የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 9/15 ገጽ 2-7
  • ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክን ያስደስታሉን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክን ያስደስታሉን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በፍሬያቸው ይታወቃሉ
  • ጥንቃቄ ያስፈልጋል
  • ፍሬውን መመልከት
  • ቁርጥ ያለ እርምጃ የምንወስድበት ጊዜ
  • አምላክ የሚቀበለው አምልኮ
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!
    የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!
  • ትክክለኛውን ሃይማኖት አግኝተኸዋልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ይቀበላል?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ አግኝተኸዋል?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 9/15 ገጽ 2-7

ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክን ያስደስታሉን?

ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክን ያስደስታሉ ብለህ ታስባለህን? ምናልባት አንተ የምታውቀው ሃይማኖት ሰዎች ቢያንስ በተወሰነ መጠን ጥሩ ጠባይ እንዲኖራቸው ያበረታታ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክን ለማስደሰት ይህ ብቻ በቂ ነውን?

‘ብቻ አምልኮትህ ከልብ ይሁን እንጂ ምንም ይሁን ምን አምላክ ይደሰትበታል። ሁሉም ሃይማኖቶች የየራሳቸው ጥሩ ጎን አላቸው’ የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል የባሃይ እምነት ይህን ዓይነት አመለካከት በመያዝ የዓለማችንን ዘጠኝ ታላላቅ ሃይማኖቶች የእምነቱ ክፍል አድርጎ እስከ መቀበል ደርሷል። ይህ ሃይማኖታዊ ቡድን እነዚህ ሁሉ ሃይማኖቶች ከመለኮታዊ ምንጭ የተገኙና የአንድ እውነት የተለያዩ ገጽታዎች እንደሆኑ ያምናል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ከዚህም በላይ አንድ ሃይማኖት ሕዝብ በሚዘዋወርባቸው ቦታዎች ላይ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ የነርቭ ጋዝ እንዲያጠምዱ አባላቶቹን የሚያዝ ከሆነ ይህ ሃይማኖት አምላክን እንዴት ሊያስደስት ይችላል? ብለህ መጠየቅህ ተገቢ ነው። ይህ ክስ የተሰነዘረው በጃፓን በሚገኝ አንድ ሃይማኖታዊ ቡድን ላይ ነበር። ወይስ ደግሞ አባላቶቹ ራሳቸውን እንዲገድሉ በሚያበረታ ሃይማኖት አምላክ ይደሰታልን? ከጥቂት ዓመታት በፊት ጂም ጆንስ በተባለው ሃይማኖታዊ መሪ ተከታዮች ላይ የደረሰው ይኸው ነበር።

መለስ ብለን የኋለኞቹን ዘመናት በመመልከት ሃይማኖቶች ከ1618 እስከ 1648 ለሠላሳ ዓመታት እንደተደረገው ያሉ ጦርነቶችን የሚቆሰቁሱ ከሆነ አምላክን ሊያስደስቱት ይችላሉን? ብለን መጠየቃችንም ተገቢ ነው። ዘ ዩኒቨርሳል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ወርልድ የተባለው መጽሐፍ እንዳስቀመጠው በካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች መካከል የነበረው ሃይማኖታዊ ግጭት “በአውሮፓ ታሪክ ውስጥ ከታዩት ጦርነቶች ሁሉ የከፋ” ነበር።

ከ11ኛው እስከ 13ኛው መቶ ዘመን የተካሄዱት ሃይማኖታዊ ጦርነቶች አሠቃቂ የደም መፋሰስ አስከትለዋል። ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው የመስቀል ጦርነት ወቅት ክርስቲያን ተብዬ ተዋጊዎች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እስላሞችና አይሁዳውያን በጭካኔ ጨፍጭፈዋል።

