ይሖዋ ታማኝ ነው
ፒተር ፓልኤሰር እንደተናገረው
ጊዜው ታኅሣሥ 1985 ነበር። ናይሮቢ ኬንያ በሚገኘው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ስንቃረብ ደስታችን እየጨመረ መጣ። ከዚያም ወደ መሃል ከተማ በመኪና እየተጓዝን ሳለ ከዚህ ቀደም አይተናቸውና ሰምተናቸው የነበሩት ነገሮች ትዝታ ውስጥ ጨመሩን።
ወደ ኬንያ የመጣነው “የጸና አቋም ያላቸው ሰዎች” በየተሰኘው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ነበር። ከአሥራ ሁለት ዓመት በፊት እኔና ባለቤቴ ኬንያን ለቀን ለመሄድ የተገደድነው በስብከት ሥራችን ላይ እገዳ በመጣሉ ነበር። ቤቴል ተብሎ በሚጠራው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ ውስጥ እንኖር ነበር። ለጉብኝት ስንሄድ ያልታሰበ አስደሳች ነገር ጠበቀን!
በቤቴል ምሳ በማዘጋጀት ትረዳ የነበረችውን ወጣት ምሥክር የምናውቃት ገና የሁለት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር። ከቤቴል ቤተሰብ አባላት መካከል ቢያንስ ስድስቱን የምናውቃቸው ገና ትንንሽ ልጆች በነበሩበት ጊዜ ነው። ዛሬ አድገው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ሁሉም ይሖዋን ሲያገለግሉ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነበር! አምላካችን ይሖዋ “ከታማኝ ሰው ጋር ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ” የሚለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈረውን ቃል በመጠበቅ ሲንከባከባቸው ቆይቷል። (2 ሳሙኤል 22:26 NW) የእኔን የወጣትነት ሕይወትና የእነዚህን ወጣቶች አርኪ ሕይወት ሳወዳድር በጣም ትልቅ ልዩነት ተመለከትኩ!
ዓላማ የሌለው የቀድሞ ሕይወት
ነሐሴ 14, 1918 በእንግሊዝ ስካርቦሮ ተወለድኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ እናቴና የእንጀራ እህቴ ወደ ካናዳ ስለሄዱ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የኖርኩት ከአባቴ፣ ከአባቴ እናትና ከአባቴ እህት ጋር ነበር። አምስት ዓመት ሲሞላኝ እናቴ ከአባቴ ዘንድ ሰርቃ ወደ ካናዳ፣ ሞንትሪያል ወሰደችኝ። ከአራት ዓመት በኋላ ከአባቴ ጋር እንድኖርና ትምህርት ቤት እንድገባ ወደ እንግሊዝ መልሳ ላከችኝ።
እናቴና የእንጀራ እህቴ በየስድስት ወሩ ይጽፉልኝ ነበር። በሚጽፉልኝ በእያንዳንዱ ደብዳቤ መጨረሻ ላይ ለንጉሥና ለአገር ታማኝ የሆንኩ ጥሩ ዜጋ እንድሆን ያላቸውን መልካም ምኞት ይገልጹ ነበር። ብሔራዊ ስሜትና ጦርነት ስህተት እንደሆኑ እንደማምን ጽፌላቸው ስለነበር የሰጠኋቸው መልስ ቅር ሳያሰኛቸው አልቀረም። ሆኖም ምንም ዓይነት ግልጽ የሆነ መመሪያ ስላላገኘሁ በወጣትነት ዕድሜዬ ዓላማ ቢስ ሆንኩኝ።
ከዚያም ሐምሌ 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ከስድስት ሳምንታት በፊት በእንግሊዝ ጦር ውስጥ ለውትድርና ተመለመልኩ። እድሜዬ ገና 20 ዓመት ነበር። እኔ የነበርኩበት ክፍለ ጦር ወዲያው ወደ ሰሜን ፈረንሳይ ተላከ። የጀርመን አውሮፕላኖች ጥቃት በሚከፍቱብን ጊዜ እኛ ወጣቶች ጠመንጃችንን እናነጣጥርና እንተኩስባቸው ነበር። መላው ሕይወታችን በፍርሃት የተዋጠ ነበር። እየገፋ ይመጣ ከነበረው የጀርመን ጦር ወደ ኋላ አፈገፈግን። ሰኔ 1940 በመጀመሪያው ሳምንት ሸሽተው ወደ ደንኪርክ ከሄዱት መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ። በባሕር ዳርቻ አካባቢ ተረፍርፎ የነበረውን የአንድ ሻለቃ ወታደሮች አስከሬን አሁንም በሰቆቃ አስታውሳለሁ። ከዚያ አስፈሪ ሁኔታ ተረፍኩና በአንዲት ትንሽ መርከብ ተሳፍሬ ከእንግሊዝ በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ሃርዊች ደረስኩ።
