የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 5/1 ገጽ 24-29
  • አምላክ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለወደፊቱ የሚሆን ኃይል ማግኘት
  • እስራት​—ጠላት እንደ መፍትሄ አድርጎ የወሰደው ነገር
  • በሊክተንበርግ
  • በራቬንስብሩክ
  • ከጦርነቱ በኋላ የነበሩት አስቸጋሪ ዓመታት
  • እንደገና በእገዳና በቁጥጥር ሥራ መዋል
  • ከይሖዋ የሚገኝ እርዳታና ኃይል
  • ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው
  • በይሖዋ እርዳታ አምባገነናዊ አገዛዞችን ተቋቁመን ማለፍ ችለናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • በይሖዋ ማዕድ ላይ መቀመጥ በጣም ያስደስታል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ከወጣትነቴ ጀምሮ ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባብቄያለሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ መታመን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 5/1 ገጽ 24-29

አምላክ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው

ሻርሎት ሙለር እንደተናገረችው

“ለዘጠኝ ዓመት በሂትለር እጅ መሠቃየት ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በእርግጥ ፀረ ጦርነት አቋም ነበረሽ፤ አሁን ግን አቋምሽ ከእኛ የሰላም እንቅስቃሴ ጋር አይስማማም!” ሲሉ አንድ የኮሚኒስት ዳኛ ተናገሩ።

ቀደም ሲል በናዚዎች ታስሬ የነበርኩባቸውን ጊዜያትና ስለ ዲሞክራሲያዊት ሪፑብሊክ ጀርመን የሶሻሊዝም ሥርዓት መጥቀሳቸው ነበር። በመጀመሪያ አንዲትም ቃል አልተነፈስኩም ነበር፤ በኋላ ግን እንዲህ ስል መለስኩ:- “አንድ ክርስቲያን ለእውነተኛ ሰላም የሚታገለው ሌሎች ሰዎች በሚታገሉበት መንገድ አይደለም። አምላክንና ሰዎችን መውደድ እንዳለብኝ የሚናገረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ለመከተል እጥራለሁ። የአምላክ ቃል በቃልም ሆነ በድርጊት ሰላማዊ እንድሆን ይረዳኛል።”

በዚያ ዕለት ማለትም መስከረም 4, 1951 ኮሚኒስቶች ስምንት ዓመት እንድታሰር ፈረዱብኝ፤ ይህም የናዚ መንግሥት ከፈረደብኝ በአንድ ዓመት ያነሰ ነው።

ሶሻሊስቶችና ኮሚኒስቶች በእኛ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት ያደርሱ በነበረበት ጊዜ “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው” የሚለው የመዝሙር 46:​1 ጥቅስ አጽናንቶኛል። ለመጽናት የሚያስችል ኃይል የሰጠኝ ይሖዋ ብቻ ነው፤ ቃሉን ይበልጥ ከራሴ ጋር ባዋሃድኩት መጠን ይበልጥ ኃይል አግኝቼአለሁ።

ለወደፊቱ የሚሆን ኃይል ማግኘት

በጀርመን በቱሪን ከተማ በጎትአዜብላበን በ1912 ተወለድኩ። ምንም እንኳን ወላጆቼ በወቅቱ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ቢሆኑም አባቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትና ጽድቅ የሰፈነበትን አገዛዝ ይፈልግ ነበር። ወላጆቼ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ስላይድና ተንቀሳቃሽ ፊልም ሲመለከቱ በጣም ተደሰቱ።a አባባ ሲፈልገው የነበረውን ነገር ማለትም የአምላክን መንግሥት አገኘ።

አባባና እማማ ከእኛ ከስድስት ልጆቻቸው ጋር መጋቢት 2, 1923 ከቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋረጡ። የምንኖረው በሳክሶኒ ኬምኒትስ ነበር፤ እዚያ በነበርንበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር እንሰበሰብ ነበር። (ከወንድሞቼና ከእኅቶቼ መካከል ሦስቱ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።)

በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስብሰባዎች ላይ የምሰማቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶችና ውድ የሆኑ እው​ነቶች በጣም ማረኩኝ፤ የልጅነት ልቤ በደስታ ተሞላ። በተለይ ደግሞ ከ50 በላይ ለምንሆን ክርስቲያን ወጣቶች እሁድ እሁድ የሚሰጥ ትምህርት የነበረ ሲሆን እኔና ኬቲ የምትባለው እኅቴ ለተወሰነ ጊዜ ይህን ትምህርት ተከታትለናል። በእኛ ቡድን ውስጥ የነበረው ወጣቱ ኮንራት ፍራንክ የእግር ጉዞ እንድናደርግና መዝሙር እንድንለማመድ ተጨማሪ ዝግጅት ያደርግ ነበር። ከጊዜ በኋላ ወንድም ፍራንክ ከ1955 እስከ 1969 ድረስ ጀርመን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል።

የ1920ዎቹ ዓመታት አልፎ አልፎ በአምላክ ሕዝቦች መካከል እንኳ ሳይቀር ሁከት የበዛባቸው ወቅቶች ነበሩ። አንዳንድ ወንድሞች መጠበቂያ ግንብን ‘በተገቢው ጊዜ እንደሚቀርብ ምግብ’ አድርገው መቀበላቸውን ስላቆሙ ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን የስብከት ሥራ እስከ መቃወም ደርሰዋል። (ማቴዎስ 24:​45) ይህም ወደ ክህደት አመራ። ሆኖም በዚ​ያን ወቅት በጣም ያስፈልገን የነበረውን ኃይል የሰጠን ይህ “ምግብ” ነበር። ለምሳሌ ያክል “ደፋሮች የተባረኩ ናቸው” (1919) እና “ይሖዋን የሚያከብረው ማን ነው?” (1926) የሚሉ ርዕሶች በመጠበቂያ ግንብ ወጥተው ነበር። ድፍረት በተሞላበት አገልግሎት ይሖዋን ማክበር እፈልግ ነበር፤ ስለዚህ ወንድም ራዘርፎርድ ያዘጋጃቸውን መጽሐፍትና ቡክሌቶች በብዛት አሰራጭቻለሁ።

መጋቢት 1933 የይሖዋ ምሥክር በመሆን ተጠመቅሁ። በዚያው ዓመት በጀርመን አገር የወንጌላዊነት ሥራችን ታገደ። በጥምቀቱ ወቅት ራእይ 2:​10 መጪውን ጊዜ በተመለከተ እንደማሳሰቢያ ሆኖ ቀርቦ ነበር፤ እንዲህ ይላል “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፣ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያስገባችሁ አለው፣ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።” በጣም ከባድ ፈተናዎች እንደሚጠብቁኝ በማሰብ ይህን ጥቅስ በጥልቅ አሰላሰልኩበት። ደግሞም የጠበቅሁት ነገር ደረሰ።

ከፖለቲካ ገለልተኞች ስለሆንን አብዛኞቹ ጎረቤቶቻችን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከቱን ነበር። የፖለቲካ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የደንብ ልብስ የለበሱ የናዚ ወታደሮች ቤታችን ፊት ለፊት ቆመው “ይህ የከሃዲዎች ቤት ነው!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ታኅሣሥ 1933 በወጣው የጀርመንኛ መጠበቂያ ግንብ ላይ “አትፍሯቸው” በሚል ርዕስ የቀረበው ትምህርት ልዩ ማበረታቻ ሆኖልኛል። እጅግ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ጭምር ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ለመቀጠል ጽኑ ፍላጎት አደረብኝ።

እስራት​—ጠላት እንደ መፍትሄ አድርጎ የወሰደው ነገር

እስከ 1935 የጸደይ ወራት ድረስ በኬምኒትስ መጠበቂያ ግንብ በድብቅ ይታተም ነበር። ከዚያም የማባዣ መሣሪያው በኦር ማውንቴንስ ወደምትገኘው ወደ ባየርፌልት ከተወሰደ በኋላ እስከ ነሐሴ 1936 ድረስ በዚያ ጽሑፎችን ለማባዛት አገልግሏል። እኔና ኬቲ አባባ በሰጠን የወንድሞች አድራሻ መሠረት ጽሑፎችን አከፋፈልን። በዚያን ጊዜ ምንም ችግር አላጋጠመንም ነበር። ሆኖም ከዚያን ጊዜ በኋላ ጌስታፖዎች በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉኝ ጀመር፤ ነሐሴ 1936 ከቤቴ ከወሰዱኝ በኋላ ለፍርድ እስከምቀርብ ድረስ በቁጥጥር ሥር እንድውል አደረጉ።

