“ለሚጠፋ መብል አትሥሩ”
ዴቪድ ለንስትረም እንደተናገረው
እኔና ኤልውድ የተባለው ወንድሜ ከመሬት 9 ሜትር ከፍታ ባለው መወጣጫ ላይ ቆመን በመጠበቂያ ግንብ ፋብሪካ ሕንፃ ላይ አንድ አዲስ ነገር በትልቁ እየጻፍን ነበር። በዚያን ጊዜ የጻፍነው “የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ አንብቡ” የሚለው ማሳሰቢያ ከተጻፈ 40 ዓመት ቢያልፈውም አሁንም እዚያው አለ። በየሳምንቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ታዋቂ በሆነው በብሩክሊን ድልድይ ላይ በመኪና ሲያልፉ ይህንን ጽሑፍ ያነቡታል።
ከልጅነት ትዝታዎቼ መካከል አንዱ የቤተሰባችን የልብስ አጠባ ቀን ነው። እናቴ ከጠዋቱ 11 ሰዓት ከመኝታዋ ተነስታ የቤተሰባችንን ልብስ ስታጥብ አባቴ ወደ ሥራ ለመሄድ ይዘጋጅ ነበር። በዚሁ ጊዜ የጦፈ ክርክር ያደርጉ ነበር። አባባ ሰው በሚልዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት አዝጋሚ ለውጥ አድርጓል ብሎ ሲከራከር እማማ ደግሞ ሰው በቀጥታ በአምላክ የተፈጠረ መሆኑን ለማሳመን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትጠቅስ ነበር።
ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ እውነትን እንደያዘች ተገንዝቤ ነበር። ለአባቴ ከፍተኛ ፍቅር ቢኖረኝም የያዘው እምነት የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ምንም ተስፋ እንደማይሰጥ ለመረዳት ችዬ ነበር። እናቴ በጣም የምትወደውን መጽሐፍ ቅዱስን ሰዎች እንዲያነቡት የሚያበረታታውን ጽሑፍ ከብዙ ዓመታት በኋላ በትልቁ የጻፉት ሁለት ልጆችዋ እንደሆኑ ብታውቅ እንዴት ትደሰት ነበር!
የሕይወት ታሪኬን ከመጀመሪያው አንስቼ አልነገርኳችሁም። ይህንን መብት ያገኘሁት እንዴት ነበር? ይህንን ለመመለስ ወደ 1906 ማለትም ከተወለድኩበት ጊዜ ሦስት ዓመት ወደኋላ መመለስ ያስፈልገኛል።
እናቴ ያሳየችው በእምነት የመጽናት ምሳሌ
በዚያን ጊዜ እናቴና አባቴ አዲስ ሙሽሮች የነበሩ ሲሆን አሪዞና ውስጥ በድንኳን ይኖሩ ነበር። በጊዜው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ እማማን አነጋገራትና በቻርልስ ቴዝ ራስል የተጻፉ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የሚል ርዕስ ያላቸው ተከታታይ መጽሐፎች አበረከተላት። ሌሊቱን ሙሉ ስታነባቸው ካደረች በኋላ ስትፈልገው የነበረውን እውነት እንዳገኘች ወዲያው ተገነዘበች። አባባ ሥራ ሊፈልግ ከሄደበት እስኪመለስ ድረስ አላስችል አላት።
አባባም አብያተ ክርስቲያናት ያስተምሩት በነበረው ነገር ስለማይረካ እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለተወሰነ ጊዜ አምኖባቸው ነበር። በኋላ ግን የራሱን ሃይማኖታዊ መንገድ መከተል ከመጀመሩም በላይ በእናቴም ላይ ችግር ይፈጥርባት ነበር። ሆኖም እናቴ የልጆችዋን አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ከማድረግ አልቦዘነችም።
እናቴ ቀኑን ሙሉ አድካሚ ሥራ ስትሠራ ውላ መጽሐፍ ቅዱስ ልታነብልን ወይም አንዳንድ መንፈሳዊ ዕንቁዎች ልታካፍለን ሁልጊዜ ማታ ማታ ከሁለተኛ ፎቅ ወደ አንደኛ ፎቅ ትመጣ እንደነበር ፈጽሞ አልረሳውም። አባቴም ጠንካራ ሠራተኛ ነበር። ዕድሜዬ ከፍ ሲል የቀለም ቅብ ሥራ አስተማረኝ። አዎን፣ አባቴ ምን እንደምሠራ አስተማረኝ፤ እናቴ ግን ኢየሱስ እንዳዘዘው ለምን ነገር መሥራት እንዳለብኝ አስተማረችኝ። ኢየሱስ ‘ለማይጠፋ መብል’ እንድንሠራ አዝዞ ነበር።—ዮሐንስ 6:27
