የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 3/15 ገጽ 26-30
  • ታላቁ ቆስጠንጢኖስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታላቁ ቆስጠንጢኖስ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ታሪካዊው ቆስጠንጢኖስ
  • ቆስጠንጢኖስ በቀየሰው ስልት ውስጥ ሃይማኖት የተጫወተው ሚና
  • ክርስቲያን ሆኖ ያውቃልን?
  • “ቅዱስ” ነውን?
  • ጥረቱ ያስገኘው ውጤት
  • እውነተኛ ክርስትና የሚገኘው የት ነው?
  • የታሪክ መስኮት—ቆስጠንጢኖስ
    ንቁ!—2014
  • ሕዝበ ክርስትና የዚህ ዓለም ክፍል ለመሆን የበቃችው እንዴት ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ማጭበርበሪያ የሆነች መንግሥት ተነሣች
    “መንግሥትህ ትምጣ”
  • ክፍል 12:-100–476 እዘአ​—የወንጌሉን ብርሃን ማዳፈን
    ንቁ!—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 3/15 ገጽ 26-30

ታላቁ ቆስጠንጢኖስ—የክርስትና ደጋፊ ነበርን?

ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ፣ ታሪክ “ታላቅ” የሚል ውብ ስም ካጎናጸፋቸው ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው። ሕዝበ ክርስትና ደግሞ “ቅዱስ፣” “አሥራ ሦስተኛው ሐዋርያ፣” “ከሐዋርያት ጋር እኩል ቅድስና ያለው” እንዲሁም ‘በመላው ዓለም ከፍተኛ ለውጥ እንዲያመጣ በአምላክ ኃይል የተመረጠ’ ትለዋለች። ከዚህ በተቃራኒ አንዳንዶች ቆስጠንጢኖስ “ደም አፍሳሽ፣ ሥፍር ቁጥር በሌላቸው የግፍና የጭከና ተግባራት የታወቀና የወጣለት አታላይ፣ . . . መሰሪ የሆነ አምባገነን መሪ፣ አሰቃቂ ወንጀሎችን የፈጸመ ሰው” መሆኑን ይናገራሉ።

ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸው የክርስትና ደጋፊዎች መካከል አንዱ ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ነው እየተባለ ሲነገራቸው ኖረዋል። ክርስቲያኖችን ከሮማ የጭቆና አገዛዝ ነፃ ስላወጣና የሃይማኖት ነፃነት ስለ ሰጣቸው ያመሰግኑታል። ከዚህም በላይ ክርስትናን ለማስፋፋት ጠንካራ ፍላጎት የነበረው የታመነ የኢየሱስ ክርስቶስ ፈለግ ተከታይ እንደሆነ በሰፊው ይነገርለታል። የምሥራቁ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ቆስጠንጢኖስንና እናቱን እሌኒን “ቅዱሳን” ብለው ሰይመዋቸዋል። ክብረ በዓላቸው ሰኔ 3 ወይም በቤተ ክርስቲያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ግንቦት 21 ላይ ይደረጋል።

ታላቁ ቆስጠንጢኖስ በእርግጥ ማን ነበር? በድህረ ሐዋርያት ዘመን በነበረው የክርስትና እድገት ላይ ምን ሚና ተጫውቷል? ታሪክና ምሁራን ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ ጠለቅ ያለ እውቀት የሚያስገኝ ነው።

ታሪካዊው ቆስጠንጢኖስ

የኮንስታንቲዩስ ክሎረስ ልጅ የሆነው ቆስጠንጢኖስ የተወለደው በኔይሰስ ሰርቢያ በ275 እዘአ ገደማ ነው። አባቱ በ293 እዘአ የሮማ ምዕራብ ግዛቶች ንጉሠ ነገሥት ሲሆን እሱም በንጉሠ ነገሥት ጋለሪየስ ትእዛዝ ሥር ሆኖ በዳኒዩብ እየተዋጋ ነበር። ቆስጠንጢኖስ በሞት ጣር ላይ በነበረው አባቱ ጎን ለመሆን በ306 እዘአ ወደ ብሪታንያ ተመለሰ። አባቱ ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሠራዊቱ ቆስጠንጢኖስን ንጉሠ ነገሥት አደረገው።

