የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 2/15 ገጽ 4-7
  • ሥቃይና መከራ የማይኖርበት ጊዜ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሥቃይና መከራ የማይኖርበት ጊዜ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ፈቃዱን ወዲያውኑ ያላስፈጸመው ለምንድን ነው?
  • ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለምን አያስገድዳቸውም?
  • ምንም ሳያጠፉ ለጉዳት የተዳረጉ ሰዎችስ?
  • ሥቃይና መከራ ለሚደርስባቸው እውነተኛ ማጽናኛ ይሆናቸዋል?
  • ‘ሁሉም ነገር የሚታደስበት’
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሆን መጽናኛ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ጥያቄ 3፦ አምላክ መከራ እንዲደርስብኝ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 2/15 ገጽ 4-7

ሥቃይና መከራ የማይኖርበት ጊዜ

አምላክ በመጀመሪያ በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ሥቃይና መከራ እንዲደርስ ዓላማ አልነበረውም። ሥቃይና መከራን ያመጣው እሱ አይደለም፤ እንዲኖርም አይፈልግም። ‘ታዲያ ሥቃይና መከራ እንዴት ጀመረ? አምላክ እስካሁን እንዲቀጥል የፈቀደውስ ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።​— ከያዕቆብ 1:​13 ጋር አወዳድር።

መልሱ ስለ ሰው ልጆች ታሪክ ከሁሉ የበለጠ ጥንታዊ ዘገባ በሰፈረበት በመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። የዘፍጥረት መጽሐፍ አዳምና ሔዋን የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ከሰይጣን ጋር ተባብረው በአምላክ ላይ እንዳመፁ ይናገራል። አዳምና ሔዋን የወሰዷቸው እርምጃዎች የአጽናፈ ዓለም ሕግና ሥርዓት መሠረት በሆነው ነገር ላይ ጥቃት የተሰነዘሩባቸው መሠረታዊ የሆኑ አከራካሪ ጉዳዮችን አስነሥተዋል። መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ራሳቸው የመወሰን መብት እንዳላቸው በተናገሩ ጊዜ የአምላክን ሉዓላዊነት ተገዳደሩ። የአምላክን የመግዛት መብትና ‘መልካምና ክፉ’ ስለ ሆኑት ነገሮች ብቸኛ ፈራጅ ለመሆን ያለውን መብት አጠያያቂ አደረጉት።​— ዘፍጥረት 2:​15-17፤ 3:​1-5

ፈቃዱን ወዲያውኑ ያላስፈጸመው ለምንድን ነው?

‘ታዲያ አምላክ ፈቃዱን በግድ ያላስፈጸመው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ብዙዎች ጉዳዩ በጣም ቀላል ይመስላቸዋል። ‘አምላክ ኃይል አለው። ዓመፀኞቹን ለማጥፋት በኃይሉ መጠቀም ነበረበት’ ይላሉ። (መዝሙር 147:​5) ይሁን እንጂ እስቲ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘ከፍተኛ ኃይል ተጠቅመው ፈቃዳቸውን በግድ የሚያስፈጽሙ ሰዎችን አላንዳች ቅሬታ እቀበላቸዋለሁ? አንድ አምባገነን መሪ ጠላቶቹን ለማጥፋት በረሻኝ ጓዶች ቢጠቀም በውስጤ የጥላቻ ስሜት አያድርብኝም?’ አብዛኞቹ ምክንያታዊ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ነገር ይቃወማሉ።

‘ግን እኮ አምላክ እንዲህ ባለው ኃይል ቢጠቀም ለምን እርምጃ ወሰደ ብሎ የሚከራከር ሰው አይኖርም’ ትል ይሆናል። እርግጠኛ ነህ? ሰዎች ስለ አምላክ ኃይል አጠቃቀም ጥያቄ አያቀርቡምን? ክፋትን ዝም ብሎ ከሚያይ ይልቅ አንዳንድ ጊዜ ለምን በኃይሉ አይጠቀምም ? ብለው ይጠይቃሉ። በተጨማሪም በሌሎች ጊዜያት ለምን በኃይሉ እንደተጠቀመ ይጠይቃሉ። ታማኙ አብርሃም እንኳ አምላክ በጠላቶቹ ላይ ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀም ለመረዳት ተቸግሮ ነበር። አምላክ ሰዶምን ለማጥፋት የወሰነበትን ጊዜ አስታውስ። አብርሃም ጥሩ ሰዎች ከክፉዎች ጋር ይጠፋሉ የሚል የተሳሳተ ፍራቻ አድሮበት ነበር። “በደል ያልሠሩትን ደጋግ ሰዎች ከኃጢአተኞች ጋር ታጠፋለህ ብዬ አላስብም” ብሏል። (ዘፍጥረት 18:​25 የ1980 ትርጉም ) እንደ አብርሃም ያሉ ትክክለኛ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እንኳ ይህ ፍጹም ኃይል አለአግባብ ጥቅም ላይ እንደማይውል ማረጋገጫ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።

