የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 8/1 ገጽ 25-29
  • በይሖዋ ማዕድ ላይ መቀመጥ በጣም ያስደስታል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በይሖዋ ማዕድ ላይ መቀመጥ በጣም ያስደስታል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ያሳለፍነው የመከራ ጊዜ
  • በካምፑ ውስጥ የሚገኝ መንፈሳዊ ምግብ
  • እስከ ሞት ታማኝ መሆን
  • መንፈሳዊ ዝግጅቶች በኖየንጋሜ
  • የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት
  • በይሖዋ እርዳታ አምባገነናዊ አገዛዞችን ተቋቁመን ማለፍ ችለናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ከእውነት የተሻለ ምንም ነገር የለም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • አምላክ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 8/1 ገጽ 25-29

በይሖዋ ማዕድ ላይ መቀመጥ በጣም ያስደስታል

በኧርንስት ቫወር እንደተነገረው

በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች መገኘት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ለእኔ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ እነዚህን ነገሮች ማድረግ በጀርመን አገር ቀላል ያልነበረበት ጊዜ ነበር። አዶልፍ ሂትለር አምባገነን ገዥ በነበረበት ከ1933 እስከ 1945 በነበሩት አመታት እንደነዚህ ባሉት ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ሕይወትን በአደጋ ላይ የሚጥል ነገር ነበር።

ሂትለር ሥልጣን ሊይዝ አንድ ዓመት ሲቀረውና እኔም የ30 ዓመት ሰው በነበርኩበት ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በድሬስደን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኘሁ። በጥር ወር 1935 ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩና ለመጠመቅ እንደምፈልግ ገለጽኩ። ሥራችን ግን ቀደም ሲል በ1933 ታግዶ ነበር። ስለዚህ “ውሣኔህ ምን ማለት እንደሆነ ተገንዝበሃል? ቤተሰብህን፣ ጤንነትህን፣ ሥራህን፣ ነፃነትህንና ሕይወትህን ሳይቀር በአደጋ ላይ ትጥላለህ” ተባልኩ።

“ምን አይነት ኪሣራ ሊጠይቅብኝ እንደሚችል ተገንዝቤአለሁ። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ለሱም ለመሞት ፈቃደኛ ነኝ” ብዬ መለስኩ።

ከመጠመቄም በፊት ቢሆን ከቤት ወደቤት መስበክ ጀምሬ ነበር። አንድ ቤት በር ላይ ኤስ ኤስ የተባለው (ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ የሆነው የሂትለር ክቡር ዘበኛ) መለዮ ለባሽ የወጣቶች ክንፍ መሪ ጋር ተገናኘሁ። እሱም “ይህ የተከለከለ መሆኑን አታውቅም እንዴ? ፖሊስ ልጠራ ነው!” ብሎ ጮኸብኝ።

እኔም ረጋ ብዬ “ጥራ እኔ የተናገርኩት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። እሱን የሚቃወም ሕግ ደግሞ የለም” ብዬ መለስኩ። ከዚያም ወደሚቀጥለው በር ሄድኩና አንድ የወዳጅነት አቀባበል ያለው ደግ ሰው ተቀበለኝና ወደ ቤት አስገባኝ። ምንም አልደረሰብኝም።

ወዲያው ካምስት እስከ ሰባት ምሥክሮች ያሉበትን የጥናት ቡድን ስብሰባ እንድመራ ተመደብኩ። ከአጐራባች አገሮች በምስጢር ወደ ጀርመን የሚገቡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን እናጠና ነበር። ስለዚህ እገዳው ቢኖርም በመንፈሳዊ እንድንጠነክር አዘውትረን “ከይሖዋ ማዕድ” እንካፈል ነበር።

ያሳለፍነው የመከራ ጊዜ

በ1936 የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ፕሬዘዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘር ፎርድ በሉሴርን ስዊዘርላንድ የተደረገውን ስብሰባ ጐበኘና በጀርመን በቲኦክራቲካዊ አመራር ቦታ ላይ የነበሩ ወንድሞችን በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ጋበዘ። የብዙ ወንድሞች ፓስፖርቶች ተወርሰውና በርካታ ወንድሞች የፖሊስ ክትትል ይደረግባቸው ስለነበር በስብሰባው ሊገኙ የቻሉት ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ። በድሬስደን የነበረው ሥራ የበላይ ተመልካች የነበረው ወንድም በሉሴረን በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድወክለው ጠየቀኝ።

