ክርስቲያን እረኞች የሚያገለግሏችሁ እንዴት ነው?
በብዙ ቦታዎች እረኞች መንጎቻቸውን እንዴት እንደሚንከባከቡ መመልከት ይቻላል። እረኞች በጎችን ይመራሉ፣ ከአደጋ ይከላከላሉ እንዲሁም የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ያቀርባሉ። ሥራቸው የእረኝነት ተግባርንም የሚጨምር ስለሆነ ይህ ሁኔታ የክርስቲያን ሽማግሌዎች ትኩረት የሚስብ ነው። ሽማግሌዎች ‘የአምላክን ጉባኤ የመጠበቅ’ እና ‘ለመንጋው በሙሉ ትኩረት የመስጠት’ ኃላፊነት እንዳለባቸው የማይካድ ነው።—ሥራ 20:28
የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከሆንክ መንፈሳዊ እረኞች የሚያገለግሉህ እንዴት ነው? ከዚህም በላይ አንተን ለመርዳት ሲሉ ለሚያደርጉት ጥረት ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብሃል? የእነርሱ እርዳታ ለጉባኤው የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
ጥበቃ የሚያገኙት ከምንድን ነው?
በጥንት ዘመን አንበሶችና ሌሎች አውሬዎች ከመንጋው መካከል አንዱን በግ አድብተው በመያዝ ይበሉ ነበር። ስለሆነም እረኞች መንጋውን ከአደጋ መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበር። (1 ሳሙኤል 17:34, 35) ሰይጣን ዲያብሎስ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራል።” (1 ጴጥሮስ 5:8) በመላው ምድራዊ የይሖዋ ድርጅት ላይ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ ላይ በቁጣ ጦርነት ከፍቷል። የሰይጣን ዓላማ ምንድን ነው? የይሖዋን ሕዝብ ተስፋ ለማስቆረጥና ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እንዳይጠብቁ’ እና ‘ስለ ኢየሱስ እንዳይመሠክሩ’ ለማድረግ ይፈልጋል።—ራእይ 12:17
ይሖዋ በጎቹ በጥንቷ እስራኤል መንግሥታዊ እረኞች ቸልተኛነት ምክንያት ‘ለምድር አራዊት ሁሉ መብል’ በመሆናቸው እረኞቹ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግሮ ነበር። (ሕዝቅኤል 34:8) ይሁን እንጂ ክርስቲያን እረኞች በቸልተኝነት ምክንያት ወይም በሰይጣን፣ በዓለም፣ ወይም በከሃዲ “ተኵላዎች” ተጽዕኖ ሳቢያ በጉባኤው ውስጥ ካሉት መካከል አንድም ሰው እንዳይጠፋ ለመጠበቅ ልባዊ ፍላጎት አላቸው። (ሥራ 20:29, 30) ሽማግሌዎች የመንጋው አባላት በሙሉ አስተዋዮችና ዘወትር ንቁዎች እንዲሆኑ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከመድረክ ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግሮች በማቅረብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ ገንቢና የሚያበረታቱ ጭውውቶችን በማድረግ የመንጋውን አባላት መርዳት ይችላሉ። ሌላው ውጤታማ ዘዴ ደግሞ ‘በጎቹን’ በግል እቤታቸው ድረስ ሄዶ መጎብኘት ነው። (ከመዝሙር 95:7 ጋር አወዳድር።) ሆኖም የእረኝነት ጉብኝት ምንድን ነው? ይህ ጉብኝት መደረግ የሚኖርበት እንዴት ነው? በተጨማሪም ጉብኝት ሊደረግላቸው የሚገባው ለእነማን ነው?
የእረኝነት ጉብኝነት ምንድን ነው?
