ሕዝበ ክርስትና የዚህ ዓለም ክፍል ለመሆን የበቃችው እንዴት ነው?
የጥንቱ የክርስትና እምነት የተጀመረባት የሮማ መንግሥት ከጊዜ በኋላ ፈራረሰች። ብዙ ታሪክ ጸሐፊዎች ይህ የሮማ መንግሥት መፈራረስ ክርስትና በአረማዊነት ላይ የመጨረሻውን ድል የተቀዳጀበት ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ። የአንግሊካን ጳጳስ የሆኑት ኢ ደብልዩ ባረንዝ ከዚህ ለየት ያለ ሐሳብ በመግለጽ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የጥናቱ የሮማና የግሪክ ሥልጣኔ ሲፈራርስ ክርስትና ቅቡዕ በሆነው በኢየሱስ የሚያምን የተከበረ እምነት መሆኑ አበቃ። ከዚህ ይልቅ በመፈራረስ ላይ ያለውን ዓለም ለማያያዝ የሚያገለግል ሃይማኖት ሆነ።“-ዘ ራይዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ
የሮማ መንግሥት ከመውደቁ በፊት በሁለተኛው፣ በሦስተኛውና በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖሩ የነበሩ ኢየሱስን እንከተላለን የሚሉ ሰዎች በብዙ መንገዶች ራሳቸውን ከሮማዊው ዓለም ለይተው እንደነበረ ታሪክ መዝግቧል። ይሁን እንጂ ኢየሱስና ሐዋርያቱ አስቀድመው እንደተናገሩት ሁሉ የመሠረተ ትምህርት፣ የአኗኗርና የድርጅታዊ አሠራር ክህደት እየተስፋፋ እንደመጣም ታሪክ ይገልጻል። (ማቴዎስ 13:36-43፤ ሥራ 20:29,30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3-12፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:16-18፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3, 10-22) ውሎ አድሮ ከግሪካዊውና ከሮማዊው ዓለም ጋር ለመስማማት ሲሉ አቋማቸውን ማላላት እንደጀመሩ እንዲያውም ክርስቲያኖች ነን ይሉ የነበሩ አንዳንዶች የዓለምን አረማዊው እምነቶች፣ (በዓላትን ማክበር እንዲሁም የእናት ሴት አምላክትንና ሦስትነት ያለውን አምላክ ማምለክን የመሳሰሉ እምነቶችን) ፍልስፍናዎችን (ነፍስ ዘላለማዊ ናት ብሎ ማመንን የመሳሰሉ ፍልስፍናዎችን) እንዲሁም አስተዳደራዊ መዋቅሮችን (የቀሳውስት ክፍል በመፈጠሩ እንደታየው ያሉትን) መቀበል ጀመሩ። በፊት አረመኔዎች የነበሩ ብዙ ሰዎች ግልብጥ ብለው ወደ ክርስትና እንዲመጡ የማረካቸው ይህ መልኩን የለወጠ የክርስትና እምነት ነው። የሮማ ንጉሠ ነገሥታት ይህንን መልኩን ለውጥ የተጠናከረውን የክርስትና እምነት በመጀመሪያ ለማጥፋት ጥረት አድርገዋል። በኋላ ግን ስምምነት ላይ ደረሱና ለራሳቸው መጠቀሚያ አደረጉት።
በዓለም ተሸነፈች
አውጉስየስ ኒያንደር የተባሉት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ በ“ክርስትና“ እና በዓለም መካከል የተመሠረተውን ይህ አዲስ ዝምድና ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ገልጸዋል። ክርስቲያኖች ከዓለም የተለዩ መሆናቸውን ቢያቆሙ “ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዓለም ጋር ስለምትደባለቅ . . . ንጽሕናዋን ታጣለች፤ እንዲሁም ዓለምን ያሸነፈች መስላ እሷ ራሷ በዓለም ትሸነፋለች“ ብለዋል።- ጄነራል ሄስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ሪሊጅን ኤንድ ቸርች፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 161
