ማክበር ያለብህ በዓለ ትንሣኤን ነው ወይስ የመታሰቢያውን በዓል?
በአውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 7 ገና ማለዳ ጎህ ሲቀድ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዓመቱ ውስጥ ከሚከበሩ በዓላት ሁሉ አስበልጠው የሚመለከቱትን በዓለ ትንሣኤ በደስታ ይቀበሉታል። በዓለ ትንሣኤ ተብሎ የተተረጎመው ኢስተር የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ሴፕቱዋጄሲማ በተባለ በዓል ተጀምሮ የሥላሴ ቀን ተብሎ በሚጠራ በዓል የሚያልቀውን 120 ቀን የሚፈጀውን የድግስና የጾም ጊዜ ያመለክት ነበር። በዛሬው ጊዜ ይህ ስም ለኢየሱስ ትንሣኤ መታሰቢያ እንዲሆን ተብሎ አንድ ቀን ብቻ ማለትም እሑድ ዕለት የሚከበረውን በዓለ ትንሣኤን ያመለክታል።
ነገር ግን በዚያው ሳምንት ውስጥ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ አንድ ምሽት ላይ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጌታ ራት ተብሎ የሚጠራውን የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ለማክበር ይሰበሰባሉ። ይህ በዓል ኢየሱስ ራሱ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻዋ ምሽት ላይ ያቋቋመው በዓል ነው። በዚያን ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት ነግሯቸው ነበር።—ሉቃስ 22:19
ማክበር ያለብህ የትኛውን ነው?
የበዓለ ትንሣኤ በዓል አመጣጥ
በብዙ አገሮች የሚሠራበት ኢስተር የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ሜዲይቨል ሆሊዴይስ ኤንድ ፌስቲቨልስ የተባለው መጽሐፍ “በዓሉ ስያሜውን ያገኘው ኦስትር ከተባለች የአረማውያን የንጋትና የፀደይ ሴት አምላክ ነው” በማለት ይነግረናል። ይህች አምላክ ማን ነበረች? ዘ አሜሪካን ቡክ ኦቭ ዴይስ የተባለ መጽሐፍ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ነጩ አምላክ ተብሎ ለሚጠራው ለቦልደር የቫልሃላን በር የከፈተችለት ኦስትር ነች። ይህንንም ያደረገችለት ቦልደር ንጹሕ በመሆኑና ግንባሩ ለሰው ዘሮች ብርሃን በመስጠቱ የተነሳ የፀሐይ አምላክ ስለሆነ ነው።” መጽሐፉ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ቤተ ክርስቲያን በተመሠረተችበት ጊዜ ጥንታዊ የሆኑ አረማዊ ልማዶችን ወስዳ ክርስቲያናዊ ትርጉም እንደሰጠቻቸው አያጠራጥርም። የኦስትር በዓል ሕይወት የሚታደስበት የፀደይ ወቅት የሚከበርበት ስለሆነ ይህንን በዓል ኢየሱስ ከሞት የተነሳበት ዕለት ወደሚከበርበት በዓል መለወጥ ቀላል ነበር። ምክንያቱም ሰዎቹ የሚሰብኩት ወንጌል ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ይናገራል።”
ይህ በዓል ከአረማውያን የተወረሰ መሆኑ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ እንደ በዓለ ትንሣኤ እንቁላሎች፣ እንደ በዓለ ትንሣኤ ጥንቸልና በበዓለ ትንሣኤ ሰሞን እንደሚበሉት ያሉ እላያቸው ላይ በክሬም መስቀል የተሠራባቸው ትንንሽ ዳቦዎች የመሳሰሉ ልማዶች ከየት እንደመጡ ግልጽ ያደርግልናል። እነዚህን ዳቦዎች የማዘጋጀት ልማድ በተመለከተ ኢስተር ኤንድ ኢትስ ከስተምስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ እሳት ስለመታቸው ቡናማ የሆኑ ዳቦዎች እላያቸው ላይ . . . የመስቀል ምልክት ይደረግባቸዋል። መስቀል ከስቅለት በዓል ጋር በዘላቂነት ከመያያዙ ከረጅም ጊዜ በፊት አረማዊ ምልክት የነበረ ሲሆን ከክርስትና ዘመን በፊት አልፎ አልፎ በዳቦዎችና በኬኮች ላይ የመስቀል ምልክት ይደረግባቸው ነበር።”
እነዚህ ልማዶች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አንድም ቦታ ካለመጠቀሳቸውም በተጨማሪ የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያምኑባቸው እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ የለም። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ “ለመዳን . . . ተንኰል የሌለበትን [“ያልተበረዘውን፣” አዓት] የቃልን ወተት ተመኙ” ብሎናል። (1 ጴጥሮስ 2:2 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ታዲያ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ግልጽ የሆኑ አረማዊ ምልክቶችና በዓላት የተቀበሉት ለምንድን ነው?