ከ13ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ለ600 ዓመታት በዘለቀው ኢንኩዊዚሽን ወቅትም ምን እንደተፈጸመ ልብ በል። በሃይማኖታዊ መሪዎች ትእዛዝ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በአሠቃቂ ሁኔታ ተደብድበዋል፤ እንዲሁም በእሳት ተቃጥለው ሞተዋል። ፒተር ዲ ሮዛ ቪካርስ ኦቭ ክራይስት—ዘ ዳርክ ሳይድ ኦቭ ዘ ፓፓሲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ አትተዋል፦ “[የኢንኩዊዚሽኑ ቅጣት ፈጻሚዎች] ከጳጳሱ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ለፈጸሙት [በሰው] ዘር ታሪክ ውስጥ ከታየው ሁሉ የከፋ ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ ግፍና ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አሠቃቂ ግድያ ተጠያቂ ናቸው።” የስፔይን ተወላጅ የሆነው ቶርኬሜዳ የተባለው የዶሚኒካን ኢንኩዊዚሽን አራማጅ ስለፈጸመው ድርጊት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “የተሾመው በ1483 ሲሆን ለአሥራ አምስት ዓመታት ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ገዝቷል። ያስገደላቸው ሰዎች ቁጥር 114,000 የሚደርስ ሲሆን 10,220 የሚያክሉት በቁማቸው በእሳት ተቃጥለው የሞቱ ናቸው።”

በእርግጥ በደም አፍሳሽነት ተጠያቂ የሚሆኑት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ብቻ አይደሉም። የፈረንሳዩ ፈላስፋ ብሌዝ ፓስካል ፖንሴ በተባለው የሥነ ጽሑፍ ሥራው ውስጥ እንደሚከተለው በማለት የታዘበውን አስፍሯል፦ “ሰዎች ለሃይማኖታቸው ሲሉ የሚያደርጉትን ያህል በሙሉ ልባቸውና በደስታ ክፋት የሚፈጽሙበት ጊዜ የለም።”

በፍሬያቸው ይታወቃሉ

አምላክ የአንድን ሃይማኖት ተቀባይነት የሚለካው በአንድ ነገር ብቻ አይደለም። አንድ ሃይማኖት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከተፈለገ ትምህርቱና ድርጊቶቹ ሁሉ በጽሑፍ ከሰፈረው ከእርሱ የእውነት ቃል ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማት ይኖርበታል። (መዝሙር 119:160፤ ዮሐንስ 17:17) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አንድ ሃይማኖት የሚያፈራቸው ፍሬዎች ይሖዋ አምላክ ካወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ጋር መስማማት ይኖርባቸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ በሐሰት አምላክን እንወክላለን ብለው የሚናገሩ ነቢያት እንደሚነሡ ጠቁሟል። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂ ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን፣ ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፣ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” (ማቴዎስ 7:15-20) እነዚህ ቃላት በመንፈሳዊ ንቁዎች መሆን እንዳለብን ያሳያሉ። አንድ ሃይማኖታዊ መሪ ወይም ቡድን በአምላክና በኢየሱስ ፊት ተቀባይነት አለው ብለን እናስብ ይሆናል፤ ግን ተሳስተን ሊሆን ይችላል።

ጥንቃቄ ያስፈልጋል

አንድ ሃይማኖት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለኝ ብሎ ሊናገርና ቀሳውስቱም ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሱ ሊሆኑ ቢችልም እንኳ ይህ ሃይማኖት አምላክን ያስደስተዋል ብሎ ለመናገር አይቻልም። መሪዎቹም አምላክ በእነርሱ እየተጠቀመ እንዳለ የሚያስመስሉ ድንቅ ነገሮች ሊያከናውኑ ይችሉ ይሆናል። የሆነው ሆኖ ግን ይህ ሃይማኖት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ፍሬዎች የማያፈራ የሐሰት ሃይማኖት ሊሆን ይችላል። በሙሴ ዘመን የነበሩት የጥንቆላ ሥራ የሚሠሩ የግብፅ ካህናት ድንቅ ነገሮችን ማከናወን ችለው ነበር፤ ይሁን እንጂ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳልነበራቸው ምንም አያጠራጥርም።—ዘጸአት 7:8-22

ዛሬም እንደ ጥንቱ ሁሉ ብዙ ሃይማኖቶች አምላክ እውነት ነው ያለውን ነገር የሙጥኝ ብለው ከመመላለስ ይልቅ የሰዎችን ሐሳብና ፍልስፍና ያራምዳሉ። እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ሲል የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ በጣም አስፈላጊ ነው፦ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”—ቆላስይስ 2:8