በቀጣዩ ዓመት ማለትም መጋቢት 1941 ወደ ሕንድ ተላኩ። እዛም የአውሮፕላን በረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያ መካኒክ ለመሆን ስልጠና አገኘሁ። በደረሰብኝ ኢንፌክሽን ሳቢያ ለረዥም ጊዜ በሆስፒታል ከቆየሁ በኋላ የሕንድ ዋና ከተማ በሆነችው በደልሂ ወደሚገኘው ክፍለ ጦር ተዘዋወርኩ። ከአገሬ ርቄና ታምሜ በነበርኩበት ወቅት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ ጀመርኩ። በተለይ ደግሞ በምንሞትበት ጊዜ ምን እንሆናለን እያልኩ አስብ ነበር።
አዲስ ዓይነት ታማኝነት ማሳየት
በደልሂ እንደ እኔው እንግሊዛዊ ከሆነ በርት ጋል ከሚባል ሰው ጋር አንድ መኝታ ቤት እንኖር ነበር። አንድ ቀን “ሃይማኖት የዲያቢሎስ ነው” በማለት የማወቅ ፍላጎቴን በጣም የሚያነሳሳ ነገር ተናገረ። ሚስቱ የይሖዋ ምሥክር ሆና ስለነበር በየጊዜው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ትልክለት ነበር። ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል ተስፋ (በእንግሊዝኛ) የተሰኘው ቡክሌት ስሜቴን ማረከው። የትንሣኤን ተስፋ አስመልክቶ የሚሰጠው ማብራሪያ እውነተኛ የሆነ እርካታ አስገኘልኝ።
በአንድ ወቅት በ1943 በርት በነበርንበት የወታደሮች ካምፕ ውስጥ ሲቪል ሠራተኛ የነበረውን ቴዲ ግሩበርት የሚባለውን አንግሎ-ሕንዳዊ አነጋገረው። በጣም የሚያስገርመው ቴዲም ምሥክር መሆኑን ተገነዘብን። በ1941 የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጁዋቸው ጽሑፎች ላይ እገዳ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም በደልሂ ምሥክሮቹ ወዳዘጋጁት ስብሰባ ወሰደን። በዚያች ትንሽ ጉባኤ በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛና ሞቅ ያለ የወዳጅነት መንፈስ አገኘሁ። ቤዝል ጻቶስ የተባለ አንድ በእድሜ የገፋ ግሪካዊ ክርስቲያን ወንድም ቀረበኝና ጥያቄዎቼን መለሰልኝ። የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው? ትንሣኤንና አምላክ ቃል የገባውን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ዓለም አስመልክቶ ለነበሩኝ ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽልጽ አድርጎ መለሰልኝ።— ሥራ 24:15፤ ሮሜ 5:12፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4
በ1942 የታተመው ሰላም—ዘለቄታ ይኖረው ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለው ቡክሌት ለየት ባለ መንገድ ስሜቴን ማረከው። “ቀዩ አውሬ” የቃል ኪዳን ማኅበር እንደሆነ ለይቶ ያመለክታል። (ራእይ 17:3) ቡክሌቱ ራእይ ምዕራፍ 17 ቁጥር 11ን ይጠቅስና “በአሁኑ ጊዜ የቃል ኪዳኑ ማኅበር ‘የነበረውና የሌለው’ ተብሎ ሊነገር ይችላል” በማለት ይናገራል። በመቀጠልም “የዓለማዊ መንግሥታት ማኅበር እንደገና ብቅ ይላል” በማለት ይገልጻል። ሦስት ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ማለትም በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ማኅበር በተቋቋመ ጊዜ የሆነው ነገር ልክ ይኼው ነበር!
