ ላይ ለውጥ አስገኝቷል?
ታኅሣሥ 10, 1997 በተከበረው የሰብዓዊ መብቶች ቀን የዩናይትድ ስቴትስ ቀዳማዊት እመቤት የሆኑት ሂላሪ ክሊንተን ለተመድ ባደረጉት ንግግር ዓለም አሁንም “ሴቶችን እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጎች አድርጎ መቁጠሩን አላቆመም” ብለዋል። ይህን አባባላቸውን የሚደግፉ ምሳሌዎች ጠቅሰዋል:- በድሃነት ከሚፈረጁት የዓለም ሕዝቦች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ትምህርት ቤት የመግባት ዕድል ካላገኙት 130 ሚልዮን የሚያክሉ የዓለም ሕፃናት መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። በዓለም ዙሪያ ካሉት 96 ሚልዮን መሃይማን መካከል ሁለት ሦስተኛዎቹ ሴቶች ናቸው። በተጨማሪም ሴቶች በቤት ውስጥ አካላዊ ድብደባ ይደርስባቸዋል፤ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል። ሚስስ ክሊንተን ስለዚህኛው ወንጀል አክለው ሲናገሩ “ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ ይፋ የማይወጣ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኝ የዓለማችን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ነው” ብለዋል።
አንዳንድ እንስቶች ግፍ የሚፈጸምባቸው ገና ከመወለዳቸው በፊት ነው። በአንዳንድ የእስያ አገሮች አንዳንድ እናቶች ከሴት ልጅ ይልቅ ወንድ ለመውለድ ስለሚመርጡ ያረገዟቸውን ሴቶች ልጆች ያስወርዳሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ወንዶች ልጆች ተመራጭ በመሆናቸው ምክንያት አንድ ጽንስ ወንድ ወይም ሴት መሆኑን አስቀድሞ ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ በጣም የሞቀ ንግድ ሆኗል። የጽንስን ጾታ የመለየት አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ክሊኒክ የሚሰጠውን አገልግሎት ሲያስተዋውቅ ወደፊት 3,800 ዶላር ለጥሎሽ ከመክፈል አሁን 38 ዶላር ከፍሎ ሴቷን ጽንስ ማስወጣት ይሻላል ብሏል። እንደነዚህ ያሉት ማስታወቂያዎች ውጤት አስገኝተዋል። በአንድ ትልቅ የእስያ ሆስፒታል ውስጥ የተደረገ ጥናት ምርመራ ተደርጎላቸው ሴት እንደሆኑ ከታወቁ ሽሎች መካከል 95.5 በመቶ የሚሆኑት እንዲወጡ ተደርጓል። ወንድ ልጆች ይበልጥ ተፈላጊ የሚሆኑባቸው ሌሎች የዓለም ክፍሎችም አሉ። አንድ የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ የቦክስ ሻምፒዮን ስንት ልጆች እንደወለደ ሲጠየቅ “አንድ ወንድ ልጅና ሰባት ስህተቶች” ሲል መልሷል። ዉሜን ኤንድ ቫዮለንስ (እንግሊዝኛ) የተባለው የተመድ ጽሑፍ “ሰዎች ለሴቶች ያላቸውን ዝንባሌና አመለካከት ለመለወጥ ገና ብዙ ዘመን፣ አንዳንዶች እንደሚያምኑት ቢያንስ የአንድ ትውልድ ዘመን፣ ምናልባትም ከዚያ የበለጠ ጊዜ ያስፈልጋል” ብሏል።
የልጅነት ሕይወት ያልቀመሱ ልጆች
ማንም ሰው ባሪያ እንዲሆን ወይም የግዳጅ አገልግሎት እንዲፈጽም አይደረግም። ማንኛውም ዓይነት ባርነትና የባሪያ ንግድ መወገድ አለበት።—አንቀጽ 4
በወረቀት ደረጃ ባርነት ተወግዷል። መንግሥታት ባርነትን ሕገ ወጥ የሚያደርጉ በርካታ ስምምነቶች ፈርመዋል። ይሁን እንጂ በዕድሜ አንጋፋነቱ የሚታወቀውና የብሪታንያ ፀረ ባርነት ማህበር ተብሎ የሚጠራው የሰብዓዊ መብቶች አስከባሪ ድርጅት “ዛሬ ከማንኛውም የታሪክ ዘመን የበለጡ ብዙ ባሮች አሉ” ብሏል። የዘመናችን ባርነት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ያካትታል። ሕፃናትን አስገድዶ ማሠራት አንዱ የዘመናችን ባርነት ገጽታ ነው።