“ታዲያ እኔ እኮ በዕድሜም በተሞክሮም ገና ያልበሰልኩ ወጣት ነኝ” አልኩት።

ሲያበረታታኝም “አሁን የሚያስፈልገው ነገር ታማኝ ሆኖ መገኘት ነው። ዋናው ነገር ታማኝነት ነው” አለኝ።

ከሉሰርን ከተመለስኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተያዝኩና ከሚስቴ ከኢቫ እና ከሁለት ትናንሽ ልጆቼ በድንገት ተነጠልኩ። በድሬስደን ወደሚገኘው የፖሊስ ጽሕፈት ቤት ስሄድ የሚመራኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅስ እንዲያስታውሰኝ አእምሮዬን አስጨነቅሁት “በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን። በራስህም ማስተዋል አትደገፍ። በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ። እሱም ጐዳናህን ያቃናልሃል” የሚለውን ምሳሌ 3:5, 6ን አስታወስኩ። ይህን ጥቅስ ማስታወሴ በመጀመሪያው ምርመራ ወቅት አበረታኝ። ከዚያ በኋላ ግን በጣም ጠባብ በሆነች ክፍል ውስጥ ተዘጋሁ። ለአንድ አፍታም ጨርሶ የተጣልኩ መስሎ ታየኝ። ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አደረብኝ። ይሁን እንጂ ለይሖዋ ብርቱ ጸሎት አቀረብኩና የሰላም የመረጋጋት መንፈስ ተሰማኝ።

ፍርድ ቤቱ የ27 ወራት እሥራት ፈረደብኝ። በባውትዘን በሚገኘው እሥር ቤት ለአንድ ዓመት ብቻዬን ተዘግቼ ቆየሁ። አንድ ቀን አንድ ጡረታ የወጣ ዳኛ ተተኪ ዳኛ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት የክፍሌን በር ከፈተና በርኅራኄ “ምንም ነገር እንድታነብ እንደማይፈቀድልህ አውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ አእምሮህን ለማሳረግ አንድ ነገር ያስፈልግህ ይሆናል” በማለት የቆዩ ጥቂት የቤተሰብ መጽሔቶችን ተወልኝና “ማታ እወስዳቸዋለሁ” አለኝ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን “አእምሮዬን ለማሳረፍ” ምንም ነገር አልፈለግሁም ነበር። ብቻዬን ተዘግቼ በነበርኩበት ጊዜ በአእምሮዬ ከያዝኳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ ንግግር እያዘጋጀሁ ጮክ ብዬ ንግግር አደርግ ነበር። ሆኖም መጽሔቶቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶችን ይዘው እንደሆነ ለማየት ሳገላብጥ ብዙ ጥቅሶች አገኘሁ። አንዱ “በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቻለሁና” የሚለው ፊልጵስዩስ 1:6 ነበር። ለዚህ ማጽናኛ ይሖዋን አመሰገንኩ። በኋላ የጉልበት ሥራ ቅጣት ወደሚሰጥበት ሠፈር ተዛወርኩ። ከዚያም እሥራቴ ሊያበቃ በተቃረበበት በ1939 የጸደይ ወራት የካምፑ ሱፐርቫይዘር ሐሳቤን ለውጬ እንደሆነ ጠየቀኝ። መልሴ “ለእምነቴ ታማኝ ሆኖ መኖር ነው ዕቅዴ” የሚል ነበር። ከዚያም ወደ ሳክስንሃውሰን ማጐሪያ ካምፕ እንደምዛወር ነገረኝ።

ከዚያም የግል ልብሶቼን አስረክቤ ሰውነቴን ታጥቤ የሰውነቴን ፀጉር ሁሉ ተላጭቼ የእሥር ቤት ልብሶች ተሰጡኝ። ከዚያም ኤስ ኤስ ወታደሮች “ጥምቀት” ብለው በሰየሙት ሥርዓት እንድካፈል ማለትም ሙሉ ልብሴን እንደለበስኩ እንደገና እንድታጠብ ተደረግኩ። ከዚያ በኋላ እንደራስኩ እስከነልብሴ እስከምሽቱ ድረስ እውጭ እንድቆም ተደረግሁ።