በምሥክሮቹ ጽሑፎች ላይ እገዳ በተጣለበት ወቅት አዲሶቹን ጓደኞቼን ለመርዳት ችዬ ነበር። አንድ ካርቶን ሙሉ ሰላም—ለዘለቄታው ይቀጥል ይሆን? የተባለው ቡክሌት በመጣ ጊዜ ደብቄ እንዳስቀምጠው ጉባኤው ለእኔ በአደራ ሰጠኝ። የተከለከለ ጽሑፍ በጦር ካምፕ ውስጥ ይኖራል ብሎ ማን ሊገምት ይችላል? ወደ ስብሰባ በምሄድበት ጊዜ ለወንድሞች ጥቂት ቡክሌቶችን ይዤ እሄድ ነበር። ሌላው ቀርቶ ቤታችን ይፈተሻል የሚል ስጋት ሲያድርባቸው የግል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን እደብቅላቸው ነበር። በመጨረሻም ታኅሣሥ 11, 1944 እገዳው ተነሳ።
በ1943 ለክፍለ ጦሩ ተብሎ በተዘጋጀው የገና በዓል ወቅት ለክርስቲያናዊ ትምህርቶቸ የነበረኝ ታማኝነት ፈተና ላይ ወደቀ። ኢየሱስ በቀዝቃዛው የታኅሣሥ ወር እንዳልተወለደና የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ገናን እንዳላከበሩ ተምሬ ስለነበር በዓሉን ላለማክበር ቁርጥ አቋም ወሰድኩ።— ከሉቃስ 2:8-12 ጋር አወዳድር።
ከታኅሣሥ 27 እስከ 31, 1944 በጃብልፖር (ጃባልፑር) በተደረገው “የተባበሩት አዋጅ ነጋሪዎች” የተባለው ትልቅ ስብሰባ በተደረገ ጊዜ 150 ከሚያክሉት ተሰብሳቢዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። አብዛኞቹ የስብሰባው ልዑካን ከደልሂ 600 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ በባቡር ተሳፍረው የመጡ ነበሩ። የይሖዋን ድርጅት እንቅስቃሴ የተመለከትኩበትን፣ ሜዳ ላይ የተደረገውን ይህን ግሩም ስብሰባ በጭራሽ አልረሳውም።
ለስብሰባው የመጡ ወንድሞች ያረፉት ትምህርት ቤት በሚገኙ መኝታ ቤቶች ሲሆን እዛም የመንግሥቱን መዝሙሮች በመዘመር በክርስቲያናዊ ወንድማማችነት አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል። በዚያ ስብሰባ ወቅት ለሕዝብ በሚደረገው የስብከት ሥራ መካፈል ጀመርኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ሥራ ለኔ ምንጊዜም እንደ ውድ ነገር ነበር።
በእንግሊዝ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
በ1946 ወደ እንግሊዝ እንደተመለስኩ በዉልቨርተን ጉባኤ መሰብሰብ ጀመርኩ። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከአሥር የማይበልጥ ቢሆንም ባይተዋርነት አልተሰማኝም። ሕንድ ካሉት ወንድሞቼ ጋር በነበርኩበት ጊዜ የነበረኝ ዓይነት እርካታ አግኝቻለሁ። ቪራ ክሊፍተን በጉባኤ ውስጥ አሳቢና ሰው ወዳድ የሆነች እህት ነበረች። እሷም እንደ እኔ አቅኚ የመሆንና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመሳተፍ ምኞት እንዳላት ስላወቅሁ ግንቦት 24, 1947 ተጋባን። እንደ ቤት ሆኖ የሚያገለግል መኪና ካዘጋጀሁ በኋላ በቀጣዩ ዓመት በሃንቲንግደን የገጠር ከተማ የመጀመሪያውን የአቅኚነት ምድባችንን ተቀበልን።
በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ በማለዳ እየተነሳን ገጠር ወደሚገኙት የአገልግሎት ክልሎች በብስክሌቶቻችን እንጓዝ ነበር። ቀኑን ሙሉ የምናከናውነውን የስብከት ሥራችንን ለጥቂት ደቂቃዎች የምናቋርጠው በምሳ ሰዓት ላይ ሳንድዊች ለመብላት ብቻ ነበር። ከፊት ለፊት የሚነፍሰው ነፋስ ምንም ያህል ኃይለኛ ቢሆን ወይም በብስክሌት ወደ ቤት በምንመለስበት ጊዜ የሚወርድብን ዝናብ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን በጌታ ሥራ እንደሰትና እንረካ ነበር።
