እውነተኛ ደህንነት አሁንም ሆነ ለዘላለም
ይሖዋ የሕዝቦቹን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። እርሱ “ሁሉን የሚችል” ነው። (መዝሙር 68:14 የ1980 ትርጉም) በዓይነቱ ብቸኛና ልዩ የሆነው ስሙ “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው። ይህም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ማናቸውንም እንቅፋቶች አሸንፎ ቃል የገባቸውን ነገሮችና ፈቃዱን የሚፈጽም ብቸኛው አካል መሆኑን ያሳያል። አምላክ ራሱ እንዲህ ብሏል፦ “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”—ኢሳይያስ 55:11
አምላክ በእርሱ የሚታመኑትን ሰዎች ደህንነት ያስጠብቃል። ቃሉ ይህንን ያረጋግጣል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል [“ጥበቃ ያገኛል፣” አዓት]” በማለት ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ‘በእግዚአብሔር የሚታመን ይጠበቃል’ ብሏል።—ምሳሌ 18:10፤ 29:25
የአምላክ አገልጋዮች ደህንነታቸው ይጠበቃል
ይሖዋ በእርሱ የሚታመኑ ሰዎችን ደህንነት ሳያስጠብቅ የቀረበት ጊዜ የለም። ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ የአምላክን ጥበቃ አግኝቷል። የባቢሎን ሠራዊት ከሃዲዋን ኢየሩሳሌም ሲከብብ ነዋሪዎቹ ‘ምግባቸውን እየመጠኑ በስጋት መብላት’ ነበረባቸው። (ሕዝቅኤል 4:16 የ1980 ትርጉም) ሁኔታው በጣም አስከፊ ደረጃ ላይ ከመድረሱ የተነሳ አንዳንድ ሴቶች ልጆቻቸውን ቀቅለው በልተዋል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:20፤ 4:10) ምንም እንኳ ኤርምያስ ያለፍርሃት በመስበኩ የተነሳ ታስሮ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ “እንጀራም ሁሉ ከከተማ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ” እንዲያገኝ አድርጎ ነበር።—ኤርምያስ 37:21
ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ ስትወድቅ ኤርምያስ በሕይወት ከመትረፉም በላይ እስረኛ ሆኖ ወደ ባቢሎን አልተወሰደም። ከዚህ ይልቅ [የባቢሎናውያን] ‘የዘበኞቹ አለቃ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶ አሰናበተው።’—ኤርምያስ 40:5
ኢየሱስ ክርስቶስ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ እንዲህ በማለት ለአምላክ አገልጋዮች ማረጋገጫ ሰጥቷል፦ “እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:31-33
ይህ ማለት የይሖዋ አገልጋዮች በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት አደጋ እንዳይደርስባቸው አምላክ ይጠብቃቸዋል ማለት ነውን? እንዲህ ማለት አይደለም። ታማኝ የሆኑ ሰዎች ምንም ዓይነት ጉዳት አይደርስባቸውም ማለት አይደለም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ይታመማሉ፣ ይሰደዳሉ፣ የወንጀል ሰለባ ይሆናሉ፣ በአደጋ ይሞታሉ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች መከራ ይደርስባቸዋል።
ይሖዋ ምንም እንኳ አገልጋዮቹ ሙሉ በሙሉ ከጉዳት እንዲጠበቁ ባያደርግም በኃይሉ ተጠቅሞ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያሟላላቸውና ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የተለያዩ ሪፖርቶች ያሳያሉ። በተጨማሪም ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለሚመሩ ከብዙ ችግሮች ድነዋል። (ምሳሌ 22:3) ከዚህም በተጨማሪ በችግር ጊዜ እርስ በርስ የሚረዳዱ አፍቃሪ የሆኑ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ባሉበት ዓለም አቀፍ ማኅበር ውስጥ ደህንነት አግኝተው ይኖራሉ። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ ሮሜ 8:28 የ1980 ትርጉም) ለምሳሌ በአውሮፓ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት በታመሰችው ሩዋንዳ ውስጥ በአሳዛኝ ችግር ላይ ለወደቁት ወንድሞቻቸው 65,000 ኪሎ ግራም የሚመዝን አልባሳትና 1,600,000 ዶላር የሚያወጣ መድኃኒት፣ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ልከውላቸዋል።—ከሥራ 11:28, 29 ጋር አወዳድር።