በካምፖቹ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በኤስ ኤስ ወታደሮቹ የተለየ ጭካኔ ይፈጸምባቸው ነበር። ብዙ ጊዜ በሰልፍ ሜዳው ለብዙ ሰዓቶች እንድንቆም ይደረግ ነበር። አንዳንዴ ከመካከላችን አንዱ “ጥሩ ምግብ ብናገኝ እንዴት መልካም ነበር?” ብሎ ኃዘኑን ይገልጽ ነበር። ሌላው “ሐሳብህን በእንደዚህ ዓይነት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አታድርግ። ለይሖዋ ስምና ለመንግሥቱ ለመቆም መቻል እንዴት ያለ ትልቅ ክብር እንደሆነ ብቻ አስብ” ብሎ ይመልስ ነበር። ሌላውም “ይሖዋ ያጠነክረናል!” ይል ነበር። በዚህ መንገድ እርስ በርሳችን እንበረታታ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ፈገግ ብሎ ራስን በአዎንታ መነቅነቅ ብቻውን “ታማኝ ሆኜ ለመገኘት እፈልጋለሁ፣ አንተም እንደኔ አድርግ” የሚል መልእክት ያስተላልፍ ነበር።

በካምፑ ውስጥ የሚገኝ መንፈሳዊ ምግብ

ወንድሞችን በመንፈሳዊ ለመመገብ አንዳንዶች የመሪነት ቦታ ወስደው ነበርና እኔም እንድረዳቸው ተመረጥኩ። የነበረን አንድ ወፍራም የሉተር መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነበር። በእርግጥ እሱንም ቢሆን መያዝ የተከለከለ ነበር። ስለዚህ ይህ ውድ ሀብት በድብቅ የተያዘ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሱን ለጥቂት ጊዜ ለማንበብ የሚፈቀድለት ከእያንዳንዱ የእሥር ቤት ክፍል የተመደበ አንድ ወንድም ብቻ ነበር። የእኔ ተራ ሲሆን የኪስ መብራት ይዤ አልጋ ሥር እገባና ለ15 ደቂቃ ያህል አነብ ነበር። በክፍላችን ካሉ ወንድሞች ጋር እንድወያይባቸው ጥቅሶቹን በቃል አጠና ነበር። በመሆኑም መንፈሳዊ ምግብ ማከፋፈሉ እስከተወሰነ ደረጃ የተደራጀ ነበር።

ወንድሞች ሁሉ ለተጨማሪ መንፈሳዊ ምግብ ይሖዋን በጸሎት እንዲጠይቁ ተበረታተው ስለነበር ይሖዋም ልመናችንን ሰማን። በ1939/40 ክረምት ወራት ላይ አንድ አዲስ የታሠረ ወንድም ከእንጨት በተሠራ አርቴፊሻል እግሩ ውስጥ አድርጎ ጥቂት አዳዲስ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን ይዞ መግባት ችሎ ነበር። ወደ ካምፑ የሚገቡ ሰዎች ሁሉ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈተሹ ስለነበረ ይህ በእውነትም ተአምር ነበር።

ለጥንቃቄ ሲባል እነዚህ መጽሔቶች ለተመረጡ ወንድሞች ብቻ በቀን አንድ ጊዜ እንዲዳረሱ ተደረገ። አንድ ጊዜ አንድ ወንድም ጋራዥ ይሠራ በነበረበት ጊዜ ከውጭ ሆኖ እየጠበቀኝ በጉድጓድ ውስጥ ተደብቄ አነበብኩ። በአንድ ሌላ ወቅት “በስፌት ሰዓት” መጠበቂያ ግንብ መጽሔቱን በጭኔ ላይ አስቀምጬው ነበር። ምሽት ላይ ጓንቲዎችንና ሌሎች ዕቃዎችን ለመጠገን በአዳራሹ ውስጥ እንቀመጥ ነበር። ወንድሞች ደግሞ ለጥበቃ ብለው በሁለቱም ጐኔ ተቀምጠው ነበር። አንድ ኤስ ኤስ ዘብ ሲመጣ መጠበቂያ ግንቡን በፍጥነት ወዲያው ደበቅሁት። ብያዝ ኖሮ ሕይወቴን ማጣቴ ነበር።