እርግጥ ነው፣ አምላክ አዳምን፣ ሔዋንና ሰይጣንን ወዲያውኑ ማጥፋት ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ሌሎች መላእክትን ወይም ውሎ አድሮ አምላክ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ሊያውቁ የሚችሉትን ወደፊት የሚፈጠሩ ፍጡራንን እንዴት ሊነካ እንደሚችል አስብ። የአምላክ አገዛዝ ትክክለኛ ስለ መሆኑ በአእምሯቸው ውስጥ እረፍት የሚነሡ ጥያቄዎች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ አይችልም ነበር? ኒትሽ እንዳለው ተቀናቃኙን ሁሉ ያለ ምሕረት የሚያጠፋ አምባገነን አምላክ እንደሆነ አድርጎ የሚያሳውቀው አይሆንም?

ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለምን አያስገድዳቸውም?

አንዳንዶች ‘አምላክ ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ሰዎችን ሊያስገድዳቸው አይችልም?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እስቲ ይህን ጭምር አስብ። በታሪክ ዘመናት ሁሉ መንግሥታት ሰዎች ከአመለካከታቸው ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ለማስገደድ ሞክረዋል። አንዳንድ መንግሥታት ወይም ገዢዎች በመድኃኒት ወይም በቀዶ ሕክምና አማካኝነት የሰዎችን አስደናቂ የነፃ ምርጫ ስጦታ ለመንጠቅ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የአእምሮ መቆጣጠሪያ ስልቶችን ተጠቅመዋል። ምንም እንኳ ይህ ስጦታ አለአግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ቢችልም ነፃ ምርጫ ማድረግ የምንችል መሆናችንን እንደ ውድ ነገር አድርገን አንመለከተውም? ማንኛውም መንግሥት ወይም ገዥ ይህን ነፃነታችንን ሊወስድ ቢሞክር እንፈቅድለታለን?

ታዲያ አምላክ ሕጉን በግድ ለማስፈጸም ወዲያውኑ ኃይል የሚጠቀምበት ምን ምክንያት ሊኖረው ይችል ነበር? ይሖዋ አምላክ የተፈጸመውን ዓመፅ በተሻለ መንገድ ለመፍታት ሕጎቹን የማይቀበሉ ሰዎች ለጊዜው ከአገዛዙ ውጪ ሆነው እንዲኖሩ ለመፍቀድ ወሰነ። ይህም የአዳምና የሔዋን ዝርያ የሆነው ሰብዓዊው ቤተሰብ ለተወሰነ ጊዜ ለአምላክ ሕጎች ሳይገዛ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር አስቻለው። አምላክ ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ከጊዜ በኋላ ፈቃዱን ለማስፈጸም ወሰን የሌለው ኃይሉን ቢጠቀምም እንኳ የሚገዛበት መንገድ ምን ጊዜም ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደሆነና በእሱ ላይ ያመፀ ማንኛውም አካል ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ አሠቃቂ መከራ እንደሚደርስበት የሚያረጋግጥ የማያጠያይቅ ማስረጃ ማግኘት እንደሚችል ስለሚያውቅ ነው።​— ዘዳግም 32:​4፤ ኢዮብ 34:​10-12፤ ኤርምያስ 10:​23

ምንም ሳያጠፉ ለጉዳት የተዳረጉ ሰዎችስ?

‘በዚህ መካከል ምንም ሳያጠፉ ለጉዳት የተዳረጉ ሰዎች ምን ይሆናሉ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ‘አንዳንድ የሕግ ዝርዝሮች እውነት መሆናቸውን ለማረጋገጥ በእርግጥ መሠቃየት ይገባቸዋል?’ አምላክ አንዳንድ ግልጽ ያልሆኑ የሕግ ክፍሎች እውነት መሆናቸው እንዲረጋገጥ ሲል ብቻ ክፋት እንዲኖር አልፈቀደም። ከዚህ በተቃራኒ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው እሱ ብቻ ሉዓላዊ መሆኑንና የሁሉም ፍጥረታቱ ሰላምና ደስታ ቀጣይነት እንዲኖረው ሕጎቹን ማክበር የግድ አስፈላጊ መሆኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ ነው።

