አምላክ፣ ፖለቲካዊ መንግሥትና አንተ
“አየርላንድ ውስጥ ፍቺን አስመልክቶ ሊካሄድ በታቀደው ሕዝበ ውሳኔ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ተፋጠጡ”
ዘኒው ዮርክ ታይምስ በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣው ይህ ርዕስ በዛሬው ጊዜ ሰዎች መንግሥት የሚፈልገውን ነገር እንምረጥ ወይስ ቤተ ክርስቲያናችን የምታስተምረውን የሚል አሻሚ ምርጫ ሊገጥማቸው እንደሚችል ያሳያል።
ጽሑፉ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ፍቺን የሚከለክለው ሕግ ከሕገ መንግሥቱ ይሰረዝ ወይስ እንዳለ ይቀጥል በሚለው ጉዳይ ላይ ድምፅ ከመሰጠቱ አንድ ወር ከማይሞላ ጊዜ በፊት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሮማ ካቶሊክ አማኞች በሚኖሩባት አየርላንድ በመንግሥት መሪዎችና በሃይማኖት መሪዎች መካከል ያልተለመደ ግጭት ተከስቷል።” መንግሥት ፍቺን የሚከለክለው ሕግ እንዲሰረዝ ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግን ፍቺንና ፈትቶ ሌላ ማግባትን አጥብቃ ትቃወማለች። የአየርላንድ ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያኗ ከያዘችው አቋምና መንግሥት ካቀረበው ሐሳብ አንዱን መምረጥ ነበረባቸው። በውጤቱም መንግሥት በጠባብ ልዩነት አሸንፏል።
ከዚህ የከፋው ግን በሰሜን አየርላንድ የሚኖሩ ሰዎች በብሔራዊ ሉዓላዊነት ጉዳይ ለብዙ ዓመታት ሲያካሄዱ የቆዩት የከረረ ግጭት ነው። ብዙ ሰዎች ተገድለዋል። የሮማ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ሰሜን አየርላንድን ለሚያስተዳድረው የብሪታንያ መንግሥት መገዛት ይሻላል ወይስ መላውን አየርላንድ የሚያስተዳድር አንድ ማዕከላዊ መንግሥት ቢኖር ይሻላል በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው።
በተመሳሳይም በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች የካቶሊክና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ጨምሮ የተለያየ እምነት አባላት ዳር ድንበርን ለማስጠበቅ ተብሎ በሚካሄድ ጦርነት እንዲዋጉ ጥያቄ አቅርበዋል። ተራው ዜጋ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ትእዛዝ የትኛው ነው? መታዘዝ ያለበት መንግሥትን እንወክላለን የሚሉትን ሰዎች ነው ወይስ “አትግደል፣ . . . ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” ሲል ያዘዘውን አምላክ?—ሮሜ 13:9
እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እኔን በፍጹም ሊነካ አይችልም ብለህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም ሊነካህ ይችላል። እንዲያውም ይህ ጉዳይ አሁንም እንኳ ሊመለከትህ ይችላል። ኦስካር ኩልማን የተባሉ አንድ የሃይማኖት ምሁር ዘ ስቴት ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በአሁኑ ዘመን ያሉ ክርስቲያኖች ከአምባገነን መንግሥታት በሚሰነዘርባቸው ዛቻ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ ሊወስዷቸው ስለሚችሉ ወይም የግድ ስለሚወስዷቸው የሕይወትና የሞት ጉዳይ የሆኑ ውሳኔዎች” ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ከዚህም በተጨማሪ “‘የተለመዱ’ እና ‘የዕለት ተዕለት’ ገጠመኞች በሚባሉት ሁኔታዎች ሥር የሚኖረውን ክርስቲያን ጨምሮ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ክርስቲያን በመሆኑ ብቻ የሚያጋጥመውን ከባድ ችግር ተቀብሎ የመወጣት ትልቅ ኃላፊነት ያለበት” ስለ መሆኑም ተናግረዋል።
ታዲያ በሃይማኖትና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት በዛሬው ጊዜ ያሉትን ክርስቲያኖች ትኩረት ሊስብ ይገባልን? አዎን፣ ትኩረታቸውን ሊስብ ይገባል። ከጥንት ዘመን ጀምሮ ክርስቲያኖች ለፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ለማዳበር ሲጥሩ ቆይተዋል። መሪያቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በሮማ መንግሥት ችሎት ፊት ቀርቦ ከተፈረደበት በኋላ ተገድሏል። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቲያናዊ ግዴታዎቻቸውን የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ከጣለባቸው ግዴታዎች ጋር ማስታረቅ ነበረባቸው። እንግዲያው ከባለ ሥልጣኖች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ወደ ኋላ መለስ ብሎ መከለሱ በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚጠቁሙ መምሪያዎችን ለማግኘት ይረዳል።
[ምንጭ]
Tom Haley/Sipa Press