የ“ዳዊት ቤት”እውነተኛ ታሪክ ነው ወይስ ልብ ወለድ?
ከጊዜ በኋላ ሙዚቀኛ፣ ገጣሚ፣ ወታደር፣ ነቢይና ንጉሥ የሆነው ወጣቱ እረኛ ዳዊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፊው የተነገረለትና የጎላ ሥፍራ የያዘ ሰው ነው። ስሙ 1,138 ጊዜ ተጠቅሷል፤ ብዙውን ጊዜ የዳዊትን ሥርወ መንግሥት ለማመልከት የሚሠራበት የ“ዳዊት ቤት” የሚለው አነጋገር 25 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። (1 ሳሙኤል 20:16) ንጉሥ ዳዊትና ሥርወ መንግሥቱ እንዲያው ልብ ወለድ ናቸውን? አርኪኦሎጂ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? የአርኪኦሎጂ ቁፋሮ በሚካሄድበት ከገሊላ በስተሰሜን ባለው በቴል ዳን በቅርቡ የተገኘው አስደናቂ ግኝት ስለ ዳዊትና ስለ ሥርወ መንግሥቱ የሚናገረው ታሪክ ሐቅ መሆኑን አረጋግጧል።
በፕሮፌሰር አቭራአም ቢራን የሚመራ አንድ የአርኪኦሎጂስቶች ቡድን በ1993 የበጋ ወራት ከጥንቷ ዳን መግቢያ ውጪ ያለውን አካባቢ ሲመነጥር በድንጋይ የተነጠፈ አንድ አደባባይ አገኘ። ከዚያም ከመሬት በላይ ገጥጦ ይታይ የነበረ አንድ ጥቁር ድንጋይ በቀላሉ ፈንቅለው አወጡ። ድንጋዩን ወደ ላይ ገልብጠው በዚያ የቀትር ፀሐይ ሲመለከቱት እላዩ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ ቁልጭ ብሎ ታየ። “ኧረ አምላኬ፣ የተቀረጸ ጽሑፍ አለበት!” ሲሉ ፕሮፌሰር ቢራን በመደነቅ ተናገሩ።
ፕሮፌሰር ቢራንና ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው የሂብሩ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት የሥራ ጓደኛቸው ፕሮፌሰር ጆሴፍ ኔቬህ ወዲያውኑ በድንጋዩ ላይ የተቀረጸውን ጽሑፍ አስመልክተው ሳይንሳዊ ሪፖርት ጻፉ። በዚህ ሪፖርት ላይ በመመርኮዝ ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው በተባለው የመጋቢት/ሚያዝያ 1994 መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፦ “(እንኳን የታይም መጽሔት ይቅርና) ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ እንኳ ብዙውን ጊዜ አንድን የአርኪኦሎጂ ግኝት የሚመለከት ርዕስ በመጀመሪያ ገጹ ላይ ይዞ አይወጣም። ይሁን እንጂ ባለፈው የበጋ ወቅት በቴል ዳን፣ ከሄርሞን ተራራ ሥር ከአንዱ የዮርዳኖስ ወንዝ ምንጭ አጠገብ በሰሜናዊ ገሊላ በሚገኘው አንድ ውብ ጉብታ የተገኘውን ግኝት አስመልክተው በመጀመሪያ ገጻቸው ላይ ዘግበዋል።
“በዚያ ሥፍራ አቭራአም ቢራንና በእሳቸው የሚመራው የአርኪኦሎጂስቶች ቡድን ስለ ‘ዳዊት ቤት’ እና ስለ ‘እስራኤል ንጉሥ’ የሚናገር በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በአንድ ድንጋይ ላይ የተቀረጸ አስገራሚ ጽሑፍ አግኝተዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ በሌላ ጥንታዊ ጽሑፍ ላይ የዳዊት ስም ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው። በድንጋዩ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ ‘ዳዊትን’ ብቻ ሳይሆን የታላቁን የእስራኤል ንጉሥ ሥርወ መንግሥት የዳዊትን ቤት የሚጠቅስ መሆኑ ነገሩን ይበልጥ አስደናቂ ያደርገዋል።