ይኸው ነገር ደረሰ። በአራተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሮማ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ በዘመኑ የነበረውን የ“ክርስትና“ ሃይማኖት በመፈራረስ ላይ ያለውን ግዛቱን አንድ ለማድረግ ተጠቅሞበት ነበር። ይህን ዓላም ለማሳካት ክርስቲይና ነን ይሉ ለነበሩት ሰዎች የሃይማኖት ነፃነት ሰጠና አረማውያን ካህናት የነበሯቸውን አንዳንድ መብቶች ወደ ቀሳውስቱ አዛወረ። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “ቆስጠንጢኖስ ቤተ ክርስቲያኗ ከዓለም መራቋን አቁማ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን እንድትቀበል አደረገ። አረማዊው ኅብረተሰብም ቤተ ክርስቲያኗን የሚቀበልበትን መንገድ አመቻቸ።“
የመንግሥት ሃይማኖት
ቆስጠንጢኖስ ከሞተ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ጁሊያን (361-363 እዘአ የገዛ) ክርስትናን በመቃወም አረማዊነት እንዲያንሠራራ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ግን አልተሳካለትም። ወደ 20 ከሚጠጉ ዓመት በኋላ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ቴዎዶሲየስ አረማዊነትን በማገድ የሮማ መንግሥት ሃይማኖት በሥላሴ የሚያምን “ክርስትና“ እንዲሆን አደረገ። ፈረንሳዊው ታሪክ ጸሐፊ ኦንሪ ማሩ እንዲህ በማለት ነገሩን በትክክል አስቀምጠውታል፦ “የቴዎዶሲየስ የግዛት ዘመን ሲያበቃ ክርስትና ወይም በይበልጥ ትክክለኛ የሆነ አገላለጽ ለመጠቀም የጥንቱ የካቶሊክ እምነት ለጠቅላላው የሮም ዓለም ኦፊሴላዊ ሃይማኖት ሆነ።“ እውነተኛው ክርስትና በጥንቱ የካቶሊክ ሃይማኖት ተተካ። የካቶሊክ እምነትም ’የዓለም ክፍል’ ሆኖ ነበር። ይህ የመንግሥት ሃይማኖት ኢየሱስ ’ከዓለም አይደላችሁም’ ያላቸው የመጀመሪያ ተከታዮቹ ይከተሉት ከነበረው ሃይማኖት በእጅጉ የተለየ ነው።-ዮሐንስ 15:19
ታሪክ ጸሐፊና ፈላስፋ የነበሩት ፈረንሳዊው ሉዊ ሩዥየ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “ክርስትና እየተስፋፋች ስትሄድ የበፊት መልኳ ጨርሶ የማይታወቅ እስከሚሆን ድረስ አዳዲስ ለውጦችን አደረገች። . . . በምፅዋት ትተዳደር የነበረችው የጥንቷ የድኾች ቤተ ክርስቲያን ስትችል የመንግሥት የበላይ በመሆን ሳትችል ደግሞ ተስማምታ በእኩልነት የምትኖር ጀብደኛ ሆነች።“
የሮማ ካቶሊክ “ቅዱስ“ አውጉስቲን በአምስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የሥነ ጽሑፍ ሥራው የሆነውን ዘ ሲቲ ኦቭ ጎድ (የእግዚአብሔር ከተማ) የተባለ መጽሐፍ አወጣ። በጽሑፉ ውስጥ ሁለት ከተሞችን ማለትም “የእግዚአብሔርንና የዓለምን“ ከተሞች ምንነት ገልጿል። ይህ ጽሑፍ የካቶሊኮችንና የዓለምን መለያየት የሚያራምድ ነበርን? አልነበረም። ፕሮፌሰር ላትሬት እንዲህ አሉ፦ “አውጉስቲን ምድራዊና ሰማያዊ የሆኑት ሁለቱ ከተሞች እርስ በርሳቸው የተያያዙ መሆናቸውን በግልጽ ተናግሯል።“ (ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ፣ ማክሮፔድያ፣ ጥራዝ 4፣ ገጽ 506) የአውጉስቲን የመጀመሪያ ዓላማ ምንም ይሁን ምን ፍልስፍናውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ በመዋጥ ይበልጥ እንድትጠላለፍ አድርጓታል።
የተከፋፈለ መንግሥት