በአንቀጾቹ ውስጥ የሚገኙ የሚያበረታቱንን ሐሳቦች በአእምሮአችን እንድንይዝ ይሖዋ ግሩም በሆነ መንገድ ረድቶናል። ብዙውን ጊዜ ማታ ማታ ከባድ ድካም ስለሚሰማኝ ከባድ እንቅልፍ ይወስደኝ ነበር። መጠበቂያ ግንብ ባነበብኩ ሌሊት ግን ብዙ ጊዜ እየነቃሁ ሐሳቦቹን በግልጽ አስታውስ ነበር። በሌሎች ክፍሎች የነበሩ ወንድሞችም ተመሳሳይ ተሞክሮዎች ነበሯቸው። ስለዚህ መንፈሳዊ ምግቦቹን ማካፈል እንችል ዘንድ ይሖዋ የማስታወስ ችሎታችንን ስሎልን ነበር። መንፈሳዊውን ምግብ የምናካፍለው እያንዳንዱን ወንድም በግል ቀርበን በማበረታታት ነበር።

እስከ ሞት ታማኝ መሆን

መስከረም 15, 1939 የእኛ የሥራ ቡድን ከተለመደው ጊዜ ቀደም ብሎ ወደ ካምፑ እንዲመለስ ተደርጎ ነበር። ምክንያቱ ምን ነበር? ከወጣት ወንድሞቻችን አንዱ የነበረው ኦገስት ዲክማን በሕዝብ ፊት የሚገደልበት ቀን ነበር። ናዚዎቹ ይህ ሁኔታ ብዙዎቹን ወንድሞቻችንን እምነታቸውን እንዲክዱ ይገፋፋቸዋል ብለው አምነው ነበር። ከግድያው በኋላ ሌሎቹ እስረኞች ሁሉ ተሸኙና የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ መንቀሳቀስ እስኪያቅተን ድረስ በሰልፍ ሜዳው ላይ እየተረገጥንና በበትር እየተደበደብን ወዲያና ወዲህ ተነዳን። እምነታችንን እንደካድን የሚናገር ወረቀት ላይ እንድንፈርም ታዘዝን። አለዚያ ግን እኛም እንደምንገደል ተነገረን።

እስከሚቀጥለው ቀን ድረስ አንድም የፈረመ ሰው አልነበረም። እንዲያውም ወደ ካምፑ እንደደረሰ ፈርሞ የነበረው አንድ አዲስ እስረኛም ሳይቀር ሐሳቡን ለውጦ ፊርማውን ቀዷል። በከሃዲነት ካምፑን ለቅቆ ከመሄድ ይልቅ ከወንድሞቹ ጋር ለመሞት መርጦ ነበር። በተከታዩ ወር በከባድና አስቸጋሪ ሥራ፣ የማያቋርጥ መጥፎ አያያዝና ምግብ በመከልከል ተቀጣን። በ1939/40 የክረምት ወራት ከመቶ በላይ ወንድሞቻችን ሞቱ። እስከመጨረሻ ድረስ ለይሖዋና ለመንግሥቱ ታማኝነታቸውን ጠበቁ።

ከዚያም ይሖዋ ጥቂት እፎይታ አመጣልን። ብዙ ወንድሞች ተጨማሪ ምግብ በሚሰጥባቸው አዲስ በተቋቋሙ ካምፖች እንዲሠሩ ተመደቡ። ከዚያም በላይ ማስፈራራቱም እየቀነሰ ሄደ። በ1940 የጸደይ ወራት እኔ ወደ ኖየንጋሜ ማጐሪያ ካምፕ ተዛወርኩ።

መንፈሳዊ ዝግጅቶች በኖየንጋሜ

እዚያ ስደርስ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌላ ምንም አይነት ጽሑፍ ያልነበራቸው ሃያ የሚያህሉ ምሥክሮች ነበሩ። በዛክሰንሃውሰን ማጐሪያ ካምፕ የተማርኩአቸውን ነገሮች በኖየንጋሜ ያሉ ወንድሞችን ለማጽናናት እጠቀምባቸው ዘንድ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። መጀመሪያ ላይ ጥቅሶችን እያስታወስኩ ለዕለት ጥቅስነት እንጠቀምባቸው ነበር። ከዚያም በዛክሰንሀውሰን ካምፕ ሳለሁ ከመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ያነበብኳቸውን አንቀጾች እንድገልጽላቸው ለስብሰባ ዝግጅት ተደረገ። አዳዲስ ወንድሞች ሲመጡ በቅርብ ከተጠኑ መጠበቂያ ግንቦች የተማሯቸውን ነገሮች ይናገሩ ነበር።

