ሕልሞች ወደፊት የሚሆነውን ነገር ሊያሳውቁን ይችላሉን?
ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅ ስለ ሕልም ለማወቅ ጠንካራ ፍላጎት አለው። ግብፃውያን ሕልም ለመተርጎም የሚያገለግሉ ብዙ መጻሕፍት ያዘጋጁ ሲሆን ባቢሎናውያንም ሕልም ፈቺዎች ነበሯቸው። ከግሪካውያን ልማዶች አንዱ የታመሙ ሰዎች በሚያዩት ሕልም አማካኝነት የጤና መመሪያ እንዲያገኙ በማለት በኤስክለፒየስ መቅደሶች ማስተኛት ነበር። በሁለተኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር አርቴሚዶረስ የሕልም ምልክቶችን ፍቺ የያዘ አንድ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጁት ብዙ ተመሳሳይ መጻሕፍት በሱ መጽሐፍ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። እስከ ዛሬ ድረስ ሕልሞችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፤ ይሁን እንጂ ሕልሞች ወደፊት ስለሚሆኑት ነገሮች ጠለቅ ያለ ማስተዋል የሚሰጡ ናቸውን?
ሕልሞች ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ሊያሳውቁን የሚችሉት ከሰው በላይ ከሆነ ኃይል ከመጡ ብቻ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምላክ በዚህ ኃይል የተጠቀመባቸውን ብዙ ቦታዎች እናገኛለን። ለአገልጋዮቹም ሆነ እሱን ለማያመልኩ አንዳንድ ሰዎች ትንቢታዊ ሕልሞችን እንዲያዩ አድርጓቸዋል። እንዲያውም ኢዮብ 33:14-16 (የ1980 ትርጉም) “በሌሊት ሰዎች በአልጋ ላይ ተኝተው አፍላ እንቅልፍ ይዞአቸው ሳለ፣ እግዚአብሔር በሕልምና በራእይ ይናገራል” ይላል።
የዘመናችን አቆጣጠር ከመጀመሩ ከ1,700 ዓመታት በፊት ይኖር በነበረው በዮሴፍ ዘመን አምላክ ለግብፁ ፈርዖን ሕልም አሳይቶት ነበር። የፈርዖን ሕልም በዘፍጥረት 41:1-7 ላይ የሚገኝ ሲሆን ከቁጥር 25 እስከ 32 ላይ ዮሴፍ ሰባቱ ዓመታት “በግብፅ ምድር ሁሉ እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው” እንደሆኑና ከዚያ በኋላ ሰባት የረሃብ ዓመታት እንደሚከተሉ በመግለጽ ሕልሙን ተርጉሟል። ዮሴፍ “እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳየው” በማለት ለፈርዖን ገልጾለታል። (ዘፍጥረት 41:28) ሕልሙ ትንቢታዊ ቁም ነገሮችን የያዘ ነበር፤ ያም በትክክል ተፈጽሟል።
አንድ የታወቀ የባቢሎናውያን ንጉሥ ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ናቡከደነፆር አንድ በጣም የሚረብሽ ሕልም ቢያይም እንኳን ሕልሙን ሊያስታውሰው አልቻለም። ስለዚህ ሕልሙንና ፍቺውን እንዲያሳውቁት አስማተኞቹን ጠራ። ይህ ጥያቄ እነሱ ሊፈጽሙት የማይችሉት ነበር።—ዳንኤል 2:1-11
ሕልሙን ለንጉሡ የሰጠው አምላክ በመሆኑ ነቢዩ ዳንኤል ሕልሙንና ትርጓሜውን እንዲያሳውቅ አደረገ። ዳንኤል 2:19 “የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት” ይላል። ዳንኤል በዚህ ሕልም ምክንያት እንዲህ በማለት አምላክን አመስግኗል፦ “ንጉሡ የጠየቀውን ምሥጢር ጠቢባንና አስማተኞች የሕልም ተርጓሚዎችና ቃላተኞች ለንጉሡ ያሳዩ ዘንድ አይችሉም፤ ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፣ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናቡከደነፆር አስታውቆታል።”—ዳንኤል 2:27, 28
አምላክ በሕልም አማካኝነት ለሕዝቡ መመሪያዎችን የሰጠበት ጊዜ አለ፤ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ መለኮታዊ ሞገስ እንዳላቸው ለማረጋገጥ ወይም እንዴት እንደሚረዳቸው እንዲያስተውሉ ለመርዳት ሕልሞችን ተጠቅሟል። አምላክ ያዕቆብን እንደ ተቀበለው በሕልም አማካኝነት ገልጾለታል።—ዘፍጥረት 48:3, 4
የኢየሱስ አሳዳጊ አባት የነበረው ዮሴፍ ማርያም እንዳረገዘች ሲያውቅ እሷን ለመፍታት ወሰነ። ከዚያም እንዲህ እንዳያደርግ በሕልም አማካኝነት መመሪያዎችን ተቀበለ። ማቴዎስ 1:20 እንዲህ ይላል፦ “እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፣ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፣ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፣ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።” ከዚያም በሕልም አማካኝነት የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ተቀበለ፦ “የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ፦ . . . ተነሣ፣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ።”—ማቴዎስ 2:13
