ባዮኤቲክስ እና ደም አልባ ቀዶ ሕክምና
በቅርብ ዓመታት በሕክምናው መስክ ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል። እነዚህ መሻሻሎች በሕክምናው ዘርፍ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ የሚያስገኙ ቢሆንም አንዳንዶቹ በሥነ ምግባር በኩል ችግር ፈጥረዋል።
አንዳንድ ጊዜ የበሽተኛውን ምርጫ ለመጠበቅ ሲባል በግዳጅ የሚሰጥ ሕክምና መቅረት አለበትን? አንድ ሐኪም ለበሽተኛው እንደሚበጅ ከተሰማው የበሽተኛውን ውሳኔ ቢጥስ ተገቢ ይሆናልን? ለሁሉም ሰው ውድ የሆነ የሕክምና አገልግሎት መስጠት በማይቻልበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው ተመጣጣኝ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ማድረግ የሚገባው እንዴት ነው? እንደሚሉት ያሉ ለውሳኔ አስቸጋሪ የሆኑ ጥያቄዎችን ሐኪሞች በጥሞና ሊያጤኑባቸው ይገባል።
ባዮኤቲክስ በመባል የሚታወቀው የሕክምና ሥነ ምግባር ጥናት መስክ እንደነዚህ የመሳሰሉትን አስቸጋሪ ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶት በማጤን ላይ ነው። የዚህ ጥናት ዓላማ የሥነ ሕይወት ምርምርና በሕክምናው መስክ የሚደረጉ መሻሻሎች በሥነ ምግባር ረገድ የሚፈጥሯቸው ችግሮች ስለሚፈቱበት መንገድ ለሐኪሞችና ለሳይንቲስቶች ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው። በአብዛኛው ለውሳኔ አስቸጋሪ የሆኑ አወዛጋቢ ጉዳዮች የሚነሱት በሆስፒታሎች ውስጥ ስለሆነ ብዙ ሆስፒታሎች የባዮኤቲክስ ኮሚቴዎች አቋቁመዋል። ሐኪሞችንና ጠበቆችን ጨምሮ የኮሚቴው አባላት ብዙውን ጊዜ በሕክምና ሥነ ምግባር ረገድ የሚነሱ ችግሮች በሚገባ በሚጤንባቸው የባዮኤቲክስ ሴሚናሮች ላይ ይገኛሉ።
እንደነዚህ በመሳሰሉት ሴሚናሮች ላይ ብዙውን ጊዜ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:- ከሃይማኖታዊ አቋም የተነሳ ደም አንወስድም የሚሉትን የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት ሐኪሞች ማክበር ያለባቸው እስከ ምን ድረስ ነው? አንድ ሐኪም ከሕክምናው አኳያ “ተገቢ” መስሎ ከታየው ያለ በሽተኛው ፍላጎት ደም ቢሰጥ ተገቢ ይሆናልን? ‘የማያውቀው ነገር የበሽተኛውን ሕሊና አይረብሸውም’ በሚል በሽተኛው ሳያውቅ ደም መስጠት ከሕክምና ሥነ ምግባር አኳያ ተገቢ ነውን?