ቀዳማዊ ቴዎዶሲየስ በ395 እዘአ ሲሞት የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ለሁለት ተከፈለ። የምሥራቁ ወይም የባይዛንታይን ግዛት ዋና ከተማ (በፊት ባይዛንቲየም አሁን ደግሞ ኢስታንቡል በመባል የምትታወቀው) ኮንስታቲኖፕል ስትሆን (ከ402 እዘአ በኋላ) የምዕራቡ ግዛት ዋና ከተማ ደግሞ በኢጣልያ የምትገኘውን ራቬና ሆነች። በዚህም ምክንያት ሕዝበ ክርስትና በፖለቲካም ሆነ በሃይማኖት ተከፋፈለች። በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል ባለው ግንኙነት ረገድ የምሥራቁ መንግሥት (ታላቁ ቆስጠንጢኖስ በኖረበት ዘመን ይኖር የነበረውን) የቂሳርያውን ዩሴቢየስ ፍልስፍና ይከተል ነበር። ዩሴቢየስ ከዓለም የተለያችሁ ሁኑ የሚለውን የክርስትና መሠረታዊ ሥርዓት ችላ በማለት ንጉሠ ነገሥቱና መንግሥት ተዋኅደው አንድ ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ ይሆናሉ፤ እንዲሁም ንጉሠ ነገሥቱ በምድር ላይ የአምላክ ተወካይ ሆኖ ይሠራል የሚል አስተሳሰብ አምጥቶ ነበር። በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ያለው ይህ ትስስር በምሥራቅ በሚገኙት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ለብዙ መቶ ዘመናት ከሞላ ጎደል ቀጥሏል። የኦርቶዶክስ ጳጳስ የነበሩት ቲሞቲ ዋር ዘ ኦርቶዶክስ ቸርች በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ “ላለፉት አሥር መቶ ዘመናት ብሔራዊ ስሜት የኦርቶዶክስን ቤተ ክርስቲያን ሲያናጋት ቆይቷል“ በማለት ይህ ትስስር ያስከተለውን ውጤት ገልጸዋል።
በ476 እዘአ በወራሪ የጀርመን ጎሣዎች አማካኝነት የምዕራባዊው የሮማ ግዛት የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት ከሥልጣኑ ወረደ። ይህም የምዕራባዊው ሮማ የግዛት ዘመን ማክተሚያ ሆነ። ከዚህ ተከትሎ የመጣውን ፖለቲካዊ ክፍተት በተመለከተ ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “አዲስ ኃይል ተነሳች። እርሷም የሮማ ቤተ ክርስቲያን በሌላ አነጋገር የሮማ ጳጳስ የሚያስተዳድራት የሮማ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ቤተ ክርስቲያኒቲ የፈራረሰው የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ተተኪ ነኝ ብላ አመነች።“ ይኸው ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “የሮማ ጳጳሶች . . . ቤተ ክርስቲያኒቱ አላት የሚሉትን ዓለማዊ መስተዳድር ከቤተ ክርስቲያኒቱ የግዛት ክልል በላይ በማስፋት በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ አለን ማለትም ክርስቶስ ለጳጳሱ ሥልጣን የሰጣቸው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ በዓለማዊ መንግሥታትም ላይ ጭምር እንድትሠለጥን ነው የሚለውን ፍልስፍና ይዘዋል።“
ብሔራዊ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት
በመካከለኛው ዘመን ኦርቶዶክስም ሆነች የሮማ ካቶሊክ በፖለቲካ፣ በዓለማዊ ሴራዎችና በጦርነቶች ውስጥ ይበልጥ መጠላለፋቸውን ቀጠሉ። የ16ኛው መቶ ዘመን የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ተሐድሶ ከዓለም የተለየውን እውነተኛ ክርስትና መልሶ አመጣውን?
