ወደ አፈር መመለስ እንዴት?
“አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።” የመጀመሪያው ሰው አዳም እነዚህን ቃላት ሲሰማ ከፊቱ ምን እንደሚጠብቀው ያውቅ ነበር። የተሠራው ከምድር አፈር ነበር አሁንም ተመልሶ አፈር ይሆናል። ፈጣሪውን ይሖዋ አምላክን ሳይታዘዝ በመቅረቱ ሞት ይጠብቀው ነበር።—ዘፍጥረት 2:7, 15-17፤ 3:17-19
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከአፈር እንደተሠሩ ይገልጻል። በተጨማሪም “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” በማለት ይናገራል። (ሕዝቅኤል 18:4፤ መዝሙር 103:14) ሞት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲያዝኑ ከማድረጉም በላይ የሞተው ሰው አስከሬን ምን ይደረግ የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ጊዜያት እንዲነሣ ምክንያት ሆኗል።
ጥንት የነበረውና ዛሬ ያለው ልማድ
ጥንት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች የሰዎችን አስከሬን ምን ያደርጉ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ወደ መጀመሪያው አካባቢ መሬት ውስጥ መቅበርን ጨምሮ ለአስከሬን የተደረጉ የተለያዩ ነገሮችን ይጠቅሳል። (ዘፍጥረት 35:8) የዕብራውያን የእምነት አባት የነበረው አብርሃም፣ ሚስቱ ሣራ እንዲሁም ልጃቸው ይስሐቅና የልጅ ልጃቸው ያዕቆብ የተቀበሩት በማክጴላ ዋሻ ነበር። (ዘፍጥረት 23:2, 19፤ 25:9 የ1980 ትርጉም፤ 49:30, 31፤ 50:13) የእስራኤል መሳፍንት የነበሩት ጌዴዎንና ሳምሶንም የተቀበሩት ‘በአባቶቻቸው መቃብር’ ነው። (መሳፍንት 8:32፤ 16:31) ይህም የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች ለቤተሰባቸው የመቃብር ቦታ ማዘጋጀትን ይመርጡ እንደነበር ያሳያል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሞት አስከሬኑ ያረፈው ከድንጋይ በተፈለፈለ አዲስ ዋሻ ውስጥ ነበር። (ማቴዎስ 27:57-60) በጥቅሉ ሲታይ የሰዎች አስከሬን መሬት ውስጥ ይቀበር ነበር ወይም በመቃብር ቤት ውስጥ ይቀመጥ ነበር። ይህ ልማድ አሁንም በአብዛኛው የምድር ክፍል ይሠራበታል።
ይሁን እንጂ ዛሬ በአንዳንድ የምድር ክፍሎች ያለው ከፍተኛ የቦታ እጥረትና ለመሬት የሚጠየቀው ዋጋ መናር የቀብር ቦታ ማግኘትን አስቸጋሪ አድርጎታል። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች አስከሬኑን ምን ማድረግ እንደሚቻል አማራጭ ሐሳብ እየፈለጉ ነው።
የሰዎችን አስከሬን በማቃጠል አመዱን መበተን በሰፊው እየተለመደ ሄዷል። በእንግሊዝ ውስጥ ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት አስከሬናቸው በእሳት ይቃጠላል። በከተማዎች ውስጥ ከሚሞቱት ሰዎች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት አስከሬኖች በእሳት በሚቃጠሉባት በስዊድን አመዱን ለመበተን የተከለሉ ጫካዎች አሉ። በሻንጋይና በሌሎችም በባሕር ዳርቻ አካባቢ በሚገኙ ጥቂት የቻይና ከተሞች ውስጥ የየከተማዎቹ አስተዳደሮች የአስከሬኖቹን አመድ አንድ ላይ በማጠራቀም በዓመት በተወሰኑ ጊዜያት ወደ ባሕር የመበተኑን ሥራ ያከናውናሉ።
አመዱ የት ሊበተን ይችላል? እንዲሁ የተገኘበት ቦታ አይበተንም። አንዳንዶች አመዱን መበተን ለአካባቢ ጎጂ ተጽእኖ ይኖረዋል የሚል ፍርሃት አድሮባቸዋል። ለነገሩ አስከሬን ማቃጠል ወረርሽኝ እንዳይከሰት መከላከያ መንገድ ነው። በእንግሊዝ አገር በሚገኙ አንዳንድ መካነ መቃብሮችና በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ የአስከሬን ማሳረፊያ ሥፍራዎች አመድ እንዲበተንባቸው ተብለው የተከለሉ የሣር መስኮች ወይም የአበባ ቦታዎች ይገኛሉ። እርግጥ ነው ክርስቲያኖችን ከዚህ ሁሉ በላይ የሚያሳስባቸው አስከሬኖችን ስለማቃጠልና አመዱን ስለመበተን ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ የሚለው ጉዳይ ነው።
ቅዱስ ጽሑፉ ምን ይላል?
