ስለ ኢየሱስ እውነቱ ምንድን ነው?
የኢየሱስን ማንነትና ያከናወናቸውን ነገሮች በተመለከተ የሚቀርቡት አስተያየቶችና መላምቶች መቋጫ ያላቸው አይመስልም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን የሚነግረን ነገር አለው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በማንበብ እነዚህን ቁልፍ እውነታዎች ትገነዘባለህ፦
◻ ኢየሱስ የአምላክ አንድያ ልጅና የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው።—ዮሐንስ 3:16፤ ቆላስይስ 1:15
◻ ኢየሱስ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ለማድረግ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት አምላክ የኢየሱስን ሕይወት ወደ አንዲት ድንግል አይሁዳዊት ማኅፀን አዛወረው።—ማቴዎስ 1:18፤ ዮሐንስ 1:14
◻ ኢየሱስ እንዲያው እንደ አንድ ጥሩ ሰው የሚታይ ብቻ አልነበረም። በማንኛውም ረገድ የአባቱ የይሖዋ አምላክ ድንቅ ባሕርያት ትክክለኛ ነጸብራቅ ነበር።—ዮሐንስ 14:9, 10፤ ዕብራውያን 1:3
◻ ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ለተቸገሩ ሰዎች በፍቅር ተነሳስቶ መልካም አድርጓል። በሽተኞችን በተአምር ፈውሷል፤ ሌላው ቀርቶ የሞቱትን አስነስቷል።—ማቴዎስ 11:4-6፤ ዮሐንስ 11:5-45
◻ ኢየሱስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለወደቀው የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን አውጅዋል፤ እንዲሁም ይህን የስብከት ሥራ እንዲቀጥሉበት ደቀ መዛሙርቱን አሰልጥኗቸዋል።—ማቴዎስ 4:17፤ 10:5-7፤ 28:19, 20
◻ ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 14 (ሚያዝያ 1 ገደማ) እንደ ወንጀለኛ ተይዞ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ተፈረደበት፤ ሕዝብን በመንግሥት ላይ አነሳስቷል በሚል የሐሰት ክስ ተሰቅሎ ተገደለ።—ማቴዎስ 26:18-20, 48 እስከ 27:50
◻ የኢየሱስ ሞት ሰውን ከወደቀበት የኃጢአት ባርነት ነፃ የሚያወጣ ቤዛ ሆኖ ከማገልገሉም በላይ በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በር ከፍቷል።—ሮሜ 3:23, 24፤ 1 ዮሐንስ 2:2
◻ ኢየሱስ ኒሳን 16 ከሞት ተነስቶ ጥቂት ከቆየ በኋላ የፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛዊ ዋጋ ለአባቱ ለመክፈል ተመልሶ ወደ ሰማይ አርጓል።—ማርቆስ 16:1-8፤ ሉቃስ 24:50-53፤ ሥራ 1:6-9
◻ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ይሖዋ የሾመው ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን አምላክ ለሰው ልጅ የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ የማስፈጸም ሙሉ ሥልጣን አለው።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ሉቃስ 1:32, 33
እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን የአምላክን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አድርጎ ያቀርበዋል። ሆኖም ይህ በቤተ ልሔም የተወለደውና ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት በምድር ላይ የኖረው በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው ሰው እውነተኛው ኢየሱስ መሆኑን እንዴት እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ?