አላመጣም። በኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ወጥ አጥባቂዎቹ ሉተራውያን፣ ካልቪኒስቶችና እንግሊዛውያን የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆች . . . ሃይማኖታዊ አመለካከታቸው ከአውጉስቲን ሃይማኖታዊ አመለካከት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ስለመሰላቸው ከእርሱ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ጋር በጥብቅ ተቆራኝተው ቆይተዋል። . . . በ16ኛው መቶ ዘመን በአውሮፓ የተቋቋሙት ሦስቱም ዋና ዋና የፕሮቴስታንት ቅርንጫፎች . . . ከሳክሶኒ [ከመካከለኛው ጀርመን]፣ ከስዊዘርላንድ እንዲሁም ከእንግሊዝ ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች ድጋፍ ያገኙ ስለነበር በመካከለኛው ዘመን እንደነበረው ቤተ ክርስቲያን ሁሉ እነርሱም ከመንግሥት ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠው መሥራታቸውን ቀጠሉ።“
የተሐድሶ ለውጡ እውነተኛውን ክርስትና መልሶ ከማቋቋም ይልቅ ለፖለቲካዊ መንግሥታት የሚያጎበድዱና ጦርነቶቻቸውን የሚደግፉ በርካታ ብሔራዊና ክልላዊ አብያተ ክርስቲያናት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኖአል። እንዲያውም የካቶሊክም ሆነ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ሃይማኖታዊ ጦርነቶችን ቀስቅሰዋል። አን ሂስቶሪያንስ አፕሮች ቱ ሪሊጅን በተባለው መጽሐፋቸው አርኖልድ ቶይንቢ እንዲህ ዓይነቶቹን ጦርነቶች አስመልክተው የሚከተለውን ጽፈዋል፦ “ጦርነቶቹ በፈረንሳይ፣ በኔዘርላንድስ፣ በጀርመንና በአየር ላንድ የሚገኙ ፕሮቴስታንቶችና ካቶሊኮች እንዲሁም በእንግሊዝና በስኮትላንድ ያሉ የተለያዩ የፕሮቴስታንት አንጃዎች በመሣሪያ ኃይል አንዱ ሌላውን ለማፈን በግፍ ሲጨፋጨፉ የሚታይባቸው መድረኮች ሆኑ።“ አየር ላንድንና የቀድሞዋን ዩጎዝላቪያ የከፋፈሏቸው በአሁን ጊዜ የሚደረጉት ግጭቶች የሮማ ካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያኖች አሁንም ቢሆን በዚህ ዓለም ጉዳዮች ውስጥ በጥብቅ የተጠላለፉ መሆናቸውን ያሳያሉ።
ታዲያ ይህ ሁሉ ከዓለም የተለየ እውነተኛ ክርስትና በምድር ላይ የለም ማለት ነውን? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይህንን ጥያቄ ይመልሳል።
[በገጽ 10 እና 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“ክርስትና“ የመንግሥት ሃይማኖት ሊሆን የበቃው እንዴት ነው?