በመጨረሻም ቤተሰባችን ከሲያትል በስተምሥራቅ 180 ኪሎ ሜትር ርቆ በዋሽንግተን ግዛት ውስጥ ወደሚገኝ ኢለንዝበርግ ወደሚባል አነስተኛ ከተማ ተዛወረ። ከእናታችን ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ መገኘት ስንጀምር የምንሰበሰበው መኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር። ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማገልገል የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ሲገለጽ በጥናት ቡድናችን ውስጥ የነበሩ ወንዶች በጠቅላላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውን አቆሙ። እናቴ ግን ምንም አላመነታችም። ይህ ሁኔታ ምንጊዜም የይሖዋ ድርጅት የሚሰጠውን መመሪያ የመከተልን አስፈላጊነት ቀርጾብኛል።
አባቴና እናቴ በጠቅላላ ዘጠኝ ልጆች ወለዱ። ጥቅምት 1, 1909 ሦስተኛ ልጃቸው ሆኜ ተወለድኩ። በአጠቃላይ ስድስታችን የእማማን ጥሩ ምሳሌ በመከተል ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።
ራስን መወሰንና መጠመቅ
በአሥራዎቹ ዕድሜዬ ማብቂያ አካባቢ ራሴን ለይሖዋ ከወሰንኩ በኋላ በ1927 ይህን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ጥምቀቱ የተከናወነው ሲያትል ውስጥ በሚገኝ ቀድሞ የመጥምቃውያን ቤተ ክርስቲያን ንብረት በሆነ አንድ አሮጌ ሕንፃ ውስጥ ነበር። የቤተ ክርስቲያኑን አሮጌ ጉልላት አንስተውት ስለነበር ተደሰትኩ። ምድር ቤት ወደሚገኘው ገንዳ ይዘውን ሄዱና እዚያ ረጃጅም ጥቁር ካባዎች ለበስን። ወደ ቀብር የምንሄድ እንመስል ነበር።
ከጥቂት ወራት በኋላ እንደገና ወደ ሲያትል ሄድኩና ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት አገለገልኩ። እንዴት ማገልገል እንደሚቻል ያሳየኝ የነበረው ወንድም “አንተ እዚህ አካባቢ ትሠራለህ እኔ በሌላኛው አቅጣጫ አገለግላለሁ” አለኝ። ምንም እንኳ ፍርሃት ቢሰማኝም የተለያዩ ቡክሌቶችን ለአንዲት በጣም ጥሩ ፍላጎት ለነበራት ሴት አበረከትኩ። ወደ ኢለንዝበርግ ስመለስ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል የቀጠልኩ ሲሆን አሁን ወደ 70 የሚጠጉ ዓመታት ቢያልፉም ይህ አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ ይሰጠኛል።
በዋናው መሥሪያ ቤት ማገልገል
ብዙም ሳይቆይ በብሩክሊን ቤቴል ማለትም በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት የሚያገለግል አንድ ወንድም ቤቴል ውስጥ በፈቃደኝነት እንዳገለግል አበረታታኝ። ይህን ከተነጋገርን ብዙም ሳይቆይ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ ለቤቴል አገልግሎት ተጨማሪ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ የሚገልጽ ማስታወቂያ ወጣ። ለመግባት እንደምፈልግ አመለከትኩ። መጋቢት 10, 1930 ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው ቤቴል ውስጥ ማገልገል እንድጀምር የሚገልጽ ደብዳቤ ሲደርሰኝ የተሰማኝን ደስታ ፈጽሞ አልረሳውም። በዚህ መንገድ ‘ለማይጠፋ መብል’ መሥራቱን የሙሉ ጊዜ ሥራ አድርጌ ተያያዝኩት።
ምናልባት ቀለም የመቀባት ችሎታ ስላለኝ አንዳንድ ነገሮች እንዲቀባ ይመደባል ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ የመጀመሪያው ሥራዬ ፋብሪካ ውስጥ የጽሑፍ መስፊያ ማሽን ላይ መሥራት ነበር። ምንም እንኳ አሰልቺ ቢሆንም ይህንን ሥራ ለስድስት ዓመታት ሠርቼአለሁ። “አሮጌው የጦር መርከብ” የሚል ቅጽል ስም ያወጣንለት ግዙፉ ሮተሪ ማተሚያ ቡክሌቶችን እያተመ በመሣሪያ አማካኝነት ወደ ፋብሪካው የታችኛ ክፍል ይልክልን ነበር። ማተሚያው ከሚያቀርብልን ቀድመን ለመጨረስ በመሞከር እንደሰት ነበር።