በ1943 በኖየንጋሜ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ወደ 70 ከፍ ብሎ ነበር። ከካምፑ ውጭ የአየር ወረራ ከደረሰ በኋላ እንደጽዳት ሥራ የመሰሉትን ከቅጥር ውጭ የሚሠሩ ሥራዎችን እንዲሠሩ የሚመረጡት የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱሶችን የመጠበቂያ ግንብ ቅጅዎችንና አንዳንድ የማህበሩን መጽሐፍትና ብሮሹሮች በሚስጢር ወደካምፑ ለማምጣት ችለን ነበር። እንዲሁም በፖስታ ቤት በኩል ተጨማሪ ጽሑፎችና ለዓመታዊ መታሰቢያ የሚሆን ቀይ ወይንና ቂጣ ታሽጎ ደረሰን። እሽጎቹን የፈተሹትን ሰዎች ይሖዋ እንዳሳወራቸው ግልጽ ነበር።

የምንኖረው በተለያዩ መደዳ አዳራሾች ተበታትነን ስለነበር ሰባት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ቡድኖች አቋቋምን። እያንዳንዱ ቡድን አንድ የጥናት መሪና አንድ ተጠባባቂ መሪ ነበረው። በጊዜያዊነት በሠራሁበት የካምፑ አዛዥ ቢሮ ውስጥ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎች በሚስጢር ይዘጋጁ ነበር። ስለዚህ እያንዳንዱ የጥናት ቡድን ለሳምንታዊው ጥናት ቢያንስ አንድ ሙሉ እትም ያገኝ ነበር። አንድም ስብሰባ ተሰርዞ አያውቅም። በተጨማሪም ቡድኖቹ በሰልፍ ሜዳው ላይ ከመጠበቂያ ግንብ የተወሰደውን ሐሳብ ጨምሮ የዕለት ጥቅሱን ቅጂ በየዕለቱ ጧት ያገኙ ነበር።

አንድ ጊዜ ኤስ ኤስ ወታደሮች በዓል ስለነበራቸው የግማሽ ቀን ስብሰባ ለማድረግና በካምፑ ውስጥ እንዴት እንደምንሰብክ ለመወያየት ችለናል። ካምፑን በክልሎች ከፋፈልነውና “የመንግሥቱን ወንጌል” ለእሥረኞቹ በብልሃት ለማድረስ ሞከርን። (ማቴዎስ 24:14) እስረኞቹ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ስለነበሩ ሥራችንንና መንግሥቱን የሚያብራሩ ባለ ብዙ ቋንቋ የምሥክርነት መስጫ ካርዶችን አዘጋጀን። በቅንዓት በመስበካችን የተነሣ የፖለቲካ እሥረኞች “የትም ቦታ ብትሄዱ የምትሰሙት ስለ ይሖዋ ሲነገር ነው!” በማለት አጉረመረሙ። የእንቅስቃሴያችን የመስክ አገልግሎት ሪፖርት በበርን ስዊዘርላንድ ለነበረው ቅርንጫፍ ቢሮ ሳይቀር ደረሰው።

ጌስታፖዎች የማጐሪያ ካምፖቹን እስከመረመሩበት እስከ 1944 ድረስ ነገሮች ሁሉ በጥሩ ሁኔታ ይካሄዱ ነበር። በኖየንጋሜ የነበረው የጽሑፍ ማስቀመጫችን አልተገኘብንም። ይሁን እንጂ ከካርል እሽቫርዘርና ከእኔ ዘንድ አንዳንድ ነገሮች ተገኙብን። ለሦስት ቀን ያህል ተመረመርንና ተደበደብን። ምርመራው ባበቃበት ጊዜ ሰውነታችን በድብደባው ሳቢያ በሰንበርና ቁስል ተሸፍኖ ነበር። ይሁን እንጂ በይሖዋ ዕርዳታ ተርፈናል።

የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት

በ1945 ግንቦት ወር በተባበሩት ሠራዊት ነፃ ወጣሁ። በተለቀቅሁ በማግስቱ ከአነስተኛ የወንድሞችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቡድን ጋር መጓዝ ጀመርኩ። በጣም ደክሞን መጀመሪያ ወደመጣንበት መንደር በሚገኝ አንድ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጥንና ውሃ ጠጣን። ከድካሜ በረታሁና መጽሐፍ ቅዱሴን በክንዴ ሥር ይዤ ከቤት ወደቤት ሄድኩ። አንዲት ወጣት ሴት እኛ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታችን ምክንያት በማጐሪያ ካምፖች እንደነበርን ስታውቅ በኃዘን ልቧ ተነካና ወደቤት ሄዳ ለቡድናችን ትኩስ ወተትና ሳንድዊች ይዛልን ተመለሰች።