ይሖዋ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ መከራ እንዲደርስ ቢፈቅድም ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬ፣ እርዳታና ጥበብ እንደሚሰጣቸው እርግጠኛ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለመሰል አማኞች እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና [መከራ] አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ [መከራ ይደርስባችሁ] ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው [ከመከራው] ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ዘ ኢምፋቲክ ዲያግሎት።
አምላክ ለሕዝቡ ያደረገው ዝግጅት
በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ መፈጸም በጣም ያስደስታቸዋል። አምላክን የሚያገለግሉት ተገድደው አይደለም፤ የሚያገለግሉት ስለሚያውቁትና ስለሚወዱት ነው። ይሖዋም በታማኝነት የሚያገለግሉትን ሰዎች ስለሚወድ ምድርን ታዛዥ ሰዎች ዘላለማዊ ሰላም፣ ጤና እና ደህንነት አግኝተው የሚኖሩባት ቦታ ለማድረግ ዓላማ አለው።—ሉቃስ 23:43
አምላክ ይህንን የሚያከናውነው እርሱ በሾመው ንጉሥ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው ሰማያዊ መስተዳድር አማካኝነት ነው። (ዳንኤል 7:13, 14) መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን መስተዳድር ‘የእግዚአብሔር መንግሥት’ እና “መንግሥተ ሰማያት” በማለት ይጠራዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:50፤ ማቴዎስ 13:44) አሁን ባሉት ሰብዓዊ መስተዳድሮች ምትክ የአምላክ መንግሥት መግዛት ይጀምራል። በምድር ላይ ብዙ መንግሥታት መኖራቸው ይቀርና አንድ መንግሥት ብቻ ይኖራል። ይህ መንግሥት በመላው ምድር ላይ በጽድቅ ይገዛል።—መዝሙር 72:7, 8፤ ዳንኤል 2:44
ሁሉም ሰዎች በመንግሥቱ ሥር እንዲኖሩ ይሖዋ ግብዣ አቅርቦላቸዋል። ይህንን የሚያደርግበት አንደኛው መንገድ መንግሥቱ ለሰው ዘር ምን እንደሚያደርግ የሚናገረው መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው እንዲሰራጭ በማድረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ በሰፊው በመሰራጨት በኩል ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ2,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል።
ይሖዋ አምላክ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንግሥቱ የሚያስተምረውን ነገር እንዲገነዘቡ ፍቅር በተሞላበት ሁኔታ ይረዳቸዋል። ይህንንም የሚያደርገው ቅዱሳን ጽሑፎችን ለሌሎች የሚያብራሩ ሰዎችን አሠልጥኖ በመላክ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከአምስት ሚልዮን በላይ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እያወጁ ነው።
እውነተኛ ደህንነት የሚያገኘው ሁሉም ሰው ነውን?
ሁሉም ሰዎች የአምላክን የጽድቅ ብቃቶች በማሟላት የመንግሥቱ ዜጎች እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ግብዣ ይቀበሉታልን? አይቀበሉትም፤ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ፍላጎት የላቸውም። የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት ገሸሽ ያደርጉታል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት የተናገረላቸው ዓይነት ሰዎች መሆናቸውን ያሳያሉ፦ “በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጀሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፣ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጀሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል።”—ማቴዎስ 13:15
ከአምላክ የጽድቅ ጎዳናዎች ጋር ተስማምቶ መኖር የማይፈልጉ ሰዎች እያሉ በምድር ላይ እውነተኛ ደህንነት ሊሰፍን የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ሁኔታ እያለ ደህንነት ሊሰፍን አይችልም። አምላክ የለሽ የሆኑ ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎችን ደህንነት አደጋ ላይ ይጥሉታል።
