ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ሀብት የሚነገረው የተጋነነ ነውን?
“በአንድ ዓመት ብቻ ለሰሎሞን የመጣለት የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ነበር።”—1 ነገሥት 10:14 አዓት
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መሠረት ንጉሥ ሰሎሞን በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 25 ቶን የሚመዝን ወርቅ አግኝቷል! ይህ በዛሬ ጊዜ ቢተመን 240,000,000 የአሜሪካ ዶላር ያወጣል። ይህም በ1800 በዓለም ዙሪያ ከተመረተው ወርቅ በጠቅላላ ሁለት እጥፍ የሚበልጥ ነው። ይህ ሊሆን ይችላልን? የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች ምን ያሳያሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰሎሞን ሀብት የሚናገረው ነገር ከሐቁ የራቀ አለመሆኑን ይመሠክራሉ። ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦
◻ የግብጹ ንጉሥ ታትሞስ ሦስተኛ (በሁለተኛው ሺህ ከዘአበ) በግምት 13.5 ቶን የሚመዝን ወርቅ በካርናክ ለሚገኘው የአሞን ራ ቤተ መቅደስ ገጸ በረከት ሰጥቷል፤ ይህም የስጦታው ገሚሱ ክፍል ብቻ ነበር።
◻ የግብጻውያን የግድግዳ ላይ ጽሑፎች ንጉሥ ኦሶርካን አንደኛ (ከዘአበ በመጀመሪያው ሺህ ዓመት መጀመሪያ ላይ) በድምሩ ወደ 383 ቶን የሚጠጋ ወርቅና ብር ለአማልክት እንዳበረከተ ይዘግባሉ።
ተጨማሪም ግሬት ኤጅስ ኦቭ ማን የተባለው መጽሐፍ ክላሲክ ግሪክ በተሰኘው ጥራዙ ላይ እንዲህ በማለት አስፍሯል፦
◻ ትሬስ ውስጥ ይገኙ የነበሩት የፓንጂን ማዕድን ማውጫ ጉድጓዶች ለንጉሥ ፊሊፕ ሁለተኛ (359-336 ከዘአበ) በየዓመቱ ከ37 ቶን በላይ ወርቅ ያስገኙለት ነበር።
◻ የፊሊፕ ልጅ ታላቁ እስክንድር (336-323 ከዘአበ) የፋርስ ግዛት ዋና ከተማ የነበረችውን ሱሳንን ሲቆጣጠር ዋጋቸው ከ1,000 ቶን ወርቅ የሚበልጥ ብዙ ውድ ንብረቶች ተገኝተዋል።—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ
እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ሀብት የሚሰጠው መግለጫ የማይመስል ነገር አይደለም። ደግሞም “ሰሎሞን በባለጠግነትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ በልጦ” እንደነበረም አትዘንጋ።—1 ነገሥት 10:23
ሰሎሞን ሀብቱን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ዙፋኑ “በጥሩ ወርቅ” የተለበጠ ነበር፣ የመጠጫ ዕቃዎቹ “ወርቅ” ነበሩ፤ እንዲሁም “ከጥፍጥፍ ወርቅ” የተሠሩ 200 ትላልቅና 300 ትናንሽ ጋሻ ነበረው። (1 ነገሥት 10:16-21) ሰሎሞን ከዚህ ሁሉ ይበልጥ ደግሞ ወርቁን የተጠቀመበት በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ነበር። የቤተ መቅደሱ መቅረዞችና እንደ ሹካ፣ ሳህን፣ ማንቆርቆሪያና መታጠቢያ ሰን ያሉት ነዋየ ቅድሳት ሁሉ ከወርቅና ብር የተሠሩ ነበሩ። በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የሚገኙት 4.5 ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ኪሩቦች፣ የዕጣን መሠዊያውና የቤቱ ውስጠኛ ክፍል ሳይቀር በወርቅ የተለበጡ ነበሩ።—1 ነገሥት 6:20-22፤ 7:48-50፤ 1 ዜና መዋዕል 28:17
ወርቅ ቅብ ስለሆነው ቤተ መቅደስስ ምን ማለት ይቻላል? የሚያስገርመው ወርቅን ለዚህ ግልጋሎት ማዋሉ በጥንት ዘመን እንግዳ ነገር አልነበረም። ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተባለው መጽሐፍ ስለ ግብጹ አሜኖፊስ ሦስተኛ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በቴቤስ ‘ሁለመናው ወርቅ ቅብ የሆነ፣ ወለሉ በብር ያጌጠ [እና] ከጥፍጥፍ ወርቅና ብር የተሠሩ ትላልቅ በሮች’ የነበሩት ቤተ መቅደስ በመገንባት ታላቁን አምላክ አሙንን አክብሮታል።” ከዚህም በተጨማሪ የአሦሩ ኤሳር ሃደን (በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ) የአሸርን ቅዱስ ስፍራ በሮች ወርቅ ቅብ ከማስደረጉም በላይ ግድግዳዎቹ በወርቅ እንዲሸፈኑ አድርጓል። በሃራን የሚገኘውን የሲን ቤተ መቅደስ በተመለከተ የባቢሎኑ ናቦኒደስ (በስድስተኛው መቶ ዘመን ከአዘበ) የሚከተለውን አስመዝግቧል፦ “ግድግዳዎቹን በወርቅና ብር አልብሻለሁ፤ እንደ ፀሐይም እንዲበሩ አድርጌአለሁ።”
እንግዲያውስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ሀብት የሚናገረው ነገር የተጋነነ እንዳልሆነ ታሪካዊ ዘገባዎች ይመሠክራሉ።