እርግጠኛ ለመሆን የሚያስችሉ መሠረቶች
አእምሮን ክፍት አድርጎ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በማንበብ ብቻ ብዙ ጥርጣሬዎችን ማስወገድ ይቻላል። እንዲህ ካደረግህ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክን ቁልጭ አድርጎ በማስፈር ረገድ ከአፈ ታሪክ ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ትገነዘባለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሞች፣ ጊዜያትና ቦታዎች በትክክል ተጠቅሰዋል። (ለምሳሌ ያህል ሉቃስ 3:1, 2ን ተመልከት።) ከዚህም በላይ ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሚያስደንቅ ሐቀኝነት በትክክል መጻፋቸው አንባቢው ትምክህት እንዲያድርበት የሚያደርግ ነው። ጸሐፊዎቹ ትክክለኛ የሆነውን ታሪክ ለመመዝገብ ፍላጎት ስለነበራቸው ስለማንኛውም ሰው ሌላው ቀርቶ ስለራሳቸው እንኳ ሳይቀር ሐቁን ቁልጭ አድርገው ጽፈዋል። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሐሳብ እውነት መሆኑን እንድትገነዘብ ያደርግሃል።—ማቴዎስ 14:28-31፤ 16:21-23፤ 26:56, 69-75፤ ማርቆስ 9:33, 34፤ ገላትያ 2:11-14፤ 2 ጴጥሮስ 1:16
ይህ ብቻም አይደለም። የአርኪኦሎጂ ግኝቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክለኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜያት አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ያህል በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእስራኤል ሙዚየም ብትጎበኝ የጰንጤናዊው ጲላጦስን ስም የሚጠቅስ ጽሑፍ የተቀረጸበት ድንጋይ ማየት ትችላለህ። ሌሎች የአርኪኦሎጂ ግኝቶች ሊሳኒዮስና ሰርጊዮስ ጳውሎስ በታሪክ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስም እነዚህን ሰዎች የሚጠቅሳቸው የጥንት ክርስቲያኖች የፈጠሯቸው ልብ ወለድ ሰዎች እንደሆኑ አድርጎ ሳይሆን በእርግጥ በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች እንደሆኑ አድርጎ ነው። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች (በአዲስ ኪዳን) ውስጥ የሰፈሩት ታሪኮች ጁቬናል፣ ታሲተስ፣ ሴኔካ፣ ሱቶኒየስ፣ ታናሹ ፕሊኒ፣ ሉሸን፣ ኬልስስ እና አይሁዳዊውን ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስን ጨምሮ ከበርካታ የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች ለትክክለኝነታቸው በቂ ማረጋገጫ አግኝተዋል።a
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉት ታሪኮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ በነበሩ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ ያለ ምንም ጥያቄ ተቀባይነት አግኝተው ነበር። ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች በተመለከተ የቀረቡትን ዘገባዎች እውነተኝነት የክርስትና ጠላቶች እንኳን አልካዱም። እሱ ከሞተ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በኢየሱስ ታሪክ ላይ የሌለ ነገር ጨማምረዋል የሚለውን ሐሳብ በተመለከተ ፕሮፌሰር ኤፍ ብሩስ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፦ “በዚያን ወቅት የተፈጸመውንም ሆነ ያልተፈጸመውን ሁኔታ ለማስታወስ የሚችሉ በርካታ ደቀ መዛሙርቱ በሕይወት በነበሩበት ወቅት አንዳንድ ደራሲዎች እንደሚያስቡት ኢየሱስ እንዲህ ብሏል ወይም እንዲህ አድርጓል ብሎ የሌለ ነገር ፈጥሮ መጻፍ በምንም ዓይነት ቀላል ሊሆን አይችልም። . . . እነሱን ሐሰተኛ አድርገው ለማቅረብ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ሰዎች ስለነበሩ ደቀ መዛሙርቱ (ሆን ብለው ሐቁን ሊያጣምሙ ይቅርና) ጥቃቅን ስህተቶች እንኳ እንዳይኖሩ መጠንቀቅ ነበረባቸው።”
የማያምኑበት ምክንያት
ሆኖም አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን አሁንም ብዙ ጥርጣሬ አላቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ልብ ወለድ ነው እያሉ አዋልድ መጻሕፍትን አንድ በአንድ ከመመርመራቸውም በላይ እነዚህን መጻሕፍት ትክክለኛ እንደሆኑ አድርገው ይቀበላሉ! ለምን? የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በዘመናችን ያሉት ብዙ ምሁራን ሊያምኑ የማይፈልጓቸውን ነገሮች እንደያዘ ግልጽ ነው።