ከዚህ በኋላ የሸክላ ማጫወቻ እንሠራበት የነበረውን ዲፓርትመንት ጨምሮ ብዛት ባላቸው ዲፓርትመንቶች ውስጥ ሠርቻለሁ። በሸክላ ማጫወቻዎች ተጠቅመን በሸክላ ላይ የተቀረጹ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶችን በሰዎች በር ላይ ሆነን እናሰማ ነበር። በእጅ የሚንጠለጠል የሸክላ ማጫወቻ የተፈለሰፈውም ሆነ የተመረተው ዲፓርትመንታችን ውስጥ ባሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ነበር። ይህ የሸክላ ማጫወቻ በሸክላ ላይ የተቀረጸውን ነገር ከማጫወቱም በተጨማሪ ቡክሌቶችና ምናልባትም ሳንድዊች መያዝ የሚችሉ ልዩ ልዩ ክፍሎች ነበሩት። በ1940 ዲትሮዪት ሚችጋን ውስጥ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የዚህን አዲስ መሣሪያ አጠቃቀም የማሳየት መብት አግኝቼ ነበር።
ሆኖም በዚህ ጊዜ አዳዲስ መሣሪያዎችን ከመፈልሰፍ በተጨማሪ ያደረግነው ነገር ነበር። አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ማስተካከያዎች አድርገን ነበር። ለምሳሌ የይሖዋ ምሥክሮች የመስቀልና የዘውድ ቅርጽ ያለው አርማ ደረታቸው ላይ ይለጥፉ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሳይሆን ቀጥ ባለ እንጨት ላይ እንደተሰቀለ በዚህ ጊዜ ተረዳን። (ሥራ 5:30) በዚህ የተነሳ እነዚህን አርማዎች ማድረግ አቆምን። ከአርማዎቹ ላይ ማያያዣዎቹን መንቀል የእኔ ሥራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ወርቁ ቀለጠና ተሸጠ።
ምንም እንኳ በየሳምንቱ ለአምስት ቀናት ተኩል በሥራ የተወጠርን ቢሆንም በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንካፈል ነበር። አንድ ቀን አሥራ ስድስታችን ተያዝንና ብሩክሊን በሚገኝ አንድ እስር ቤት ውስጥ ታሰርን። የታሰርነው ለምንድን ነው? በዚያን ጊዜ ሁሉም ሃይማኖቶች የሐሰት ሃይማኖት እንደሆኑ እንናገር ነበር። ስለዚህ በአንድ በኩል “ሃይማኖት ወጥመድና ማጭበርበሪያ ነው” የሚል በጀርባው ደግሞ “አምላክንና ንጉሡን ክርስቶስን አገልግሉ” ተብሎ የተጻፈባቸው መፈክሮች ይዘን እንዞር ነበር። የታሰርነው እነዚህን መፈክሮች ይዘን በመዞራችን ምክንያት ሲሆን የመጠበቂያ ግንብ ጠበቃ የነበረው ሄይደን ኮቪንግተን ዋስ ሆኖ አስፈታን። በዚያን ጊዜ የአምልኮ ነፃነትን የሚመለከቱ ብዙ ጉዳዮች በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታዩ ስለነበር ቤቴል ውስጥ ሆኖ ስላገኘናቸው ድሎች ከሌሎች በፊት ሪፖርት መስማት ያስደስት ነበር።
በመጨረሻ ቀለም የመቀባት ችሎታዬን እንድጠቀምበት በሚጠይቅ ሥራ ላይ ተመደብኩ። በኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ የራሳቸው ምክር ቤት ካሏቸው አምስት ክፍላተ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው በስቴትን አይላንድ ደብልዩ ቢ ቢ አር የተባለ የሬዲዮ ጣቢያ ነበረን። የሬዲዮ ጣቢያው ግንቦች ከ60 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ሲሆን የተለያዩ መሣሪያዎች የያዙ ሦስት አንቴናዎች ነበሯቸው። ዘጠና ሴንቲ ሜትር ርዝመት፣ ሃያ ሴንቲ ሜትር ስፋት ባለው በጠንካራ ገመድ በታሰረ ጠፍጣፋ እንጨት ላይ እቀመጥና አብሮኝ የሚሠራው ሰው ገመዱን እየጎተተ ወደ ላይ ያወጣኝ ነበር። ከመሬት በጣም ከፍ ብሎ በሚገኝ ቦታ፣ በዚያች አነስተኛ መቀመጫ ላይ ተቀምጬ የአንቴና ሽቦዎቹንና ግንቦቹን ቀብቼአለሁ። አንዳንዶች ይህንን ሥራ ስትሠሩ ብዙ ጸልያችሁ ነበር? ብለው ጠይቀውኛል!