“‘የእስራኤል ንጉሥ’ የሚለው አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለይም ደግሞ በነገሥት መጽሐፍ ውስጥ በብዛት ይገኛል። ይሁን እንጂ ይህ ግኝት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ እስራኤልን አስመልክቶ በሴማዊ ቋንቋ ከተዘጋጁት ጽሑፎች ሁሉ ጥንታዊው ሊሆን ይችላል። ሌላው ቢቀር ይህ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስን የሚተቹ አንዳንድ ምሁራን ከሚሰጡት ሐሳብ ተቃራኒ በሆነ መልኩ እስራኤልም ሆነች ይሁዳ በዚያ ዘመን ታላላቅ መንግሥታት እንደነበሩ ያሳያል።”
በድንጋዩ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ የተጻፈበትን ዘመን ለማወቅ የተቻለው በጽሑፉ ቅርጽ፣ ከድንጋዩ ስባሪ አጠገብ በተገኘው የሸክላ ሥራ ላይ በተካሄደ ጥናትና በጽሑፉ ይዘት ላይ በመመርኮዝ ነው። በሦስቱም መንገዶች የተደረገው ጥናት ጽሑፉ የተጻፈው ከንጉሥ ዳዊት ዘመን አንድ መቶ ዓመት በኋላ በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንደሆነ ይጠቁማል። ምሁራን ይህ በድንጋይ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ የ“እስራኤልም ንጉሥ” ሆነ “የዳዊት ቤት [ንጉሥ]” ጠላቶች በነበሩት በአራምውያን ዳን ውስጥ የተተከለ የድል ማስታወሻ ሐውልት አንድ አካል ነው የሚል እምነት አላቸው። አራምውያን ከእስራኤል በስተ ምሥራቅ ይኖሩ የነበሩና በስፋት የሚታወቀውን ሃዳድ የተባለ የዓውሎ ነፋስ አምላክ ያመልኩ የነበሩ ሰዎች ናቸው።
በ1994 የበጋ ወራት የዚህ ሐውልት ተጨማሪ ሁለት ስባሪዎች ተገኙ። ፕሮፌሰር ቢራን “በእነዚህ ሁለት ስባሪዎች ላይ የአራምውያን አምላክ የሆነው የሃዳድ ስም እንዲሁም በእስራኤላውያንና በአራምውያን መካከል ስለተደረገ ጦርነት የሚገልጽ ጽሑፍ ሰፍሮ ይገኛል” ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል።
በ1993 የተገኘው ዋናው ስባሪ በጥንታዊ የዕብራይስጥ ጽሑፍ የተጻፉና በከፊል የሚታዩ 13 መስመሮችን ይዟል። በዚያ ዘመን ቃላትን ለያይቶ ለማስቀመጥ በቃላት መሐል ነጥቦችን ይጠቀሙ ነበር። ይሁን እንጂ “የዳዊት ቤት” የሚለው አነጋገር “በየተ” (ቤት)፣ ነጥብ ከዚያ “ደወደ” (ዳዊት) ተብለው ሳይሆን “በየተደወደ” (በአማርኛ ፊደላት ሲቀመጡ) በሚሉት ፊደላት እንደ አንድ ቃል ተደርጎ ተጽፏል። “በየተደወደ” የሚሉትን ፊደላት በመተርጎም ረገድ አንዳንድ ጥያቄዎች እንደተነሱ ምንም ጥርጥር የለውም።