ኢየሱስ ስለ መልካምና ክፉ ፍሬ ከተናገረ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:21-23

ፍሬውን መመልከት

እንግዲያውስ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ሃይማኖት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው ብለን ከመደምደማችን በፊት የሚያፈራውን ፍሬ መመልከታችን የግድ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል ይህ ሃይማኖት በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ይገባልን? እንደዚያ ከሆነ በያዕቆብ 4:4 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን እነዚህን ቃላት ልብ በል፦ “የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ስለ እውነተኛ ተከታዮቹ ሲናገር “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:16) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃይማኖት ‘በክፉው’ ማለትም በማይታየው መንፈሳዊ ፍጡር በሰይጣን ዲያብሎስ መዳፍ ‘በተያዘው’ ዓለም ፖለቲካ ውስጥ እጁን አያስገባም። (1 ዮሐንስ 5:19) ከዚህ ይልቅ ግን አምላክ የሚቀበለው ሃይማኖት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን መንግሥት በታማኝነት ይደግፋል፤ እንዲሁም ይህን ሰማያዊ መስተዳድር የሚመለከት ምሥራች ያውጃል።—ማርቆስ 13:10

አንድ ሃይማኖት ሕዝባዊ ዓመፅን የሚያበረታታ ከሆነ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋልን? የሚከለተውን የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር የምንቀበል ከሆነ መልሱ ግልጽ ነው፦ “ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ . . . እንዲሆኑ አሳስባቸው።” (ቲቶ 3:1) ኢየሱስም ተከታዮቹ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር” ማስረከብ እንዳለባቸው ተናግሯል።—ማርቆስ 12:17

አንድ ሃይማኖት ብሔራት በሚያደርጓቸው ጦርነቶች ውስጥ መካፈልን የሚያበረታታ ከሆነስ? አንደኛ ጴጥሮስ 3:11 ‘መልካምን እንድናደርግ’ ‘ሰላምን እንድንሻ እንድንከተላትም’ አጥብቆ ይመክረናል። አንድ ሃይማኖት አባላቱ ጦርነት ውስጥ ገብተው በሌላ አገር ያሉ የእምነት መሰሎቻቸውን ለመግደል ፈቃደኛ ሆነው የሚገኙ ከሆነ እንዴት አምላክን ሊያስደስት ይችላል? በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የአንድ ሃይማኖት አባላት የአምላክን ዋነኛ ባሕርይ ይኸውም ፍቅርን ያንጸባርቃሉ። ኢየሱስም እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:35) ይህ ፍቅር በብሔራት መካከል በሚደረጉት ጦርነቶች ላይ ከሚንጸባረቀው የመረረ ጥላቻ ጋር አንዳችም ኅብረት የለውም።

እውነተኛ ሃይማኖት ጦርነት ወዳድ የሆኑ ሰዎችን ሰላም ወዳድ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህ ሁኔታ በሚከተሉት ቃላት በትንቢት ተነግሯል፦ “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” (ኢሳይያስ 2:4) እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች የጥላቻ ቃላት ከመሰናዘር ይልቅ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” ከሚለው ትእዛዝ ጋር ተስማምተው ይመላለሳሉ።—ማቴዎስ 22:39

እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ሥነ ምግባር የጎደለውን አኗኗር ለመከተል አሻፈረኝ በማለት ከይሖዋ አምላክ ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው ለመኖር ይጣጣራሉ። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

ቁርጥ ያለ እርምጃ የምንወስድበት ጊዜ

በሐሰተኛ አምልኮና በእውነተኛው ሃይማኖት መካከል ያለውን ልዩነት አበጥሮ ማወቁ የግድ አስፈላጊ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የራእይ መጽሐፍ ላይ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ የተጠራች ሲሆን ‘የምድር ነገሥታት አብረዋት እንደሚሴስኑ’ ምሳሌያዊ ጋለሞታ ተደርጋ ተገልጻለች። የደም ባለዕዳ ከመሆኗም በላይ “በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ” ይዛለች። (ራእይ 17:1-6) በአምላክ ዘንድ የሚወደድ አንዳችም ነገር የላትም።