ደቡብ አሜሪካዊው ዴሪቫን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ‘ለፍራሽ መሥሪያ የሚያገለግለውን እሾሃማ የቃጫ ተክል ቅጠሎች የሚሰበስብባቸው ትናንሽ እጆቹ ቆሳስለዋል። ሥራው ቅጠሎቹን ከማከማቻ መጋዘን አውጥቶ በ90 ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው የማባዘቻ መሣሪያ መውሰድ ነው። የ12 ሰዓት ርዝመት በሚኖረው በእያንዳንዱ የሥራ ቀን መጨረሻ ላይ አሥር ኩንታል የሚያክል ቅጠል አግዞ ይጨርሳል። ዴሪቫን ይህን ሥራ የጀመረው በአምስት ዓመት ዕድሜው ነው። ዛሬ 11 ዓመት ሆኖታል።’—ወርልድ ፕሬስ ሪቪው
ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት በሚሰጠው ግምት መሠረት በአሁኑ ጊዜ ከ5 እስከ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ምንደኞች ሩብ ቢልዮን ይሆናሉ። እነዚህ ትናንሽ ሠራተኞች የብራዚልንና የሜክሲኮን ጠቅላላ ሕዝብ ያክላሉ ማለት ነው! ከእነዚህ የልጅነት ሕይወት ለመቅመስ ካልታደሉት ልጆች መካከል ብዙዎቹ ከማዕድን ጉድጓዶች ከሰል ሲያጓጉዙ፣ በግብርና ሥራ ጭቃ ውስጥ ሲማስኑ ወይም በምንጣፍ መሸመኛ መሣሪያ ላይ ላባቸውን ሲያንጠፈጥፉ ይውላሉ። ገና ሦስት፣ አራትና አምስት ዓመት ያላለፋቸው ጨቅላ ሕፃናት እንኳን አንድ ላይ ተቀናጅተው ከጀንበር መውጫ እስከ ጀንበር መጥለቂያ ሲቆፍሩ፣ ሲዘሩና ማሳዎችን ሲቃርሙ ይውላሉ። በአንድ የእስያ አገር የሚኖር ባለርስት “ሕፃናትን ማሠራት የሚጠይቀው ወጪ ከትራክተር በጣም ያነሰ ሲሆን የሥራ ቅልጥፍናቸው ደግሞ ከበሬዎች የተሻለ ነው” ብሏል።
የራስን ሃይማኖት የመምረጥና የመለወጥ መብት
ማንኛውም ሰው የሐሳብ፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነት ባለ መብት ነው። ይህ መብት ደግሞ ሃይማኖት የመለወጥ ነፃነትን ይጨምራል።—አንቀጽ 18
ጥቅምት 16 ቀን 1997 “ማንኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊ አለመቻቻል ስለማስወገድ የተዘጋጀ ሪፖርት” ለተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቧል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ልዩ ቃል አቀባይ በሆኑት በአብደልፋታህ አሞር የተዘጋጀው ይህ ሪፖርት አንቀጽ 18 የተጣሰባቸውን የተለያዩ ሁኔታዎች ዘርዝሯል። በጣም በርካታ የሆኑ የተለያዩ አገሮችን ከጠቀሰ በኋላ ‘እንግልት፣ ማስፈራራት፣ ግፍና እስራት የደረሰባቸውን እንዲሁም አድራሻቸው የጠፋውንና የተገደሉትን’ በዝርዝር ጠቅሷል።
የዩናይትድ ስቴትስ የዲሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሥራ ቢሮ ያዘጋጀው የ1997 የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት በተመሳሳይ ለረዥም ዘመን የቆየ የዲሞክራሲ ባሕል ያላቸው አገሮች እንኳን “አናሳ የሆኑ የእምነት ቡድኖችን በጅምላ ‘የማይታወቁ ሃይማኖቶች’ ብለው በመፈረጅ ነጻነታቸውን ለመገደብ ፈልገዋል” ሲል ጠቁሟል። እንደነዚህ ያሉት አዝማሚያዎች በጣም አሳሳቢ ናቸው። ዋና መሥሪያ ቤቱን ብራሰልስ ላይ ያደረገው ድንበር የለሽ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት ዊሊ ፎትራ “የሃይማኖት ነጻነት በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሰብዓዊ ነጻነት ምን ያህል እንደተከበረ የሚጠቁም ጥሩ መስፈርት ነው” ብለዋል።
ወገብ እስኪቆረጥ ሲሠሩ ውሎ ባዶ ኪስ መመለስ
ማንኛውም ሠራተኛ ለድካሙ ፍትሐዊና ተመጣጣኝ፣ እንዲሁም ራሱንና ቤተሰቡን ለሰብዓዊ ክብር በሚመጥን ደረጃ ለማኖር የሚበቃ ክፍያ የማግኘት መብት አለው።—አንቀጽ 23