ወዲያውም አገልግሎታችንን ለማስፋትና በሌሎች አገሮች ለሚገኙ ሰዎች ‘ምሥራቹን’ ለማካፈል ጓጓን። (ማቴዎስ 24:14) ስለዚህም በኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ፣ ሳውዝ ላንሲግ በሚገኘው የጊልያድ ሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል አመለከትን። በመጨረሻም በየካቲት 1956 በተመረቀው በ26ኛው የጊልያድ ክፍል ተቀባይነት አገኘን።
ሰፊ የአገልግሎት መስክ በአፍሪካ
ሚስዮናዊ ሆነን የተመደብነው በአፍሪካ በሰሜናዊ ሮዴሺያ (በአሁኗ ዛምቢያ) ነበር። እዚያም ከደረስን በኋላ ብዙ ሳይቆይ በቤቴል እንድናገለግል ተጠራን። በቤቴል ውስጥ ከነበረኝ ሥራ አንዱ ምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ጉባኤዎች ጋር የሚደረገውን የመጻጻፍ ሥራ ማከናወን ነበር። በ1956 በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙት አገሮች መካከል አንዷ በሆነችው በኬንያ የነበሩት ምሥክሮች አራት ብቻ ሲሆኑ በሰሜን ሮዴሺያ ግን ከ24,000 የሚበልጡ ምሥክሮች ነበሩ። እኔና ቪራ ሠራተኞች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደን ብናገለግል ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ ማሰብ ጀመርን።
ከዚያም ሳይታሰብ ጊልያድ ትምህርት ቤት እንድሄድ ሌላ ጥሪ ቀረበልኝ። በዚህ ጊዜ የተጠራሁት ለበላይ ተመልካቾች የተዘጋጀውን የአሥር ወር ኮርስ ለመከታተል ነበር። ቪራን በሰሜን ሮዴሺያ ትቼ በዚያን ጊዜ የጊልያድ ትምህርት ቤት ወደሚገኝበት ወደ ኒው ዮርክ ሲቲ አቀናሁ። በኅዳር 1962 ኮርሱን ከጨረስኩ በኋላ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ለማቋቋም በኬንያ ተመደብኩ። በዚህ ጊዜ በኬንያ ከመቶ የሚበልጡ ምሥክሮች ነበሩ።
ቪራን ለማግኘት ወደ ሰሜን ሮዴሺያ እየተጓዝኩ ሳለሁ ለአጭር ቆይታ በናይሮቢ ኬንያ ማለፍ ነበረብኝ። ይሁን እንጂ እዛ ስደርስ የ25ኛው ክፍል የጊልያድ ተመራቂ የሆነው ቢል ኒዝበት አገኘኝና በዚያኑ ዕለት ኬንያ ለመግባት ሕጋዊ ፈቃድ የማግኘት አጋጣሚ እንዳለ ነገረኝ። የስደተኞች ባለ ሥልጣናትን ሄደን ካነጋገርናቸው በኋላ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ የአምስት ዓመት የሥራ ፈቃድ አገኘሁ። በዚህም የተነሳ ወደ ሰሜን ሮዴሺያ ተመልሼ ሳልሄድ ቀረሁ። ከዚያ ይልቅ ከቪራ ጋር ናይሮቢ ተገናኘን።
በተዘጋጀልን የስዋሂሊ ቋንቋ ኮርስ ከተካፈልን በኋላ ናይሮቢ ከሚገኝ ከአንድ ትንሽ ጉባኤ ጋር በአገልግሎት መሳተፍ ጀመርን። አንዳንድ ጊዜ በስዋሂሊ ቋንቋ የተዘጋጀውን ስብከት ካነበብን በኋላ የቤቱ ባለቤት “እንግሊዝኛ አላውቅም!” ብሎ ይመልስልን ነበር። ይህ ሁኔታ ቢገጥመንም በቋንቋ በኩል የነበረብንን ችግር በጽናት ተቋቁመን አሸነፍን።