በክረምት እንሠራው የነበረውን የፋብሪካ ሕንፃ መስኮቶች የማጠብና የመስኮቶቹን ታችኛ ክፈፍ ቀለም የመቀባት ሥራ ፈጽሞ አልረሳውም። የክረምት ዕረፍታችን ብለን እንጠራው ነበር። መጎተቻ ያለው የእንጨት መወጣጫ እንሠራና ባለ ስምንቱን ፎቅ ሕንፃ እንወጣና እንወርድ ነበር።
ደጋፊ ቤተሰብ
በ1932 አባቴ ሞተ። ወደ ቤት ተመልሼ እናቴን መጦር ይኖርብኝ እንደሆነና እንዳልሆነ ማሰብ ጀመርኩ። ስለዚህ አንድ ቀን ከምሳ በፊት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ራዘርፎርድ በሚቀመጥበት በዋናው ጠረጴዛ ላይ አንድ ማስታወሻ አስቀመጥኩ። በማስታወሻው ላይ ላነጋግረው እንደምፈልግ ገልጬ ነበር። ያለኝን ሐሳብ ካወቀና እቤት የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች እንዳሉኝ ከተረዳ በኋላ “ቤቴል ቆይተህ የጌታን ሥራ መሥራት ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀኝ።
“አዎን፣ እፈልጋለሁ” ብዬ መለስኩለት።
ቤቴል ለመቆየት ባደረግኩት ውሳኔ ትስማማ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ለእናቴ እንድጽፍላት ሐሳብ አቀረበልኝ። ደብዳቤውን ከጻፍኩላት በኋላ ሙሉ በሙሉ እንደምትስማማ የሚገልጽ መልስ ላከችልኝ። ወንድም ራዘርፎርድ ያሳየኝን ደግነትና የሰጠኝን ምክር በጣም ነው የማደንቀው።
በቤቴል ባሳለፍኳቸው አያሌ ዓመታት እናቴ እኔን ታበረታታኝ እንደነበረ እኔም ለቤተሰቦቼ ዘወትር እየጻፍኩ ይሖዋን እንዲያገለግሉ አበረታታቸው ነበር። እናቴ ሐምሌ 1937 ሞተች። ለቤተሰባችን ትልቅ በረከት ነበረች! ከቤተሰባችን ውስጥ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑት ታላቅ ወንድሜ ፖል፣ ታላቅ እህቴ ኤስተር እና ታናሽ እህቴ ሎአስ ብቻ ነበሩ። ሆኖም ፖል ለሥራችን ቀና አመለካከት የነበረው ሲሆን እርሱ በሰጠን ቦታ ላይ የመጀመሪያ የመንግሥት አዳራሻችንን ሠርተናል።
በ1936 እህቴ ኢቭ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነች። በዚያው ዓመት ራልፍ ቶማስን ያገባች ሲሆን በ1939 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችን ለማገልገል በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ተመደቡ። ከጊዜ በኋላ በመንግሥቱ ሥራ እገዛ ለማበርከት ወደ ሜክሲኮ የተዛወሩ ሲሆን እዚያም 25 ዓመታት አሳልፈዋል።
በተጨማሪም አሊስ እና ፍራንሲስ የተባሉ እህቶቼ በ1939 አቅኚ ሆኑ። አሊስ በ1941 በሴንት ሉዊስ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የሸክላ ማጫወቻ መሣሪያውን አጠቃቀም በተመለከተ ገለጻ በሚደረግበት ጠረጴዛ ላይ ሠርቶ ማሳያ ስታቀርብ መመልከቴ በጣም አስደስቶኛል። ለዚህ መሣሪያ መሠራት እኔም የበኩሌን አስተዋጽዖ አበርክቻለሁ። ምንም እንኳ አሊስ በቤተሰብ ኃላፊነቶች የተነሳ አልፎ አልፎ አቅኚነቷን ለማቋረጥ ብትገደድም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በአጠቃላይ 40 ዓመታት አሳልፋለች። ፍራንሲስ በ1944 በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ከተማረች በኋላ ፖርቶ ሪኮ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በሚስዮናዊነት አገልግላለች።