በካሪብያን ደሴቶች የሚኖሩ ሸንኮራ አገዳ ቆራጮች በቀን 25 ብር ያህል ሊያገኙ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የተክሎቹ ባለቤቶች የሚጭኑባቸው የቤት ኪራይና የመሣሪያ ዋጋ ባዶ እጃቸውን አስቀርቶ ጭራሹኑ ባለ ዕዳ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም ደመወዝ የሚከፈላቸው በገንዘብ ሳይሆን በቲኬት ነው። ቆራጮቹ የሸንኮራ ተክሉ ኩባንያ ንብረት ከሆነ ሱቅ ሌላ በአቅራቢያቸው ምንም ሱቅ ስለማያገኙ ዘይት፣ ሩዝና ባቄላ የመሰሉትን ሸቀጦች ከዚሁ ሱቅ ለመግዛት ይገደዳሉ። ሱቁ ግን በቲኬት ስለ ሸጠላቸው ብቻ ከቲኬቱ ዋጋ ላይ ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚደርስ የአገልግሎት ዋጋ ይቀንስባቸዋል። የሰብዓዊ መብት ጠበቆች ኮሚቴ ምክትል ዲሬክተር የሆኑት ቢል ኦኒል በተመድ ራዲዮ ባሰሙት ንግግር “ለበርካታ ሳምንታትና ለወራት ወገባቸው እስኪቆረጥ ሠርተው ባዶ ኪሳቸውን ይቀራሉ። ጥቂት ገንዘብ ማጠራቀም ይቅርና ከወር እስከ ወር መድረስ እንኳን ያቅታቸዋል” ብለዋል።
የሕክምና አገልግሎት ማዳረስ
ማንኛውም ሰው በቂ ምግብ፣ ልብስ፣ መኖሪያና ሕክምና ማግኘትን ጨምሮ ለራሱና ለቤተሰቡ ጤናና ደህንነት የሚመጥን ኑሮ የማግኘት መብት አለው።—አንቀጽ 25
‘ሪካርዶና ሁስቲና በአቅራቢያቸው ከሚገኝ ከተማ 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኝ አካባቢ የሚኖሩ ድሃ የላቲን አሜሪካ ገበሬዎች ናቸው። ሕፃን ልጃቸው ሄማ በታመመች ጊዜ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የግል ክሊኒክ ወሰዷት። የክሊኒኩ ሠራተኞች ግን ሪካርዶ የሚከፍለው ገንዘብ እንደሌለው ስለ ተረዱ ልጁን ለማከም ፈቃደኛ አልሆኑም። በማግስቱ ሁስቲና ለአውቶቡስ መሳፈሪያ የሚሆን ገንዘብ ከጎረቤቶቿ ተበደረችና ወደ ከተማ የሚወስደውን ረዥም ጉዞ ጀመረች። ሁስቲና ሕፃን ልጅዋን ይዛ በከተማው ወደሚገኘው አነስተኛ የመንግሥት ሆስፒታል ስትደርስ አልጋ ባለመገኘቱ በማግስቱ እንድትመጣ ተነገራት። በከተማው ውስጥ ዘመድ ስለሌላትና የማደሪያ ክፍልም የምትከራይበት ገንዘብ ስላልነበራት በገበያ ቦታ በነበረ ጠረጴዛ ላይ ተኝታ አደረች። ሁስቲና ሕፃኗን እቅፍ አድርጋ በመያዝ ምቾትና ሙቀት እንድታገኝ ለማድረግ ሞከረች፣ ግን አልሆነላትም። ሕፃኗ ሄማ በዚያው ሌሊት ሞተች።’—ሂውማን ራይትስ ኤንድ ሶሻል ወርክ
በመላው ዓለም ከ4 ሰዎች መካከል አንዱ በአንድ ዶላር የቀን ገቢ ጎስቋላ ኑሮ የሚመራ ነው። ሪካርዶና ሁስቲና ያጋጠማቸው ዓይነት ችግር ይደርስበታል። የግል ሕክምና በቅርብ ይገኛል፣ ግን ገንዘቡ ከአቅም በላይ ይሆናል። የመንግሥት ሕክምና ደግሞ የሚጠይቀው ወጪ ከአቅም በላይ ባይሆንም በቅርብ አይገኝም። ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡ የዓለም ድሃ ሕዝቦች ‘ሕክምና የማግኘት መብት’ አላችሁ ይባሉ እንጂ አሁንም የጤና እንክብካቤ ተጠቃሚዎች አልሆኑም።
ሰብዓዊ መብቶች የተረገጡባቸውን ሁኔታዎች ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ከላይ እንደተዘገቡት ያሉትን ሁኔታዎች መቶ ሚልዮን ጊዜ ማባዛት ይቻላል። የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶች በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥረት ቢያደርጉም፣ በሺህ የሚቆጠሩ የሰብዓዊ መብት አራማጆች በመላው ዓለም የሚኖሩ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ኑሮ ለማሻሻል ሲሉ የገዛ ራሳቸውን ሕይወት ለአደጋ እስከማጋለጥ የሚደርስ መሥዋዕትነት ቢከፍሉም ሰብዓዊ መብቶችን ለሁሉ ሰው ማዳረስ ገና እውን ያልሆነ ሕልም ነው። እውን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አዎን፣ መምጣቱ አይቀርም። ከዚያ በፊት ግን መከናወን የሚገባቸው ብዙ ለውጦች አሉ። የሚቀጥለው ርዕስ ከእነዚህ ለውጦች ሁለቱን ይዳስሳል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy MgM Stiftung Menschen gegen Minen (www.mgm.org)
[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
UN PHOTO 148051/J. P. Laffont—SYGMA
WHO photo/PAHO by J. Vizcarra