ሐኪሞች እንደነዚህ የመሳሰሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው ትክክለኛውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች አቋም ጥሩ ግንዛቤ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ግጭት እንዳይፈጠር ሊረዳ እንደሚችል ስለሚገነዘቡ ስለ አቋማቸው ለሐኪሞች ለማስረዳት ምንጊዜም ዝግጁዎች ናቸው።
የሐሳብ ልውውጥ
ፕሮፌሰር ዲያጎ ግራስያ የተባሉ አንድ የታወቁ ስፔናዊ የባዮኤቲክስ ምሁር ተማሪዎቻቸው ከላይ በተነሱት ነጥቦች ላይ ውይይት እንዲያካሂዱ ፈልገው ነበር። እኚህ ፕሮፌሰር “እናንተን [የይሖዋ ምሥክሮችን] ከደም ጋር የተያያዘ የተለያየ ውዝግብ ስለሚገጥማችሁ . . . አቋማችሁን የምታስረዱበት መድረክ ማዘጋጀቱ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ስለዚህ ሰኔ 5, 1996 በስፔይን ማድሪድ ኮምፕሉቴንሴ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ስለ አቋማቸው እንዲያስረዱ ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ተወካዮች ተጋበዙ። አርባ የሚያክሉ ሐኪሞችና ሌሎች ባለሙያዎች በዚያ ተገኝተው ነበር።
ምሥክሮቹ አጭር ንግግር ካደረጉ በኋላ ስብሰባው የተለያዩ ጥያቄዎችን ለማንሳት ክፍት ሆነ። በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ በዐዋቂ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ በሽተኛ አንድን የሕክምና ዓይነት አልፈልግም ለማለት መብት ሊኖረው ይገባል በሚለው ሐሳብ ተስማሙ። በተጨማሪም ተማሪዎቹ በሽተኛው ስለሚደረግለት ሕክምና ተነግሮት ካልተስማማ በስተቀር በፍጹም ደም መሰጠት የለበትም የሚል አቋም ነበራቸው። ሆኖም የምሥክሮቹ አቋም የሚያስከትላቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ተማሪዎቹን አሳስቧቸው ነበር።
አንዱ ጥያቄ ገንዘብን የሚመለከት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደም አልባ ቀዶ ሕክምና እንደ ሌዘር ሰርጀሪ ያሉትን ልዩ መሣሪያ የሚጠይቁ ሕክምናዎችና ቀይ የደም ሴሎች ቁጥራቸው እንዲጨምር የሚያደርገውን ኤሪትሮፖየቲንን የመሳሰሉ ውድ መድኃኒቶች ያስፈልጋሉ። አንድ ሐኪም ምሥክሮቹ አነስተኛ ወጪ የሚጠይቀውን አማራጭ (ተመሳሳይ የደም ዓይነት ለመውሰድ) እምቢ የሚሉ ከሆነ የሚያሳክማቸው መሥሪያ ቤት እነሱን በውድ በማሳከም ከሌሎች የተለየ መብት እንዲሰጣቸው መፈለጋቸው እንደሆነ ተሰምቶታል።
ገንዘብ ሐኪሞችን ሊያሳስባቸው የሚገባ አንዱ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑ ባይካድም ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ለበሽተኛው ደም መስጠት የሚያስከትላቸውን ስውር የሆኑ ወጪዎች አስመልክቶ የተደረጉ ጥናታዊ ዘገባዎችን አቅርቧል። እነዚህ ወጪዎች በሽተኛው ደም መውሰዱ ባስከተለው መዘዝ የሚከሰቱ ችግሮችን ማከም የሚጠይቃቸውን ወጪዎችና ደም መውሰዱ ባስከተለበት ሕመም የተነሳ በሽተኛው የሚያጣውን ገቢ የሚጨምሩ ናቸው። ምሥክሩ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ሰፊ ጥናት ጠቅሷል፤ ይህ ጥናት በአማካይ የሚወሰደው 500 ሚሊ ሊትር ደም መጀመሪያ ላይ የሚጠይቀው ወጪ 250 የአሜሪካ ዶላር ብቻ ቢሆንም የሚጠይቃቸው ተጨማሪ ወጪዎች ሲደማመሩ ከ1,300 ዶላር በላይ እንደሚሆኑና ይህም መጀመሪያ ላይ ከጠየቀው ወጪ ከአምስት እጥፍ በላይ መሆኑን የሚጠቁም ነበር። ጉዳዩ በዚህ መንገድ በስፋት ከታየ ደም አልባ ቀዶ ሕክምና ብዙ ወጪዎችን የሚያስቀር መሆኑን አስረዳ። ከዚህም በላይ ደም አልባ ቀዶ ሕክምና ያስከትላል የሚባለው አብዛኛው ተጨማሪ ወጪ ለመሣሪያ ሲሆን መሣሪያው ደግሞ በድጋሚ ሊያገለግል የሚችል ነው።