ከአምላክ ያልመጡ ሕልሞች
የአምላክ ሕዝቦች ባልሆኑ ሰዎች መካከል የሕልም ትርጓሜ የተስፋፋ መሆኑ ሕልሞች ባጠቃላይ የወደፊቱን ጊዜ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ያሳውቃሉ ለማለት እንደማይቻል ያሳያል። የአምላክ ነቢይ በነበረው በኤርምያስ ዘመን የሐሰት ነቢያት “አለምሁ አለምሁ” ይሉ ነበር። (ኤርምያስ 23:25) ዓላማቸው አምላክ በእነሱ አማካኝነት እንደሚናገር ሕዝቡን ማሳመን ነበር። ኤርምያስ እነዚህን ሕልም አላሚዎች በተመለከተ እንዲህ ሲል በመንፈስ አነሣሽነት ተናግሯል፦ “የእስራኤልም አምላክ የሆንሁ እኔ በመካከላችሁ በሚገኙ ነቢያት ነን ባይዎችና ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድመን እናውቃለን በሚሉ በማንኛዎቹም ሐሰተኛ ተናጋሪዎች ሁሉ ራሳችሁን እንዳታታልሉ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ለሕልማቸውም ምንም ዋጋ አትስጡት። እነርሱ በእኔ ስም የሚነግሩአችሁ ትንቢት ሁሉ ሐሰት ነው፤ . . . እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”—ኤርምያስ 29:8, 9 የ1980 ትርጉም
እነዚህ ሐሰተኛ ነቢያት ‘ምዋርተኞች’ ስለሆኑ ሕልሞቻቸው ሕዝቡን ለማታለል የሚሹት የክፉ መናፍስታዊ ኃይሎች ተጽዕኖ ሊኖርበት ይችላል። በዘካርያስ 10:2 ላይ ተመሳሳይ ነገር ተገልጿል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ተራፊም ከንቱን ተናግረዋልና፣ ምዋርተኞችም ውሸትን አይተዋልና፤ ሕልምንም የሚያዩ በሐሰት ተናግረዋል።”
በኤርምያስና በዘካርያስ ዘመን የነበሩ ሐሰተኛ ነቢያት እንዳደረጉት ሁሉ ውሸታቸውን አምላክ በራእይና በሕልም ይናገረናል በሚሉ የሃይማኖት መሪዎች ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲጠቀም የኖረው ዋነኛ አታላይ ዲያብሎስ ነው። እነዚህን ሰዎች አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ አነሣሽነት ከጻፉት ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ይሁዳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸው ነበር፦ “የሚፈረድባቸው መሆኑ ከብዙ ጊዜ በፊት የተጻፈባቸው አንዳንድ ሰዎች ወደ እናንተ ሾልከው ገብተዋል፤ እነርሱ የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት የሚለውጡ ኃጢአተኞች ናቸው፤ እርሱ ብቻ ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስንም ይክዳሉ።” ይሁዳ እነዚህ ሰዎች ይህን ያደረጉት “በሕልም እየተመሩ” ነው ብሏል።—ይሁዳ 4, 8 የ1980 ትርጉም
የሚናገሩት እውነት መሆኑን አረጋግጥ
አንድ ሰው አምላክ በሕልም እንዳነጋገረው ወይም ወደፊት የሚሆነውን ነገር በተመለከተ የሚያያቸው ሕልሞች እንደተፈጸሙ ቢናገርም እሱን ለማመንና በጭፍን ለመከተል ይህ በቂ ምክንያት አይሆንም። በዘዳግም 13:1-3, 5 ላይ ለእስራኤላውያን የተጻፉላቸውን የሚከተሉትን መመሪያዎች ልብ በል፦ “በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፣ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፣ እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፣ እርሱም፦ ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፣ . . . የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ። . . . ያ ነቢይ ወይም ያ ሕልም አላሚ ይገደል።” አምላክ እነዚህ ሰዎች ሐሰት እንዲናገሩ የፈቀደው የሕዝቡን ታማኝነት ለመፈተን ነው።
ተአምር እንሠራለን የሚሉ ሕልም አላሚዎችን በጭፍን ከማመን ይልቅ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው” የማይታየው ቀንደኛ አታላይ እንዳያስተን የሚናገሩት እውነት መሆኑን ማረጋገጣችን ጥበብ ነው። (ራእይ 12:9) ይሁን እንጂ በትክክል ልንመረምራቸው የምንችለው እንዴት ነው?