ነቢዩ ኢሳይያስ ‘በባቢሎን ንጉሥ ላይ’ ባስተላለፈው የፍርድ መልእክት ውስጥ እንዲህ ብሏል፦ “አንተ ግን መቀበሪያ አጥተህ ተጥለሃል።” (ኢሳይያስ 14:4, 19 አዓት) የአስከሬንን አመድ መበተን መዋረድን ከሚያሳየው ከዚህ ሁኔታ ጋር ሊነፃፀር ይችላልን? አይችልም፤ ምክንያቱም እዚህ ላይ አስከሬንን ስለማቃጠልና ካቃጠሉ በኋላ አመዱን ስለማቆየትም ሆነ አመዱን ስለመበተን የተጠቀሰ ነገር የለም።
ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚከተለው ባለ ጊዜ በእርሱ የሺህ ዓመት ግዛት ስለሚከናወነው ምድራዊ የሙታን ትንሣኤ መናገሩ ነበር፦ “[“በመታሰቢያ፣” አዓት] መቃብር ያሉቱ ሁሉ ድም[ፄ]ን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል።” (ዮሐንስ 5:28, 29) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ትንሣኤ እንዲያገኝ የግድ አንድ የተወሰነ መቃብር እንደማያስፈልገው ስለ ትንሣኤ በተሰጠ ሌላ ትንቢታዊ መግለጫ ላይ በጉልህ ተቀምጧል። ራእይ 20:13 እንዲህ ይላል፦ “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ።” ስለዚህ ወሳኙ ነገር አንድ ሰው ‘ወደ አፈር የተመለሰው’ የትና እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ዘንድ መታሰቡና ትንሣኤ ማግኘቱ ነው። (ኢዮብ 14:13-15፤ ከሉቃስ 23:42, 43 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ሰዎችን ለማስታወስ እንዲረዳው የሚያምር መቃብር ሊሠራለት እንደማያስፈልገው ግልጽ ነው። የግለሰቡ አስከሬን መቃጠሉ ትንሣኤ እንዳያገኝ አያግደውም። የአስከሬኑን አመድ መበተን ከሐሰት ሃይማኖት ሥርዓቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እስከሌለውና በትክክለኛ አመለካከት እስከተደረገ ድረስ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር አይቃረንም።
አስከሬኑን በማቃጠል አመዱን ለመበተን የሚወስኑ ካሉ የአገሩን ሕግ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የሟቹን ዘመዶችና የሌሎችንም ሰዎች ስሜት መጠበቃቸው ተገቢ ይሆናል። የይሖዋ አገልጋዮች በዚህ ረገድ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጧቸውን ነፃነት ሲጠቀሙ ክርስቲያኖች ያላቸውን መልካም ስም የሚያጎድፍ ነገር ላለማድረግ መጠንቀቃቸው የተገባ ነው። ይህ በተለይ አስከሬንን ማቃጠልና አመዱን መበተን በሕግ በተፈቀደባቸው ነገር ግን በኅብረተሰቡ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ባላገኘባቸው አገሮች ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነው። እርግጥ ነው አንድ ክርስቲያን የሰው ነፍስ አትሞትም በሚለው እምነት ላይ ከተመሠረቱ ከማንኛቸውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ወይም ባሕሎች ሙሉ በሙሉ ይርቃል።
መቃብር ፈጽሞ የማያስፈልግበት ጊዜ!
የአስከሬኑን አመድ መበተንን ደግፈው የሚከራከሩ አንዳንድ ሰዎች ከመቃብር መገላገል እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ከመቃብር ሙሉ በሙሉ የምንገላገለው ‘የኋለኛው ጠላት ሞት ይሻራል’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሲፈጸም ብቻ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:24-28
ይህም ማለት መቀበሪያ ጉድጓዶች፣ የመቃብር ዋሻዎች፣ ሬሳን ማቃጠልና አመድ መበተን ሳይቀር ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ። አዎን፣ ከዚያ ወዲያ ሞት አይኖርም። ሐዋርያው ዮሐንስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” ይህ ሁሉ የሚፈጸመው በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣው ሰብዓዊ ሞት በአምላክ መንግሥት ሥር ጨርሶ ሲወገድ ነው። የዚያን ጊዜ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አፈር የመመለስ ዕጣ አይጠብቃቸውም።—ራእይ 21:3, 4
[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የሰው አስከሬን የሚያርፍባቸው የተለመዱ መንገዶች
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጃፓን የሳጋሚ ባሕረ ሰላጤ የአስከሬን አመድ ሲበተን
[ምንጭ]
Courtesy of Koueisha, Tokyo