በዚያን ጊዜ አውጉስቲ [ንጉሠ ነገሥት] ነን የሚሉ ሌሎች አምስት ግለሰቦች ነበሩ። ከ306 እስከ 324 እዘአ የነበረው ዘመን የማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት የተካሄደበት ወቅት ነበር። ከዚያ በኋላ ቆስጠንጢኖስ ብቸኛው ንጉሠ ነገሥት ሆነ። ቆስጠንጢኖስ ያደረጋቸው ሁለት የጦር ዘመቻዎች በሮማ ታሪክ ውስጥ ያለውን ቦታ ያረጋገጠበትና በሮማ ግዛት ላይ ብቸኛው ገዥ እንዲሆን ያስቻሉት ነበሩ።

በ312 እዘአ ከሮማ ውጪ በሚልቪያን ድልድይ ላይ በተካሄደው ውጊያ ቆስጠንጢኖስ ተቃዋሚውን ማክሰንቲዩስን አሸነፈ። የክርስትና ጸሐፊዎች እንደሚሉት በዚያ ውጊያ ላይ “በዚህ ምልክት ድል ታደርጋለህ” የሚል ትርጉም ያላቸውን ኢን ሆክ ሲኞ ቪንክስ የሚሉትን የላቲን ቃላት የያዘ የሚንቦገቦግ መስቀል ከፀሐይ በታች ታየ። በተጨማሪም ቆስጠንጢኖስ በወታደሮቹ ጋሻ ላይ የክርስቶስን ስም የመጀመሪያዎቹን ሁለት ፊደላት በግሪክኛ እንዲቀባ በሕልም እንደታየው ይነገራል። ይሁን እንጂ ይህ ታሪክ ስለተፈጸመበት ጊዜና ቦታ ብዙ የተለያዩ ሐሳቦች ቀርበዋል። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ “ይህ ሕልም ስለታየበት ትክክለኛ ጊዜ፣ ቦታና ማብራሪያ ተቃራኒ አስተያየቶች አሉ” ብሏል። አንድ አረማዊ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቆስጠንጢኖስን በሮም አቀባበል ሲያደርግለት ታላቁ አውጉስቶስ እና ፖንቲፌክስ ማክሲመስ ማለትም የአ​ረማዊው ግዛት ሃይማኖት ሊቀ ካህናት ብሎ ሰይሞታል።

ቆስጠንጢኖስ በ313 እዘአ የምሥራቃዊው ግዛቶች ንጉሠ ነገሥት ከሆነው ከሊሲኒየስ ጋር ሽርክና ለመፍጠር ዝግጅት አደረገ። በሚላኑ ውሳኔ አማካኝነት ሁለቱም ነገሥታት ለሁሉም የሃይማኖት ቡድኖች የአምልኮ ነፃነትና እኩል መብት አጎናጸፉ። ይሁን እንጂ በርካታ ታሪክ ጸሐፊዎች ይህ ሰነድ ተራ መንግሥታዊ ደብዳቤ እንጂ ክርስትናን በተመለከተ የፖሊሲ ለውጥ መኖሩን የሚያመለክት ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ንጉሠ ነገሥታዊ ሰነድ ስላልሆነ ያን ያህል ዋጋ የለውም ይላሉ።

በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ቆስጠንጢኖስ የቀረውን ተቀናቃኝ ማለትም ሊሲኒየስን ድል በማድረግ የሮማዊው ዓለም ብቸኛ ገዥ ሆነ። በ325 እዘአ ገና ሳይጠመቅ የኒቂያ ድንጋጌ የሚል ስያሜ ያለውን አርዮሳዊነትን ያወገዘና ስለ መሠረታዊ እምነቶች ዝርዝር ሐሳብ የያዘ መግለጫ ያወጣውን የመጀመሪያውን የ“ክርስቲያን” አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጉባኤ በሊቀ መንበርነት መራ።

