በረከት ሊያስገኝ የሚችል ጉብኝት
1 ዘኬዎስ ኢየሱስን በቤቱ በእንግድነት የተቀበለው በደስታ ነበር። ይህ ጉብኝት እንዴት ያለ ታላቅ በረከት አስገኝቷል!—ሉቃስ 19:2-9
2 በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ሽማግሌዎች ‘የእግዚአብሔርን መንጋ እንዲጠብቁ’ አመራር ይሰጣቸዋል። (1 ጴጥ. 5:2, 3፤ ዮሐ. 21:15-17) የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች በስብሰባዎች ላይ ከሚሰጡት ትምህርትና በግንባር ቀደምትነት ከሚያከናውኑት የመስክ አገልግሎት በተጨማሪ ለእያንዳንዱ የጉባኤ አባል በግለሰብ ደረጃ ፍቅራዊ ድጋፍ ይሰጣሉ። ይህም በመሆኑ አልፎ አልፎ በቤትህ፣ በመንግሥት አዳራሽ፣ መስክ አገልግሎት አብረሃቸው ስትወጣ ወይም በሌሎች አጋጣሚዎች ሽማግሌዎች በግል ትኩረት ሰጥተው ሊያነጋግሩህ ይችላሉ። ሽማግሌዎች የሚያደርጉት ይህን የመሰለው ጉብኝት ስጋት ሊፈጥርብህ ይገባልን? በጭራሽ። እነሱ አንተን ለመጠየቅ መምጣታቸው የሆነ ጉድለት ተገኝቶብሃል ማለት አይደለም። ታዲያ የእረኝነት ጉብኝት ዓላማ ምንድን ነው?
3 ጳውሎስ ወንድሞች ‘እንዴት እንዳሉ ለማወቅ’ ሲል ሊጎበኛቸው ፈልጎ ነበር። (ሥራ 15:36) አዎን፣ ሽማግሌዎች አፍቃሪ እረኞች እንደመሆናቸው መጠን ስላለህበት ሁኔታ ማወቅ ይፈልጋሉ። አንተን የሚጠቅምና የሚገነባ መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ይፈልጋሉ። አፍቃሪው እረኛችን ይሖዋ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ ይህን የመሰለ እንክብካቤ እንድናገኝ ይፈልጋል።—ሕዝ. 34:11 የ1980 ትርጉም
4 የሽማግሌዎችን ጉብኝት በደስታ ተቀበሉ፦ ጳውሎስ ወንድሞቹን የጎበኘው ‘ይጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ ለማካፈልና እርስ በርስ ለመጽናናት’ ነው። (ሮሜ 1:11, 12) በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናት ሁላችንም መንፈሳዊ ማበረታቻ የሚያስፈልገን ከመሆኑም በላይ በእምነት ጸንተን መቀጠል እንድንችል እርዳታ ያስፈልገናል። ለሚደረግላችሁ የእረኝነት ጉብኝት የምትሰጡት አዎንታዊ ምላሽ እርስ በርስ ለመተናነጽ እንደሚያስችል ምንም አያጠራጥርም።
5 ሽማግሌዎች በሚያከናውኑት የእረኝነት ሥራ የሚገኙትን በርካታ ጥቅሞች አድንቁ። አንድ የሚያሳስባችሁ ጉዳይ ወይም ጥያቄ ካላችሁ በጉባኤው ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች እናንተን ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውሱ። መንፈሳዊ ደኅንነታችሁን ሊጎዳ የሚችል ማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ሲገጥማችሁ ከእነሱ ጋር ለመወያየት አታመንቱ። ይሖዋ ያቋቋመውን ይህን ፍቅራዊ ዝግጅት አድንቁ እንዲሁም ይህን የመሰለው ጉብኝት የሚያስገኛቸውን በረከቶች ቅመሱ።