የካቲት 1937፣ 25 ወንድሞችና ሁለት እኅቶች (እኔን ጨምሮ) በዛክሰን አንድ ልዩ ፍርድ ቤት ቀረብን። የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ዓመፅ የሚያነሳሳ ድርጅት ነው የሚል ክስ ቀረበ። መጠበቂያ ግንብ ያትሙ የነበሩት ወንድሞች አምስት ዓመት እስራት ተፈረደባቸው። እኔ ሁለት ዓመት ተፈረደብኝ።

እስራቴን ስጨርስ ነፃ በመለቀቅ ፋንታ ጌስታፖዎች ይዘውኝ ሄዱ። ከእንግዲህ ወዲህ የይሖዋ ምሥክር አይደለሁም የሚል ሰነድ መፈረም ይጠበቅብኝ ነበር። ይህን ፈጽሞ እንደማላደርገው ስገልጽ አዛዡ በንዴት ከተቀመጠበት ዘሎ ብድግ በማለት በእስር እንድቆይ ማዘዣ ጻፈ። የጻፈው ማዘዣ በፎቶ ግራፉ ላይ ይታያል። ቤተሰቦቼን እንዳይ ሳይፈቀድልኝ በቀጥታ በኢልቢ ወንዝ አጠገብ ሊክተንበርግ ወደሚገኝ አንድ አነስተኛ የሴቶች ማጎሪያ ካምፕ ተወሰድኩ። ከዚያም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኬቲን አገኘኋት። ከታኅሣሥ 1936 ጀምሮ ሞሪን በሚገኘው ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ነበረች፤ ነገር ግን ማጎሪያ ካምፑ ሲዘጋ እሷና ሌሎች እኅቶች ወደ ሊክተንበርግ መጡ። አባቴም እስር ቤት ነበር፤ እስከ 1945 አላየሁትም።

በሊክተንበርግ

ቅጣታችን የተለያየ ስለነበረ ከሌሎች ሴት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብሬ መሆን አይፈቀድልኝም ነበር። ከአዳራሾቹ በአንዱ ውስጥ ሁለት የሴት እስረኞች ቡድን ማለትም በማዕድ ዙሪያ የሚቀመጡ እንዲሁም ሙሉ ቀን በርጩማ ላይ ተቀምጠው የሚውሉና ምንም ምግብ የማይሰጣቸው የይሖዋ ምሥክር እስረኞች ተመልክቻለሁ።b

እንደ አጋጣሚ ኬቲን አገኛት ይሆናል በማለት ማንኛውንም የሥራ ምድብ ያለማንገራገር እቀበል ነበር። ደግሞም የተመኘሁት ተሳካልኝ። እሷና ሌሎች ሁለት እስረኞች ወደ ሥራ ሲሄዱ መንገድ ላይ ተገናኘን። በጣም ተደስቼ እቅፍ አደረግኳት። ሆኖም ጠባቂዋ ይህን በቀጥታ ሪፖርት አደረገች። የምርመራ ጥያቄ ከቀረበልን በኋላ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፈጽሞ እንዳንገናኝ ተደረግን። ይህ በጣም ከባድ ነበር።

በሊክተንበርግ ምን ጊዜም የማልረሳቸው ሌሎች ሁለት አጋጣሚዎች ተከስተዋል። አንድ ቀን ሂትለር የሚያደርገውን ፖለቲካዊ ንግግር በሬዲዮ ለማዳመጥ እስረኞች በሙሉ ግቢው ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ብሔራዊ ስሜትን የሚያንጸባርቁ ሌሎች ሥርዓቶችም ስለሚከናወኑ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች አንገኝም አልን። ዘቦቹ በእሳት አደጋ ማጥፊያ ጎማ ከቧንቧ ኃይለኛ ውኃ በላያችን ላይ በመርጨት ከአራተኛ ፎቅ እያባረሩ ወደ ቅጥር ግቢው እንድንወርድ አደረጉን። ብስብስ ብለን በግድ እዚያ እንድንቆም ተደረግን።