ቆስጠንጢኖስ በ337 እዘአ በማይድን በሽታ ተለከፈ። በሞት ጣር ላይ እያለ ከተጠመቀ በኋላ ሞተ። ከሞተ በኋላ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ከሮማውያን አማልክት መካከል አንዱ አደረገው።

ቆስጠንጢኖስ በቀየሰው ስልት ውስጥ ሃይማኖት የተጫወተው ሚና

በሦስተኛውና በአራተኛው መቶ ዘመን የነበሩ ሮማውያን ንጉሠ ነገሥታት ለሃይማኖት የነበራቸውን አጠቃላይ አመለካከት በመጥቀስ ኢስዶሪያ ቱ ኤሊኒኩ ኤትኑስ (የግሪክ መንግሥት ታሪክ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “ሌላው ቀርቶ እነዚያ በንጉሠ ነገሥታዊ ዙፋን ላይ የተቀመጡ ሰዎች ለሃይማኖት የጠለቀ ፍላጎት ባይኖራቸውም እንኳ በጊዜው ተስፋፍቶ ለነበረው አስተሳሰብ በመንበርከክና ለድርጊቶቻቸው ሃይማኖታዊ መልክ በመስጠት በፖለቲካዊ እቅዶቻቸው ውስጥ ለሃይማኖት ቅድሚያ መስጠትን አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል።”

በእርግጥም ቆስጠንጢኖስ ስለሚኖርበት ዘመን አስተሳሰብ የሚያውቅ ሰው ነበር። ሥራውን በጀመረበት ወቅት “መለኮታዊ” ድጋፍ አስፈልጎት ነበረ። ይህን ድጋፍ ግን በሕዝቡ ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ እየቀነሰ ከመጣው የሮማውያን አማልክት ሊያገኝ አልቻለም። ግዛቱ፣ ሃይማኖቱንና ሌሎች ተቋሞቹን ጨምሮ በመዳከም ላይ ስለነበረ እንዲያንሰራራ ለማድረግ አዲስና እንደገና የሚያጠናክር ነገር አስፈልጎ ነበር። ኢድሪያ የተባለው ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ብሏል:- “ቆስጠንጢኖስ ያገኘውን ድል ብቻ ሳይሆን ግዛቱ በአዲስ መልክ መዋቀሩን በመደገፏ ጭምር በተለይ በክርስትና ላይ ትኩረቱን ሊያደርግ ችሏል። በየቦታው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ፖለቲካዊ ደጋፊዎቹ ሆኑ። . . . በጊዜው ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸውን ሊቃነ ጳጳሳት በዙሪያው ሰበሰበ . . .፤ እንዲሁም አንድነታቸውን እንዲጠብቁ ጠየቀ።”

ምንም እንኳ የ“ክርስትና” ሃይማኖት ከሃዲና እጅግ የተበላሸች ብትሆንም ቆስጠንጢኖስ ንጉሠ ነገሥታዊ የበላይነት ለማግኘት የነበረውን ታላቅ ውጥን ከግብ ለማድረስ በአዲስ መልክ ጥንካሬ ለማምጣትና አንድነት ለማስፈን የሚያስችል ተጽእኖ ለማሳደር ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊጠቀምባት እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። የራሱን ፖለቲካዊ ውጥኖች ለማራመድ እንዲችል ድጋፍ ለማግኘት ሲል የከሃዲዋን ክርስትና መሠረት በመቀበል ሕዝቡን በጠቅላላ በአንድ “ካቶሊካዊ” ወይም ዓለም አቀፋዊ ሃይማኖት ሥር ለማሰባሰብ ወሰነ። አረማዊ ወጎችና በዓላት “ክርስቲያናዊ” ስሞች ተሰጧቸው። እንዲሁም “ክርስቲያን” ቀሳውስት ሥልጣን፣ ደሞዝ እና እንደ አረማዊ ካህናት ተጽእኖ የማሳደር ኃይል እንዲኖራቸው ተደረገ።