ቁጥር ያለ እርምጃ የምንወስድበት ጊዜ አሁን ነው። እስካሁንም ድረስ በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ለሚገኙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አፍቃሪው ፈጣሪያችን የሚከተለውን ጥሪ ያሰማል፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።”—ራእይ 18:4

አምላክን ደስ የሚያሰኘውን ሃይማኖት ለመከተል የምትፈልግ ከሆነ ለምን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ይበልጥ አትተዋወቅም? ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ የቀረበው ሰንጠረዥ እነርሱ ከሚያምኑባቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ከነቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎቻቸው ይዟል። ምሥክሮቹ የሚያምኑባቸው ነገሮች ከአምላክ ቃል ጋር ይስማሙ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስህን አውጥተህ ተመልከት። ሃይማኖታቸው እውነተኛው ሃይማኖት ሊያሳይ ይገባዋል የምትለውን ፍሬ ያፈራ እንደሆነና እንዳልሆነ አረጋግጥ። እንደዚያ ሆኖ ካገኘኸው አምላክን ደስ የሚያሰኘውን ሃይማኖት አግኝተሃል ማለት ነው።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

እምነታቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ

የአምላክ ስም ይሖዋ ነው ዘጸአት 6:3 (1879 እትም)፤ መዝሙር 83:18 አዓት

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ ነው ማቴዎስ 3:16, 17፤ ዮሐንስ 14:28

የሰው ልጅ የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ሳይሆን በፍጥረት ነው ዘፍጥረት 1:27፤ 2:7

ሰዎች የሚሞቱት በመጀመሪያው ሰው ኃጢአት ምክንያት ነው ሮሜ 5:12

ነፍስ ሟች ነው መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4

ሲኦል የሰው ልጅ የጋራ መቃብር ነው ኢዮብ 14:13፤ ራእይ 20:13

የሙታን ተስፋ ትንሣኤ ነው ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:25፤ ሥራ 24:15

ክርስቶስ ለታዛዥ የሰው ልጆች ሕይወቱን ማቴዎስ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 2:24፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል

ጸሎት መቅረብ ያለበት በክርስቶስ በኩል ለይሖዋ ብቻ ነው ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 14:6, 13, 14

የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕጎች መታዘዝ አለብን 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም አይገባንም ዘጸአት 20:4-6፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14

ከመናፍስታዊ እምነት መራቅ ይኖርብናል ዘዳግም 18:10-12፤ ገላትያ 5:19-21

አንድ ሰው ደም ወደ ሰውነቱ ውስጥ ማስገባት አይኖርበትም ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ሥራ 15:28, 29

የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ከዓለም የተለዩ ናቸው ዮሐንስ 15:19፤ 17:16፤ ያዕቆብ 1:27፤ 4:4

ክርስቲያኖች ምሥራቹን በማወጅ ይመሠክራሉ ኢሳይያስ 43:10-12፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በመጥለቅ የሚከናወን ጥምቀት ማርቆስ 1:9, 10፤ ዮሐንስ 3:22፤ ሥራ 19:4, 5

ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን ያሳያል

ሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የላቸውም ኢዮብ 32:21, 22፤ ማቴዎስ 23:8-12

የምንኖረው ‘በመጨረሻው ቀን’ ነው ዳንኤል 12:4፤ ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

የክርስቶስ መገኘት በዓይን አይታይም ማቴዎስ 24:3፤ ዮሐንስ 14:19፤ 1 ጴጥሮስ 3:18

ሰይጣን በዓይን የማይታይ የዚህ ዓለም ገዥ ነው ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19

አምላክ ይህን ክፉ ሥርዓት ያጠፋዋል ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 16:14, 16፤ 18:1-8

በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 6:10

ምድርን በጽድቅ ያስተዳድራል

ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዛው “ታናሽ መንጋ” ነው ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 14:1-4፤ 20:4

የአምላክን ሞገስ የሚያገኙት ሌሎች ሰዎች ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16፤ ራእይ 21:1-4

ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተካሄዱት ኢንኩዊዚሽኖች ወቅት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመስቀል ጦርነቶች አሠቃቂ ደም መፋሰስ አስከትለዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነተኛው ሃይማኖት በመልካም ፍሬዎቹ ተለይቶ ይታወቃል

[ምንጭ]

Cover: Garo Nalbandian

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