አንድ ጊዜ ደግሞ የሂትለር የልደት ቀን ሲቃረብ ከጌርትሩት ኦኢሚ እና ከገርቴል ቡርሌን ጋር በመሆን ጠቅላይ መምሪያውን በመብራቶች እንዳስጌጥ ታዘዝኩ። ሰይጣን በዘዴ በትንንሽ ነገሮች አቋማችንን እንድናላላ በማድረግ የጸና አቋማችንን ለማበላሸት እየሞከረ እንዳለ በመገንዘብ እምቢ አልን። ለቅጣት ሲባል ሁላችንም ወጣት እኅቶች ለየብቻ በአንዲት ጠባብና ጨለማ የእስር ቤት ክፍል ውስጥ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት እንድንቆይ ተደረግን። ሆኖም በእንደዚያ ዓይነቱ አስፈሪ ቦታ እንኳ ሳይቀር ይሖዋ ዘወትር ከጎናችን ነበር፤ በዚህም ይሖዋ መጠጊያችን መሆኑን አረጋግጧል።

በራቬንስብሩክ

በሊክተንበርግ የነበሩ እስረኞች ግንቦት 1939 ወደ ራቬንስብሩክ ማጎሪያ ካምፕ ተዛወሩ። በዚያም ከሌሎች በርካታ የይሖዋ ምሥክር እኅቶች ጋር በልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍል ተመደብኩ። ጦርነቱ እንደፈነዳ የስዋስቲካ ባንዲራ እንድንሰበስብ ታዘዝን፤ እኛ ግን እምቢ አልን። ከዚህ የተነሳ እኔና ሚልኬን ኧርነስት ቅጣት በሚፈጸምበት ሕንፃ ውስጥ እንድንቀመጥ ተደረግን። በጣም ከባድ ከሚባሉት ቅጣቶች አንዱ ይህ ነው፤ የአየሩ ጠባይ ምንም ዓይነት ይሁን እሁድ እንኳን ሳይቀር በየቀኑ አድካሚ ሥራ እንሠራ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ቅጣት ቢበዛ ለሦስት ወር የሚቆይ ነበር፤ እኛ ግን አንድ ዓመት በዚያ እንድንቆይ ተደረግን። የይሖዋን እርዳታ ባላገኝ ኖሮ በፍጹም በሕይወት አልቆይም ነበር።

በ1942 በእስረኞች ላይ የነበረው ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን በረድ አለ፤ ከካምፑ ብዙም ሳይርቅ ለአንድ የኤስ ኤስ ቤተሰብ የጽዳት ሠራተኛ እንድሆን ተመደብኩ። የምሠራበት ቤተሰብ የተወሰነ ነፃነት ሰጥቶኝ ነበር። ለምሳሌ አንድ ቀን ልጆቹን በእግር ሳንሸራሽር የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ባለሦስት ማዕዘን ምልክት ያደረጉ ዮዜፍ ሬቫልድ እና ጎትፍረት ማልሆርን የተባሉ ሁለት እስረኞች አግኝቼ ጥቂት የማበረታቻ ቃላት ተለዋወጥን።c

ከጦርነቱ በኋላ የነበሩት አስቸጋሪ ዓመታት

በ1945 የኅብረ ብሔሩ ጦር እየቀረበ ሲመጣ እሠራበት የነበረው ቤተሰብ ሸሸ፤ እኔም አብሬያቸው መሄድ ነበረብኝ። ከሌሎች በርካታ የኤስ ኤስ ቤተሰቦች ጋር በመሆን በስተ ምዕራብ ጉዞ ጀመሩ።

ያለፉት ጥቂት የጦርነቱ ቀናት ሁከትና አደገኛ ዓመፅ የበዛባቸው አደገኛ ጊዜያት ነበሩ። በመጨረሻ የተወሰኑ የአሜሪካ ወታደሮች አገኘን፤ እነሱም በሚቀጥለው ከተማ እንደማንኛውም አንድ ነፃ ሰው እንድመዘገብ ፈቀዱልኝ። እዚያ ማንን አገኝ ይሆን? ዮዜፍ ሬቫልድን እና ጎትፍረት ሚልሆርንን አገኘሁ። በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ የነበሩ ምሥክሮች በሙሉ በጣም አደገኛ የሞት ጉዞ ካደረጉ በኋላ ወደ ሽፋረን ከተማ እንደደረሱ ሰምተው ነበር። ስለዚህ ሦስታችንም 75 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ወደዚህ ከተማ ጉዞ ጀመርን። ኮንራት ፍራንክን ጨምሮ ከማጎሪያ ካምፕ በሕይወት የተረፉ ታማኝ ወንድሞችን በጠቅላላ በሽፋረን ማግኘት ምንኛ የሚያስደስት ነበር!