አምላክ ሰዎች በግድ እንዲለወጡ ባያደርግም ክፋትን ለዘላለም ዝም ብሎ አይመለከትም። ይሖዋ ምሥክሮቹን እየላከ ስለ ጎዳናዎቹና ስለ ዓላማዎቹ በትዕግሥት በማስተማር ላይ ቢሆንም ይህ የማስተማር ሥራ ለረጅም ጊዜ አይቀጥልም። ኢየሱስ ክርስቶስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተንብዮአል።—ማቴዎስ 24:14
የአምላክን የአቋም ደረጃዎች አንቀበልም ያሉ ሰዎች “መጨረሻው” ምን ያስከትልባቸዋል? ፍርዳቸውን ተቀብለው ይጠፋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘እግዚአብሔርን የማያውቁት፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙት በዘላለም እሳት እንደሚጠፉ’ ይናገራል።—2 ተሰሎንቄ 1:6-9
በመጨረሻ እውነተኛ ደህንነት ለዘላለም ይሰፍናል
በይሖዋ የሰላም ጎዳና ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ከጠፉ በኋላ የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ላሉት ጻድቅ ሰዎች ደህንነት የሰፈነበት አስደሳች ዘመን ያመጣል። (መዝሙር 37:10, 11) ይህ አዲስ ዓለም አሁን ካለንበት ዓለም ምንኛ የተለየ ይሆናል!—2 ጴጥሮስ 3:13
የምግብ እጥረትና ረሃብ አይኖርም። ሁሉም ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ይኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሕዝቡ ሁሉ የሰባ ምግብ ይመገባል’ ይላል። (ኢሳይያስ 25:6) ‘በምድሩ ላይ በቂ እህል ስለሚኖርና ተራራዎች በሰብል ስለሚሸፈኑ’ የምግብ እጥረት አይኖርም።—መዝሙር 72:16 የ1980 ትርጉም
ሰዎች በደሳሳ ጎጆዎችና በቆረቆዙ ከተማዎች ውስጥ አይኖሩም። በአምላክ መንግሥት ሥር ሁሉም ሰዎች የተሻሉ መኖሪያ ቤቶች ይኖሯቸዋል፤ እንዲሁም የራሳቸው መሬት ያፈራውን ምግብ ይመገባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ” በማለት ተስፋ ይሰጣል።—ኢሳይያስ 65:21
በአሁኑ ጊዜ ተስፋፍቶ በሚገኘው ሥራ አጥነት ፋንታ ምርታማ ሥራ ስለሚኖር ሰዎች ከሥራቸው መልካም ውጤቶች ያገኛሉ። የአምላክ ቃል “እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። . . . በከንቱ አይደክሙም” ይላል።—ኢሳይያስ 65:22, 23
በዚህ ንጉሣዊ መንግሥት የሚተዳደሩ ሰዎች በበሽታ ምክንያት አይሠቃዩም፤ አይሞቱምም። የአምላክ ቃል “በዚያ የሚቀመጥ፦ ታምሜአለሁ አይልም” በማለት ያረጋግጥልናል።—ኢሳይያስ 33:24
በቅርቡ እውን በሚሆነው ምድራዊ ገነት ውስጥ ሥቃይና ሕመም፣ ሐዘንና ሞት አይኖርም። አዎን፣ ሞት እንኳ አይኖርም! ሰዎች በገነት ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ! መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአል” በማለት ይናገራል።—ራእይ 21:4
‘በሰላሙ ገዢ’ በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ሥር በመጨረሻ በምድር ላይ የሚኖረው ሕይወት ዋስትና ያለው ይሆናል። በእርግጥም ብቻውን በጽድቅና በፍቅር በሚገዛው መስተዳድር ማለትም በአምላክ መንግሥት ሥር ዓለም አቀፋዊ ደህንነት ይሰፍናል።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ራእይ 7:9, 17
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ሰዎች ደህንነት እንዲሰማቸው የሚያደርገው የወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መሆን . . . በተለይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች መረጋጋት ነው።”—እስያ ውስጥ የምትኖር ሴት
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ከሁሉ በላይ ደህንነት እንዳይሰማችሁ የሚያደርገው ዓመፅና ወንጀል ነው። በፖሊስ ላይ እምነት መጣል አለመቻሉም ደህንነት እንዳይሰማን ያደርጋል።”—በደቡብ አሜሪካ የሚኖር ሰው
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በወረራው ወቅት . . . ደህንነት አይሰማኝም ነበር። አንድ አገር በጦርነት ላይ እያለ ሕዝቡ እንዴት ደህንነት ሊሰማው ይችላል?”—በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ተገድጄ እደፈር ይሆናል የሚል ስጋት ሳያድርብኝ በምሽት በጎዳናዎች ላይ መጓዝ እንደምችል ሳውቅ ያን ጊዜ ደህንነት ይሰማኛል።”—አፍሪካ ውስጥ የምትኖር አንዲት ተማሪ