በቋንቋ ጥናት ኤክስፐርት የሆኑት ፕሮፌሰር አንሰን ሬኒ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “ጆሴፍ ኔቬህና አቭራአም ቢራን ስለ ጽሑፉ ዝርዝር መግለጫ አልሰጡም፤ ምናልባትም ይህን ያላደረጉት አንባቢዎች በእንዲህ ዓይነቱ የአጻጻፍ ስልት በተለይ ደግሞ ቃላቱ ለረጅም ጊዜ አንድ ላይ ተጣምረው ሲሠራባቸው የቆዩ ትክክለኛ መጠሪያ ከሆኑ ቃላቱን ለመለያየት የሚገባው ነጥብ ብዙውን ጊዜ የሚቀር መሆኑን ይረዳሉ የሚል አስተሳሰብ አድሮባቸው ይሆናል። ‘የዳዊት ቤት’ የሚለው አነጋገር በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ በነበሩት ዓመታት ትክክለኛ የሆነ ፖለቲካዊና ጂኦግራፊያዊ መጠሪያ ነበር።”
ሌላ የአርኪኦሎጂ ማስረጃ
ከዚህ ግኝት በኋላ በሜሻ ሐውልት (የሞዓባውያን ጽላት ተብሎም ይጠራል) ጥናት ኤክስፐርት የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሬ ለሜር ይኼኛውም ጽላት ስለ “ዳዊት ቤት” እንደሚናገር ገልጸዋል።a በ1868 የተገኘው የሜሻ ሐውልት ከቴል ዳን ሐውልት ጋር ብዙ ተመሳሳይነት አለው። ሁለቱም የተሠሩት በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከአዘበ ሲሆን የተሠሩበት ነገርም ሆነ መጠናቸው ተመሳሳይ ነው፤ በተጨማሪም እላያቸው ላይ በሴማዊ ቋንቋ የተጻፈው ጽሑፍ ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል።
በሜሻ ሐውልት ላይ ከተጻፈው ጽሑፍ መካከል በአንደኛው መስመር ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል የተደረገውን ጥረት አስመልክተው ፕሮፌሰር ለሜር ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል፦ “የቴል ዳን ስባሪ ከመገኘቱ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የሜሻ ሐውልት ስለ ‘ዳዊት ቤት’ የሚናገር ሐሳብ ይዟል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሼ ነበር። . . . ስለ ‘ዳዊት ቤት’ የሚናገር ሐሳብ መያዙ ቀደም ሲል ሊታወቅ ያልቻለው የሜሻ ሐውልት ትክክለኛ ኤዲቲዮ ፕሪንኬፕዝ [የመጀመሪያ እትም] ስላልነበረው ሊሆን ይችላል። የሜሻ ሐውልት ከተገኘ ከ125 ዓመታት በኋላ እያዘጋጀሁት ያለሁት ይህንን ነው።”
አንድ መልአክ፣ ኢየሱስ ራሱ፣ ደቀ መዛሙርቱና ሰዎች በጠቅላላ ስለ ዳዊት ታሪክ እውነተኛነት የመሰከሩ በመሆኑ ይህ የአርኪኦሎጂ መረጃ ትኩረት የሚስብ ነው። (ማቴዎስ 1:1፤ 12:3፤ 21:9፤ ሉቃስ 1:32፤ ሥራ 2:29) የአርኪኦሎጂ ግኝቶች ዳዊትና የእሱ ሥርወ መንግሥት የሆነው የ“ዳዊት ቤት” ልብ ወለድ ሳይሆኑ እውነተኛ ታሪክ መሆናቸውን በግልጽ ይደግፋሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን የሚያነቡ ሰዎች የሜሻን ሐውልት ያውቁታል። (የሚያዝያ 15, 1990 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 30-1 ተመልከት።) ሐውልቱ ፓሪስ በሚገኘው የሉቭር ሙዚየም ውስጥ ይገኛል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1993 ከገሊላ በስተ ሰሜን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተገለጸችው የዳን ከተማ የተገኘው የቴል ዳን ስባሪ*
* ሥዕሉ የተወሰደው ኢዝራኤል ኤክስፕሎሬሽን ጆርናል በተባለ መጽሔት ላይ ከወጣው ፎቶግራፍ ነው።