የተጻፈው የአምላክ ቃል ወደ እውነት የሚመራን መለኮታዊ ስጦታ ነው። እሱን በተመለከተ ኢየሱስ ክርስቶስ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:17) ስለዚህ በ1 ዮሐንስ 4:1 ላይ “ወዳጆች ሆይ፣ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል። የሚናገሯቸውን ነገሮች፣ ፍልስፍናዎችና ድርጊቶች በጥንቃቄ ስንመረምራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫሉ። እውነቱ ምን እንደሆነ ማረጋገጥ የሚቻለው በአምላክ ቃል ነው።
ልዩ እውቀት አለኝ የሚለው ሕልም አላሚ አስማት ወይም ሌሎች መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይጠቀማልን? እንዲህ የሚያደርግ ከሆነ በአምላክ ቃል የተወገዘ ነው። “ምዋርተኛም፣ ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ መተተኛም፣ በድግምት የሚያስጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።”—ዘዳግም 18:10-12
ሕልም አላሚው የማትሞት ነፍስ አለችኝ የሚል ከሆነ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” በማለት በግልጽ ከሚናገረው የአምላክ ቃል ጋር እየተቃረነ ነው። (ሕዝቅኤል 18:4) ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግና የራሱን ተከታዮች ለማፍራት የሚጥር ሰው ነውን? ማቴዎስ 23:12 “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል” የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። በተጨማሪም ሥራ 20:30 ክርስቲያኖችን ሲያስጠነቅቅ “ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ” ይላል።
ሕልም አላሚው የዓመፅ ድርጊቶችን ይደግፋልን? ያዕቆብ 3:17, 18 እንዲህ ሲል ያወግዘዋል፦ “ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፣ በኋላም ታራቂ [“ሰላማዊ፣” አዓት]፣ ገር፣ እሺ ባይ፣ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፣ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።” በዓለም ውስጥ ፖለቲካዊ ሥልጣን ወይም ተደማጭነት ለማግኘት ይፈልጋልን? የአምላክ ቃል “የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” በማለት አጥብቆ ያወግዘዋል። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሐሰት የሆነውን ነገር ያጋልጣል።—ያዕቆብ 4:4
አንድ ግለሰብ ስለ አንድ የቤተሰቡ አባል ወይም ስለ አንድ ወዳጁ ሞት ሕልም ያየው ምናልባት ስለዚህ ግለሰብ ስላሰበ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ በዚያው ሌሊት መሞቱ ብቻ ሕልሙ ትንቢታዊ ለመሆኑ ማረጋገጫ አይሆንም። ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሕልሞች መካከል በትክክል የተፈጸመ የሚመስል ቢገኝ እንኳ ከስንት መቶው አንድ ነው።
ምንም እንኳ በጥንት ዘመን አምላክ ቃሉን በጽሑፍ በሚያዘጋጅበት ወቅት ትንቢታዊ ሁኔታዎችን ለማሳወቅና ትምህርቶችን ለመስጠት በሕልሞች የተጠቀመ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ እንዲህ ማድረግ አያስፈልገውም። ይህ የተጻፈ ቃል የሰው ልጅ በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጉትን የአምላክ መመሪያዎች በሙሉ የያዘ ሲሆን በውስጡ ያሉት ትንቢቶች ገና ወደፊት ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ጭምር የሚፈጸሙ ሁኔታዎችን የሚመለከቱ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ስለዚህ ሕልሞቻችን አምላክ ወደፊት የሚፈጸመውን ነገር እንደገለጸልን የሚጠቁሙ ነገሮች ሳይሆኑ አእምሯችን በትክክል መሥራቱን እንዲቀጥል ለማድረግ የሚረዱ የግድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንደሆኑ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፈርዖን ሕልም ስለ መጪዎቹ ነገሮች እንዳሳወቀ ሁሉ የአምላክ ቃልም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስፈላጊውን እውቀት ይሰጠናል