ክርስትና በፍጹም የዚህ ዓለም ክፍል መሆን የለበትም። (ማቴዎስ 24:3,9፤ ዮሐንስ 17:16) ሆኖም በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ’ክርስትና’ የሮማ መንግሥት ኦፊሴላዊ ሃይማኖት እንደሆነ የታሪክ መጻሕፍት ይነግሩናል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ከኔሮ (54-68 እዘአ የገዛ) አንስቶ እስከ ሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ የተነሱት የሮማ ንጉሠ ነገሥታት በሙሉ አንድም ክርስቲያኖችን አሳደው ነበር አለዚያም ስደት እንዲደርስባቸው ፈቅደው ነበር። በክርስቲያኖች ላይ ምንም እርምጃ እንዳይወሰድ የሚያዝዝ አዋጅ ያወጣው የመጀመሪያው ንጉሠ ነገሥት ጋሌኒየስ (253-268 እዘአ የገዛ) ነበር። ያን ጊዜም ቢሆን ክርስትና በግዛቱ ሁሉ የተወገዘ ሃይማኖት ነበር። ከጋሊኒየስ ሞት በኋላ ስደቱ ቀጠለ፤ በዲዮቅላጥያንና (284-305 እዘአ የገዛ) ከእርሱ ቀጥለው በተነሱት ነገሥታት ዘመን ደግሞ ጭራሽ እየበረታ ሄደ።
ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስትና ተለወጠ ከተባለበት ከአራተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ ግን ሁኔታው ተለወጠ። የቆስጠንጢኖስን ወደ ክርስትና “መለወጥ“ በተመለከተ ቴዎ-ኑቬል ኦንሲክሎፔዲ ካቶሊክ (ቴኦ-አዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ) የተባለው በፈረንሳይኛ የተጻፈ እንዲህ ይላል፦ “ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ንጉሥ ነኝ ይል ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የተጠመቀው እንኳ ሊሞት ሲል ነበር።“ ይሁን እንጂ በ313 እዘአ ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖችም ሆነ ለአረማውያን የሃይማኖት ነፃነት የሚሰጥ አዋጅ አወጁ። ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች የአምልኮ ነፃነት መስጠቱ ትልቅ ለውጥ ያስከተለ እርምጃ ነበር። የተሰጠው ነፃነት አረማዊ እምነቶች ብቻ ሳይሆኑ ክርስትናም ጭምር እንደ ፌሊጂዮ ሊኪታ ተደርጎ [ማለትም ሕጋዊ እንደሆነ ሃይማኖት ተደርጎ] እንዲታይ አስችሏል።“
ይሁን እንጂ ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው “እርሱ [ቆስጠንጢኖስ] ክርስትናን የመንግሥቱ ሃይማኖት እንዲሆን አላደረገም።“ የፈረንሳይ ኢንስቲትዩት አባል የሆኑት ፈረንሳዊው ታሪክ ጸሐፊ ዣንሬሜ ፓላንክ “የሮማ መንግሥት ግን . . . አረማዊ መንግሥት ሆኖ ቆይቷል። ቆስጠንጢኖስ ክርስቶስ የመሠረተው ሃይማኖት ተከታይ ሲሆን ይህ አምልኮ እንዲያቆም አላደረገም“ ሲሉ ጽፈዋል። ዘ ሌጋሲ ኦቭ ሮማ በተሰኘው ጽሑፋቸው ላይ ፕሮፌሰር ኸርነስት ባርከር እንዲህ ብለዋል፦ “[ቆስጠንጢኖስ ያገኘው ድል] ክርስትና ወዲያውኑ የመንግሥት ሃይማኖት ሆን እንዲቋቋም አላደረገም። ቆስጠንጢኖስ ክርስትናን በግዛቱ ውስጥ ካሉት ሕዝባዊ አምልኮዎች እንደ አንዱ ሆኖ እንዲቆጠር በማድረጉ ብቻ ረክቶ ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት ሰባ ዓመታት የጥንቶቹ አረማዊ የሃይማኖት ሥርዓቶች በሮማ ውስጥ በይፋ ይካሄዱ ነበር።“