የቤተሰባችን የመጨረሻዎቹ ሁለት ልጆች ማለትም ጆኤል እና ኤልውድ በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሞንታና ውስጥ አቅኚ ሆኑ። ጆኤል ታማኝ ምሥክር ሆኖ የጸና ሲሆን አሁን በዲቁና እያገለገለ ነው። ኤልውድ በ1944 ቤቴል ሲገባ በጣም ተደሰትኩ። እኔ ከቤት ስወጣ አምስት ዓመት አይሞላውም ነበር። በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው በፋብሪካ ሕንፃ ላይ ያለውን “የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ አንብቡ” የሚለውን ማሳሰቢያ የጻፍነው ከእርሱ ጋር ሆነን ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ይህንን ማሳሰቢያ ያነበቡ ምን ያህል ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ለማንበብ ተገፋፍተው ይሆን በማለት ሁልጊዜ ራሴን እጠይቃለሁ።
ኤልውድ ኤማ ፍሊትን እስካገባበት እስከ 1956 ድረስ በቤቴል አገልግሏል። ኤልውድ እና ኤማ ለብዙ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሠሩ ሲሆን ለጥቂት ጊዜያት በአፍሪካ ኬንያ ውስጥ እንዲሁም በስፔይን አገልግለዋል። ኤልውድ ካንሰር ያዘውና በ1978 ስፔይን ውስጥ ሞተ። ኤማ እስካሁን ድረስ ስፔይን ውስጥ በአቅኚነት እያገለገለች ነው።
ትዳርና ቤተሰብ
መስከረም 1953 በነበርኩበት በብሩክሊን ሴንተር ጉባኤ ውስጥ የነበረች አሊስ ሪቬራ የተባለችን አቅኚ ለማግባት ከቤቴል ወጣሁ። ሰማያዊ ተስፋ እንዳለኝ ብነግራትም ልታገባኝ ተስማማች።—ፊልጵስዩስ 3:14
ከ23 ዓመት የቤቴል ኑሮ በኋላ እኔና አሊስ በአቅኚነት ሥራ ለመቀጠል የሚያስችለንን ገንዘብ ለማግኘት በቀለም ቀቢነት ሥራ መሰማራት ከፍተኛ ለውጥ ማድረግን የሚጠይቅ ነበር። አሊስ በጤና ችግሮች የተነሳ አቅኚነትን ለማቆም ብትገደድም ለእኔ ምንጊዜም የድጋፍ ምንጭ ነበረች። በ1954 አሊስ የመጀመሪያ ልጃችንን እርጉዝ ነበረች። ልጃችን ጆን ደህና ቢሆንም አሊስ የተገላገለችው በሰላም አልነበረም። በቀዶ ሕክምና እንድትወልድ በሚደረግበት ጊዜ ብዙ ደም ስለፈሰሳት ዶክተሮች ትተርፋለች ብለው አላሰቡም ነበር። እንዲያውም አንድ ጊዜ ሐኪሞች የልብ ትርታዋን ለማዳመጥ በጣም ተቸግረው ነበር። ሆኖም ሌሊቱን በሕይወት አደረች፤ ከዚያም ቀስ በቀስ ሙሉ በሙሉ ዳነች።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአሊስ አባት ሲሞቱ ከእናቷ ጋር ለመኖር ወደ ሎንግ አይላንድ ተዛወርን። መኪና ስላልነበረን የምጓጓዘው በእግሬ አሊያም ደግሞ በአውቶብስና በባቡር ነበር። በዚህ መንገድ በአቅኚነት ሥራ መቀጠልና ቤተሰቤን መደገፍ ችዬአለሁ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚገኘው ደስታ ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕትነት ሊከፈልለት ይገባል። ጥሩ የቤዝ ቦል ተጫዋች ቢሆንም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ሲል ይህንን ሥራውን እንዳቆመው እንደ ጆ ናታል ያሉ ሰዎችን መርዳቱ ካገኘኋቸው ብዙ በረከቶች መካከል አንዱ ነው።
በኒው ዮርክ ውስጥ ሁኔታዎች እየከበዱ ሲሄዱ በ1967 አሊስንና ጆንን ይዤ ወደ ትውልድ አገሬ ወደ ኢለንዝበርግ ተመለስኩ። የእናቴ የልጅ ልጆችና ልጆቻቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈሉ ማየቱ መልሶ የሚክስ መሆኑን ተመልክቻለሁ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ቤቴል ገብተው እያገለገሉ ነው። ጆን፣ ሚስቱና ልጆቹም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ናቸው።
የሚያሳዝነው በ1989 ውዷን ሚስቴን አሊስን በሞት አጣሁ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሥራ መወጠሬ ሐዘኔን እንድቋቋም ረድቶኛል። እኔና እህቴ አሊስ አብረን በአቅኚነት እያገለገልን ነው። እንደገና በአንድ ቤት ውስጥ አብረን መኖሩና በዚህ አንገብጋቢ ሥራ ራሳችንን ማስጠመዳችን እንዴት ደስ ይላል!