በብዙዎቹ ሐኪሞች አእምሮ ውስጥ ይጉላላ የነበረው ሌላው ጥያቄ የጉባኤ አባላት ከሚያሳድሩት ተጽእኖ ጋር የተያያዘ ነው። ሐኪሞቹ አንድ የይሖዋ ምሥክር አቋሙን ቢያላላና ደም ቢወስድ ምን ይደርስበታል? ምሥክሮቹ ይህን ግለሰብ ያገሉታልን? የሚል ጥያቄ ነበራቸው።
የአምላክን ሕግ መጣስ በጣም ከባድ ጉዳይ ስለሆነ ይህን የሚወስነው በወቅቱ የተፈጸመው ሁኔታ ነው፤ ይህ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌዎች የሚመረምሩት ጉዳይ ይሆናል። ለሕይወት የሚያሰጋ ከባድ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለት ደም የወሰደ ግለሰብ ካለ ምሥክሮቹ ይህን ሰው ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የፈጸመ ምሥክር እንደሚጸጸትና ከአምላክ ጋር ያለው ዝምድና በጣም እንደሚያሳስበው ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ግለሰብ ችግሩን የሚገነዘብለትና የሚረዳለት ሰው ያስፈልገው ይሆናል። የክርስትና ዋና መሠረት ፍቅር ስለሆነ ሽማግሌዎች ሌሎች የፍርድ ጉዳዮችን በሚያዩበት ጊዜ እንደሚያደርጉት ሁሉ ጥብቅነትንና ምሕረትን ሚዛናዊ በመሆነ መንገድ ማሳየት ይፈልጋሉ።— ማቴዎስ 9:12, 13፤ ዮሐንስ 7:24
ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ አንድ የባዮኤቲክስ ፕሮፌሰር “የሥነ ምግባር አቋማችሁን እንደገና ብታጤኑት ምን ይመስላችኋል? በቅርብ ዓመታት አንዳንድ ሃይማኖቶች ይህን አድርገዋል” የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር።
ምሥክሮቹ የደምን ቅድስና በተመለከተ ያላቸው አቋም በየጊዜው መጤንና መሻሻል ያለበት የሥነ ምግባር ጉዳይ ሳይሆን ምንጊዜም የማይለወጥ መሠረታዊ እምነት እንደሆነ ለፕሮፌሰሩ ተነገራቸው። በግልጽ የተቀመጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሊደረግበት አይችልም። (ሥራ 15:28, 29) ለአንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ዓይነቱን መለኮታዊ ሕግ መጣስ ማለት ጣዖት አምልኮን ወይም ዝሙትን እንደቀላል ነገር አድርጎ የመመልከት ያህል ነው።
በማድሪድ በተደረገው የባዮኤቲክስ ሴሚናር ላይ ተገኝተው እንደነበሩት ሐኪሞች ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረተው ጽኑ እምነታቸው ጋር የሚስማማ አማራጭ ሕክምና በመፈለግ ውሳኔያቸውን ለማክበር ፈቃደኛ የሆኑ ሐኪሞችን የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ያደንቃሉ። ባዮኤቲክስ በበሽተኛና በሐኪም መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትና የበሽተኞች ፍላጎት ይበልጥ እንዲከበር እንደሚያደርግ አያጠራጥርም።
ሐኪሞች “የሚሠሩባቸው መሣሪያዎች ፍጹም እንዳልሆኑና ይሠራል ብለው ያሰቡት ዘዴ ስህተት ሊሆን እንደሚችል” ዘወትር ማስታወስ አለባቸው በማለት አንድ የታወቁ ስፔይናዊ ሐኪም እንደተናገሩ ተዘግቧል። ስለዚህ “በተለይ አንድ የማይታወቅ ነገር በሚኖርበት ጊዜ ዘወትር ፍቅር ማሳየት እንዳለባቸው ጽኑ እምነት” ሊኖራቸው ያስፈልጋል።