የእረኝነት ጉብኝት ስለ ተራ ጉዳዮች ጭውውት የሚደረግበት ማኅበራዊ ጥየቃ አይደለም። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል፦ “አብዛኞቹ አስፋፊዎች አንድ ጥቅስ ቢነበብ ወይም በአንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ላይ ውይይት ቢደረግ ደስ ይላቸዋል። እርግጥ ሽማግሌው ብቻ መናገር የለበትም። ጉብኝት እየተደረገለት ያለው የመንግሥቱ አስፋፊ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ሐሳብ መግለጹ የሚያስደስተው ከመሆኑም በተጨማሪ ይህን ማድረጉ እምነቱን ያጠነክርለታል። ሽማግሌው በአንድ የሚያንጽ ርዕስ ላይ ውይይት ለማድረግ እንዲችል አንድ መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! መጽሔት ይዞ ሊሄድ ይችላል። የእረኝነት ጉብኝትን ከማኅበራዊ ጥየቃ የሚለየው ይህ መንፈሳዊ ውይይት ሳይሆን አይቀርም።”
ተሞክሮ ያለው አንድ ሌላ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል፦ “ሽማግሌው ጉብኝቱን ከማድረጉ በፊት አስፋፊው ምን እንደሚያስፈልገው ያስባል። አስፋፊውን ሊያንጸው የሚችለው ነገር ምንድን ነው? ከልብ የመነጨ ምስጋና አንድን ግለሰብ እንዲጸና የሚያደርገውን ብርታት ስለሚሰጠው የእረኝነት ጉብኝት እጅግ አስፈላጊ ክፍል ነው።” አዎን፣ የእረኝነት ጉብኝት በጉባኤው ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ ሊያደርገው የሚችለው ወዳጃዊ ጥየቃ ብቻ አይደለም።
አንድ እረኛ የሚጎበኛችሁ ለምንድን ነው?
አንድ ሽማግሌ ጉብኝት የሚያደርገው የእምነት ጓደኞቹን ለማበረታታትና በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ ለመርዳት ተዘጋጅቶ ነው። (ሮሜ 1:11) ስለዚህ አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌዎች ሊጎበኟችሁ በሚፈልጉበት ወቅት ምን ምላሽ ትሰጣላችሁ? “የእረኝነት ጉብኝት የሚደረገው አንድ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት ብቻ ቢሆን ኖሮ አንድ ሰው ጉብኝት እንደሚደረግለት ሲነገረው ‘ምን አጥፍቼ ይሆን?’ የሚል ስሜት ያድርበት ነበር” በማለት አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ተናግሯል። አፍቃሪ እረኞች መዝሙራዊውን የተንከባከበውንና ዘወትር በተለይም በመከራና ለየት ያለ ችግር በሚያጋጥመው ወቅት ‘መንፈሱን ያደሰለትን’ ይሖዋን ይመስላሉ።—መዝሙር 23:1-4
የእረኝነት ጉብኝት ዓላማ ‘ማነጽ እንጂ ማፍረስ አይደለም።’ (2 ቆሮንቶስ 13:10) ጉብኝት የሚደረግለት ግለሰብ ላሳየው ጽናት፣ ቅንዓትና ላከናወነው የታማኝነት ተግባር አድናቆት ቢቸረው ይበረታታል። አንድ ሽማግሌ የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል፦ “አንድ ሰው የእረኝነት ጉብኝት በሚያደርግበት ወቅት ምን ችግሮች እንዳሉ ለማወቅና ስለ እነርሱ ለመወያየት አቅዶ እንደመጣ ማሳየቱ ጥሩ አይደለም። እርግጥ አስፋፊው ራሱ ስለ አንድ ችግር መናገር ሊፈልግ ይችላል። በተጨማሪም አንድ በግ ማነከስ ከጀመረ ወይም ከመንጋው ራሱን ካገለለ ሽማግሌዎች እርሱን ለመርዳት አንድ ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል።”
ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሚከተሉት ቃላት ለተገለጹት ዓይነት ግለሰቦች ልዩ እንክብካቤ እንደሚያደርጉላቸው አያጠራጥርም፦ “[እኔ ይሖዋ] የጠፋውን እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ።” (ሕዝቅኤል 34:16) አዎን፣ በጎች መፈለግ፣ ከጠፉበት መመለስ፣ የተጎዳ አካላቸው መታሰር ወይም ማበረታቻ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። እስራኤላውያን እረኞች እነዚህን ኃላፊነቶች ችላ ብለው ነበር። አንድ እረኛ እንደነዚህ ያሉትን ሥራዎች ለማከናወን እንዲችል ወደ አንድ በግ መቅረብና በጉ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማድረግ ይኖርበታል። በመሠረቱ በዛሬው ጊዜ የሚደረገው የእያንዳንዱ የእረኝነት ጉብኝት አንዱ ገጽታ ይህ መሆን ይኖርበታል።
ጤነኛ በጎችም እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል
በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ መንፈሳዊ እረኞች ለጤነኛ በጎች የተለየ ትኩረት ማድረግ የለባቸውም ብለን መደምደም ይኖርብናልን? አንድ በግ በእረኛው የሚተማመን ከሆነ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ወቅት እርሱን መርዳት በይበልጥ ቀላል ይሆናል። አንድ የመመሪያ መጽሐፍ “በጎች በተፈጥሯቸው ከሰዎች ይሸሻሉ፤ ብዙውን ጊዜ የእነርሱን አመኔታ ማትረፍ ቀላል አይሆንም” ይላል። መጽሐፉ ከሰጣቸው የበጎችን አመኔታ ለማትረፍ የሚያስችሉ ሐሳቦች መካከል የሚከተለው መመሪያ ይገኝበታል፦ “ዘወትር ከበጎቹ ጋር ተነጋገሩ። ድምፃችሁን ይለምዱታል፤ ይህም እንዲረጋጉ ያደርጋቸዋል። በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ ግጦሽ ስፍራቸው ሄዳችሁ በጎቹን ጎብኟቸው።”—አሌስ ፉር ዳስ ሻፍ። ሃንድቡክ ፉር ደ አርቲገሬክት ሃልቱግ። (ሁሉም ነገር ለበጎች። በጎችን በሚገባ ለመጠበቅ የሚረዳ የመመሪያ መጽሐፍ።)
ስለዚህ በእረኛውና በበጎቹ መካከል መተማመን የሰፈነበት ዝምድና እንዲኖር በግል መገናኘታቸው የግድ አስፈላጊ ነው። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። አንድ ሽማግሌ “በጉባኤው ውስጥ በጎቹን ዘወትር የሚጎበኝ ሽማግሌ ሆኖ መታወቅ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የሚደረገውን ጉብኝት በይበልጥ ቀላል ያደርገዋል” በማለት ገልጿል። ስለዚህ መንፈሳዊ እረኞች በጎቹን በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ብቻ ለመመገብና ለመንከባከብ መጣር የለባቸውም። ሽማግሌዎች ሁኔታዎቹ የሚፈቅዱላቸውን ያህል ቤታቸው ሄደው የእረኝነት ጉብኝት በማድረግ በጎቹን ማወቅ ይኖርባቸዋል። አንድ ክርስቲያን አዲስ የተሾመ ሽማግሌ በነበረበት ወቅት ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ስልክ ደውሎ በአንድ አሰቃቂ የመኪና አደጋ ምክንያት ልጁ የሞተችበትን አንድ ወንድም እንዲጎበኘውና እንዲያጽናናው ጠይቆት እንደነበር ያስታውሳል። ሽማግሌው እንዲህ በማለት አምኗል፦ “ወንድምን ቀደም ሲል አንድም ቀን ስላልጠየቅሁትና ቤቱን እንኳ ስለማላውቅ በጣም አዘንኩ! አንድ የጎለመሰ ሽማግሌ ከእኔ ጋር እንደሚሄድ ሲገልጽልኝ እፎይታ ተሰማኝ።” አዎን፣ በእረኝነት ጉብኝቶች ወቅት ሽማግሌዎች እርስ በርስ ይረዳዳሉ።