በ1994 ፀደይ ወቅት ከ25 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤቴልን ጎበኘሁ። ከ40 ዓመታት በፊት አብሬያቸው ስሠራ የነበሩትን ብዙዎቹን ማየቱ ምንኛ ያስደስታል! በ1930 ቤቴል ስገባ የቤተሰቡ አባላት 250 ብቻ የነበሩ ሲሆን ዛሬ ግን ብሩክሊን የሚገኙት የቤቴል ቤተሰብ አባላት ከ3,500 በላይ ሆነዋል!
በመንፈሳዊ ምግብ መደገፍ
አብዛኛውን ጊዜ በጠዋት ተነስቼ እቤታችን አቅራቢያ በሚገኘው ያኪማ ወንዝ ዳርቻ ቀስ እያልኩ በእግሬ እጓዛለሁ። ከዚያ ሆኜ አናቱ በበረዶ የተሸፈነውን ሬኒር የተባለውን አስገራሚ ተራራ እመለከታለሁ። ይህ ተራራ ከ4,300 ሜትር በላይ ከፍታ አለው። በጣም ብዙ የዱር አራዊት ይገኙበታል። አልፎ አልፎ ድብ አያለሁ፤ እንዲያውም አንድ ጊዜ ግዙፍ የድብ ዝርያ አይቻለሁ።
ብቻዬን የምሆንባቸው እነዚህ ጊዜያት አስደናቂ በሆኑት የይሖዋ ዝግጅቶች ላይ እንዳሰላስል አስችለውኛል። አምላካችንን ይሖዋን በታማኝነት እያገለገልኩ ለመቀጠል የሚያስችል ጥንካሬ እንዳገኝ እጸልያለሁ። በተጨማሪም ቀስ እያልኩ በእግሬ ወዲያ ወዲህ ስል መዘመር እወዳለሁ። በተለይ “ታላቁ አምላክ ፈቃድህን ለመፈጸም መሃላ ገብተናል፤ ሥራህን የምታከናውነው በጥበብ ነው። አፍቃሪ ልብህን ለማስደሰት የበኩላችንን ማድረግ እንደምንችል አውቀናል።” የሚሉ ስንኞች ያሉትን “የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት” የተባለውን መዝሙር መዘመር ያስደስተኛል።
የይሖዋን ልብ የሚያስደስት ሥራ ለመሥራት በመምረጤ ደስተኛ ነኝ። የምጠባበቀውን ሰማያዊ ሽልማት እስካገኝ ድረስ ይህንን ሥራ እየሠራሁ መቀጠል እችል ዘንድ እጸልያለሁ። ይህ ታሪክ ሌሎችም ሕይወታቸውን ‘ለማይጠፋ መብል’ ለመሥራት እንዲጠቀሙበት እንዲገፋፋቸው እመኛለሁ።—ዮሐንስ 6:27
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኤልውድ “የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ አንብቡ” የሚለውን ማሳሰቢያ ሲጽፍ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1940 በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከግራንት ሱተርና ጆን ኩርዘን ጋር አዲሱን የሸክላ ማጫወቻ ሳሳይ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1944 ሁላችንም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነበርን። ከግራ ወደ ቀኝ፦ ዴቪድ፣ አሊስ፣ ጆኤል፣ ኢቭ፣ ኤልውድ እና ፍራንሲስ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉት ወንድማማቾችና እህትማማቾች ከግራ ወደ ቀኝ፦ አሊስ፣ ኢቭ፣ ጆኤል፣ ዴቪድ እና ፍራንሲስ