ኤስ ኦስቲን አልቦን በ1871 በታተመው ዩኒየን ባይብል ካምፓኒየን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ እውነተኝነት የሚጠራጠሩ ሰዎችን የሚቃወም ሐሳብ አስፍረዋል። እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “የወንጌል ታሪኮች የያዙትን እውነት እጠራጠራለሁ የሚለውን ማንኛውንም ሰው ቄሣር ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዳለ መሞቱን ወይም በ800 ንጉሠ ነገሥት ሻርለማኝን የምዕራብ ንጉሠ ነገሥት አድርገው ዘውድ የጫኑለት ፖፕ ሊዮ ሦስተኛ መሆናቸውን እንዲያምን ያደረገው ምን እንደሆነ ጠይቁት። . . . እነዚህን ሰዎች በተመለከተ የተነገረውን . . . ሁሉ እናምናለን፤ ምክንያቱም ስለ እውነተኝነታቸው የሚመሰክሩ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉልን። . . . እነዚህ ታሪካዊ ማስረጃዎች እያሉላቸው ለማመን አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች ካሉ ምንም የማይገባቸው ደረቆች ወይም ደንቆሮዎች ብለን መተው ነው እንጂ መቼም ምንም ልናደርጋቸው አንችልም። የቅዱሳን ጽሑፎችን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡትን በርካታ ማስረጃዎች እያዩ አላምን የሚሉትን ታዲያ ምን እንበላቸው? . . . ክብራቸውን ዝቅ የሚያደርግባቸውንና አኗኗራቸውን እንዲለውጡ የሚያስገድዳቸውን ነገር አምነው መቀበል አይሹም።”
አንዳንድ ተጠራጣሪዎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዳይቀበሉ የሚያደርግ አንድ በውስጣቸው የተሰወረ ግፊት አለ። እነሱ ችግራቸው ከቅዱሳን ጽሑፎች ተአማኒነት ሳይሆን ከአቋም ደረጃዎቻቸው ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ “እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:14) ሆኖም አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮች ከፍተኛ ደም መፋሰስ ባስከተሉ ጦርነቶች እንኳ ሳይቀር በዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ በጣም ተጠላልፈዋል። ራሳቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ከማስማማት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ከእነሱ የአቋም ደረጃዎች ጋር እንዲስማማ ይፈልጋሉ።
የሥነ ምግባር ጉዳይንም እንመልከት። ዝሙት መፈጸምን በቸልታ ይመለከት ለነበረው የቲያጥሮን ጉባኤ ኢየሱስ ኃይለኛ ምክር ሰጥቷል። “ኩላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፣ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ” ብሏቸዋል።b (ራእይ 2:18-23) ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ክርስቲያን ነን ባዮች የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎችን አሽቀንጥረው ጥለዋቸው የለምን? የብልግና አኗኗራቸውን ከመተው ይልቅ ኢየሱስ የተናገረውን አንቀበልም ቢሉ ይቀላቸዋል።
የሃይማኖት ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱሱን ኢየሱስ ላለመቀበል ሲሉ የራሳቸውን ኢየሱስ ፈጥረዋል። የሌለ ታሪክ ፈጥረው ጽፈዋል ብለው የወንጌል ጸሐፊዎችን በሐሰት ይከሳሉ እንጂ ይህን እያደረጉ ያሉትስ እነሱ ራሳቸው ናቸው። ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚናገረውን ታሪክ እነሱ ሊቀበሉት የሚፈልጉትን የተወሰነ ክፍል ብቻ ካስቀሩ በኋላ የራሳቸውን አንዳንድ ዝርዝር ሐሳብ ይጨምሩበታል፤ የቀረውን ግን አይቀበሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ ከቦታ ወደ ቦታ የሚዞር ፈላስፋ ወይም የማኅበራዊ አብዮት አራማጅ የሚል የተለያየ ስም የሚሰጡት ኢየሱስ እውነተኛው ኢየሱስ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምሁራን ራሳቸው በምናባቸው የፈጠሩት ኢየሱስ ነው።
እውነተኛውን ኢየሱስ ማግኘት
ኢየሱስ እውነትንና ጽድቅን የተራቡ ሰዎችን ልብ ለመቀስቀስ ብዙ ጥሯል። (ማቴዎስ 5:3, 6፤ 13:10-15) እንደነዚህ ያሉት ሰዎች “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ለሚለው የኢየሱስ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ።—ማቴዎስ 11:28-30
እውነተኛው ኢየሱስ የሚገኘው ዘመናዊ የሃይማኖት ምሁራን በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ አይደለም፤ ወይም ደግሞ ሰው ሠራሽ የሆኑ ወጎች መፍለቂያ በሆኑት የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥም አይደለም። ትክክለኛውን ኢየሱስ በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታገኘዋለህ። ስለ እሱ በይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? በዚህ ረገድ የይሖዋ ምስክሮች ሊረዱህ ዝግጁ ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ገጽ 55-70 ተመልከት።