አንድ ሽማግሌ ለበላይ ተመልካችነት ‘መልካም ሥራ’ ከሚጣጣር ዲያቆን ጋር ለእረኝነት ጉብኝት ዝግጅት ወይም እረኝነት ሊያደርግ ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) አንድ ሽማግሌ የእረኝነት ጉብኝት በማድረግ በጎቹን ሲያገለግል አንድ ዲያቆን በሚመለከትበት ወቅት እንዴት ይጠቀማል! በዚህ መንገድ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በጉባኤው ውስጥ የክርስቲያናዊ ፍቅርና አንድነት ትስስር እንዲጠናከር በማድረግ ከሁሉም ጋር በይበልጥ ይቀራረባሉ።—ቆላስይስ 3:14
ለእረኝነት ጉብኝት እቅድ ማውጣት
አንድ የሽማግሌዎች አካል የእረኝነት ጉብኝት የማድረግ ኃላፊነቱን ለጉባኤ መጽሐፍ ጥናት መሪዎች ሲሰጥ በአንዳንድ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች በሙሉ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ተጎበኙ። የሌሎች ቡድኖች አስፋፊዎች ግን አንዳቸውም ቢሆኑ ሳይጎበኙ ቀሩ። በዚህ ምክንያት አንድ ሽማግሌ “አንዳንድ ሽማግሌዎች በራሳቸው አነሣሽነት ብዙ የእረኝነት ሥራ ሲያከናውኑ ሌሎች ግን እንደዚህ እንዲያደርጉ የሌሎች ሽማግሌዎች ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ይመስላል” ብሏል። ስለዚህ የአንዳንድ ጉባኤዎች የሽማግሌ አካላት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ሁሉም አስፋፊዎች እንዲጎበኙ ዝግጅት አድርገዋል።
እርግጥ አንድ ሽማግሌ ወይም ማንኛውም ሌላ አስፋፊ የተለየ ዝግጅት እስኪደረግ ድረስ ሳይጠብቅ በጉባኤው ውስጥ የሚገኝ ግለሰብን ሊጠይቅ ይችላሉ። አንድ ሽማግሌ የእረኝነት ጉብኝት ከማድረጉ በፊት ስልክ ደውሎ “በየወሩ አንድ ቤተሰብ እጎበኛለሁ። በሚቀጥለው ወር ለአንድ ሰዓት ያህል ልጎበኛችሁ እችላለሁ? መቼ ይመቻችኋል?” ይላል።
የእረኝነት ጉብኝት የሚያስገኛቸው በረከቶች
ከዚህ ክፉ ዓለም የሚመጡት ተጽዕኖዎች እየጨመሩ በሄዱ መጠን አሳቢ እረኞች የሚያደርጓቸው የሚያበረታቱ ጉብኝቶች በይበልጥ ጠቃሚ ይሆናሉ። በመንጋው ውስጥ የሚገኙት ሁሉ በእረኝነት ጉብኝት አማካኝነት ማበረታቻና እርዳታ ሲሰጣቸው እያንዳንዱ በግ ከአደጋ ነፃ እንደሆነና እንደተረጋጋ ይሰማዋል።
ሁሉም የመንግሥቱ አስፋፊዎች ዘወትር በእረኞች የሚጎበኙበትን ጉባኤ በተመለከተ እንዲህ የሚል ሪፖርት ቀርቧል፦ “አስፋፊዎቹ ስለ እረኝነት ጉብኝት አዎንታዊ አመለካከት አላቸው። አንድ አስፋፊ በቀድሞው ጉብኝት ከሽማግሌዎች ጋር ባደረገው የሚያንጽ ውይይት በመደሰቱ ምክንያት ከሽማግሌዎች ወደ አንዱ ቀርቦ ሌላ ጉብኝት የሚደረግለት መቼ እንደሆነ መጠየቁ በጣም የተለመደ ነገር ነው።” እረኞች በዚህ መንገድ በፍቅር ሲያገለግሉ ጉባኤው በፍቅር፣ በአንድነትና ሞቅ ባለ የመውደድ ስሜት ሊያድግ እንደሚችል ሌሎች ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው!
ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጉብኝት የሚያደርጉት የበጎቹን መንፈሳዊ ደኅንነት ለመጠበቅ ነው። ሽማግሌዎች የእምነት ጓደኞቻቸውን ለማበረታታትና ለማጠናከር ይፈልጋሉ። በተለይ ሽማግሌው ከአንድ ዲያቆን ጋር ሆኖ እረኝነት በሚያደርግበት ወቅት ምክር እንዲሰጥበት የሚያስፈልግ አንድ ከባድ ችግር ብቅ ካለ በሌላ ጊዜ ውይይት ለማድረግ እቅድ ማውጣት የተሻለ ሊሆን ይችላል። በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን የእረኝነት ጉብኝቱን በጸሎት መደምደም ተገቢ ነው።
አንድ ሽማግሌ በቅርቡ ቤታችሁ ድረስ መጥቶ ሊጎበኛችሁ ፈልጓልን? እንዲህ ከሆነ የሚሰጣችሁን ማበረታቻ በደስታ ተጠባበቁ። ወደ እናንተ የሚመጣው ሊያገለግላችሁና ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው መንገድ ላይ ለመቆየት ያደረጋችሁትን ቁርጥ ውሳኔ ሊያጠናክርላችሁ ነው።—ማቴዎስ 7:13, 14
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የእረኝነት ጉብኝት ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦች
◻ ቀጠሮ ያዙ፦ ብዙውን ጊዜ አስቀድሞ ቀጠሮ መያዝ ጥሩ ነው። አንድ ሽማግሌ አንድን ከባድ ችግር ለመፍታት ካሰበ ለአስፋፊው ስለጉዳዩ በቅድሚያ ማሳወቁ ተገቢ ነው።
◻ ዝግጅት፦ የሰውዬውን ባሕርይና ሁኔታ አስብ። ልባዊ ምስጋና አቅርብ። ዓላማህ የሚያበረታታና እምነት የሚያጠነክር “መንፈሳዊ ስጦታ” ማካፈል ይሁን።—ሮሜ 1:11, 12
◻ ከማን ጋር እንደሚኬድ፦ ከሌላ ሽማግሌ ወይም ብቃት ካለው ዲያቆን ጋር መሄድ ይቻላል።
◻ በጉብኝቱ ወቅት፦ ሽማግሌው ዘና ያለ፣ አፍቃሪ፣ አዎንታዊ አመለካከት ያለውና እንደሁኔታው ሊሆን የሚችል መሆን ይኖርበታል። ቤተሰቡን፣ ደኅንነታቸውንና የመሳሰሉትን ነገሮች ጠይቅ። በጥሞና አዳምጥ። ከባድ ችግሮች ብቅ ካሉ በሌላ ጊዜ ልዩ የእረኝነት ጉብኝት ለማድረግ ዕቅድ ማውጣት የተሻለ ሊሆን ይችላል።
◻ የጉብኝቱ ርዝመት፦ የተስማማችሁበትን ሰዓት አክብር። የምታነጋግረው ሰው ከመሰላቸቱ በፊት ውይይታችሁ እንዲያበቃ አድርግ።
◻ ጉብኝቱን መደምደም፦ በጸሎት መደምደም ተገቢ ከመሆኑም በላይ ጉብኝቱ የተደረገላቸውን ሰዎች በጣም ያስደስታል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን እረኞች መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርጋሉ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የእረኝነት ጉብኝት መንፈሳዊ ማበረታቻ ለማግኘት ጥሩ አጋጣሚዎችን ይፈጥራል