በአእምሯችን ልንይዘው የሚገባን አንዱ አስፈላጊ ነገር ክፋት በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ያስከተለውን ጉዳት አምላክ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንደሚችል የሚያውቅ መሆኑን ነው። ለጊዜው ሥቃይና መከራ እንዲኖር መፈቀዱ የኋላ ኋላ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ያውቃል። ሐኪሙ ልጁን ሊገድል ከሚችል አንድ በሽታ ለመጠበቅ ሲከትበው ልጅዋን አጥብቃ የምትይዝ እናትን እንውሰድ። የትኛዋም እናት ብትሆን ልጅዋ እንዲሠቃይ አትፈልግም። ማንኛውም ሐኪም በሽተኛውን ማሠቃየት አይፈልግም። ምንም እንኳ ልጁ ለጊዜው የተሠቃየበትን ምክንያት ባይገነዘብም በኋላ ግን እንዲሠቃይ የተፈቀደው ለምን እንደሆነ ያውቃል።

ሥቃይና መከራ ለሚደርስባቸው እውነተኛ ማጽናኛ ይሆናቸዋል?

አንዳንዶች እነዚህን ነገሮች ማወቅ ብቻ በሥቃይና በመከራ ላይ ያሉትን ሰዎች እምብዛም አያጽናናም ብለው ያስቡ ይሆናል። ሃንስ ኩንግ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የተፈቀደበትን ምክንያት በተመለከተ ምክንያታዊ ማብራሪያ መስጠት “ጠኔ ለያዘው ሰው ስለ ምግብ ጥናት ትምህርት ከመስጠት ያልተሻለ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። “ሥቃይና መከራ ለበዛበት ሰው የሚቀርብለት የብልሃት ሐሳብ በእርግጥ ሊያበረታታው ይችላልን?” ሲሉ ጠይቀዋል። እርግጥ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ችላ የሚሉ ሰዎች የሚያቀርቡት “የብልሃት ሐሳብ” ሁሉ በሥቃይና በመከራ ላይ ላሉት ሰዎች መጽናናት አያመጣላቸውም። እንደዚህ ዓይነቱ ሰብዓዊ አስተሳሰብ አምላክ ሰውን የፈጠረው እንዲሠቃይ ነው፤ ምድር የተሠራችው ደግሞ የእንባ አምባ ወይም የፈተና ቦታ እንድትሆን ነው የሚል ሐሳብ ስላለው ችግሩን የበለጠ ያባብሰዋል። ይህ እንዴት ያለ ስድብ ነው!

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ማጽናኛ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ ሥቃይና መከራ ለምን እንደተፈቀደ ብቻ ሳይሆን አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር በመፍቀዱ ምክንያት የደረሱትን ጉዳቶች ሁሉ እንደሚያጠፋና እሱ በሰጠው ተስፋ ላይ እንዴት መታመን እንደምንችል ያብራራል።

‘ሁሉም ነገር የሚታደስበት’

በቅርቡ አምላክ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓውያን ፍጥረታት ከማመፃቸው በፊት በነበረው ዓላማ መሠረት ሁሉ ነገር እንዲታደስ ያደርጋል። የሰው ልጅ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር አምላክ የወሰነው ጊዜ ሊያልቅ ነው። አሁን የምንኖረው ‘እግዚአብሔር አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደተናገረው ዓለም ሁሉ እስኪታደስ ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ የሚገባውን’ ኢየሱስን ሊልክ በተቃረበበት ጊዜ ነው።​— ሥራ 3:​20, 21

ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያደርጋል? የአምላክ ጠላቶች የሆኑትን ሁሉ ከምድረ ገጽ ያጠፋቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 1:​6-10) ይህ አምባገነን ሰዎች እንደሚያደርጉት በችኮላ የሚሰጥ ፍርድ አይደለም። የሰው ልጅ ትክክለኛ ያልሆነ አገዛዝ ያስከተላቸውን አስከፊ ውጤቶች የሚያሳዩት አያሌ ማስረጃዎች አምላክ ፈቃዱን ለማስፈጸም በቅርቡ ገደብ የሌለው ኃይሉን መጠቀሙ ሙሉ በሙሉ ተገቢ መሆኑን ያረጋግጣሉ። (ራእይ 11:​17, 18) ይህ ሁኔታ በመጀመሪያ በኖኅ ዘመን ከደረሰው ጋር የሚመሳሰል ግን ከዛ በጣም የከፋ ታይቶ የማይታወቅ “መከራ” እንዲከሰት ያደርጋል። (ማቴዎስ 24:​21, 29-31, 36-39) ከዚህ “ታላቅ መከራ” በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች አምላክ “በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ” የተናገራቸው ተስፋዎች ሲፈጸሙ ሲያዩ “የመጽናናት ዘመን” ይመጣላቸዋል። (ሥራ 3:​19፤ ራእይ 7:​14-17) አምላክ የሰጠው ተስፋ ምንድን ነው?