ፖለቲካውን ለማራመድ ሲል የሃይማኖትን አንድነት የፈለገው ቆስጠንጢኖስ የተቃውሞ ድምፅ በሚያሰሙት ላይ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። ይህን ያደረገው ለመሠረተ ትምህርታዊ እውነት ተጨንቆ ሳይሆን የብዙሃኑን ተቀባይነት ለማግኘት ሲል ነበር። ክፉኛ በተከፋፈለችው “ክርስትና” ውስጥ የነበረው የመሠረተ ትምህርት ልዩነት ቆስጠንጢኖስ “በአምላክ የተላከ” መካከለኛ በመምሰል ጣልቃ እንዲገባ አጋጣሚውን ከፈተለት። በሰሜን አፍሪካ ከሚገኙት ዶናቲስታውያን እና በግዛቱ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኙት የአርዮስ ተከታዮች ጋር ከነበረው ግንኙነት ለማየት እንደቻለው ጠንካራና አንድነት ያለው እምነት ለማቋቋም ሰዎችን ማሳመኑ ብቻ በቂ አለመሆኑን ወዲያውኑ ተገነዘበ።a በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የክርስትና አንድነት ስብሰባ የጠራው ከአርዮሳውያን ጋር የነበረውን ውዝግብ ለመፍታት ሲል ነበር።​—⁠“ቆስጠንጢኖስ እና የኒቂያ ጉባኤ” የሚለውን ሳጥን ተመልከት።

ታሪክ ጸሐፊው ፖል ጆንሰን ቆስጠንጢኖስ “ክርስትናን ታግሦ ከኖረበት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ እሱም ሆነ መንግሥቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ ትምህርቶችን በተመለከተ ያላትን ደንብ የመቆጣጠር አጋጣሚ በማግኘታቸው ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል።

ክርስቲያን ሆኖ ያውቃልን?

ጆንሰን “ቆስጠንጢኖስ የፀሐይ አምልኮን ትቶ አያውቀም እንዲሁም ከሳንቲሞቹ ላይ የፀሐይን ምስል አላስወገደም” ሲሉ ተናግረዋል። የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “ቆስጠንጢኖስ ሁለቱንም ሃይማኖቶች በእኩል ዓይን ይመለከታቸው ነበር። ፖንቲፌክስ ማክሲመስ እንደመሆኑ መጠን አረማዊ አምልኮን በበላይነት ይቆጣጠርና መብቱንም ያስጠብቅ ነበር” ብሏል። ኢድሪያ የተባለው ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚከተለው ይላል:- “ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ሆኖ አያውቅም። የሕይወት ታሪኩን የጻፈው የቂሣርያው ዩሴቢየስ እንደተናገረው ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን የሆነው በሕይወቱ ማብቂያ ላይ ነው። ይህ ደግሞ አሳማኝ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም [ቆስጠንጢኖስ] ፖንቲፌክስ ማክሲመስ የሚል ማዕረግ ያለው በመሆኑም ጭምር ከአንድ ቀን በፊት ለዜዩስ መሥዋዕት አቅርቧል።”

ቆስጠንጢኖስ በ337 እዘአ እስከ ሞተበት እለት ድረስ የሃይማኖታዊ ጉዳዮች የበላይ ባለ ሥልጣን መሆኑን በሚያመለክተው ፖንቲፌክስ ማክሲመስ በሚለው አረማዊ ማዕረግ ይጠራ ነበር። ጥምቀቱን አስመልክቶ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሣት ተገቢ ነው:- በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተገልጾ በሚገኘው ብቃት መሠረት ከልብ ንስሐ ገብቶና የአኗኗር መንገዱን ለውጦ ተጠምቋልን? (ሥራ 2:​38, 40, 41) ቆስጠንጢኖስ ራሱን ለይሖዋ አምላክ መወሰኑን ለማሳየት ሲል ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጠልቆ ተጠምቋልን?​—⁠ከሥራ 8:​36-39 ጋር አወዳድር።

“ቅዱስ” ነውን?

ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ቆስጠንጢኖስ ታላቅ ተብሎ የተጠራው ባገኛቸው ስኬቶች እንጂ በማንነቱ አይደለም። በጠባዩ ቢመዘን ኖሮ ጥንትም ይሁን ዛሬ [ታላቅ] የሚል የቅጽል ስም ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል የመጨረሻውን ደረጃ እንደሚይዝ የተረጋገጠ ነው።” እንዲሁም ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ “ግልፍተኛና ጨካኝ መሆኑን የሚገልጹ ጥንታዊ ዘገባዎች ይገኛሉ። . . . ለሰው ሕይወት ቅንጣት ታህል ደንታ አልነበረውም። . . . ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ የግል ሕይወቱ በጭካኔ የተሞላ ሆነ” በማለት ይናገራል።

ቆስጠንጢኖስ ከፍተኛ የባሕርይ ችግር እንደነበረው የተረጋገጠ ነው። አንድ የታሪክ ተመራማሪ “ብዙውን ጊዜ ወንጀል እንዲፈጽም ይገፋፋው የነበረው ቁጡነቱ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። (“በንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ የተፈጸሙ ግድያዎች” የሚለውን ሳጥን ተመልከት።) ታሪክ ጸሐፊው ኤች ፊሸር ሂስትሪ ኦቭ ዩሮፕ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ቆስጠንጢኖስ “ክርስቲያናዊ ባሕርይ” የለውም ብለዋል። ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ቆስጠንጢኖስ ‘አዲሱን ሰው የለበሰ’ እና የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ የውሃትንና ራስን መግዛትን ያፈራ እውነተኛ ክርስቲያን አልነበረም።​—⁠ቆላስይስ 3:​9, 10፤ ገላትያ 5:​22, 23

ጥረቱ ያስገኘው ውጤት

ቆስጠንጢኖስ የአረማዊው ፖንቲፌክስ ማክሲመስ ማለትም የሮማዊው ግዛት ሃይማኖታዊ መሪ እንደመሆኑ መጠን የከሃዲዋን ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ለማግባባት ሞከረ። የሮማ መንግሥት የሃይማኖት ሹሞች ሆነው ከፍተኛ ሥልጣን፣ ክብርና ሀብት እንደሚያገኙ ቃል ገባ። የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ሲል አምኗል:- “አንዳንድ ቀሳውስት በቤተ መንግሥቱ ባገኙት ታላቅ ክብር ታውረው ንጉሠ ነገሥቱን የአምላክ መልአክ፣ ቅዱስ የሆነ ሕያው አካል ብለው እንደማወደስና ልክ እንደ አምላክ ልጅ በሰማይ ይነግሣል የሚል ትንቢት እስከ መናገር ደርሰው ነበር።”

የክህደት ክርስትና ከፖለቲካዊ መንግሥት ጋር ይበልጥ ባበረ መጠን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የራቀና ከጊዜ ወደ ጊዜ የዚህ ዓለም ማለትም የዚህ ዓለማዊ ሥርዓት ክፍል እየሆነ ሄደ። (ዮሐንስ 15:​19፤ 17:​14, 16፤ ራእይ 17:​1, 2) በዚህም ምክንያት “ክርስትና” እንደ ሥላሴ፣ የነፍስ አለመሞት፣ እሳታማ ሲኦል፣ መንጽሔ፣ ለሙታን ጸሎት እንደማቅረብ እንዲሁም በመቍጠሪያዎች፣ በቅርጾችና በምስሎች መጠቀምን ከመሳሰሉት የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችና ልማዶች ጋር ውህደት ፈጠረች።​—⁠ከ2 ቆሮንቶስ 6:​14-18 ጋር አወዳድር።