b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኩላሊት አንዳንድ ጊዜ የአንድን ሰው ውስጣዊ አስተሳሰብና ስሜት ያመለክታል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብዙ መቶ ዘመናት ያስቆጠረ ትችት
ጀርመናዊው ፈላስፋ ኸርማን ዛምዩኤል ሬይማሩስ (1694-1768) “ሐዋርያት በጽሑፍ ያሰፈሩት ትምህርትና ኢየሱስ ራሱ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ያስተማረው ትምህርት ፈጽሞ የተለያየ ነው ብንል ማንም ተሳስታችኋል ሊለን አይችልም” የሚል አስተያየት ከሰጠበት ከዛሬ 200 ዓመታት በፊት ጀምሮ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ትችት ሲሰነዘር ቆይቷል። ከሬይማሩስ ጀምሮ ብዙ የሃይማኖት ምሁራን ተመሳሳይ አመለካከት አድሮባቸዋል።
እውነተኛው ኢየሱስ (ዘ ሪየል ጂሰስ) የተባለው መጽሐፍ ብዙዎቹ የጥንቶቹ ተቺዎች ራሳቸውን እንደ ከሀዲዎች አድርገው እንደማይቆጥሩ ይገልጻል። ከዚህ ይልቅ “ከቤተ ክርስቲያን ሕግና ከአጉል እምነት ማነቆ የተላቀቁ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥሩ ነበር።” በመጽሐፍ ቅዱስና በጸሐፊዎቹ ላይ የሚደረገው ጥናትና ትችት “የጠራ ክርስትና” ያስገኛል ብለው ያምኑ ነበር።
ሐቁ ሕዝበ ክርስትና የሰዎች ወግና ልማድ መፍለቂያ ሆናለች፤ ይህም በጣም የሚያሳዝን ነው። ነፍስ አትሞትም፣ ሥላሴና እሳታማ ሲኦል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከሚጋጩት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ሆኖም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች በዚህ እውነትን የማጣመም ተግባር ተጠያቂዎች አይደሉም። እንዲያውም ጳውሎስ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች መካከል ‘እየሠራ’ የነበረውን ክህደት አስመልክቶ በጻፈበት በመጀመሪያው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የሐሰት ትምህርትን ገና ከጅምሩ ተቃውመዋል። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 7) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በታሪክም ሆነ በመሠረተ ትምህርት ደረጃ የያዙት ሐሳብ እውነት መሆኑን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወንጌሎች የተጻፉት መቼ ነው?
ብዙዎቹ የአዲስ ኪዳን ተቺዎች ወንጌሎች የተጻፉት በውስጣቸው የሚገኘው ታሪክ ከተፈጸመ ከብዙ ጊዜ በኋላ ስለሆነ ስሕተት እንደሚገኝባቸው ምንም ጥርጥር የለውም ብለው ይከራከራሉ።
ይሁን እንጂ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ የተጻፉበት ዘመን ተቺዎቹ ከሚገምቱት ቀደም ያለ መሆኑን ማስረጃዎች ያሳያሉ። ጥንት በእጅ በተጻፉት አንዳንድ የማቴዎስ ቅጂዎች ላይ የሚገኙት የግርጌ ማስታወሻዎች የመጀመሪያው ቅጂ የተጻፈው በ41 እዘአ እንደሆነ ይጠቁማሉ። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ (ተጽፎ ያለቀው በ61 እዘአ ሳይሆን አይቀርም) ጸሐፊው ሉቃስ ‘የመጀመሪያ መጽሐፉን’ ማለትም ወንጌሉን ቀደም ሲል ጽፎ እንደነበረ ስለሚገልጽ የሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በ56 እና በ58 እዘአ መካከል ባሉት ጊዜያት ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 1:1) የማርቆስ ወንጌል ደግሞ በመጀመሪያው ወይም በሁለተኛው የሐዋርያው ጳውሎስ እስራት ወቅት ማለትም በ60 እና በ65 እዘአ መካከል ባለው ጊዜ በሮም ውስጥ እንደተጻፈ ይገመታል።
ፕሮፌሰር ክሬግ ኤል ብሎምበርግ ወንጌሎች በእነዚህ ዘመናት የተጻፉ መሆናቸውን ይስማማሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የተጻፈውን የዮሐንስ ወንጌል ስንጨምር እንኳ “ከብዙዎቹ ጥንታዊ የሕይወት ታሪኮች ጋር ሲነጻጸር ታሪኩ ከተፈጸመበት ዘመን ብዙም እንዳልራቅን ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል አሪየን እና ፕሉታርክ የተባሉት ሁለቱ ጥንታውያን የታላቁ እስክንድር የሕይወት ታሪክ ጸሐፊዎች ታሪኩን የጻፉት እስክንድር በ323 ከዘአበ ከሞተ ከአራት መቶ ዓመታት በላይ ካለፉ በኋላ ቢሆንም ታሪክ ጸሐፊዎች እነዚህን ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ የእስክንድርን የሕይወት ታሪክ አስመልክቶ የተለያዩ አፈ ታሪኮች መነገር የጀመሩ ቢሆንም አብዛኞቹ አፈ ታሪኮች መነገር የጀመሩት እነዚህ ሁለቱ ጸሐፊዎች ከጻፉ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ነው።” የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የያዟቸው ታሪኮች ቢያንስ ቢያንስ የሌሎች ዓለማዊ ታሪኮችን ያህል ተቀባይነት ማግኘት ይገባቸዋል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በምትመጣው ምድራዊ ገነት ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ በጣም ይደሰታሉ