የአምላክ የጥንት ነቢያት ጦርነትና ደም መፋሰስ የሚያስከትለው ሥቃይና መከራ እንደሚወገድ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 46:​9 “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል” ይላል። ምንም ሳያጠፉ ለጉዳት የሚዳረጉና አሳዛኝ የሆኑ ስደተኞች እንዲሁም ጭካኔ በተሞላባቸው ጦርነቶች ተገደው የተደፈሩ፣ የአካል ጉዳተኞችና የተገደሉ ሰዎች አይኖሩም! ነቢዩ ኢሳይያስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም” ብሏል።​— ኢሳይያስ 2:​4

ነቢያቱ ወንጀልና የፍርድ መጓደል የሚያስከትለው ሥቃይና መከራ እንደሚወገድም ተንብየዋል። ምሳሌ 2:​21, 22 “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና” ካለ በኋላ የሥቃይና መከራ ቆስቋሽ የሆኑ ሰዎች “ከእርስዋ ይነጠቃሉ” የሚል ተስፋ ይሰጣል። ‘ሰው ሰውን ለጉዳቱ መግዛቱ’ ያከትማል። (መክብብ 8:​9) ክፉዎች በሙሉ ለዘላለም ይጠፋሉ። (መዝሙር 37:​10, 38) ሁሉም ሰው ከሥቃይና ከመከራ ተገላግሎ በሰላም ያለ ስጋት ይኖራል።​— ሚክያስ 4:​4

ከዚህም በላይ ነቢያት ወደፊት በአካላዊ ሕመምና በስሜት መቃወስ ሳቢያ የሚመጣ ሥቃይና መከራ እንደማይኖር አብስረዋል። (ኢሳይያስ 33:​24) ዓይነ ስውራን፣ መስማት የተሳናቸው፣ የአካል ጉዳተኞችና በበሽታ የተጠቁ ሰዎች በሙሉ እንደሚፈወሱ ኢሳይያስ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 35:​5, 6) አምላክ ሞት ያስከተላቸውን ችግሮች እንኳ ያስወግዳል። ኢየሱስ “በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር፣” NW ] ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል” ሲል ተንብዮአል። (ዮሐንስ 5:​28, 29) ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ‘አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ራእይ በተመለከተበት ወቅት “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ . . . እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” ተብሎ ተነግሮታል። (ራእይ 21:​1-4) እስቲ አስበው! ሕመም፣ እንባ፣ ልቅሶና ሞት በሌላ አነጋገር ማንኛውም ሥቃይና መከራ ፈጽሞ አይኖርም!

ለጊዜው ክፋት እንዲኖር በተፈቀደበት በዚህ ወቅት የተከሰቱ ማናቸውም አሳዛኝ ሁኔታዎች መፍትሔ ያገኛሉ። በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያልነበረው በሰው ልጅ ላይ የደረሰው ሥቃይና መከራ ትዝታዎች እንኳ ፈጽሞ ከአእምሮ ይፋቃሉ። ኢሳይያስ “የቀደመው ጭንቀት ተረስቷልና፣ . . . የቀደሙትም አይታሰቡም” ሲል ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 65:​16, 17) አምላክ በገነት ምድር ላይ የተሟላ ሰላምና ደስታ አግኝቶ የሚኖር ፍጹም ሰብዓዊ ቤተሰብ ለመፍጠር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ሙሉ በሙሉ እውን ይሆናል። (ኢሳይያስ 45:​18) በሉዓላዊነቱ ላይ ፍጹም መተማመን ይኖራል። አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይና መከራ በሙሉ በሚያስወግድበትና ኒትሽ እንደከሰሰው “አምባገነን፣ አስመሳይ፣ አጭበርባሪና ነፍሰ ገዳይ” ሳይሆን ፍጹም ኃይሉን ምን ጊዜም በፍቅር፣ በጥበብና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀም መሆኑን በሚያረጋግጥበት ጊዜ በሕይወት መኖር እንዴት ያለ መታደል ነው!

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ገዢዎች የሰዎችን ነፃ ምርጫ ለመንጠቅ የአእምሮ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል

[ምንጭ]

UPI/Bettmann

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥቃይና መከራ በሚያከትምበት ጊዜ ሰዎች ሁሉ በሕይወት ሙሉ በሙሉ ይደሰታሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