የአገልግሎት ክልላችን ኢየሩሳሌምና ኢያሪኮ የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ስያሜ ያላቸውን ሰፊ የመኖሪያ ቤት ሕንፃዎችን የሚጨምር ነበር። ፍላጎት ያላቸው ወዲያው ይገኙ ስለነበር ከነዚህ አካባቢዎች ብዙ አዳዲስ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ተገኝተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በእነዚህ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል! ለአምላክ መንግሥት ታማኝ መሆን በይሖዋ ሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲኖር ስላደረገ የጎሳ የበላይነት ስሜት ጨርሶ አይታይም። እንዲያውም የተለያየ ጎሳ ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ ይጋባሉ። ይህ ሁኔታ ምስክር ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ ያልተለመደ ነገር ነበር።
አዳዲስ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እውነትን የሚቀበሉት በቅንዓት ነው። ለምሳሌ ያህል ሳምሶን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ወደ መኖሪያ አካባቢው ዘልቆ እንዲገባ ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረው አቅኚዎች እንዲላኩ አጥብቆ ይጠይቅ ነበር። እንዲያውም ለአቅኚዎቹ ማረፊያ እንዲሆን በኡካምባን አካባቢ ከቤቱ ጋር የተያያዘ ተጨማሪ ክፍል ሠርቶ ነበር። ወዲያውም የመንግሥቱን አዋጅ ነጋሪዎች የያዘ አንድ አዲስ ጉባኤ በዚህ አካባቢ ተቋቋመ።
በምሥራቅ አፍሪካ በምትገኘው በኢትዮጵያ ያሉትን ወንድሞች ብዙ ጊዜ ጎብኝቻቸዋለሁ። እስር፣ ድብደባና ያልተቋረጠ ክትትል ይደረግባቸው የነበረ ቢሆንም በወር በአማካይ ከ20 የሚበልጥ ሰዓት በአገልግሎት ያሳልፉ ነበር። አንድ ጊዜ ሁለት አውቶቡስ ሙሉ የኢትዮጵያ ወንድሞችና እህቶች ኬንያ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አደገኛ የሆኑ ተራራማ መንገዶችን አቋርጠው ለአንድ ሳምንት ተጉዘዋል። የመንግሥቱን ጽሑፎች ወደ አገራቸው ይዘው ለመሄድ የተጠቀሙበት ዘዴ በጣም የሚያስገርም ነበር። በኬንያ የነበርነውም ጽሑፎችን ለእነርሱ ለመላክ ደስተኞች ነበርን።
በ1973 መንግሥት ኬንያ በነበረው ሥራችን ላይ እገዳ አደረገና ሚስዮናውያን አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አደረገ። በዚያን ጊዜ በኬንያ ከ1,200 የሚበልጡ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ መጥተው የማይረሳ አሸኛኘት አድርገውልናል። የእነርሱ እዚያ መገኘት አንድ ዓይነት በዓል አክብረን የመጣን እየመሰላቸው አብረውን ይጓዙ የነበሩ መንገደኞች ይጠይቁን ነበር። እኔና ቪራ ወደ እንግሊዝ ተመለስንና እዚያም የሥራ ምድብ ተሰጠን። ሆኖም ወደ አፍሪካ ለመመለስ እንጓጓ ነበር።
ወደ አፍሪካ መመለስ
ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራት በኋላ በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው የጋና ዋና ከተማ በሆነችው አክራ በሚገኘው ቤቴል እንድናገለግል አዲስ የሥራ ምድብ ተሰጠን። እዚያ ከነበሩኝ ሥራዎች መካከል አንዱ በዚያ አገር ያሉት ወንድሞች ይገጥማቸው ከነበረው ችግር ጋር እንድጋፈጥ አደረገኝ። ምግብና ለቤቴል ቤተሰብ የሚሆኑ ቁሳቁሶች በምገዛበት ወቅት የምግብ ዋጋ ከመጠን በላይ መወደዱ በጣም አስገረመኝ። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው የሚያስፈልጉትን የምግብ ዓይነቶች መግዛት አይችልም። የነዳጅ እጥረትና የመለዋወጫ ዕቃዎች እንደ ልብ አለማግኘት ተጨማሪ ችግር ፈጠረ።