ኪዩሪዮሲቲስ ኦቭ ፖፕዩለር ከስተምስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል፦ “አረማዊ የአምልኮ ሥርዓቶችን ጠብቆ ለማቆየት ክርስቲያናዊ ትርጉም እንዲኖራቸው ማድረግ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ መመሪያ ነበር። በተለይ በዓለ ትንሣኤን ወደ ክርስትና በዓልነት የለወጡት በቀላሉ ነው። ፀሐይ ደምቃ በመውጣቷና በበረዶ ወራት ምክንያት የከሰሙት ተክሎች በመለምለማቸው ምክንያት የነበረው ደስታ በጽድቅ ፀሐይ መነሳት ማለትም በክርስቶስ ከመቃብር መውጣት ተተካ። ግንቦት 1 ገደማ ይከናወኑ የነበሩ አንዳንድ አረማዊ ሥርዓቶች ወደ በዓለ ትንሣኤ ተላልፈዋል።” የሃይማኖት መሪዎች እነዚህን ግልጽ የሆኑ አረማዊ ልማዶችና አስማታዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ከማስወገድ ይልቅ ተቀባይነት እንዲያገኙና “ክርስቲያናዊ ትርጉም” እንዲኖራቸው አድርገዋል።
‘ይህ ምን ጉዳት አለው?’ ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል። አንዳንዶች ምንም ጉዳት የለውም ብለው ያስባሉ። አለን ደብልዩ ዋትስ የተባሉ የኤፒስኮፓል ቄስ ኢስተር—ኢትስ ስቶሪ ኤንድ ሚኒንግ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “እንደ ክርስትና የመሳሰለው ሃይማኖት በአንድ ሕዝብ መካከል መስፋፋት በሚጀምርበት ጊዜ የዚያን ሕዝብ አንዳንድ የቆዩ ሃይማኖታዊ ባሕሎችና ልማዶች እንዳሉ ይቀበላል። ሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያን ከምታስተምረው ትምህርት ጋር መሠረታዊ አንድነት ያላቸው የሚመስሉ በወግ ላይ የተመሠረቱ የአምልኮ ሥርዓቶች መርጣ ትቀበላለች።” ብዙ ሰዎች እነዚህን የአምልኮ ሥርዓቶች የሚቀበሉት ቤተ ክርስቲያናቸው እነዚህን የአምልኮ ሥርዓቶች ስለሚቀበላቸውና ቅዱስ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ብቻ ነው። አንገብጋቢዎቹ ጥያቄዎች ግን ችላ ተብለዋል። አምላክ ስለ እነዚህ በዓሎች ምን ይሰማዋል? ስለዚህ ጉዳይ መመሪያ ሰጥቶናልን?
አምላክ ያለውን አመለካከት ማወቅ
ክሪስቲና ሆል ኢስተር ኤንድ ኢትስ ከስተምስ በተባለው መጽሐፋቸው “የጌታችን ትንሣኤ የሚከበርበት በዓለ ትንሣኤ በክርስቲያን ሃይማኖት ከሚከበሩት በዓላት ሁሉ ይበልጣል” ብለዋል። ሌሎች ጸሐፊዎችም ከዚህ ጋር ይስማማሉ። ሮበርት ጄ ሚርዝ ሴሌብሬሽን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በክርስቲያኖች ዘንድ የትኛውም በዓል ወይም ድግስ በዓለ ትንሣኤ ከሚከበርበት እሑድ ጋር አይወዳደርም” በማለት ገልጸዋል። ሆኖም ይህ አንዳንድ ጥያቄዎች ያስነሳል። በዓለ ትንሣኤን ማክበር ይህን ያህል አስፈላጊ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንድናከብር የሚናገር ትእዛዝ ለምን አልተሰጠም? የኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት እሑድ የሚውለውን በዓለ ትንሣኤን እንዳከበሩ የሚናገር ታሪክ አለን?
መጽሐፍ ቅዱስ የትኛውን በዓል ማክበር እንዳለብንና እንደሌለብን ይነግረናል። አምላክ በዓላትን በተመለከተ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ አንድ በአንድ ነግሯቸው ነበር። በተጨማሪም ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ክርስቲያኖች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ እንዲያከብሩ ግራ የማያጋባ ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 11:23-26፤ ቆላስይስ 2:16, 17) ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ የተባለው መጽሐፍ የቀድሞ እትም እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “በአዲስ ኪዳን ውስጥም ሆነ በሐዋርያት አባቶች ጽሑፎች ውስጥ በዓለ ትንሣኤ ይከበር እንደነበር የሚገልጽ ፍንጭ የለም። አንዳንድ ቀናትን ማክበር በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ አልነበረም። . . . ጌታም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ይህ በዓል ወይም ሌላ በዓል እንዲከበር አላዘዙም።”
አንዳንድ ሰዎች በእነዚህ በዓላት ላይ ያለው ፍንደቃና በዓላቱ የሚያመጡት ደስታ እነዚህ በዓላት መከበር እንዳለባቸው የሚያሳዩ ነገሮች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ነገር ግን እስራኤላውያን የግብጻውያንን የአምልኮ ሥርዓት በመቅዳት “የእግዚአብሔር በዓል” ብለው ከሰየሙት በዓል ትምህርት መውሰድ እንችላለን። እነርሱም “ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሱ።” ሆኖም ሥራቸው ይሖዋን በጣም ስላስቆጣው ክፉኛ ቀጥቷቸዋል።—ዘጸአት 32:1-10, 25-28, 35
የአምላክ ቃል ግልጽ ነው። በእውነተኛው እምነት ‘ብርሃንና’ በሰይጣን ዓለም “ጨለማ” መካከል ሕብረት ሊኖር አይችልም፤ ክርስቶስና አረማዊ አምልኮ ‘ሊስማሙ’ አይችሉም። “ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ፦ እኔም እቀበላችኋለሁ” ተብለናል።—2 ቆሮንቶስ 6:14-18
መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዘው ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን ሳይሆን የመታሰቢያውን በዓል ብቻ እንዲያከብሩ ስለሆነ የመታሰቢያውን በዓል ማክበር ይገባናል። ታዲያ ይህንን በዓል በአግባቡ ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን “የእግዚአብሔር በዓል” ያሉት በዓል ይሖዋን በጣም አስቆጥቶት ነበር
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሽፋን: M. Thonig/H. Armstrong Roberts