ቤተ ክርስቲያን ከቆስጠንጢኖስ ፈላጭ ቆራጭ የመሆን ዝንባሌንም ወርሳለች። ሄንደርሰንና በክ የተባሉት ምሁራን እንዲህ ብለዋል:- “በቀላል መንገድ የቀረበው ወንጌል ተበላሸ፤ ራስን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ተግባራትና ሥርዓቶች ተጨመሩ፤ የክርስትና መምህራን ዓለማዊ ክብርና ጥቅማ ጥቅሞች ተሰጧቸው፤ እንዲሁም የክርስቶስ መንግሥት በአብዛኛው በዚህ ዓለም መንግሥት ተለወጠ።”

እውነተኛ ክርስትና የሚገኘው የት ነው?

ታሪካዊ ማስረጃዎች ከቆስጠንጢኖስ “ታላቅነት” በስተጀርባ ያለውን እውነት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ሕዝበ ክርስትና የእውነተኛው ጉባኤ ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተች ሳትሆን በከፊል አረማዊው ንጉሠ ነገሥት ለፖለቲካዊ ጥቅሙ ሲል ያቋቋማት የተንኮል ውጤት ነች። ታሪክ ጸሐፊው ፖል ጆንሰን “ንጉሠ ነገሥታዊው ግዛት ለክርስትና እጁን ሰጠ ወይስ ክርስትና ከግዛቱ ጋር አመነዘረች?” ብለው መጠየቃቸው ተገቢ ነው።

ንጹህ የሆነውን ክርስትና ለመከተል የሚፈልጉ ሁሉ በጊዜያችን የሚገኘውን እውነተኛውን የክርስቲያን ጉባኤ ለይተው እንዲያውቁና ከእሱም ጋር እንዲተባበሩ እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነተኛውን ክርስትና ለይተው እንዲያውቁና አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዲያመልኩ ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው።​—⁠ዮሐንስ 4:​23, 24

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዶናቲስታዊነት በአራተኛውና በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የነበረ “ክርስቲያናዊ” ኑፋቄ ነው። ተከታዮቹ እንደሚሉት የቁርባን ሥነ ሥርዓት ዋጋማነት የተመካው ቁርባኑን በሚቀበለው አገልጋይ የሥነ ምግባር ባሕርይና ቤተ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችን ከአባልነት በመሰረዟ ላይ ነው። አርዮሳዊነት የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊነት ያልተቀበለ የአራተኛው መቶ ዘመን “ክርስቲያናዊ” እንቅስቃሴ ነው። አርዮስ አምላክ አልተወለደም፤ መጀመሪያም የለውም ሲል አስተምሯል። ወልድ ግን የተወለደ ስለሆነ ከአብ ጋር በሚመሳሰል መንገድ አምላክ አይደለም። ወልድ ከአምላክ ጋር እኩል ዘላለማዊነት የሌለው በአብ ፈቃድ የተፈጠረና የሚኖር ነው ብሏል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቆስጠንጢኖስ እና የኒቂያ ጉባኤ

ያልተጠመቀው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ በኒቂያ ጉባኤ ላይ ምን ሚና ተጫውቷል? ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ቆስጠንጢኖስ ራሱ ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት መርቷል። በውይይቱም በንቃት ተካፍሏል። . . . ከሁለት ጳጳሳት በስተቀር ጳጳሳቱ በሙሉ ንጉሡን በመፍራት አለፍላጎታቸው በድንጋጌው መስማማታቸውን በፊርማቸው አረጋገጡ።”

ሁለት ወራት ከፈጀ የተጧጧፈ ሃይማኖታዊ ክርክር በኋላ ይህ አረማዊ የፖለቲካ መሪ ጣልቃ በመግባት ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው የሚሉትን የሚደግፍ ውሳኔ አስተላለፈ። ግን ለምን? ኤ ሾርት ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያን ዶክትሪን የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “ቆስጠንጢኖስ በግሪክ የሃይማኖት ትምህርቶች ላይ ስለሚነሱት ጥያቄዎች ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።” እሱ የሚያውቀው የሃይማኖት መከፋፈል ለግዛቱ አደገኛ መሆኑን ብቻ ነበር። ግዛቱን ለማጠናከር ብርቱ ፍላጎት ነበረው።