ከዚያ በኋላ የካምፑን ልብሳችንን እንደለበስን በዚያ መንደር በሙሉ የመንግሥቱን መልእክት ካወጅን በኋላ ሌላ መንደር ደግሞ ሰፊ ግብዣ አደረገልን። ለዓመታት አጥተናቸው የነበሩትን ምግቦች አዘጋጅቶ አስተናገደን። ምግቦቹን ማየቱ ብቻ አፍን በምራቅ የሚሞላ ነበር! ሆኖም ምግቡን ዝም ብለን አልበላንም። ረጋ ባለና ሥርዓት ባለው መንገድ ጸሎት አደረግን። ይህም ተመልካቾችን በጣም ከመመሰጡ የተነሣ ከዚህ በኋላ ባደረግነው ስብሰባ ላይ የተሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር አዳመጡ። አንዲት ሴት መልእክቱን ተቀበለች። ዛሬ መንፈሳዊ እህታችን ሆናለች።

ጉዞአችንን ስንቀጥል በአስደናቂ መንገዶች የይሖዋን እንክብካቤ ቀመስን። በይሖዋ ድርጅት የሚታተሙትን ሁሉንም መንፈሳዊ ምግቦች አሁን በነፃነት ማግኘትና ከሌሎች ጋር መካፈል በጣም ያስደስታል። በቀጠሉት ዓመታት በይሖዋ የነበረን ፍጹም ትምክህት በተደጋጋሚ ተባርኳል።

ከ1945 እስከ 1950 በማግድበርግ ቤቴል ውስጥ የማገልገል መብት አገኘሁ። ከዚያም እስከ 1955 በበርሊን በመጠበቂያ ግንብ ማህበር ጽሕፈት ቤት አገለገልኩ። ከዚያ በኋላ ሚስቴ ሂልደ እንዳረገዘች እስከተናገረችበት እስከ 1963 ድረስ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገለገልኩ። (የመጀመሪያ ሚስቴ ኢቫ ታስሬ በነበርኩበት ጊዜ ሞታ ነበርና በ1958 እንደገና አገባሁ) ሴት ልጃችን በኋላ ቀናተኛ ምሥክር ሆነች።

ከመጀመሪያ ሚስቴ የወለድኳቸው ልጆቼስ? ወንዱ ልጄ ለእውነት ፍላጎት አላሳየም። ሴቷ ልጄ ጊሴላ ግን ፍላጎት አሳይታለች። በ1953 በሚስዮናዊነት ትምህርት ቤት ተካፈለች። አሁን ከባሏ ጋር በጀርመን ካሉት የትልቅ ስብሰባ አዳራሾች በአንዱ ታገለግላለች። ከይሖዋ እርዳታ ጋር ከ1963 ጀምሮ በዘወትር አቅኝነት አገልግሎት ለመቆየትና ይበልጥ እርዳታ ባስፈለገባቸው ቦታዎች በመጀመሪያ በፍራንክፈርት ከዚያም በቱቢንገን ለማገልገል ችያለሁ።

እስከዚህ ዕለት ድረስ የይሖዋ ድርጅት ለእምነት ቤተሰቦች በሚያዘጋጃቸው ዝግጅቶች ሁሉ መደሰቴን ቀጥያለሁ። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) በአሁኑ ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት በጣም ቀላል ነው። ግን ሁልጊዜ በአድናቆት እንቀበለዋለንን? ይሖዋ በራሱ ለሚታመኑት፣ በታማኝነት ለሚጸኑትና፣ በማዕዱ ለሚመገቡት ሁሉ የተትረፈረፉ በረከቶችን እንዳዘጋጀላቸው እርግጠኛ ነኝ።

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሳክሰንሀውሰን የማጎሪያ ሰፈር

ሀ. የኤስ ኤስ ሰፈር

ለ. ስም የሚጠራበት ቦታ

ሐ. የጠባብ እስር ቤቶች ሕንፃ

መ. ማግለያ ስፍራ

ሠ. ቅማል ማራገፊያ ቦታ

ረ. የመግደያ ቦታ

ሰ. የጋዝ ማፈኛ ቦታ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