የጋና ወንድሞች አዳብረውት የነበረውን ታጋሽ የመሆንን አስፈላጊነት ተማርኩ። ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በጉቦ አማካኝነት የማግኘት ፈተናን ተቋቁመው የነበራቸውን የደስተኝነት ዝንባሌ ማየት በጣም የሚያበረታታ ነበር። በውጤቱም በጋና የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በሐቀኝነታቸው በሰፊው በመታወቃቸው በብዙ ባለሥልጣናት ፊት ጥሩ ስም አትርፈዋል።
የቁሳቁስ እጥረት የነበረ ቢሆንም እንኳን እያደገ የሚሄድ መንፈሳዊ ብልጽግና ነበር። በመላ አገሪቱ በእያንዳንዱ ሰው ቤት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ይገኙ ነበር። እንዲሁም በ1973 እኛ ወደዚህች አገር ስንገባ 17,156 የነበረው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር በ1981 ወደ 23,000 ከፍ ሲል ተመልክተናል። በዚያው ዓመት የቆዳ ካንሰር ስለ ጀመረኝ ቀጣይ የሆነ ሕክምና ለማግኘት ጋናን ለቀን ወደ እንግሊዝ ለመሄድ ተገደድን። በሕንድና በአፍሪካ ለብዙ ዓመታት ለፀሐይ መጋለጤ የቆዳ ካንሰሩን እንዳባባሰብኝ ጥርጥር የለውም።
በእንግሊዝ የገጠመን አዲስ ሁኔታ
ለእኔ ወደ እንግሊዝ መመለስ ማለት በአገልግሎቴ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማድረግ ማለት ነበር። ቀደም ሲል አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያከብሩ ሰዎች ጋር በቀላሉ እነጋገር ነበር። ይሁን እንጂ በለንደን እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ማግኘት ቀላል አልነበረም። በብሪታንያ ይኖሩ የነበሩት ወንድሞች በሚያሳዩት ጽናት በጣም ተደነቅሁ። ይህም በመንፈሳዊ “ተጨንቀውና ተጥለው” ለሚገኙ ሰዎች የጠለቀ አሳቢነት የማሳየትን አስፈላጊነት እንድገነዘብ አደረገኝ።— ማቴዎስ 9:36
ከአፍሪካ ከተመለስን በኋላ መስከረም 1991 ቪራ በ73 ዓመቷ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ለንደን በሚገኘው ቤቴል አብረን አገልግለናል። ለብዙ ዓመታት ከጎኔ ተሰልፋ በአገልግሎት የተካፈለችን እንደ እርሷ ያለ ታማኝ የሥራ ባልደረባ ማጣት ቀላል አልነበረም። እሷን ማጣቴ በጣም ይሰማኛል። ሆኖም 250 የሚጠጉ የቤቴል አባላት በሚሰጡኝ ጥሩ ማበረታቻ ደስተኛ ነኝ።
የይሖዋ ድርጅት ወደ ፊት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መመልከትና ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የኑሯቸው ክፍል ሲያደርጉ ማየቴ እንደ መብት እቆጥረዋለሁ። “እግዚአብሔር . . . ቅዱሳኑንም አይጥላቸውም” ከሚለው የተሻለ ሌላ ምንም ዓይነት የሕይወት መንገድ እንደ ሌለ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ።— መዝሙር 37:28
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከ1947 እስከ 1955 በእንግሊዝ በአቅኚነት አገልግለናል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሕንድ ተደርጎ በነበረ በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በአገልግሎት ስካፈል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰሜናዊ ሮዴሺያ ሚስዮናዊ በነበርንበት ጊዜ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1985 ለ12 ዓመታት ተለይተናቸው ከነበሩት ወዳጆቻችን ጋር