በታኅሣሥ 1945 በአገሪቱ ውስጥ የነበረው ሁኔታ በመሻሻሉ በባቡር ለመጓዝ ቻልኩ። ስለዚህ ወደ ቤት ለመሄድ ተነሳሁ! በእርግጥ ጉዞው ቀላል አልነበረም፤ አንዳንድ ጊዜ በባቡሩ ፉርጎ ጣራ ላይ መተኛትንና ባቡሩ ጠርዝ ላይ ቆሞ መጓዝን የሚጨምር ነበር። ኬምኒትስ እንደደረስኩ ከባቡር ጣቢያው ቀድሞ በቤተሰብ እንኖርበት ወደነበረው ቦታ ጉዞ ጀመርኩ። ሆኖም ያኔ የናዚ ወታደሮች ቆመው “ይህ የከሃዲዎች ቤት ነው!” እያሉ ይጮሁበት በነበረው ጎዳና ከነበሩት ቤቶች መካከል አንድም ቤት ለምልክት አልተረፈም። አካባቢው ሙሉ በሙሉ በቦምብ ወድሟል። በጣም የሚያስደስተው ግን እማማን፣ አባባን፣ ኬቲን እንዲሁም ወንድሞቼንና እኅቶቼን በሕይወት አገኘኋቸው።

ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን ውስጥ የኢኮኖሚው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ያም ሆኖ ግን በመላው ጀርመን የአምላክ ሕዝብ ጉባኤዎች እየጨመሩ መጡ። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለስብከቱ ሥራ እኛን ለማስታጠቅ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ናዚዎች ዘግተውት የነበረው በማግደበርግ ያለው የቤቴል ሥራ እንደገና ቀጠለ። በ1946 የጸደይ ወራት እዚያ እንድሠራ ተጠራሁና ወጥ ቤት ተመደብኩ።

እንደገና በእገዳና በቁጥጥር ሥራ መዋል

ማግደበርግ የምትገኘው ኮሚኒስቶች በተቆጣጠሩት የጀርመን ክፍል ነበር። ነሐሴ 31, 1950 ሥራችንን አገዱ፤ በማግደበርግ የሚገኘውንም ቤቴል ዘጉ። ትልቅ ሥልጠና ያገኘሁበት የቤቴል አገልግሎቴ በዚህ ሁኔታ አበቃ። በኮሚኒስቶች አገዛዝ ሥርም ቢሆን እውነትን የሙጥኝ ብዬ መያዜንና በሥቃይ ውስጥ ላለው የሰው ዘር ብቸኛ መፍትሄ የአምላክ መንግሥት መሆኑን ማወጄን ለመቀጠል ወደ ኬምኒትስ ተመለስኩ።

ሚያዝያ 1951 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን ለማምጣት ከአንድ ወንድም ጋር ወደ በርሊን ሄድኩ። ስንመለስ የኬምኒትስ ባቡር ጣቢያ በሲቪል ፖሊሶች ተከቦ ስናገኘው በጣም ደነገጥን። እንደምንመጣ እየተጠባበቁ ስለነበረ ወዲያው በቁጥጥር ሥር አዋሉን።

ለፍርድ ከመቅረቤ በፊት በእስር ወደምቆይበት እስር ቤት ስገባ ናዚዎች ለበርካታ ዓመታት እንዳሰሩኝ የሚገልጽ ማስረጃ ይዤ ነበር። ከዚህ የተነሳ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች በአክብሮት ነው የያዙኝ። ከጥበቃ ኃላፊዎች አንዷ “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ወንጀለኞች አይደላችሁም፤ እናንተ መታሰር የማይገባችሁ ሰዎች ናችሁ” አለችኝ።