ስለዚህ በዚያ ዘመን “ክርስትና“ በሮማ ግዛት ውስጥ ሕጋዊ አቋም ያለው ሃይማኖት ነበር። ታዲያ ሙሉ በሙሉ ኦፊሴላዊ የመንግሥት ሃይማኖት የሆነው መቼ ነበር? በኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ ላይ እንደሚከተለው እናነባለን፦ “በክርስቲያኖች ላይ ስደት አስነስቶ ከነበረው ከጁሊያን [361-363 እዘአ] በስተቀር ከቆስጠንጢኖስ በኋላ የተነሱት ነገሥታት በሙሉ የእርሱን [የቆስጠንጢኖስን] ፖሊሲ ተከትለው ነበር። ከጁሊያን ሞት በኋላ ግን ስደቱ በድንገት አቆመ። በመጨረሻም በአራተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ታላቁ ቴዎዶሲየስ (379-395 እዘአ) የመንግሥቱ ሃይማኖት ክርስትና እንዲሆን በማድረግ አረማዊ አምልኮ እንዳይካሄድ አገደ።“
የዚህን ሁኔታ እውነታነት ሲያረጋግጡና አዲሱ የመንግሥት ሃይማኖት ምን እንደነበር ሲገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑርና ታሪክ ጸሐፊ የነበሩት ኤፍ ጄ ፎክስ ጃክሰን እንዲህ ብለው ጽፈዋል፦ “በቆስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት ክርስትና እና የሮማ መንግሥት እርስ በርስ ተባባሪ ሆነው ነበር። በቴዎዶሲየስ ዘመነ መንግሥት ደግሞ አንድ ላይ ተሳሰሩ። . . . ከዚያ ወዲያ አብን ወልድንና መንፈስ ቅዱስን እኩል ሰጥተው የሚያፈቅሩ ሁሉ ካቶሊክ ይባሉ ጀመር። የንጉሠ ነገሥቱ መላው የሃይማኖት ፖሊሲ በዚህ ላይ የተመሠረተ ነበር። በዚህም ምክንያት ብቸኛው የሮማውያን ሕጋዊ ሃይማኖት የካቶሊክ ሃይማኖት ሆነ።“
ዣንሬሜ ፓላንክ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “ቴዎዶሲየስ አረማዊ ሃይማኖቶችን ሲዋጋ ጥናታዊውን [የካቶሊክ] ቤተ ክርስቲያን ይደግፍ ነበረ። በ380 እዘአ የመንግሥቱ ዜጎች በሙሉ የፓፓ ዳማሰስንና [የሥላሴ እምነት ደጋፊ የሆነውን] የአሌክሳንድርያውን ጳጳስ እምነት ይዘናል እንዲሉ የሚያዝዝና ይህንን አንቀበልም የሚሉትን ግን የአምላኮ ነፃነት የሚከለክል አዋጅ አወጣ። በኮንስታንቲኖፕል የተካሄደውም ታላቅ ጉባኤ (381) መናፍቅነትን ሁሉ የሚያወግዝ እንዲሁም ንጉሠ ነገሥቱ መናፍቅነትን የሚደግፍ ጳጳስ አለመኖሩን እንዲከታተል የሚያዝዝ ነበር። [የሥላሴ እምነት ደጋፊ የሆነው] የኒቅያው የክርስትና እምነት በደንብ የሚታወቅ የመንግሥት ሃይማኖት ሆኖ ነበር። . . . ቤተ ክርስቲያኒቱ ከመንግሥ ጋር በቅርብ የተሳሳረች ስትሆን መንግሥትም እርሷን ይደግፍ ነበር።“
እንግዲያው የሮማ መንግሥት ሃይማኖት የሆነው በሐዋርያት ዘመን የነበረው ያልተበረዘው ክርስትና አይደለም። የመንግሥት ሃይማኖት በሆነው በቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ቴዎዶሲየስ አስገዳጅነት የተመሠረተውና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምትከተለው በዚያን ጊዜም ሆነ ዛሬ የዚህ ዓለም ክፍል የሆነው በአራተኛው መቶ ዘመን የተቋቋመው በሥላሴ የሚያምነው የካቶሊክ እምነት ነው።
[ምንጭ]
Emperor Theodosius I: Real Academia de la Historia, Madrid (Foto Oronoz)
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Scala/Art Resource, N.Y.