በቆስጠንጢኖስ ድጋፍ በኒቂያ የተቀናበረውን ሰነድ አስመልክቶ ኢስዶሪያ ቱ ኤሊኒኩ ኤትኑስ (የግሪክ መንግሥት ታሪክ) እንዲህ ይላል:- “ሰነዱ [ቆስጠንጢኖስ] ለመሠረተ ትምህርቶች የነበረውን ግድየለሽነት፣ . . . የተከፈለው ተከፍሎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት እንዲኖር ለማድረግ የነበረው ድርቅ ያለ አቋምና በመጨረሻም ‘ከክርስትና ውጪ ላሉት ሃይማኖቶች ሊቃነ ጳጳሳት’ እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ረገድ የመጨረሻውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳለው ያምን እንደነበረ ያሳያል።” በዚያ ጉባኤ ላይ የተላለፉት ውሳኔዎች የአምላክ መንፈስ ድጋፍ ሊኖራቸው ይችላልን?​— ከሥራ 15:​28, 29 ጋር አወዳድር።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ የተፈጸሙ ግድያዎች

በዚህ ርዕስ ሥር ኢስዶሪያ ቱ ኤሊኒኩ ኤትኑስ (የግሪክ መንግሥት ታሪክ) የተባለው መጽሐፍ “ቆስጠንጢኖስ በቤተሰቡ ውስጥ የፈጸማቸው አሰቃቂ ወንጀሎች” የሚላቸውን ይገልጻል። ሥርወ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላ ያገኘውን ያልተጠበቀ ስኬት እንዴት እንደሚጠቀምበት በመዘንጋት በዙሪያው ከብቦት የሚገኘው አደጋ ታየው። ተጠራጣሪ ሰው በመሆኑና ምናልባትም ከእሱ ጥቅም ለማግኘት በሚፈልጉ ሰዎች በመታለሉ ሳይሆን አይቀርም፣ የወንድሙን ልጅ ሊሲኒየስን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ጀመረ። ሊሲኒየስ ቆስጠንጢኖስ ቀደም ሲል ያስገደለው የአውጉስቶስ ተባባሪ ገዥ የነበረው ሰው ልጅ ነው። የወንድሙ ልጅ ከተገደለ በኋላ የራሱ የቆስጠንጢኖስ የበኩር ልጅ የሆነውን ክሪስፐስን ደግሞ እንጀራ እናቱ የራሷ ልጅ ሥልጣን ላይ እንዳይወጣ እንቅፋት ይሆናል ብላ ስላሰበች እንዲገደል አደረገች።

በመጨረሻም ለራሷ ለፋውስታ አስደንጋጭ ሞት ምክንያት የሆነው ነገር ይህ አድራጎቷ ነበር። አውጉስታ እሌኒ ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን እስከ መጨረሻው ትቆጣጠረው የነበረ ሲሆን በዚህም ግድያ ውስጥ እጅዋን ሳታስገባ አትቀርም። ከዚህም በላይ ቆስጠንጢኖስ የነበረው ጭፍን ስሜት ለበርካታ ጓደኞቹና ወዳጆቹ ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኖ ነበር። ሂስትሪ ኦቭ ዘ ሚድል ኤጅስ የተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን የማጠቃለያ ሐሳብ ሰጥቷል:- “የራሱን ልጅና የራሱን ሚስት በሞት መቅጣቱ በክርስትና መንፈሳዊ ተጽእኖ ቅንጣት ታህል እንዳልተነካ ያሳያል።”

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሮም የሚገኝው ይህ ቅስት የቆስጠንጢኖስ ክብር መታሠቢያ ሆኖ ቆይቷል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Musée du Louvre, Paris

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