አንድ ቀን ከሌሎች ሁለት እኅቶች ጋር ወደ ታሰርኩባት ክፍል መጥታ አንዱ አልጋ ሥር ደብቃ አንድ ነገር አስቀመጠች። ምን ነበር? የራሷን መጽሐፍ ቅዱስ ነበር አምጥታ የሰጠችን። በሌላ ቀን ደግሞ ወላጆቼ የሚኖሩበት አካባቢ ከእስር ቤቱ ብዙም ስለማይርቅ እቤት ሄዳ ጠየቀቻቸው። መጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችና ትንሽ ምግብ በጉያዋ ደብቃ የታሰርኩባት ክፍል ድረስ አመጣችልኝ።

አንድ ሌላም የማልረሳው ነገር አለ። አንዳንድ ጊዜ እሁድ ጠዋት ቲኦክራሲያዊ መዝሙሮቻችንን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ስንዘምር ሌሎች እስረኞች ከመደሰታቸው የተነሳ ለእያንዳንዱ መዝሙር ያጨበጭቡ ነበር።

ከይሖዋ የሚገኝ እርዳታና ኃይል

መስከረም 4, 1951 ጉዳያችን በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ሳለ ዳኛው በዚህ ተሞክሮ መግቢያ ላይ የገለጽኩትን ነገር ተናገሩ። የተፈረደብኝን እስራት መጀመሪያ በቮልትሂም ቀጥሎ በሆል በመጨረሻም በሆኔክ አሳለፍኩ። አምላክ ለእኛ ለይሖዋ ምሥክሮች መጠጊያችንና ኃይላችን እንደነበረና ቃሉ እንዴት እንዳበረታን አንድ ወይም ሁለት አጭር አጋጣሚዎችን ብቻ መጥቀስ ይበቃል።

በቮልትሂም እስር ቤት የይሖዋ ምሥክር እኅቶች በጠቅላላ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ለማድረግ ዘወትር አንድ ላይ እንሰበሰብ ነበር። እስር ቤቱ ውስጥ በእርሳስና ወረቀት መጠቀም ባይፈቀድም አንዳንድ እኅቶች “በጣም ማራኪ በሆነ ቅድስና ይሖዋን አምልኩ” የሚለውን የ1953 የዓመት ጥቅስ ለማዘጋጀትና ለመስቀል የሚያስችላቸውን ቁርጥራጭ ጨርቅ አግኝተው ነበር።​— መዝሙር 29:​2 አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን

ከሴት የወኅኒ ቤት ጠባቂዎች አንዷ ድንገት ደረሰችብንና ወዲያው ሄዳ ተናገረች። የእስር ቤቱ ዋና ኃላፊ መጣና ሁለት እኅቶች ጨርቁን ከፍ አድርገው ዘርግተው እንዲይዙ አዘዘ። “ይህን የሠራው ማን ነው? ለመሆኑ ትርጉሙ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።

ከእኅቶች መካከል አንዷ ራሷን ተጠያቂ አድርጋ ለማቅረብና እኛን ከጥፋተኝነት ነፃ ለማድረግ ፈለገች፤ ሆኖም ቶሎ ብለን በሹክሹክታ እርስ በርሳችን ከተነጋገርን በኋላ ሁላችንም ተጠያቂዎች መሆን እንዳለብን ተስማማን። “እኛ ነን እምነታችንን ለማጠንከር ስንል የሠራነው” በማለት መለስን። ጨርቁ ተወሰደብን፤ ለቅጣት ተብሎ ምግብ ተከለከልን። አበረታች የሆነውን ጥቅስ በአእምሮአችን ለመቅረጽ እንድንችል እየተጠየቅን በነበርንበት ወቅት እኅቶች በሚገባ እንዲነበብ አድርገው ዘርግተው ይዘውት ነበር።

በቮልትሂም የሚገኘው የሴቶች እስር ቤት ሲዘጋ እኅቶች ወደ ሆል እስር ቤት ተዛወርን። በእዚህ እስር ቤት የተጠቀለሉ እቃዎችን መቀበል ይፈቀድልን ነበር፤ አባባ በላከልኝ ነጠላ ጫማዎች ውስጥ ተሰፍቶ የመጣልኝ ምን ነበር? የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፍ ነበር! “እውነተኛ ፍቅር ጠቃሚ ነው” እና “ውሸት ሕይወት ያሳጣል” የሚሉትን ርዕሶች እስከ አሁን ድረስ አስታውሳቸዋለሁ። እነዚህም ሆኑ ሌሎች ርዕሶች ለእኛ በጣም ብርቅ ነበሩ፤ ከአንዳችን ወደ ሌላችን በድብቅ ስናስተላልፍ ሁሉም ለየራሳቸው ማስታወሻ ይይዙ ነበር።

አንዷ የወኅኒ ቤቱ ጠባቂ ድንገት ስትፈትሽ በሣር ፍራሼ ውስጥ የግል ማስታወሻዎቼን አገኘች። ለጥያቄ ጠራችኝና “ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች በ1955 ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ነገር” የሚለውን ርዕስ ትርጉም ለማወቅ እንደምትፈልግ ነገረችኝ። እሷ ኮሚኒስት ስለ ነበረች በ1953 የመሪዋ የስታሊን መሞት በጣም ተሰምቷትና የወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ቢስ ሆኖባት ነበር። እኔ በጊዜው ባልገነዘበውም እንኳ የወደፊቱ ጊዜ ባለንበት የእስር ሁኔታ ላይ አንዳንድ መሻሻሎችን የሚያመጣ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የወደፊት ተስፋ ምንጊዜም ብሩህ እንደሆነ በእርግጠኝነት ገለጽኩላት። ለምን? “እምነቱ ጽኑ ስለሆነና በእግዚአብሔርም ስለሚተማመን፣ ክፉ ወሬ አያስደነግጠውም” የሚለውን የጭብጡን ጥቅስ መዝሙር 112:​7ን ጠቀስኩላት።​— የ1980 ትርጉም

ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው

በጠና ስለታመምኩ የተፈረደብኝ የእስር ጊዜ ከማለቁ ከሁለት ዓመት በፊት መጋቢት 1957 ከእስር ቤት ተለቀቅኩ። በይሖዋ አገልግሎት በማደርገው እንቅስቃሴ የተነሳ የምሥራቅ ጀርመን ባለ ሥልጣኖች እንደገና በእኔ ላይ ተጽእኖ ማሳደር ጀመሩ። ስለዚህ ግንቦት 6, 1957 ቀስ ብዬ ወደ ምዕራብ በርሊን ከሄድኩ በኋላ ከዚያም ወደ ምዕራብ ጀርመን ገባሁ።

ከእስር ከወጣሁም በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት ጤናዬ አልተመለሰልኝም ነበር። መንፈሳዊ ፍላጎቴ ግን እስከ አሁን ድረስ በጣም ጥሩ ነው፤ እያንዳንዱን አዲስ መጠበቂያ ግንብ እትም በጉጉት እጠባበቃለሁ። አሁንም መንፈሳዊ አመለካከት አለኝ? ጥሩ ባሕርያትን ኮትኩቻለሁን? የተፈተነው የእምነት አቋሜ ለይሖዋ ውዳሴና ክብር እያመጣ ነውን? እያልኩ በየጊዜው ራሴን እመረምራለሁ። በሁሉም ነገር አምላክን የማስደሰት ግብ አለኝ። አምላክ ለዘላለም መጠጊያዬና ኃይሌ ሆኖ እንዲቀጥል በማንኛውም ነገር እሱን ለማስደሰት እጥራለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a “ፎቶ ድራማ” ከ1914 ጀምሮ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ተወካዮች በስፋት ሲያሳዩት የነበረ ስላይድና ተንቀሳቃሽ ፊልም ነው።

b ስዊዘርላንድ በርን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተመው ትሮስት (መጽናኛ) የተባለው መጽሔት ግንቦት 1, 1940 በገጽ 10 ላይ ባወጣው ዘገባ በአንድ ወቅት በሊክተንበርግ የሚገኙ ሴት የይሖዋ ምሥክሮች የናዚ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ የክብር ሰላምታ አንሰጥም በማለታቸው ለ14 ቀን ምሳ እንደተከለከሉ ዘግቧል። በዚያም 300 የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙ ነበር።

c ስለ ዮዜፍ ሬቫልድ የሚገልጽ ሪፖርት በየካቲት 8, 1993 ንቁ! ገጽ 20-3 ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሬቨንስብሩክ የሚገኘው የኤስ ኤስ ቢሮ

[ምንጭ]

ከላይ:- Stiftung Brandenburgische Gedenkstätten

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከካምፑ ውጭ ለመሥራት የሚያስችለኝ የይለፍ ወረቀቴ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